Wednesday, February 1, 2023

እስራኤል ወደ አፍሪካ ለምን?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እ.ኤ.አ. ከ1980ዎቹ ጀምሮ በተናጠል ለአገሮች ካልሆነ በስተቀር ለአፍሪካ አኅጉር የፖለቲካ ለውጦች ትኩረት የነፈገችው እስራኤል፣ ከ30 ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን ገርበብ ያለ በሯን ለአፍሪካ መክፈቷን በይፋዊ ጉብኝት አስታውቃለች፡፡

የወቅቱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትያናሁ ይፋዊ ጉብኝታቸውን በአራት የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ባለፈው ሳምንት አድርገዋል፡፡

ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያና ኢትዮጵያ ለእስራኤል ጉብኝት የተመረጡ አገሮች ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. ጁላይ 6 ቀን 2016 በኬንያ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ፣ ‹‹እስራኤል በድጋሚ ወደ አፍሪካ እየተመለሰች ነው፣ አፍሪካም ወደ እስራኤል፤›› በማለት የሚጐበኟቸው አገሮች መሪዎች እስራኤል ቀደም ሲል በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ የነበራትን የታዛቢነት ደረጃ ለማግኘት እንዲደግፉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በኡጋንዳ ቆይታቸውም ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሲቬኒ ጋር ከመነጋገራቸው በተጨማሪ፣ ጐን ለጐን በጠሩት ስብሰባ የሰባት ምሥራቅ አፍሪካ አገሮች መሪዎች ተገኝተዋል፡፡

እነዚህም የሩዋንዳ፣ የኬንያ፣ የኡጋንዳ፣ የዛምቢያ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የታንዛኒያና የኢትዮጵያ ናቸው፡፡

በዚህ ስብሰባቸው ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትር ኔትያንያሁ በዋናነት በአካባቢው የፀጥታ ሁኔታን በተመለከተ ከአገሮቹ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡

‹‹የአፍሪካ መሪዎች አገራቸውን ቦኮ ሐራም፣ አልሸባብና ሌሎች አሸባሪ ቡድኖች ከፈጠሩት ሥጋት ሊጠብቁ ይገባል፡፡ ከእስራኤል ጋር የትብብር ግንኙነት የማይፈልግ የአፍሪካ አገር የለም፡፡ ትብብራችንም በዚህ ዙሪያም ሊጠናከር ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ኤምባሲዎቻቸውን በእስራኤል ከፍተው ማየት ምኞታቸው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ጉብኝታቸውን በመቀጠል ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ፣ ከሌሎቹ አገሮች በተለየ ለሁለት ቀናት በኢትዮጵያ ቆይተዋል፡፡ በቆይታቸውም ከሌሎቹ የጐበኟቸው የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በተለይ በአገሪቱ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ተገኝተው በቀጥታ ለሕዝብ በተላለፈ ሥርጭት ንግግር አድርገዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ትስስር በሰለሞን ዘመነ መንግሥት የተጠነሰሰና በክርስትና መስፋፋት ወቅት የቀጠለ መሆኑን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሁለቱ አገሮች ታሪካዊ ትስስር እሴታዊ መስተጋብርን ከፍ እንዳደረገ ተናግረዋል፡፡

‹‹እናንተ ኢትዮጵያውያን ለነፃነታችሁ እንደተጋደላችሁ በሞታችሁም ነፃነታችሁን እንዳስከበራችሁ፣ የውጭ አገዛዝን እምቢ ብላችሁ አባቶቻችሁ ባወረሷችሁ ነፃ መሬት ላይ ነፃ ሕዝብ ሆናችሁ በመጠቀላችሁ እንኮራባችኋለን፡፡ እናከብራችኋለን፡፡ ለነፃነት ያደረጋችሁት ትግልም አንድ ያደርገናል፤›› ብለዋል፡፡

እስራኤል በትልቁ ወደ አፍሪካ መመለሷን የሚናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔትኒያሁ፣ ሽብርተኝነትን በጋራ መዋጋት ዋነኛ አጀንዳቸው ቢሆንም፣ እስራኤል የአፍሪካን ብሎም የኢትዮጵያን ዕምቅ የኢኮኖሚ አቅም እንደተመለከተች ገልጸዋል፡፡ በእስራኤል የሚታተሙ ጋዜጦች በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሶማሊያ መንግሥት ፕሬዚዳንት ጋርም ጉብኝታቸውን ከመጀመራቸው አስቀድሞ መነጋገራቸውን ዘግበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትኒያሁ በአራቱም የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጉብኝታቸው ከመሪዎቹ የጠየቁት ቁልፍ ነገር፣ እስራኤል ቀድሞ በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ የነበራት የታዛቢነት ደረጃ እንዲመለስላት ነው፡፡

እስራኤል እ.ኤ.አ. እስከ 1980ዎቹ ድረስ በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ የታዛቢነት ደረጃ የነበራት ሲሆን፣ በርካታ የአፍሪካ አገሮች በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የአፓርታይድ አገዛዝ ከመቃወማቸው ጋር ተያይዞ ፊቷን ከአፍሪካ እንዲሁም የነበራትን የታዛቢነት ደረጃም ገሸሽ አድርጋ ቆይታለች፡፡

ለምን አሁን?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔትኒያሁን፣ ‹‹እስራኤል ወደ አፍሪካ በትልቁ ተመልሳለች፤›› በማለት ያደረጉት ንግግርን በአካባቢው ካለው አለመረጋጋት፣ ከሽብር ዓለም አቀፋዊ ባህርይና ከአፍሪካ አስፈላጊነት ጋር ያያያዙት ቢሆንም፣ ሌሎች በርካታ ኃያላን አገሮች ይህንን ሥጋት ቀድመው በመገንዘብ ትኩረታቸውን ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ካደረጉ አሥር ዓመት ባስቆጠሩበት ወቅት፣ እንዲሁም የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በራሳቸው ሽብርን እንዲዋጉ የሚችሉበት አቅምን መፍጠር ከጀመሩ በኋላ መሆኑ ጥያቄ ያጭራል፡፡

አዲስ የተፈጠረ ሥጋት ሳይኖር እስራኤል ወደዚህ አካባቢ ለምን አተኮረች የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ቢሆንም፣ ተንታኞች ግን ትኩረታቸውን በኤደን ባህረ ሰላጤ ባለው አለመረጋጋት ላይ አድርገዋል፡፡

የኤደን ባህረ ሰላጤ በደቡብ ጠርዝ በሶማሊያ አለመረጋጋት፣ እንዲሁም በሰሜን ጠርዝ ማለትም የዓረብ ፔንሱላ በሆነችው የመን ከሽብር ጋር ተያይዞ የተፈጠረው አለመረጋጋት አገሪቱን ወደ መንግሥት አልባነት ከመቀየሩም በላይ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራውን የዓረብ አገሮች የየመን የጦር ጥምረት ፋይዳ ቢስነት እስራኤል ጉዳዩን በይበልጥ እንድትከታተለው አስገድዷታል በማለት ትንተናቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

ሳዑዲ ዓረቢያ በምትመራው የኤደን ባህረ ሰላጤ የጦር ጥምረት ውስጥ አባል የሆኑ አገሮች በሙሉ በእስራኤልና በዓረብ ፖለቲካ ውስጠ ለዘብተኛ አቋም ያላቸው በመሆኑ፣ የጀመሩት የጦር ጥምረት ለእስራኤል ሥጋት ከመሆን ይልቅ በዓረብ ፔኑሱላ ያለውን ሥጋት በማስወገድ እስራኤል የምትገኝበት ቀጣና የተረጋጋ እንዲሆን እንደሚያደርገው ይጠቅሳሉ፡፡

በቅርቡ ግብፅ ሁለት የቀይ ባህር አካባቢ ደሴቶችን ለሳዑዲ ዓረቢያ ለመስጠት መወሰኗንና ይህም በእስራኤል ይሁንታን ያገኘ መሆኑ፣ ከምሥራቅ አፍሪካ በአመዛኙ አልሸባብ ከሚገኝበት የኤደን ባህረ ሰላጤ የደቡብ ጠርዝ ከሆነችው ሶማሊያ ሊመጣ የሚችለውን የሽብር ሥጋት ለመቀነስ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡

በተለይ በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራው የየመን ጦር ኅብረት በየመን መረጋጋትን ከማምጣቱ ይልቅ ሁኔታዎች እየተባባሱ መሄዳቸው፣ ብሎም በምሥራቅ አፍሪካ የፀጥታ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት የነበራት እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት በመውጣት ለራሷ የውስጥ ጉዳይ ትኩረት ለመስጠት ማቀዷ፣ ለምሥራቅ አፍሪካ የፀጥታ ክፍተት ከመፍጠሩም በላይ የአውሮፓ ኅብረትን የምሥራቅ አፍሪካ ትኩረት እስከማስቀየር የሚደርስ ተፅዕኖ እንዳለው ይናገራሉ፡፡

አሜሪካ በኢትዮጵያ ያላትን የሰው አልባ የጦር አውሮፕላን ቤዝ መዝጋቷ ሌላኛው ክፍተት እንደሆነና ይህም በሰላጤው ካለው አለመረጋጋት ጋር ለእስራኤል ሥጋት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

በመሆኑም በዚህ አካባቢ በአሁኑ ወቅት የታየውን ክፍተት ከአገሮቹ ጋር በመሆን መከታተልና ሥጋቶችን መቀልበስ ለእስራኤል የተሰጠ ተልዕኮ፣ አልያም የራሷ የቤት ሥራ በመሆኑ የመጣ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡    

  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -