Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበኢትዮጵያ እግር ኳስ ፊት የተደቀኑት ተግዳሮቶች

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፊት የተደቀኑት ተግዳሮቶች

ቀን:

(ክፍል ሁለት)

በዶ/ር ኤልያስ አቢ ሻክራ

ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ተግዳሮቶች መካከል እግር ኳሱ ያለበትን ዝቅተኛ ደረጃ፣ የአሠልጣኞቻችንን ችሎታ  ወስንነትና ለአካል ብቃት ያላቸውን የተሳሳተ ግንዛቤና የተጫዋቾቻችንን ዝቅተኛ የንቃት ደረጃ ዳስሻለሁ፡፡ ቀጣዩ ክፍል እነሆ፡፡

ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ

የፈረንሣይ አገር ብሔራዊ ፌዴሬሽን አሠልጣኝ ለመቅጠር ሲፈልግ ለአገሩ የፕሮፌሽናል አሠልጣኞች ማኅበር ደብዳቤ ይጽፋል፡፡ ማኅበሩ መሥፈርቶቹን የሚያሟሉ ሙያተኞች ጠርቶ ካወዳደረና ካነጋገረ በኋላ ብቃት ያለውን ግለሰብ ለፌዴሬሽኑ ያቀርባል፡፡ ይኼን ካደረገ በኋላ ጠቅላላ የአገሪቱ አሠልጣኞች በሙሉ የብሔራዊ ቡድኑን አሠልጣኝ ይደግፉታል፡፡ የፈለገው ውጤት ቢመጣ የሙያተኞቹ ድጋፍ አይለየውም፡፡ የማኅበሩና የፌዴሬሽኑ ሙሉ ድጋፍ ስላለው ሚዲያ ሹመቱን አክብረው በሆነው ባልሆነው አሠልጣኙን አይተቹትም፡፡ መብቱን ከጣሱ በሕግ ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ ስድብ የሚባል ነገር በፍፁም አይታሰብም፡፡ ያለው የሌለው የኳስ አሠልጣኝ ነግ በኔ ብሎ በመፍራት የተሰየመውን አሠልጣኝ ይደግፈዋል፣ የማይነቅፈው በተራው ነገ እሱ በቦታው ቢሾም በሰላም ለመሥራ ስለሚፈልግ ነው፡፡ አሠልጣኞች እርስ በርስ መወቃቀስ፣ መጠላለፍ፣ መበላላት፣ አደባባይ ወጥቶ በሚዲያ መሳደብ የማይታሰብ ነገር ነው፡፡ በሙያ ሥነ ምግባር ስለታነፁ አንዳቸውም አሠልጣኙን የሚነካ ትችት፣ ሞራሉን የሚሸረሽር ንግግር ከአፋቸው አይወጣም፡፡ ለማስታወስ ያህል የአገራችን አሠልጣኞች ከዛሬ አምስትና ስድስት ዓመት በፊት ከግጥሚያ በኋላ እንኳን በእጅ አይጨባበጡም ነበር፡፡ ያቋቋሙት ማኅበር ተመሥርቶ እንደፈረሰና እንደገና እንደተቋቋመ የሚረሳ አይደለም፡፡ መጠላለፍና መሰዳደብ የለተመደበት የሙያተኞች ስብስብ ነው፡፡ አንዱ ከአንዱ የሚያንስበት፣ የማይበልጥበት (በዚህ አሥር ዓመት ውስጥ ከውበቱ አባተ በስተቀር ማን ዋንጫ አነሳ?) የሙያተኞች ስብስብ ነው፡፡ የሚገርመው የአገራችን አሠልጣኞች ገበያ በጣም ጠባብና ውስን መሆኑ ነው፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የምርጫ ችግር ቢገጥመው ምንም አያስደንቅም፡፡ በሌላ በኩል ምርጫውን የሚረብሽ አወዛጋቢ ክስተትም ያጋጥማል፡፡ ሌላ አገር አንድ አሠልጣኝ የያዘውን ቡድን አውርዶ በዓመቱ አንድ ትልቅ ቡድን፣ በተለይ ብሔራዊ ቡድን እንዲያሠለጥን አይሰጠውም፡፡ እዚህ የያዘውን ቡድን ታችኛው ዲቪዥን አውርዶ የብሔራዊ ቡድን እንዲያሠለጥን ይጠራል፡፡ አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ብሔራዊ ቡድንን አሠልጥኖ በአንፃሩ ተሳክቶለታል ማለት ይቻላል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አሠልጣኝ አብረሃም ተክለ ሃይማኖት ሁለቱ የሴቶቹን ብሔራዊ ቡድን አሠልጥኖ ከሽፏል፡፡ አሠልጣኝ አሥራት ኃይሌ በክለብ ደረጃ ካሉት የአገር አሠልጣኞች በሙሉ የተሻለ ውጤት ያለምንም ተፎካካሪ ያስመዘገበ እሱ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የሚያሠለጥነውን ክለብ በአኅጉሩ ውድድር ምንም ውጤት ሳያስመዘግብ ቀርቷል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑን ይዞ ከሴካፋ ዋንጫ በስተቀር ምንም አመርቂ ውጤት አላገኘም፡፡

መጨረሻ በተካፈልነው የአፍሪካ ዋንጫና በሁለቱም ቻኖች ካፍ እግር ኳሳችንን ሲገመግመው በቴክኒክ፣ በታክቲክ እንዲሁም በአካል ብቃት የመጨረሻ ደረጃ እንደያዝን ያመለክተናል፡፡ ሦስቱም ጊዜ በአገር በቀል አሠልጣኞች ነው ብሔራዊ ቡድኑ የሠለጠነው፡፡ ቀጥታ የውጤቱ ተጠያቂ ባይሆኑም የተወሰነ ድርሻ መውሰዳቸው የማይቀር ነው፡፡ ይኼ እውነት ለምንድነው ለሕዝቡ የሚደበቀው? እውነት ምንጊዜም መራራ ኪኒን ናት፡፡ ሆኖም ተቀብሎ ለዋጣት ከጊዜ በኋላ ወደ ማገገምና ወደ መዳን ጎዳና ያለምንም ጥርጣሬ መገስገስ ይጀምራል፡፡ እግር ኳሳችን የወደቀ ነው፣ ክለቦቻችንም ሆኑ የተለያዩ ብሔራዊ ቡድኖቻችን ውጤት አልባ ከሆኑ ሰንበት ብለዋል፡፡ በሆነው ባልሆነው መሳደብ ምንም ትርፍ አያመጣም፡፡ ይልቁኑም ልክ የዛሬ 20 ዓመት ገደማ በአቶ መላኩ ጴጥሮስ ተነሳሽነት አንድ ዓውደ ጥናት ትምህርት ሚኒስቴር ተከፍቶ ያለውን ችግር ዝርግፍ አድርጎ፣ ዘላቂ እንኳን ባይሆንም ጊዜያዊ መፍትሔ ተገኝቶ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን እንደዚህ ዓይነቱ ብሔራዊ ውይይት ቢደረግና ለተጋረጡት ችግሮች መፍትሔ ቢቀርብ እግር ኳሳችን ከገባበት ማጥ ውስጥ ለማውጣት ትልቅ ተስፋ አለው፡፡

ብሔራዊ ቡድን ሲመረጥና ለውድድር በሚዘጋጅበት ጊዜ ፌዴሬሽኑ አሠልጣኙን የሚረዳ ግብረ ኃይል ማቋቋም አለበት፡፡ ለ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ በከፊል ተሞክሮ ነበር፡፡ ሆኖም አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው የአካል ብቃት አዘጋጅ አያስፈልገኝም፣ ከፊፋ ድረ ገጽ ያገኘሁት የአካል ብቃት መርሐ ግብር ‘ዳውንሎድ’ አድርጌ እኔ ራሴ አሠራቸዋለሁ ብሎ ሌላ ሰው እንዳይገባ ከለከለ፡፡ ፊፋ በድረ ገጹ የሚያስቀምጠው የአካል ብቃት ልምምድ መርሐ ግብር ዕውቀቱ ለሌላቸው ለጀማሪ አሠልጣኞች እንደ መነሻ እንዲጠቀሙበት አማካይ የሥልጠና መርሐ ግብር የልምምድ ዘዴ እንጂ ቀኖና አድርጎ አላስቀመጠውም፡፡ ደግሞም ፊፋ የኡመድን፣ የሽመልስን፣ የአዳነን፣ የጌታነህን፣ ወዘተ. የአካል ብቃት ደረጃ መረጃ አለው እንዴ? ደቡብ አፍሪካ ከተሳተፉት ቡድኖች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብቻ ነው የአካል ብቃት አሠልጣኝ ይዞ ያልሄደው፡፡ ትንሽዋ ኒጀር እንኳን ሁለት የአካል ብቃት አዘጋጆች ይዛ ነው የሄደችው፡፡ የደቡብ አፍሪካ ቻን መሳተፉን ሲያረጋግጥ አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው በልበ ሙሉነት ቢያንስ ግማሽ ፍፃሜ እንደሚደርስ አልያም አሸንፎ ዋንጫ ይዞ እንደሚመለስ ተናግሮ ነበር፡፡ መለስ ብዬ ሳየው የአሠልጣኙ ከመጠን በላይ በራሱ የተማመነው ከምን ተነስቶ ነው ብዬ መጠየቄ አልቀረም፡፡ እርግጥ ያለምንም ጥርጣሬ አሠልጣኙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዓለም ዋንጫ በር አፍ ማድረሱ ማንም የአገሩ አሠልጣኞች ያላደረጉትን አድርጓል፣ ተሳክቶለታል፡፡  በዚህ የሞቅታ ስሜት ተነሳስቶ ይመስላል የማስተዋል ችሎታው የተረበሸው፡፡ አሥር ምርጥ የአፍሪካ ቡድን እንዲገባ የረዱት እነ ሳላህዲን፣ ሽመልስ፣ አዲስ፣ ኡመድና ጌታነህ እንደማይገቡ የዘነጋው ይመስላል፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና ጫና ፈጣሪ ነበሩ፡፡ ከቡድኑ ሲቀነሱ ቡድናችን ተራ ቡድን ደረጃ እንደሚወርድ የረሳው ይመስላል፡፡ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የካን ቴክኒክ ግምገማ ቢመለከት እንዴት በረዳው ነበር፡፡ በሌላ በኩል ተጫዋቾቹ ከዓለም ዋንጫ በር አፉ ላይ ደርሰው መቅረታቸው ምን ያህል የሞራል ውድቀት እንደደረሰባቸው ግምት ውስጥ ያስገባው አይመስልም፡፡ በዚህን ጊዜ ነበር እውነተኛ የስፖርት ሥነ ልቦና አዋቂ ጋር ተባብሮ መሥራት የነበረበት፡፡ ለአንድ እግር ኳስ ተጫዋች የመጨረሻ ግቡ ዓለም ዋንጫ መሳተፍ ነው፣ ቀጥሎም የአኅጉሩ ዋንጫ ለእኛ የአፍሪካ ዋንጫ መካፈል፣ ከዚያም የቻን ውድድር መወዳደር፣ በመጨረሻ የቀጣናው ውድድር፣ ማለትም ለእኛ ሴካፋ መሳተፍ ናቸው፡፡ የተለያዩትን ውድድሮች ማዕረግ ለማስረዳት አንድ ምሳሌ ልውሰድ፡፡ የዓለም ዋንጫ ምርጥ በየዓይነቱ ምግብ ቁርጥ መጨመር ያለበት ነው፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ በየዓይነቱ ቀርቦ ቁርጡ ተቀንሷል፡፡ በመቀጠል ቻን ሁሉ ተነስቶ የክክ ወጥ ብቻ ይቀርባል፣ በመጨረሻም ሴካፋ እንጎቻ ብቻ ለበላተኛው ይሰጣል፡፡ ታዲያ ትልቅ ድግስ እንደሚበላ ተስፋ ለተሰጠው ተጫዋች በተራ ክክ ወጥ ለማነሳሳት ይሞክራል እንዴ? አንዳንዶቹ ተጫዋቾች በዕድሜያቸው መግፋት የተነሳ ከዚህ በኋላ ዓለም ዋንጫ እንደማይሳተፉ ያውቃሉ፣ ይኼም ይህ ነው የማይባል የቁጭት መንፈስ ይያዛሉ፣ ተስፋም ይቆርጣሉ፡፡ እዚህ ላይ ነበር አሠልጣኙ አዲስ ደም አምጥቶ ጥሩ ተሞክሮ ካላቸው ነባር ተጫዋቾች ጋር ቀላቅሎ ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናት የነበረበት፡፡ ያመጣውም ውጤት በግልጽ እንደተሳሳተ ያሳያል፡፡

የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ቴክኒክ ኮሚቴ ከሚያቀርብለት ተጫዋቾች መካከል የራሱን የምርጫ ዘዴ ተጠቅሞ ቡድኑን ይመሠርታል፡፡ በራሱ ሥልጣን ከስብስቡ ውጪ ጥሩና ብቁ ናቸው የሚላቸውን ሌላ ተጫዋቾች መምረጥ መብት አለው፡፡ ምርጫውን በደንብ እንዲያካሂድ የአካል ብቃት ግምገማ ማድረግ ይችላል፡፡ የግጥሚያ ዕለት ለጨዋታው ያስፈልጋሉ ብሎ የገመታቸውን ተጫዋቾች ማሰለፍ ሙሉ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ የጨዋታ ሥልት መምረጥና መጠቀም ሙሉ መብቱ ነው፡፡ እሱ በወሰነው ሰዓት የፈለገውን ተጫዋች ወይም ተጫዋቾች ቀይሮ ተጠባባቂ ማስገባት ሙሉ ሥልጣን አለው፡፡ ስለዚህ ለሚመጣው ውጤት ሙሉ ተጠያቁ እሱ ብቻ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ብቃታቸው ዝቅተኛ የሆኑ ተጫዋቾች ሲቀርቡለት ካሉት ትንሽ የተሻሉትን ተጫዋቾች ይመርጣል፡፡ በተለይ የተሰጠው ጊዜ አጭር ከሆነ ለቡድኑ ድክመት በምንም ዓይነት ተጠያቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ሰውነት ቢሻው፣ ማሪያኖ ባሬቶ፣ ዮሐንስ ሣህሌ ከቀረቡላቸው ተጫዋቾች ነው ቡድኑኑ የገነቡት፡፡ አስማት ወይም ተዓምር ሊፈጥሩ አልተቀጠሩም፡፡ ክለባቸው እያሉ ዝቅተኛ የአካል ብቃት ይዘው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚመረጡ ተጫዋቾች በአንዴ አይለወጡም፡፡ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚገቡት ድክመታቸውን ይዘው ነው፡፡ የሚሰበሰቡት ጊዜ አጭር ከሆነ አሠልጣኙ ምንም ማድረግ አይችልም፡፡ መወቀስ ያለበት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሳይሆን ግዴታቸውን በደንብ ሳይወጡት አበላሽተው የላኩት የክለብ አሠልጣኞች ናቸው፡፡ የክለብ አሠልጣኞች የሚጠበቅባቸውን የቤት ሥራ በአግባቡ መወጣት አለባቸው፡፡ በክለባቸው ጠንካራ ተጫዋቾች ከሆኑ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ትልቅ ሸክም ከትከሻው ያነሳለታል፡፡

አሠልጣኝ የሚቀጠረው በጠባዩ ሳይሆን በችሎታው ነው፡፡ ስለአሠልጣኝ ሲወራ ሁሌ ስለዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ አንድ አትሌት ያለው ትዝ ይለኛል፡፡ ‹‹የዶ/ርን ስድብና ጩኸት ከቻልክ የዓለም ሻምፒዮን ትሆናለህ፤›› ብሎ ተናገረ፡፡ ዶ/ር ይሳደብ እንጂ ሙያውን እንደሱ የሚያከብር አሠልጣኝ እዚህ አገር እስካሁን አላየሁም፡፡ ሙያውን ማክበር ደግሞ በሚያሠለጥናቸው አትሌቶች ወዲያውኑ ይንፀባረቃል፡፡ ማንም አርፍዶ አይመጣም፣ ማንም አይለግምም፣ ሁሉም ከልቡ ይሠራል፡፡ ከሆስፒታል ወጥቶ ሜዳ ሆኖ ሲያሠለጥን አትሌቶቹ ሲሟሟቁ እሱ ፑሽአፕ ይሠራ ነበር፡፡ ጉዳት ሳይደርስበት የሚሠራው ልምምድ የሚገርም ነበር፡፡ ቦርጭ የሚባል ነገር ምንም አይታይበትም ነበር፡፡ በምሳሌ ማስተማር ማለት ይኼ ነው፡፡ ስንቱ የእግር ኳስ አሠልጣኝ ተጫዋቾቹ ሜዳ ላይ እየተለማመዱ ጆሮው ላይ ሞባይሉን ለጥፎ ሲያወራ ይታያል፡፡ ብሔራዊ ቡድን እንዲያሠለጥኑ እየተሰጣቸው ለረዳታቸው ሥራውን ይሰጡና በሞባይል ሲያወሩ ይታያሉ፡፡ ዶ/ር ወልደ መስቀል በሰዓቱ ሜዳ ላይ ይገኝ ነበር፣ እያንዳንዱን አትሌት ያርማል፣ ሙሉ ትኩረቱን ሜዳ ላይ ያውለዋል፡፡ ስለሰውዬው ውጤት ታዲያ እንናገር እንዴ? እስቲ የትኛው የአገራችን አሠልጣኝ ነው አንድ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ወደ አውሮፓ እንዲሄድ ያደረሰው? እነ ኤቶ፣ ድሮግባ፣ ካኑ፣ አብዲ ፔሌ፣ ኬይታ፣ ዌያ፣ ቱሬ ወዘተ. በአገር በቀል አሠልጣኞች ነው የተፈጠሩት፡፡ ዕድሜ ለሱፐር ሰፖርት በአሁኑ ወቅት እንኳን የመጨረሻው ዙር ውድድር ይቅርና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ብዙ ተመልካች አለው፡፡ ታዲያ የአገራችን እግር ኳስ እስከዚህ ምርጥ ቢሆን፣ ተጫዋቾቻችን ድንቅ ቢሆኑ ለምን አንዳቸውም የአገራችን ተጫዋቾች የተጫዋች ደላላ ዓይን መሳብ አቃታቸው? ትልቅ ድንቅ ችሎታ ያለው ተጫዋች ቢገኝ ሽሚያው አይጣል ነበር፡፡ እስካሁን ወደ አውሮፓ የተሸጋገረ የአገር ተጫዋች አልተገኘም፡፡ በዚህ ውጤት ብቻ የአገራችን አሠልጣኞች ማንነታቸውን ባይረሱ ጥሩ ነበር፡፡

 ስለውጭ አሠልጣኞች

ጋርዚያቶና ኦኑራ አንዳንድ ምርጥ ተጫዋቾች እንዳሉ አነጋግረውኛል፡፡ ጋርዚያቶ ዮርዳኖስ ዓባይና አሸናፊ ግርማ በግላቸው ሊያሠራቸው አቅዶ ነበር፡፡ የአካል ብቃታቸውን ደረጃ ከፍ ቢያደርጉት አውሮፓ ሄደው ለመጫወት ተስፋ እንዳላቸው ነግሮኝ ነበር፡፡ ኦኑራ አገር ለቆ ሊሄድ መሰነባበቻ ግብዣ ላይ ለብቻዬ አነጋግሮኝ፣ ‹‹እባክህ ኡመድ ኡኩሪ፣ ሽመልስ በቀለና በተለይ ተስፋዬ አለባቸው የአካል ብቃታቸውን ከፍ ብታደርግልኝ እንግሊዝ ላስመጣቸው እችላለሁ›› ብሎ ጠየቀኝ፡፡ የውጭ አሠልጣኞች እዚህ ሲመጡ ሁለት ችግር ይዘው ይገባሉ፡፡ አንደኛ ገና የውላቸው ፊርማ ቀለም ሳይደርቅ ከሌላ የውጭ ክለብ ጋር ድርድር ይጀምራሉ (ሚቾ፣ ኖይ፣ ስቶይኮቭ)፡፡ በሌላ በኩል ለአንድ ጭንቅላት ሁለት የሥልጣን ባርኔጣ አድርገው ይመጣሉ፡፡ አንድ ሰው አሠልጣኝና የተጫዋች ደላላ መሆን አይችልም (ሚቾ፣ ሴንፊት፣ ባሬቶ)፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሲያሠለጥኑ ሲመጡ አንዳንድ ተጫዋቾችን ተስፋ በመስጠት ሥነ ልቦናቸውን ይረብሻሉ፡፡ ክለቡ ሲጫወት ምንም የአሠልጣኙን ልዩ ትኩረት ያልሳበ ድንገት አውሮፓ ክለብ ላገኝልህ እችላለሁ ሲለው አዕምሮው ለምን አይረበሽም? ክለቡ ሲመለስ የባህሪ ለውጥ ማሳየት ይጀምራል፡፡ እዚህ ላይ ፌዴሬሽኑም ሆነ ክለቦች አንድ የውጭ አሠልጣኝ በሚቀጥሩበት ጊዜ ይኼን ጉዳይ በትክክል መነጋገርና ማጣራት አለባቸው፡፡ ባሬቶ ሁለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ፖርቱጋል ሊወስዳቸው አስቦ ነበር፡፡ ለሙከራ ሄደው ሳይሳካላቸው ቀረ፡፡ ሳስበው ይኼ አሠልጣኝ የእነዚህን ተጨዋቾች እውነተኛ የብቃት ደረጃ ያውቅ ነበር ወይ? ብዬ ጥያቄ እጠይቃለሁ፡፡ ብሔራዊ ቡድን ሲጠሩ በእውነት ብቃታቸውን ለክቶ ያውቅ ነበር ወይ? እንዳጋጣሚ ሁለቱንም ለክቼ ነበር የአካል ብቃታቸው በምንም አኳኋን አውሮፓ ሄደው ለመጫወት አያስችላቸውም ነበር፡፡ በነገራችን ላይ እንደመጣ ሂድና አነጋግረው ተብዬ የአካል ብቃት የሚያሠራ ሰው አለህ ወይ? ብዬ ስጠይቀው ምክትል አሠልጣኞቼ ያሠራሉ ብሎ እንደማይፈልገኝ ነገረኝ፡፡ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አካል ብቃቱ እዛው ምድር ቤቱ እንደተኛ ቀረ፡፡ የውጭ አሠልጣኞች አካል ብቃትን በተለከተ አብዛኞቹ ግነዛቤ እንጂ ዕውቀቱ የላቸውም፡፡ ምክንያቱም አገራቸው ጂም በየቦታው ከመኖሩም በላይ ከፍተኛ የጥንካሬ ሥልጠና ሙያተኞች ስላሉ የጥንካሬውን ልምምድ ለነሱ ይተውታል፡፡ ሆዜ ሞሪንዮ ብናስመጣው የአካል ብቃት ራሱ እንደማያሠራ አትጠራጠሩ፡፡ ነገር ግን ስለ ጥቅሙ ከፍተኛ ግንዛቤ ስላለው ሙያተኛ መድቡልኝ አለበለዚያ አገሬ እመለሳለሁ ብሎ እንደሚያስጠነቅቀን አትጠራጠሩ፡፡ ስለዚህ እዚህ በሚመጡት የፈረንጅ አሠልጣኞች በአካል ብቃት ዕውቀታቸው ማነስ ምንም መደነቅ አያስፈልግም፡፡ እርግጥ በአንድ በኩል አልፈርድባቸውም፡፡ ምክንያቱም አገራቸው በሌላ ሙያተኛ ሥራ ጣልቃ መግባት አይችሉምና፡፡ ሆኖም የአገራችንን ተጨዋቾች ችግር እያዩት በግላቸው ጥረት አለማድረጋቸው በጣም ይገርመኛል፡፡ በተለይ በኢንተርኔት ዘመን ቅዱስ ጊዮርጊስ ካስመጣቸው አሠልጣኞች ማርት ኖይ ብቻ ነው ስለተጨዋቾቹ የስብ መጠን አንዲለካ የጠየቀው፡፡ ሌላው መሸሽግ የሌለበት ችግር ደግሞ በመጠኑም ቢሆን ዘረኞች ናቸው፡፡ ከአውሮፓ ወደ አፍሪካ ሲመጡ እነሱ ሊቅ የአገሬው ሰው መኃይም አድርገው ነው የሚመለከቱት፡፡ እነሱ አንድ ጥቁር ሰው ፊት ቀርበው አለማወቃቸውን ከማመን ምድር ብትውጣቸው ይመርጣሉ፡፡ ሰው አይምጣብኝ የሚሉትም ለዚህ ነው፡፡ ድክመታቸውንና አለማወቃቸው እንዳይነቃ ልክ እንደኛዎቹ አሠልጣኞች ብቻዬን ልሥራ ወይም ከውጭ ሌላ ሰው ይምጣልኝ የሚሉ ጮሌዎች ናቸው፡፡ የሚያሠለጥኑት የአገራችን ተጨዋቾች ችግር እንዳለ መቀጠሉ ውጤታቸውን ስለሚመሰክር ሀተታ መጨመር አያስፈልግም፡፡ የጡንቻና የነርቭ ፊዝሎጂ ዕውቀትና አጠቃቀሙ ጉሊት ገበያ የሚገኝ ተራ ሸቀጥ እንደ ስኳር ድንች ወይም ሽንኩርት አይደለም፡፡ ነጭ ቆዳ ሰውነቱ ላይ ስለለበሰ መንፈስ ቅዱስ ለሱ የተለየ አስተያየት አድርጎ የኤክሰርሳይስ ፊይዝዮሎጂ ዕውቀት አልረጨበትም፡፡ እንደማንም ሱሪውን ፈትጎ ተምሮ ነው ዕውቀቱን መያዝ የሚችለው፡፡

ሌላ ችግራቸው ለሙያቸው እውነተኛ ፍቅር የላቸውም፡፡ ስንትና ስንት የውጭ አሠልጣኞች መጥተው አንድም ተጨዋች አበረታተው፣ ገፋፍተው፣ ረድተው፣ ጥሩ ደረጃ አድርሰው ወደ ከፍተኛ ሊግ (አውሮፓ) ሳያስገቡ ተመለሱ፡፡ አብዛኛው አልትሩኢዝም(Altruism) የሚባል ፀባይ/አቋም ያልተላበሱ፣ ለሆዳቸው ብቻ የሚያስቡ ናቸው፡፡ አልትሩኢዝም ለማስረዳት ንብ ጥሩ ምሳሌ ናት፡፡ በየቀኑ ከጠዋት እስከ ማታ ያሉትን አበባዎች ፍለጋ፣ ወለላ ቀስማ፣ ቀፎ ተመልሳ ንግሥቲቷን መመገብ፣ ግልገል ንቦቹን መቀለብ፣ የውጭ ጠላት ሲመጣ ተከላክላ፣ ሲያስፈልግም ሕይወቷን አሳልፋ ትሰጣለች፡፡  ስትናደድ ከመርፌዋ ጋር የሆድ ዕቃዋ ስለሚወጣ ትሰዋለች፡፡ ባጭሩ አልትሩኢስት (Alturist) የራሱን ጥቅም ወደ ጎን ትቶ ለሌላ የሚያስብና የሚጨነቅ ሰው ነው (ቅድስት ማዘር ቴሬዛ)፡፡ ሦስት ዓመት ሙሉ አሥራት መገርሳን የመሰለ ጥሩ ቴክኒክ ያለውን ተጨዋቾች ሲያሠለጥን ስቶይኮቭ ምነው ምክር ነፈገው? ሚቾ ሙሉጌታ ምህረትን፣ ያሬድ ዝናቡን፣ ደጉን፣ ወዘተ ለምን ደረጃቸው ከፍ እንዲል አልመከራቸውም? አልገፋፋቸውም? አልሞከረም? እነ ዳንዬሉና ዶሴና አዳነን፣ አሉላንና፣ ኡመድን ወዘተ … ለምን አልመከሯቸውም?  አልረዷቸውም?  ቢያንስ የእነዚህን ተጨዋቾች ህሊና ቀስቅሰው የፈለገው ጥቅሙን ተረድቶ፣ ለፍቶ ደረጃውን ቢያሻሽል በእውነት ግዳጃቸውን በአግባቡ በተወጡት ነበር፡፡ ከፍተኛ ዓላማቸው ባጭር ጊዜ ከብረው መሄድ ብቻ ነው፡፡

የአገራችን ሰው በወንዞች ንጉሥ ቁጭት ተነስቶ ‹‹ዓባይ ማደሪያ የለውም ግንድ ይዞ ይዞራል›› ብሎ ሲተርት ነበር፡፡ አፍሪካ መጥተው የሚያሠለጥኑት የውጭ አገር አሠልጣኞች ረግተው የሚኖሩበት አገር የላቸው ከአገር አገር ይዘዋወራሉ፡፡ ሃይማኖታቸው አንድ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ዶላር›› ዛምቢያን ያሠለጠነው ሔርቬ ረናር ዛምቢያ ጀመረ፣ ከዚያ ወደ አይቮሪኮስት አቀና፣ አሁን በመጨረሻ ደግሞ ሞሮኮ ገባ፡፡ ክሎድ ለሯ ካሜሩን፣ ሴኔጋል፣ ኮንጎ ዲአርሲ ቀጥሎ ሱዳን፣ ከዚያም አልጄሪያ እንደገና ሱዳን ተመለሰ፡፡ ቶም ሴንፊት ከኢትዮጵያ የመን፣ ከየመን ቶጎ ሄዷል፡፡ ከዚያም ወደ ዚምባቡዌና ናሚቢያ ተዘዋውሯል፡፡ ሚቾ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ከዚያ እንደገና አዲስ አበባ፣ ቀጥሎም ሩዋንዳ፣ ከዚያ ሱዳን በመጨረሻም ኡጋንዳ ሄዷል፡፡ ዋንጫ የወሰዱት ሔርቬ ረናር፣ ክሎድ ልሯና ጋርዚቶ ብቻ ናቸው፡፡

ጥሩ አሠልጣኝ በውድ ዋጋ መቅጠር ግዴታ አለ ወይ? በቀላል ክፍያ ልምጣ የሚል የውጭ አሠልጣኝ አጭበርባሪ ነው፣ ሆኖም በውድ ዋጋ ሁሌ ጥሩ አሠልጣኝ አይገኝም፡፡ ጋርዚቶ በ8,000 ዶላር ነበር እዚህ ያሠለጠነው፣ ማንም የማይክደው ለውጥ አምጥቶ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ወቅት የኤሜ ዣኬ ረዳት የነበረው ሮዤ ለሜር ዩሮ 2000 ፈረንሣይን አሠልጥኖ ለዋንጫ ያበቃበት የቱኒዚያ ብሔራዊ ቡድን ያሠለጠነው በ25 ሺሕ ዶላር ወርኃዊ ክፍያ ነበር፡፡ ቱኒዚያ ዋንጫ እንድታገኝ አላበቃትም፡፡ ጋርዚቶ አል ሜሪክን ያለፈው ዓመት ሲያሠለጥን 40 ሺሕ ዶላር ይከፈለው ነበር፡፡ (የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ ደርሶ ማዜምባ ተሸነፈ)፣ ደግሞ የወጣት ቡድኑን ለማሠልጠን 20 ሺሕ ዶላር ይቀበል ነበር፡፡ እርግጥ ውጤታማ አሠልጣኝ በቀላል ክፍያ አይመጣም፡፡ ሆኖም ጊዜ ወስዶ፣ አፈላልጎ፣ ሙያውን የሚወድና የሚያከብር፣ ዝና የጠማው፣ የሚያሠለጥነውን ቡድን ከፍተኛ ደረጃ ማድረስ የቻለውን ያህል የሚጥር፣ ብዙ ለፍቶ መስዋትነትም ከፍሎ ለውጥ ማምጣት የሚችል ከአሥር እስከ 15ሺሕ ዶላር ተከፍሎት ከመቶ አንድ ሰው ማግኘት ይቻላል (እንደ ጀማሪው ጋርዚቶ) ይህን ሰው ደግሞ ቶሎ ውጤት እንዲያመጣ ማስጨነቅ አያስፈልግም፡፡ አሠልጣኙን መቅጠር ለረዥም ጊዜ ለውጥ ነው፣ ማለትም ቢያንስ ለአምስትና ለስድስት ዓመት ሲሆን እሱ በመረጣቸው ወጣቶች (U17-U19) ቢሆን የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ፈረንጆች ለጊዜ ጊዜ ስጡት ይላሉ፡፡ የአገራችን አባባል ደግሞ ዛሬ አርግዙ ዛሬ ውለዱ አይባልም ብሎ ነገሩን ደምድሞታል፡፡

 ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ

ካፍ ፊፋ ባወጣው መስፈርት ስለሚመራ ወደ ካፍ ላይሰንሲንግ መግባት በጣም የሚደገፍ አካሄድ ነው፡፡ ሆኖም ይኼ ሒደት ለእግር ኳሳችን ለውጥ እንዳላመጣ መካድ አያስፈልግም፡፡ ነገሩ ቀደም ብሎ ስለገባውና የአገራችን አሠልጣኞች ችሎታ ውስንነት ተገንዝቦ ቅዱስ ጊዮርጊስ የውጭ አሠልጣኝ ማስመጣት ጀመረ፡፡ የውጭ ተጫዋች ማስመጣትም እሱ ቀደሰ፡፡ የአገራችን እግር ኳስ ችግር የጨዋታ ሥልት እንዳልሆነ በግልጽ ይታያል፡፡ ሆኖም ምንም ለውጥ አላመጡም፡፡ የቀድሞው የቴክኒክ ኮሚቴ ይኼን ችግር ሳያይ በዚያው ቀጥሎ ምንም ለውጥ ሳያመጣ ቆየ፡፡ አዲሱ ቴክኒክ ኮሚቴ ያለፈው ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ አንድ ሙያተኛ ስለአካል ብቃት ኮርስ እንዲሰጡ ጋበዘ፡፡ ያው እንደተለመደው ሜዳ ላይ በኳሱ ዙርያ ያተኮረ ሥልጠና ነበር፡፡ እንድታዛብ ተጋብዤ መጨረሻው ዕለት አስተያየት እንድሰጥ ተጠየቀ፡፡ ኮርሱ ያለምንም ጥርጥር ጠቃሚ ቢሆንም፣ ጎዶሎ ነው አልኩኝ፡፡ አንድ ነገር ስለጂም አጠቃቀም ሳይተነፍስ፣ ስለአካል ብቃት ግምገማና ትንታኔ፣ ስለ ወርኃዊና ዓመታዊ ዕቅድ አወጣጥ እንዲሁም የውጤቶች አጠቃቀም ሳያወራ ኮርሱ ተገባደደ፡፡ ባሁኑ ወቅት በየሆቴል ቤቱ አዳዲስ ጂሞች እየተከፈቱ ሳለ፣ ልክ እንደ አንደ ደህና መናጢ አገር ተቆጥረን ያልተሟላ ኮርስ ተሰጠን፡፡ ለወደፊት አንድ ከፍተኛ የውጭ ባለሙያ ከመምጣቱ በፊት ስለአገሪቱ እግር ኳስ ወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ ቢሰጠው አይከፋም፡፡ ከዚያ ኮርሱን አስተካክሎ አሠልጣኞቹ እንዲጠቀሙበት ማድረግ ይቻላል፡፡ አሁንም ቢሆን ችግሩ የቴክኒክ ወይም የታክቲክ አይደለም፡፡ የአካል ብቃት እንጂ፡፡ ዎኪንግ ፍትቦል (የሚራመድ፣ የሚያዘግም) ቢባል ይሻላል፡፡ እግር ኳስ እያሉ ጋዜጠኞች ሲያሾፉ ውሸት አይደለም ማለት አንድ ዝሆን ከአንድ ሸምበቆ በሰተኋላ ቆሞ ለመደበቅ እንደ መሞከር ነው፡፡

በሌላ በኩል አብዛኞቹ አሠልጣኞች የቋንቋ ችግር እንዳለባቸው ኮሚቴው እያወቀ ዝም ብሎ መቀመጥ አይችልም፡፡ ለምንድነው የራሱ ድረ ገጽ ከፍቶ አስፈላጊ መረጃዎች የማያቀርበው? አስፈላጊ ጽሑፎች በአማርኛ ተተርጉመው ቢቀመጡ ብዙ ጥቅም ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ በሰበቡም ለሚመጡት ተሳታፊዎች ኢንተርኔት አጠቃቀም ማስተማር፡፡ ለሥልጠና ድጋፍ የሚሰጡ ጠቃሚ ፊልሞች ተመርጠው ቢካተቱ መሻሻል ለሚፈልጉ አሠልጣኞች ከፍተኛ አሰተዋፅኦ ሊያበረክት እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ ፈረንሣዮች አንድ ጥሩ አባል አላቸው እሱም፣ ‹‹ነገሮች ስለሚካበዱ አይደለም የማንደፍረው ስለማንደፍር ነው እንጂ የሚካበዱት፡፡››

ፌዴሬሽኑ አሠራሩን ያስተካክል

ዘንድሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተመሠረተበት 70ኛ ዓመት በዓሉን እያከበረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዛሬ ሁለት ዓመት ደግሞ 75ኛ ዓመት በዓሉን ለማክበር እየተዘጋጀ ነው፡፡ ሁሉቱም በአገር በቀል ዜጎች ነው የሚተዳደሩት፡፡ ታዲያ የሁለቱንም ዕድገትና አሠራር ለማነፃፀር ማን ደፍሮ ይሞክራል? ደግሞም የአሠልጣኞቻችን በሽታ ፌዴሬሽኑ ሠራተኞች ላይ ተጋባ እንዴ? አሠልጣኞቻችን ጎናቸው ምርጥ የአትሌቲክስ አሠልጣኞች እያሉ አለማወቅን እንደ ውርደትና ሽንፈት እየቆጠሩ፣ ስለጽናት ልምምድ ብለው በተሳሳተና በአሳፋሪ መንገድ እግር ኳሳችንን መሳቂያ ሲያደርጉት ታዲያ፣ የፌዴሬሽናችን አመራሮች ምነው ከአየር መንገዳችን የአስተዳደርና ማኔጅመንት ልምድ አይወስዱም? አየር መንገዳችን የአገር ክብር ከመሆን አልፎ የአኅጉራችን አምባሳደር ለመሆን በቅቷል፡፡ መማር ያስከብራል፡፡

የሁለቱም ፆታዎች በተለያዩ ዕድሜ ደረጃ የሚገኙት የአገራችን ብሔራዊ ቡድኖች ዝግጅት ዝብርቅርቅ ያለ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ለዋናው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትልቅ ትኩረት ሲሰጥ ለሌሎቹ ግን እምብዛም ትኩረት አይሰጣቸውም፡፡ ሌሎቹ ቡድኖች በተሰበሰቡ ቁጥር አሠልጣኞቹም ሆኑ ተጫዋቾቹ ሁሌ የሚያነሱት ጉዳይ ቢኖር ለአጭር ጊዜ መሰብሰባቸው ነው፡፡ ይኼ አሠራር ዋጋ አስከፍሎናል እያስከፈለንም ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ከአብዛኛዎቹ ትልልቅ የዓለምም ሆነ የአኅጉራዊ ውድድሮች ወጥተናል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት አሠራር ከቀጠልን ውጤቱ ተመሳሳይ እንደሚሆን ምንም ጥርጣሬ የለውም፡፡ ለምን ድክመቱ እየታወቀ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዛው መንገድ ይቀጥላል? ችግሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሳይሆን የክለቦች ነው፡፡ አብዛኞቹ ክለቦች ትኩረት የሚሰጡት ለዋናው የእነሱ አምባሳደርና መጠሪያቸው ለሆነው ፕሪሚየር ሊግ ለሚሳተፈው አዋቂ ወንድ ቡድን ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለቦች የተለያዩ ዕድሜ ያላቸው የወንድ ቡድኖች እንዲሁም የሴት ቡድኖች እንዲያካትቱ ባያስገድዳቸው ኖሮ እርግፍ አድርገው አንደሚተዋቸው ምንም አያጠራጥርም፡፡ ለዋናው የወንዶች ቡድን በየቀኑ ቁርስ፣ ምሳና ራት፣ ሕክምና፣ ትጥቅ ሲችሉ ለሌሎቹ ቡድኖች ግን አብዛኛውን ጊዜ የልምምድ ዕለት ብቻ ነው የሚመግቡት፡፡ እሱም ቢሆን ምሳ ብቻ ነው፡፡ የአገራችን የእግር ኳስ ተስፋ እንደዚህ እየተናቀ የት እንደሚደርስ እግዚአብሔር ብቻ ይወቀው፡፡ ለእነዚህ ቡድኖች ነው ትልቅ ትኩረት መስጠት ያለበት፡፡ በተለይ በዋናው የአካል ዕድገት ዘመናቸው ስለሚገኙ ከፍተኛ እንክብካቤ ያሻቸዋል፡፡ በዚህ ዕድሜ ለአካል ዕድገትና ግንባታ ጥሩ ምግብ ቢያገኙ ጠንካራ ወጣቶት ሆነው ያድጉና ለወደፊት የስፖርተኛ ሕይወታቸው ጥሩ ዋስትና ያገኛሉ፡፡ የዛሬ 15 ዓመት አቶ መላኩ ጴጥሮስ ፈረንሣይ አገርን እንደ የእግር ኳስ አካዳሚ ጎብኝቼ ሪፖርት እንዳቀርብለት ጠይቆኝ ነበር፡፡ ፈረንሣይ ውስጥ ስድስት የክልል አካዳሚዎች እንዲሁም አንድ ብሔራዊ አካዳሚ አለ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እኔ የምኖርበት ክልል አንድ አካዳሚ ስለሚገኝ አንድ ሙሉ ቀን ውዬ የፈለጉትን ጥያቄ ጠይቄ መልስ አግኝቼ ሪፖርቴን አቀረብኩ፡፡ በተለይ አንድ ወሳኝና አንገብጋቢ ጥያቄ ወጣቶች መቼ የጥንካሬ ለምምድ እንደሚጀምሩ ዳይሬክተሩን ጠየኩት፡፡ መልሱ በ16 ዓመታቸው ነው ብሎ ሦስት ምክንያቶች ሰጠኝ፡፡ አንደኛ 16 ዓመት ዕድሜ ሲደርሱ ወንዶች ከብልታቸው ቴስቶስቴሮን የሚባል ሆርሞን የሚያመነጩበት ምርጥ ወቅት ነው፡፡ ይኼም ሆርሞን ከሰውነታችን የሚመነጭ ሥነ ሕይወታዊና ተፈጥሯዊ የጡንቻ ማዳበሪያ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ወቅት የጥንካሬ ልምምድ ባሳይንሳዊ መንገድ ቢሠራ የልጁ ጡንቻዎች ይደነድናሉ፣ ይጠነክራሉ፣ ጉልበትም በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል፡፡ ሁለተኛ በዚህ ዕድሜ ወጣቶቹ ማንነታቸውን ለማሳወቅ በጣም ፉክክር ይወዳሉ፡፡ ከሌሎች አኩዮቻቸው ጋር መወዳደር በጣም ይሞክራሉ፡፡ ሦስተኛ በተለይ ይኼን ወቅት ሳትጠቀምበት ካሳለፍከው ወጣቱ በኋላ የጥንካሬ ልምምድ መሥራት እምብዛም አይፈልግም፣ ያምፃል፡፡ ስለዚህ ትክክለኛውን የጥንካሬ ልምምድ ታይሚንጉ (Timing) ወቅት ልክ ይኼ ዕድሜው ነው ብሎ አሳሳበኝ፡፡ ታዳያ የኛ የክለብ ኃላፊዎች ለወጣቱ ለምን ትክክለኛውን ትኩረት አይሰጡትም? ቤቱን ባዶ አድርጎ ለዋና ቡድን ብቻ ትኩረት መስጠት ከግዙፍ ዋርካ በስተኋላ በረሃ የሚባለው አባባል ይሆናል፡፡ ወጣት መናቅ የወደፊት ዕድላችን በር መዝጋት ነው፡፡ በትክክል ቢያዙ ለዋናው ቡድን ተስፋ ከመሆንም በላይ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ውጭ ተሸጠው ጥሩ የገቢ ምንጭ ይሆኑ  ነበር፡፡ ሌላው ጉዳይ ይህ ድክመት እንዳለ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እያወቀ ለምን ነገሩን ቀድሞ ለመፍታት አይሞክርም? ክለቦች አሠራራቸውን ያስተካክሉ ማለት ትክክለኛ አቋም ቢሆንም፣ ለምን ራሱ ጊዜያዊ ዕርምጃ አይወስድም? ለምሳሌ በታላቁ የዕረፍት ወቅት 30 ምርጥ ወጣቶች መልምሎና መርጦ በካምፕ ሰብስቦ የአካል ብቃት ልምምድ እንዲወስዱ ለምን ዕድሉን አይሰጣቸውም? ከዚያም አልፎ ለእነዚህ ተስፋ ላላቸው ልጆች ለምን ፌዴሬሽኑ ጂም ከፍሎላቸው ልምምዳቸውን ሳያቋርጡ ዓመቱን ሙሉ እንዲቀጥሉ አያደርግም? የምግብ ድጋፍ ቢሰጥም ምን ይጎዳዋል? መቼ ይሆን ከሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ አስተሳሰብ የምንላቀቀው? እነዚህ ወጣት ቡድኖች ሲሰበሰቡ ሁሌ አሰልቺ የሆነው ንግግራቸው ‹‹ልምምድ አሪፍ ነው ነገር ግን ለመለማመድ በቂ ጊዜ አላገኘንም፤›› ነው፡፡ ይኼ የፌዴሬሽኑ አሠራር ተመርጠው ለሚመደቡት አሠልጣኞች ለሚያስከትለው መጥፎ ውጤት ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥሩ ሰበብ ይሆንላቸዋል፡፡ አንድ አሠልጣኝ አንድ ቡድን ይዞ የሚያሠለጥነው አስማት ወይንም ተዓምር ለመሥራት አይደለም፡፡  ስኬታማ ለመሆን ነገሮች ካልተሟሉለት ወደ አቦ ሰጥና ወደ ቁማር መሄዱ አይቀርም፡፡

የዛሬ ሦስት ዓመት በግሌ ተነሳሽነት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ለመርዳት አንድ ሰፊ ጥናት አኪያሂጄ ነበር፡፡ የግብፅ፣ የቱኒዝያና የኬንያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብሮች አጥንቼ ከእዚህኛው ጋር አነፃፅሬ የአገራችን ችግር በደንብ አውጥቼ የሚያሳይ ጥናት በራሴ ወጪ አንድ ብር ሳልጠይቅ ለፌዴሬሽኑ በነፃ አበርክቼ ነበር፡፡ ይኼ ያካሄድኩት ጥናት አውሮፓ ዩኒቨርሲቲ አንድ የስፖርት ማኔጅመንት ተማሪ ቢያቀርበው ቢያንስ የቢኤ ዲግሪ ማግኘት ይችል ነበር፡፡ ብጠበቅ ያን ጥናት እንዳቀርብ አንድም አጋጣሚ ሳይሰጠኝ ጊዜው አለፈ፡፡ በተለይ አሁን ካለው ሁኔታ አዲስ ክስተት ተፈጥሮ ራቅ ያሉ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ክለቦች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቢቀላቀሉ (አሶሳ፣ ሁመራ፣ ጎዴ ወዘተ…) እንዴት ችግሩን መፍታት ይቻላል ብዬ መላምት አስቀምጬ ነበር፡፡ ጎርፍ ከመምጣቱ በፊት ነው ቦይ መሠራት ያለበት ብዬ ለማሳሰብ ነበር ይኼን ጥናት የሰጠሁዋቸው፡፡ ምንም ስላላስከፈልኳቸው ይሆን እንዴ ጥናቱን ትኩረት ያልሰጡት? የናቁት? ዝብርቅርቅ ያለው የአገራችን የፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ለእግር ኳሱ ዕድገት ማነቆ መሆኑ ምንም ጥርጣሬ የለውም፡፡ ውጤታማ የአኅጉሩ ሊጎች አንደኛ የተዘበራረቀ አኪያሄዱ የላቸውም፡፡ የኢፕሊ በአዲስ አወቃቀር ሲጀምር ለአፍሪካ የክለብ ሻምፒዮና ለሚካፈሉ ቡድኖች እንዲዘጋጁ መርሐ ግብሩ ይቋረጥ ነበር፡፡ ቢያዩት ምንም ለውጥ ስላላመጣ ልክ እንደ ውጭ መሥራት ተጀመረ፡፡ ሻምፒዮናው እየቀጠለ ቡድኖቹ የውጪ ውድድራቸውን በመሳተፍ ቀጠሉ፡፡ ለብሔራዊ ቡድናችን በሆነው ባልሆነው የኢፕሊ መቋረጥ የለበትም፡፡ ደካማ ፕሪሚየር በምንም ተዓምር ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን አይፈጥርም፡፡ የኢፕሊ መዳከም፣ መግደል ብሔራዊ ቡድኑን ማዳከም፣ መግደል ነው፡፡ ወርቅ እንቁላል የምትጥለውን ዶሮ አትረድ ይላል የፈረንጅ አባባል፡፡ መሠረታዊ ችግሩ በየክለቦቹ የአካል ብቃት ዝግጅት የሚገባውን ቦታ አለመስጠቱ ሆኖ ሳለ መርሐ ግብሩን በሆነው ባልሆነው ምክንያት እየቆራረጡ የብሔራዊ ቡድን ችግር ሳይፈታ እንደቀጠለ ይሄዳል፡፡ ለምን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እያንዳንዱን የኢፕሊ ተሳታፊዎች እንዳቅማቸው ቢያንስ አንድ ችሎታ ያለው የአካል ብቃት አዘጋጅ እንዲቀጥሉ አስገዳጅ ሕግ አያወጣም? ለአገራችን እግር ኳስ ዋና ዘላቂ መፍትሔ ያኔ እንደሚገኝለት አትጠራጠሩ፡፡     

በሌላ በኩል በተቻለ ሁኔታ የካፍን ዓመታዊ የውድድር መርሐ ግብር አክብሮ ሥራ ላይ ማዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በወቅቱ የወዳጅነት ጨዋታዎች እንዲያደርግ በቂ ዕድል ያስፈልጋል፡፡ ይኼ ካልሆነ መቼ ነው የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ አዲስ ተጨዋች የመፈተሽ ዕድል የሚያገኘው? ፈረንሣዮች ማስተዳደር አስቀድሞ ማቀድ ነው ይላሉ፡፡ ከበፊት አሠራር ለውጥ ቢታይም ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ አሁን የዓመቱ ውድድር የሚጀመርበት ቀን ቀደም ብሎ ይታወቃል፡፡ ይኼ ራሱ ከድሮ ትልቅ መሻሻል ነው፡፡ ሆኖም እንደሌላው ውጤታማ አገር ለምንድነው የዓመቱ መርሐ ግብር በአንዴ የማይወጣው? ጥርጣሬ መፍጠሩ ስለማይቀር ለምን የግማሽ ዓመቱ መርሐ ግብር ብቻ ይወጣል? (የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የመጀመርያውን ዙር ውጤት ዓይቶ ነው ወይ የሁለተኛውን ዙር መርሐ ግብር የሚያወጣው? የሚል ጥርጣሬ ማንሳቱ አይቀርም) ያሁኑ መርሐ ግብር አወጣጥ በተለይ ሁለተኛው ዙር ለመጨረስ ያለው ጥድፊያ የአካል ብቃት ፀር ነው፡፡ በጨዋታዎች መካከል ያለው የማገገሚያ ጊዜ በጣም አጭር በመሆኑ፣ ቡድኖች ለመሄድና ለመመለስ የሚያባክኑት ቀናት፣ በጨዋታዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከመፍጠሩም በላይ ለአካል ጉዳት ያጋልጣቸዋል፡፡ አሁንም ደግሜ ደጋግሜ እናገረዋለሁ መሠረታዊ ችግሩ በክለቦች ደረጃ በቂና ትክክለኛ የአካል ብቃት ስለማይሠራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ትኩረት መስጠት ያለበት ለክለቦች እንጂ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አይደለም፡፡ መርሐ ግብር በሚወጣበት ወቅት ሳይንስን መፃረር የለበትም፡፡ የማገገሚያ ጊዜ መጠበቅ አለበት፡፡ በሌላ በኩል የቴክኒክና የአካል ብቃት ልምዳቸውን ማስተጓጎል የለበትም፡፡ አብዛኛዎቹ የአውሮፓ ሊጎች 38 ሳምንታት ሲቆዩ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26 ሳምንታት ብቻ ነው የሚውለው፡፡ እንዴት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ይኼን አጭር ሻምፒዮና ቀልጠፍ ባለ መንገድ ማስተናገድ አቃተው? በግጥሚያዎች መካከል ያለው የቀናት ልዩነት፣ በአንደኛውና በሁለተኛው ግማሽ መርሐ ግብር መካከል ያለው የእረፍት ቀናት ብዛት፣ በመጨረሻም ታላቁ ዓመታዊ እረፍት ለስንት ሳምንታት መቋረጥ እንዳለበት በምድብ ተጠንቶ መቀመጥ አለበት፡፡ ልምምድ አካልን ልክ እንደሚገነባ ግምብ ከፍ ሲያደርገው በተቃራኒው መንገድ ደግሞ ልምምድ ሲቆም የግምቡ ብሎኬቶች እየተነሱ ግምቡ ቀስ በቀስ ይፈርሳል፡፡ እረፍቱ ከመጠን በላይ ከረዘመ ተጨዋቾቹ ብቃታቸው በጣም ይወርድና ወደ ልምምድ ሲመለሱ ድሮ ወደ ነበሩበት የብቃት ደረጃ ለመመለስ በጣም ይቸገራሉ፣ ይለፋሉ፡፡ መሻሻል የጠፋውም አንዱ ምክንያት ይኼ ነው፡፡ የአገራችን ተጨዋች የሚለማመደው ለማሻሻል ሳይሆን ቀድሞ ወደነበረው ደረጃው ለመመለስ ብቻ ነው፡፡ እግር ኳሳችን ሁሌ ታጥቦ ጭቃ ሆኖ የቀረው ለዚህ ነው፡፡ የተለያዩ የአገራችን የስፖርት ተቋማት የተለያዩ የስፖርት ሙያተኞች ደጋግመው የመጠቀም ዝንባሌ ያሳያሉ፡፡ ጥሎ የማይጥለው የስፖርት አስተዳደር ሰብዓዊ ግዴታውን ልክ እንደ አንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት ይወጣው እንጂ ለስፖርቱ ማደግ ማነቆ መሆኑ እንደቀጠለ ነው፡፡ የዑደት አጠቃቀም ችሎታ (Recycling Capacity) የሚያስገርም ቢሆንም፣ በአገራችን ችሎታና ብቃት ያላቸው ሙያተኞች ገበያ ላይ እምብዛም እንደማይገኙ ያሳያል፡፡ እነዚህ አሠልጣኞች ከስህተታቸው መማር ስለማይችሉና ስለማይፈልጉ ደጋግመው የለመዱትን ስህተት መልሰው ይሠራሉ፡፡ አንድን ተመሳሳይ ነገር ደግሞ ደጋግሞ በመሥራት የተለየ ውጤት መጠበቅ አይቻልም ብሎ ሊቁ አንስታይን ተናግሯል፡፡ የአገራችን እግር ኳስ የዚህ ሁኔታ ሰለባ መሆኑ አያስደንቅም፡፡ የአገራችን ፌዴሬሽን ቤቱን በኩራዝ መብራት እያበራ እግር ኳሳችንን በኤሌክትሪክ ብርሃን እንዲያንፀባርቅ መመኘት የለበትም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...