Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየሞርጋን ቤተሰብ በልደት ዋዜማ

የሞርጋን ቤተሰብ በልደት ዋዜማ

ቀን:

‹‹ሙዚቃ በየምንሔድበት አገር እናቀርባለን፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በዚህ የበዓል ወቅት መምጣት ግን ሙዚቃ ከማቅረብም በላይ ነው፡፡ ለገና በዓል በኢትዮጵያ መገኘታችን ታላቅ ደስታ ሰጥቶናል፤›› በማለት ነበር የሞርጋን ሔሪቴጅ ባንድ ወንድማማቾች የተናገሩት፡፡ በልደት በዓል ዋዜማ በኤቪ ክለብ ሙዚቃዎቻቸውን ለማስደመጥ ከናይሮቢ፣ ኬንያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ባለፈው ሳምንት ነበር፡፡

የጃማይካዊው አቀንቃኝ ደንሮይ ሞርጋን አምስት ልጆች ‹‹ሞርጋን ሔሪቴጅ›› በሚል የባንዳቸው መጠሪያ ከሁለት አሠርታት በላይ በሬጌ ሙዚቃ በተወዳጅነት ዘልቀዋል፡፡ ‹‹የገና በዓልን ከኢትዮጵያውያን ጋር ለማክበር ነው የመጣነው፤›› ያሉትም በበዓሉ ዋዜማ ሙዚቃዎቻቸውን ከማቅረባቸው ቀደም ብሎ ነበር፡፡

ሞርጋን ሔሪቴጅ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ የባንዱ አባላት ከዚህ ቀደም መጥተው ሥራዎቻቸውን ለሕዝብ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ለልደት በዓል ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ከሙሉ ባንዳቸው ጋር ባይሆንም፣ በዓሉን ከሕዝብ ጋር በማክበራቸው ክብር እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የልደት በዓል ዋዜማ በተለያዩ አካባቢዎች በሚዝናኑና በሚሸምቱ የከተማዋ ነዋሪዎች የደመቀ ነበር፡፡ ኤቪ ክለብም ከምሽቱ አራት ሰዓት ጀምሮ በሞርጋን ሔሪቴጅ አድናቂዎች መሙላት ጀምሯል፡፡ ዲጄው በመረጣቸው ሬጌ ሙዚቃዎች እየተወዛወዙም ጥቂት ቆዩ፡፡ ከሞርጋን ሔሪቴጂ በፊት በመድረኩ ያቀነቀኑት ኢትዮጵያዊያኑ የሬጌ ድምፃውያን ራስ ጂኒና ዮሀና ነበሩ፡፡

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በሬጌ ሙዚቃ ስማቸው ከሚነሱ ወጣት ድምፃውያን አንዱ ዮሀና (ዮዮ)፣ የቦብ ማርሌን ዘፈኖች አስደምጧል፡፡ ‹‹ስካ›› የተሰኘውንና የስካ ሙዚቃ ስልት ያለው ዘፈኑንም አቅርቧል፡፡ ‹‹ሰላምታ››ን ጨምሮ ሌሎችም ተወዳጅ ዜማዎቹን ያስደመጠው ራስ ጂኒም ከታዳሚው የሞቀ ምላሽ አግኝቷል፡፡

ኤቪ ክለብ ማስተናገድ ከሚችለው ታዳሚ ቁጥር ውስንነት አንፃር፣ ድምፃውያኑ ሥራዎቻቸውን ሰፋ ባለ ቦታ ለምን አላቀረቡም? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አልቀረም፡፡ አዘጋጆቹ ኤችኤይኤም ኢንተርናሽናል ኢቨንትስና ሐበሻ ዊክሊ፣ ከአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ሰፋ ባለ ክፍት ቦታ (ኦፕን ኤር) መርሐ ግብሩን ማካሄድ እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

ሞርጋን ሔሪቴጅ ወደ መድረከ የወጡት ‹‹ቴል ሚ ሃው ካም›› በተሰኘ ዜማቸው ነበር፡፡ አስከትለውም ባለፉት ሁለት አሠርታት ከለቀቋቸው 23 አልበሞች መካከል ተወዳጅ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ፒተር ሞርጋን (ፒታ)፣ ሮይ ሞርጋን (ግራምፕስ)፣ ናክማያ ሞርጋን (ሉካስ)፣ መማልታል ሞርጋን (ሚስተር ሞጆ)ና እህታቸው ኡና ሞርጋን በአንድነት ባንዱን የመሠረቱት እ.ኤ.አ. በ1994 ነበር፡፡

ድምፃዊው አባታቸው፣ በወጣትነቱ ወደ አሜሪካ ካቀና በኋላ ኒው ዮርክ ውስጥ የወለዳቸው አምስት ልጆቹ፣ የሙዚቃ ዝንባሌ ያደረባቸው ታዳጊ ሳሉ ነበር፡፡ ‹‹ሙዚቃ ከልጅነታችን ጀምሮ ያደግንበት ነው፡፡ ሙዚቃ የጀመርነው እንደ ቤተሰብ አንድ ሆነን ነው፤›› በማለት ፒተር የልጅነታቸውን ወቅት ለሪፖርተር ይገልጻል፡፡

በአሜሪካ ሲኖሩ፣ ከሌሎቹ የዕድሜ እኩዮቻቸው በተለየ የአገራቸውን ባህል ተከትለው ይኖሩ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ‹‹እንደሌሎቹ ወጣቶች ሳይሆን በአገራችን የአነጋገር ዘዬ እናወራ ነበር፤›› ይላል፡፡ ከልጅነታቸው አንስቶ ጃማይካዊ ማንነታቸው ጎልቶ ይሰማቸው ነበር፡፡ ወደ ጃማካይካ አቅንተው ሙዚቃ መሥራት የጀመሩት ቤተሰቦቻቸው ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ነው፡፡

የመጀመሪያ አልበማቸው ‹‹ሚራክልስ›› ከተለቀቀቀ በኋላ በጃማይካ በሬጌ ስልት ከሚታወቁ ሙዚቀኞች ጋር በጥምረት መሥራት ቀጠሉ፡፡ ‹‹ፕሮቴክት አስ ጃ›› አልበምን ከለቀቁ በኋላ በተለያየ የዓለም ክፍል እየተዘዋወሩ ሙዚቃ መሥራትና ማስደመጡን ገፉበት፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 የለቀቁት ‹‹ስትሪክትሊ ሩትስ›› የግራሚ ተሸላሚ አድርጓቸዋል፡፡

ዓምና የወጣው አልበም ‹‹አቭራከዳብራ›› የግራሚ ዕጩ ያደረጋቸው ሲሆን፣ የግራሚ ዕጩ በሆኑበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ትልቅ ዋጋ እንዳለው ይናገራሉ፡፡ ‹‹አቭራከዳብራ የሚለው ቃለ መነሻው አብራከዳብራ ነው፡፡ መነሻው ከሒብሩ በፊት የነበረው የአማርኛ ቃል ነበር፡፡ ትርጉሙም የምናገረውን እፈጥራለሁ ማለት ነው፤›› ሲል ሮይ ያብራራል፡፡ የአልበሙ ሽፋን ላይ ቃሉ የተጻፈው እንግሊዝኛን ከአማርኛ ፊደላት ጋር በማዋሃድ ነው፡፡

አልበሙን የሠሩት በአፍሪካ፣ እስያ፣ አውሮፓና ደቡብ አሜሪካ እየተዘዋወሩ ነው፡፡ ሮይ እንደሚለው፣ የአፍሪካ ደም ያላቸውና በተለያየ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ድምፃውያን አዘውትረው ወደ አህጉሪቷ ሲመጡ አይስተዋልም፡፡ ‹‹ለአፍሪካ ምን ማድረግ እንችላለን? የሚለውን ሳይሆን አፍሪካ ምን ልታደርግልን ትችላለች? የሚለውን ብቻ ያስባሉ፤›› ይላል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይኼ አመለካከት እየተቀየረ እንደመጣ አመልክቶ፣ ‹‹አፍሪካ እያንሰራራች ነው፡፡ በምዕራቡ ዓለም ያሉ ትውልደ አፍሪካውያን አፍሪካን ለማሳደግ እንዲረባረቡም ጥሪ እናቀርባለን፤›› ይላል፡፡

ወንድማማቾች ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የተሰማቸውን ሐሴት ያስታውሳሉ፡፡ ኬንያ ውስጥ መኖር ከመጀመራቸው በፊት በምዕራብ አፍሪካ አገሮች በናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ጋና እና ጋምቢያ ተዘዋውረዋል፡፡ አሁን በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች እየተዘዋወሩ ሲሆን፣ ‹‹ኃላፊነታችንን እየተወጣን እንገኛለን፡፡ ሆኖም ትልቅ አህጉር በመሆኗ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፤›› ሲል ሮይ ይናገራል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በሙሉ ባንድ ታጅበው ኮንሰርት ማካሄድ የቅርብ ጊዜ እቅዳቸው ነው፡፡ ሻሸመኔን የመጎብኘት ፍላጎትም አላቸው፡፡ ‹‹አፍሪካ ውስጥ እንደ ሞርጋን ሔሪቴጅ ሙዚቃ ያቀረበ አርቲስት የለም፤›› ይላሉ፡፡ ሙዚቃዎቻቸው ስለ ፍቅር፣ መቻቻል፣ እኩልነት፣ ፍትሕና አንድነት ያወሳሉ፡፡ ፒተር፣ ‹‹ከኛ በፊት ብዙዎች የኛን መልዕክት የመሰለ ይዘት ያለው ሙዚቃ ሠርተዋል፡፡ በኛ ዘመንም ብዙ ተመሳሳይ ሙዚቀኞች አሉ፡፡ ከኛ በኋላም መልዕክት የሚያስተላልፍ ሙዚቃ የሚሠሩ ይመጣሉ፤›› በማለት የባንዱ ዋነኛ ግብ መልዕክት አዘል ሙዚቃ መሥራት መሆኑን ያክላል፡፡

‹‹መልካም መንፈስ ያለው ሙዚቃ እንሠራለን፡፡ ለራሳችን ታማኝና እውነተኛ ሆነን ቀና መልዕክት አዘል ሙዚቃ በማስደመጥ እንቀጥላለን፤›› ሲል ይናገራል፡፡ ማኅበረሰቡን የሚጠቅም መልዕክት ለሚያስተላልፍ ሙዚቃ ተገቢው ቦታ ባይሰጠውም፣ ወጣቱን የሚያስተምር ሙዚቃ ከመሥራት ወደ ኋላ እንደማይሉ ያክላል፡፡ የዓመታት መልዕክት አዘል ሙዚቃ ጉዟቸው፣ ‹‹ንጉሣዊ የሬጌ ቤተሰብ›› (ሮያል ፋሚሊ ኦፍ ሬጌ) የሚል ቅፅል ስም አሰጥቷቸዋል፡፡

ፒተር፣ ‹‹ዓለም በኛ ውስጥ ንጉሣዊነትን በመመልከቱ ፈጣሪን እናመሰግናለን፤›› በማለት ለቤተሰባቸው በተሰጠው የክብር ስም የሚሰማውን ደስታ ይገልጻል፡፡ በሙዚቃቸው ሰዎችን ወደተሻለ መንገድ በመምራት እንደሚዘልቁም ያክላል፡፡ ቦብ ማርሌ ልጆች ስቴፈን ማርሌ፣ ዴሚያን ማርሌና ዚጊ ማርሌን ጨምሮ ከበርካታ ድምፃውያን ጋር በጥምረት ሠርተዋል፡፡ ከቀደምቶቹ ሙዚቀኞች ካፕልተንና ከወጣቶቹ ክሮኒክሰን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ወንድማማቾቹ፣ በየትኛውም ዕድሜ ክልል ካለ ሙዚቀኛ ጋር ተጣምሮ መሥራት እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ፡፡ በቀደሙት ዓመታት ቦብ ማርሌ፣ ፒተር ቶሽ፣ በርኒንግ ስፒርና ሌሎችም የሙዚቃ ፈርጦች መልዕክት አዘል ሙዚቃ ለዓለም አበርክተዋል፡፡ ሞርጋን ሔሪቴጅም በዚህ መንገድ እየተጓዙ ካሉት እንደ ሎረን ሒል፣ ጂል ስኮትና ጆን ሌጀንድ ያሉ ሙዚቀኞች ጎን ለጎን እየሠሩ ነው፡፡ ‹‹ሁሌም መልዕክት አዘል ሙዚቃ የሚሠራ አርቲስት አለ፡፡ ሚዲያው አጉልቶ የሚያሳየው ይኼንን ባይሆንም፤›› ይላል ፒተር፡፡

ወጣቶች በዕውቀት የበለፀጉና ዓለምን ለመለወጥ የተዘጋጁ እንዲሆኑ በማስቻል ረገድ የመልዕክት አዘል ሙዚቃ ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ‹‹ከልጅነት እስከ ዕውቀት ሕይወታችንን ያሳለፍነው በሙዚቃ ነው፡፡ የምንወደው ነገር በመሆኑም ሙሉ ጉልበታችንን የምንሰጠው ለሙዚቃ ነው፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡ በዓለም ላይ ያለውን ክፉ ነገር በመልካም ነገር ለማሸነፍ ሙዚቃቸውን እንደሚጠቀሙም ያስረዳሉ፡፡

ሞርጋን ሔሪቴጅ፣ ስለ ኢትዮጵያ ካቀነቀኑ የሬጌ ሙዚቀኞች መካከል ናቸው፡፡ ከንግሥተ ሳባ ታሪክ አንስቶ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የመሰሉ ነገሥታትና ሌሎችም በርካታ የኢትዮጵያ መገለጫዎች ከኢትዮጵያ ጋር እንደሚያስተሳስሯቸው ይናገራሉ፡፡ ከሙዚቃዎቸቸው በአንዱ ስለ መስቀል አደባባይን የሚያወሱት፣ ከታሪክ ትምህርታቸው በመነሳት ዓለም ስለ ኢትዮጵያ እንዲያውቅ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ፒተር እንደሚለው፣  በቀጣይም ከአፍሪካ ጋር የሚያስተሳስሯቸው ሙዚቃዎች በመሥራት ይገፉበታል፡፡ ‹‹ትልቁ ግባችን ከበርካታ አፍሪካውያን ሙዚቀኞች ጋር በጥምረት መሥራት ነው፤›› ይላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...