Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአዲስ ከተማ መልሶ ማልማት ፕሮጀክት ነዋሪዎች ምሬታቸውን እየገለጹ ነው

በአዲስ ከተማ መልሶ ማልማት ፕሮጀክት ነዋሪዎች ምሬታቸውን እየገለጹ ነው

ቀን:

  • የነዋሪዎች ቅሬታ በመግፋቱ ለጊዜው ቤቶችን ማፍረስ ቆሟል

ዘግይቶ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በደረሰው የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት ነዋሪዎች ምሬታቸውን ገለጹ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከቂርቆስ፣ ከአራዳና ከልደታ ክፍላተ ከተሞች በመቀጠል በ2008 ዓ.ም. በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት ጀምሯል፡፡

ከጅማሬው በውዝግብ የታጀበው የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት እስከ ሰኔ 2008 ዓ.ም. ቤቶቹ ተነስተው፣ በ2009 ዓ.ም. ወደ ግንባታ ይገባል የሚል ዕቅድ ቢኖርም፣ ይህ ሊሆን ግን አልቻለም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሌሎች የመልሶ ማልማት ፕሮግራሞች በቂ ልምድ ወስዶ የተሻሉ ጠቃሚ አሠራሮችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ቢገልጽም፣ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 አሜሪካ ግቢ ተነሺዎች ግን እየተካሄደ ያለው የማንሳት ሥራ ሰብዓዊነት የጎደለውና ሕግን ያልተከተለ መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

የወረዳ 1 የልማት ተነሺዎች ያቋቋሙት ኮሚቴ አባል አቶ ታመነ ክብረት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ችግር እየፈጠሩ ተነሺውን ሕዝብ ሥጋት ውስጥ ጥለውታል ብለዋል፡፡

በአስተዳደሩ እየተካሄደ ያለው አሠራር ችግር ፈጣሪ ነው ከሚሉት ተነሺዎች መካከልም አቶ ነስሩ ሽፋና አቶ ረሺድ አወል ይገኙበታል፡፡

አቶ ነስሩ ዕድሜያቸው 60 ሲሆን፣ ከባለቤታቸውና ከስድስት ልጆቻቸው ጋር በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ይተዳደራሉ፡፡ አቶ ነስሩ እንደገለጹት በወረዳ 1 አሜሪካ ጊቢ አካባቢ 45 ዓመት ኖረዋል፡፡

መኖሪያቸውም ንግድ ቤታቸውም ሙሉ መረጃ ቢኖረውም፣ እስካሁን ዛሬ ነገ እየተባለ ተለዋጭ እንዳልተሰጣቸው ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ከጎንና ጎን ያሉ ቤቶች፣ ከጀርባ ያሉ የሌሎች ሰዎችና የጎረቤት ቤቶች በመፍረሳቸው የቀረው የእሳቸው ቤት ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹የውኃ መስመር ተቋርጧል፡፡ አካባቢው ቆሻሻ ውጦታል፤›› በማለት አቶ ነስሩ አስረድተዋል፡፡

‹‹መንግሥት ተለዋጭ ሳይሰጥ ቤቴን ያፈርሳል ብዬ አልገምትም፡፡ ዛሬ ነገ ሲባል ግን ሥጋት ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ ከዚህ ባለፈም የበሽታ ወረርሽኝ ሊነሳ እንደሚችልና የፀጥታ ችግር መኖሩ ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ከቶኛል፤›› በማለት አቶ ነስሩ ገልጸዋል፡፡

ከአቶ ነስሩ በተጨማሪ አቶ ረሺድ አወል ሥጋት ውስጥ ከወደቁ 280 ተነሺዎች መካከል ይገኛሉ፡፡ አቶ ረሺድ ለሪፖርተር እንደገለጹት ተወልደው ያደጉት እዚሁ አሜሪካ ግቢ ነው፡፡

ሙሉ ቤተሰቡ የቀበሌ ቤት ቅጽ ላይ ቢኖርም አስተዳደሩ ተለዋጭ ቤት ለመስጠት እያቅማማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ ረሺድ ቤት ከማግኘት ሥጋት ባለፈ፣ ከጎን ያሉ ቤቶች ፈርሰው አካባቢው በደረቅና በፍሳሽ ቆሻሻ በመዋጡ፣ የአራት ዓመት ሕፃን ልጅ በሦስት ቀናት ሕመም ሕይወቷ እንዳለፈ ሐዘን በተሞላበት ስሜት ተናግረዋል፡፡

የእነዚህ ሁለት ነባር ነዋሪዎች ቅሬታ የአሜሪካ ግቢ ተነሺዎች ቅሬታ መሆኑን፣ አካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች ለችግር እየተዳረጉ መሆናቸውን ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው፡፡

አስተዳደሩ በቂ ጥናት አድርጎ አንድ ላይ ማንሳት ሲገባው አልፎ አልፎ ማፍረሱና በሕጋዊ መንገድ ተለዋጭ ቤት በፍጥነት አለመስጠቱም እያሳቀቃቸው መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ጉዳዩ ለከፍተኛ የደኅንነት ሥጋት እንደዳረጋቸው ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማ ብርሃኑ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የነዋሪዎች ቅሬታ በመግፋቱና የ59 ተነሺዎች ጉዳይ በድጋሚ እንዲታይ በመወሰኑ ቤቶችን ማፍረስ ለጊዜው እንዲቆም ተደርጓል፡፡

ሕጋዊ የሆኑ ባለቤቶች ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም በሙሉ እንደሚያገኙ አቶ ግርማ ገልጸው፣ የተነሺዎቹ ቅሬት ተገምግሞ ምላሽ እስኪሰጥ ሁሉም ተረጋግቶ እንዲቀመጡ አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቂርቆስ፣ በልደታና በአራዳ ክፍላተ ከተሞች ካካሄደው መልሶ ማልማት በተጨማሪ፣ ትኩረቱን አዲስ ከተማና የካ ክፍላተ ከተሞች ላይ አድርጓል፡፡ በአዲስ ከተማ በዚህ ዓመት ከተጀመረው መልሶ ማልማት በተጨማሪ፣ የጎጃም በረንዳ ቁጭራ ሠፈርና የአውቶቡስ ተራ አካባቢዎችን ለማንሳት ታቅዷል፡፡ በየካ ክፍለ ከተማ አቧሬና መገናኛ አካባቢ የሚገኙ ነባር ሠፈሮችን ጨምሮ በአዲሱ በጀት ዓመት በአጠቃላይ በአምስት ክፍላተ ከተሞች 360 ሔክታር መሬት ላይ ያረፉ ነባር መንደሮችን ለማንሳት መታቀዱን አቶ ግርማ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...