Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እኩል ለማነቆ አሠራሮችም መፍትሔ

የአገሪቱ ኢኮኖሚ በየጊዜው ዕድገት እያሳየ መጓዙ እርግጥ ነው፡፡ የአገሪቱን ዓመታዊ የዕድገት መጠን የሚገልጹ የመንግሥትና የሌሎች ተቋማት አኃዞች ቢለያዩም ዕድገቱ ስለመኖሩ የሚመሰክሩ ናቸው፡፡ በኢኮኖሚያዊ የዕድገት እውነታው ላይ ስምምነት ካለን፣ አንዳንድ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ነጥለን ስንመለከት ግን የሚታሰበውን ያህል ዕድገት የማያሳዩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ለምሳሌ የወጪ ንግድና ኢንዱስትሪ በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የእነዚህን ዘርፎች ክንዋኔ የሚያመለክቱ አኃዛዊ መረጃዎች ሲታዩ ውጤታቸው ፀጉር የሚያስነጭ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ዘርፎቹን ወደፊት ለማራመድ ተደረጉ የተባሉት ጥረቶች እንደታሰበው ለውጥ አላመጡም፡፡ ሁለቱ ዘርፎች የሚጠበቅባቸውን ያህል አለመጓዛቸውም አጠቃላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ምናልባትም አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ጣዕም እንዳይሰጥ አድርገውታል ማለት ይቻላል፡፡

ከዚህ ቀደምም ቢሆን የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደኋላ ከመጐተት ባሻገር ለፋይናንስ ዘርፉ እንቅስቃሴም ፈተና ሆኖ ቆይቷል፡፡ የሁለቱ ዘርፎች አዝጋሚነትም ኢንዱስትሪን አሳድጐ ከውጭ የሚገባውን ምርት በአገር ውስጥ መተካት እንዳይቻል አድርጓል፡፡ የኢንዱስትሪ አምራችነት አልተጀመረም ማለት ያስችላል፡፡ ቢጀመርም 12 ከመቶ የኤክስፖርት ድርሻ ያለው በመሆኑ አገሪቱ በጠቅላላው ጥሬ ዕቃ ላኪ እንድትሆን አስገድዷታል፡፡ ከውጭ ጥሬ ዕቃዎችን በማስገባት የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች በሚፈልጉት መጠን የውጭ ምንዛሪ እንዳያገኙና እንደ ልብ እንዳይሠሩ አድርጓል፡፡

በአጠቃላይ በእነዚህ ዘርፎች ደካማነትና በሌሎችም ምክንያቶች በቂ የውጭ ምንዛሪ ማፍራት ባለመቻሉ የውጭ ምንዛሪ የሚፈልጉ ደንበኞች በወረፋ እንዲስተናገዱ አስገድዷል፡፡ ሁሉም በሚፈለገው መጠን የውጭ ምንዛሪ አግኝቶ ሥራውን በአግባቡ ቢሠራ ሊኖር የሚችለውን ለውጥ መገመት ቀላል ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱም አሁን ከሚታየው በላይ ሊሆን እንደሚችል ለመገንዘብ ኢኮኖሚስት መሆንን አይጠይቅም፡፡ ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የውጭ ምንዛሪን በተመለከተ ከተናገሩት ንግግር መገንዘብ እንደሚቻለውም፣ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምን ያህል እንደሆነ የሚጠቁመን ነው፡፡ በንግግራቸው እጥረቱ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ በሚገባ ያስገነዘቡበት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

በመሆኑም የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ የሞት ሽረት ጉዳይ እንደሆነ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ በንግግራቸው መሠረት የውጭ ምንዛሪ ግኝታችንን ማሳደግ ግዴታ ሆኖ ይታያል፡፡ ይህም እንዲሆን አስፈላጊው ጥረት ሁሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በውጭ ምንዛሪ ዙሪያ ያለው ችግር ግን የአቅርቦት እጥረት ብቻ እንደሆነ ተደርጐ መወሰድ የለበትም፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ለማሳደግ ሊደረጉ የሚገባቸው ጥረቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ያለውንም በአግባቡ የመጠቀሙ ጉዳይ በእኛ ሁኔታ ራሱን የቻለ ችግር እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

በእጅ ያለውን በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እስካልተቻለ ድረስና የውጭ ምንዛሪውን በአግባቡና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሊያስተዳድር የሚችል አሠራር ማስፈን እስካልተቻለ ድረስ ጉዳቱ ቀላል አይሆንም፡፡

ከሰሞኑ እንደሰማነውም የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ለወራት መጠበቁ ሳያንስ፣ ከወራት ጥበቃ በኋላ ሲገኝም፣ በቅናሽ ዋጋ አወዳድሮ ምርት ለመግዛት የሚያስችለው ዕድል ተዘግቷል መባሉን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ 

ከነጋዴዎች እንደተሰማው የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ወረፋ በሚጠበቅበት ወቅት በተገኘው ምንዛሪ የባንክ መተማመኛ ወይም ኤልሲ ሲከፈት መጀመሪያ ውለታ ከተገባለት ውጭ ግዥ መፈጸም አይቻልም መባሉ፣ የውጭ ምንዛሪው በተፈቀደበት ወቅት የተሻለ ዋጋ ሊያቀርብ ከሚችል ኩባንያ ግዥ መፈጸም እንዳይቻል ማገዱ ነጋዴውን እየጐዳ ነው፡፡ ከጥቂት ወራት ወዲህ የተጀመረው አዲስ አሠራር፣ በቁጠባ ልንጠቀምበት የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ እንድናባክን እያደረገ ብቻ ሳይሆን ይህንን አሠራር የተገነዘቡ ዕቃ አቅራቢዎችም ዋጋቸውን ሰቅለው ጫና እንዲያሳድሩ በር ከፍቶላቸዋል፡፡ 

ከመነሻው የዋጋ ማቅረቢያው ከገባለት ኩባንያ ውጭ ግዥ መፈጸም መከልከሉ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ያለአግባብ እንዲባክን እያደረገ ነው በሚል ጉዳቱን የሚያሳይ መረጃ ጭምር በማቅረብ መንግሥት ጉዳዩን እንዲያጤን ለቀረበው ጥያቄ መልስ አለመስጠቱ እየተነገረ ነው፡፡ እንዲህ ያሉት ችግሮች ጥቃቅን ይምሰሉ እንጂ የውጭ ምንዛሪን በአግባቡ እንዳንጠቀም እንቅፋት ይሆናሉ፡፡ ይህ መሆኑ በደንብ ከታወቀ ደግሞ አሠራሩን ማሻሻል ምን ይገዳል? ያለውን የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ ለመጠቀም የተዘረጋው አሠራር ችግር አስከተለ ከተባለ፣ ነገሩን አጢኖ እርምት መውሰድ ይገባል፡፡ እርግጥ ነው እጥረት ባለቁጥር ችግር ይፈጠራል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ግን የባንኮች የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት የጠራ እንዲሆን ማድረግ እንጂ የባሰ ችግር የሚያስከትል አሠራር መዘርጋት የለበትም፡፡ እጥረቱ በሚፈጥረው ቀዳዳ የአገልግሎት መጓደል ብሎም ለሙስና በር መክፈቱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ከደካማ አሠራር ጋር ተዳምሮ በየፈርጁ ብዙ ችግር ማስከተሉ አይጠረጠርም፡፡ ስለዚህ የጠራ አሠራር መዘርጋት የግድ ይላል፡፡

ኤልሲ ከተከፈተና የውጭ ምንዛሪው ከተፈቀደ በኋላ በአማራጭ ለመጠቀም የሚያስችለው አዲስ አሠራር ካልተስተካከለም የሚያሳድረው ተፅዕኖ በደንበኞች ምሬት ላይ ብቻ አይገደብም፡፡ ለበጐ የታሰበው አሠራር አገራዊ ጉዳት ለማስከተል ምክንያት ሊሆን ስለሚችል፣ ገዥው ብሔራዊ ባንክ ጉዳዩን ሊፈትሽ ይገባል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሞት ሽረት ትግል ያሻል እንደተባለው ሁሉ ያለውንም ዝቅተኛ የውጭ ምንዛሪ መጠን በአግባቡ መጠቀም ብሎም በፍትሐዊነት እንዲከፋፈል ማድረግ፣ ግልጽና በተሻለ ደረጃ ሁሉንም በእኩል የሚያገለግል አሠራር ይዘርጋ፡፡ የአገር ዕድገትም የበለጠ ትርጉም የሚኖረው የውጭ ምንዛሪን ግኝትን ከማሳደግ ጐን ለጐን ለአጠቃቀሙም ሲደከም፣ ሲጣር ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት