Monday, March 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ግንባታ ስምምነት አለመፈረሙ ተገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያና የኬንያ መንግሥታት ከኬንያ ላሙ ወደብ አዲስ አበባ የሚደርስ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ግንባታ ስምምነት እንደተፈረመ ተደርጎ የተሰራጨው ዘገባ ስህተት መሆኑን የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ ቶሎሳ ሻጊ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ስምምነቱ በሁለቱ መንግሥታት እንደተፈረመ ተደርጎ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የተሠራጨው ዘገባ ሐሰት ነው፡፡ አቶ ቶሎሳ በኬንያ በኩል ሐሳቡ ቀርቦ እንደነበር ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ልዑክ ዕቅዱን በሚገባ መገምገም እንደሚፈልግ አስታውቆ ስምምነቱ ሳይፈረም መቅረቱን አስረድተዋል፡፡

‹‹የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ግንባታ ስምምነት አልተፈራረምንም፡፡ በኬንያ በኩል ሐሳቡ አለ፡፡ ይህ ግን በችኮላ የምንገባበት አይደለም፡፡ የቀረበውን ዕቅድ ቀስ ብለን አንድ በአንድ መመልከት ይኖርብናል፤›› ያሉት አቶ ቶሎሳ፣ የፕሮጀክቱ የኢኮኖሚና የቴክኒክ አዋጭነት መጠናት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

‹‹ጉዳዩን በዝርዝር መመልከት ይኖርብናል፡፡ የእኛም የሕግ ባለሙያዎች ዕቅዱን ገምግመው አስተያየት መስጠት አለባቸው፤›› ያሉት አቶ ቶሎሳ፣ አስፈላጊው ጥናት ተካሂዶ አዋጪነቱ ከታመነበት በኋላ ስምምነቱ በሌላ ጊዜ ሊፈረም እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ‹‹በዚህ አቋማችን የኬንያ መንግሥትም ተስማምቷል፡፡ ምናልባትም በ2016 መጨረሻ ሊፈረም ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑክ በቅርቡ በኬንያ ጉብኝት ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ የሁለቱ አገሮች የጋራ የሚኒስትሮች ጉባዔ ተካሂዷል፡፡ በወቅቱ ታዋቂ የኬንያ የዜና አውታሮች ሁለቱ መንግሥታት ከኬንያ ላሙ ወደብ አዲስ አበባ የሚደርስ የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ለመዘርጋት ስምምነት እንደፈረሙ መዘገባቸው አይዘነጋም፡፡

ዘገባውን ያስተባበሉት አቶ ቶሎሳ በሁለቱ መንግሥታት የተፈረመው የተፈጥሮ ዘይትና ጋዝ ትብብር ስምምነት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹የፈረምነው የመግባቢያ ሰነድ ነው፡፡ በኬንያ በተለያዩ ቦታዎች ነዳጅ ማግኘታቸው ይታወቃል፡፡ የፈረምነው ስምምነት የልምድ ልውውጥና ሥልጠና ማካሄድ የሚያስችል ነው፤›› ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

ከተፈጥሮ ዘይትና ጋዝ ትብብር ስምምነት በተጨማሪ ሁለቱ መንግሥታት በትምህርት፣ በእንስሳት ጤናና በስፖርት ዘርፎች ትብብር ለማድረግ ስምምነት ፈርመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ወደብ አዋሽ አርባ ከተማ የሚደርስ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ለመዘርጋት ዕቅድ አላት፡፡ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧውን ለመገንባትና ለማስተዳደር ዕቅድ ያቀረበው ብላክ ራይኖ የተሰኘ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ 1.6 ቢሊዮን ዶላር የተገመተ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ዕቅዱን በመሠረተ ሐሳብ ደረጃ ተቀብሎ ዝርዝር ጥናቱ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ዘመናዊ የነዳጅ ማመላለሻ ዘዴ በመሆኑ ወጪ ቆጣቢ፣ የነዳጅ ብክነትንና ስርቆትን እንደሚከላከል የመስኩ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች