Sunday, May 26, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ድህነት ቅነሳ ላይ የሚያተኩረው በጀት የጎንዮሽ ችግሮችንም ማየት አለበት!

ከሐምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በፓርላማው የፀደቀው አዲሱ በጀት በሥራ ላይ መዋል ጀምሯል፡፡ ለ2009 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት በጀት 274.3 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ከዚህ በጀት ውስጥ 65.2 በመቶ ያህሉ በድህነት ቅነሳ ትኩረት ለተሰጣቸው ለመንገድ ግንባታ፣ ለትምህርት፣ ለግብርና፣ ለጤናና ለገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራሞች እንደሚውል ዕቅድ ተይዟል፡፡ በተጨማሪም በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ሽግግር ያመጣሉ የተባሉት የኢንዱስትሪ ልማት፣ የወጪ ንግድ መስፋፋትና የሥራ ዕድል ፈጠራ የበጀቱ የትኩረት አካል መሆናቸው ተገልጿል፡፡ እንዲሁም የአየር ንብረት ተፅዕኖ ተጋላጭነትን ለመቋቋም፣ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎችን ለመገንባት፣ የመንግሥታዊ ተቋማትን አደረጃጀት ለማዘመንና ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማስፈጸም የሚያስችል አመቺ ሁኔታ ለመፍጠርም ጠቀሜታው ተብራርቷል፡፡ የአዲሱ ዓመት በጀት በዚህ ሥሌት ሲዘጋጅና ሲፀድቅ የጎንዮሽ ችግሮችም መታየት አለባቸው፡፡

ለአዲሱ በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ከሚፈልገው 274.3 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ ወጪን ሙሉ በሙሉ ለመሸፈን የ35.5 ቢሊዮን ብር በጀት ጉድለት ይታያል፡፡ እንደተለመደው ይህን ጉድለት ለመሸፈን የታቀደው ከአገር ውስጥ በሚገኝ ብድር ነው፡፡ የአገር ውስጥ ብድሩ መጠን ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት አንፃር ሁለት በመቶ ብቻ ስለሆነ፣ ማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ጫና የማያሳድርና የዋጋ ንረትን የማያስከትል መሆኑን መንግሥት በሙሉ ልብ ይናገራል፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ በጉድለት የሚሟላ ብር በብድር የሚገኝ ነው ከተባለ ከየት ነው የሚገኘው? መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረው ከሆነና ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት ከሦስት በመቶ በልጦ ከሄደ የዋጋ ግሽበትን ያባብሳል፡፡ ከግምጃ ቤት ሰነዶች ሽያጭ የሚገኝ ከሆነና በገበያ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ ስለሆነ ያን ያህል ችግር አይፈጠርም፡፡ ችግር እንዳይፈጠር ማስተማመኛ ሲሰጥ በተግባር የሚታይ መሆን አለበት፡፡ የበጀት ጉድለቱ ሽፋን ጉዳይ ሲነሳ ከድህነት ቅነሳ በተቃራኒ የሚመጡ የጎንዮሽ ችግሮች ሊታሰብበሳቸው ይገባል፡፡ የዋጋ ግሽበትን የሚያባብሱ ስለሆኑ፡፡

መንግሥት በአዲሱ በጀት ዓመት 13 ቢሊዮን ብር ያህል ለዕዳ ከፍያ መድቧል፡፡ ለመምህራን የደመወዝ ጭማሪ አምስት ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ አለበት፡፡ ከቅጥር ከሚገኝ የገቢ ታክስ ቅናሽ ሦስት ቢሊዮን ብር ገቢ ይቀንስበታል፡፡ በተለይ የመምህራን ደመወዝ ጭማሪና የገቢ ታክስ ቅናሽ ሲደረግ በገበያው ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበቶች የድህነት ቅነሳው ዓላማ ተፃራሪዎች ናቸው፡፡ ዘላቂ ልማት በማስፈን ድህነትን ለማስወገድ ዓይተነኛ ሚና ያላቸው ከፍላተ ኢኮኖሚዎች ላይ ሲተኮር፣ ሕዝቡን በዕለት ተዕለት ሕይወቱ የሚያጋጥሙት ሰው ሠራሽ ችግሮች አስፈላጊ ጫና እንዲያሳድሩበት አይገባም፡፡ በወረቀት ላይ የሰፈረውና በተግባር የሚታየው እንዲጣጣሙ ካልተደረገ፣ ሕዝቡ ለአልጠግብ ባዮችና ለራስ ወዳዶች ከመጋለጡም በላይ፣ ለሚታቀዱ የልማት ክንውኖች የባለቤትነት ስሜት ያጣል፡፡ ወጪዎችን የሚያካክሱ የውጭ ብድርና ዕርዳታ መጠናቸው ሲቀንስም ጫናው የዚያን ያህል ነው፡፡ መንግሥት ፖሊሰውን ሲያስፈጽም የጎንዮሽ ችግሮችን መቃኘት አለበት፡፡

በአዲሱ በጀት ዓመት መንግሥት ከታክስ 170 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ዕቅድ ይዟል፡፡ ከተጠናቀቀው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ21 በመቶ ብልጫ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ዕቅዱ ግቡን ሙሉ ለሙሉ አሳክቶ የታሰበውን ገንዘብ ለመሰብሰብ ከተቻለ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከታክስ ማሰባሰብ ጋር በተያያዘ እንደ ምሳሌ የሚነሳ ጉዳይ አለ፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት መሰብሰብ የነበረበት አጠቃላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ከወዲያኛው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 28 በመቶ ቅናሽ ታይቶበታል፡፡ በዚህን ያህል መጠን ተጨማሪ እሴት ታክስ አልተሰበሰበም ማለት በፍሬ ግብር ላይ ያለው ጉድለት ቀላል አይባልም፡፡ የታክስ ሥርዓቱ መሠረቱን አስፍቶ የመንግሥትን ገቢ ለመጨመር፣ ፍትሐዊ እንዲሆን፣ ከኋላቀርነት ተላቆ እንዲዘምን፣ በታችኛውና በቀላሉ ሊገኝ በሚችለው ሕዝብ ላይ ብቻ እንዳያተኩር፣ ወዘተ መደረግ አለበት፡፡ ግብር በማጭበርበርና በመሰወር፣ ከታክስ መረቡ በመደበቅና በአሻጥር ከፍተኛ የአገር ሀብት እየባከነ ብዙኃኑን ሕዝብ ብቻ ማስጨነቅ የድህነት ቅነሳውን ዓላማ ይፃረራል፡፡ ይኼም ከፍተኛና አጣዳፊ ትኩረት ይሻል፡፡ በተለይ ከቀረጥና ከግብር የሚጭበረበረው የአገር ሀብት ሁነኛ መላ ያስፈልገዋል፡፡ ጠንካራ የታክስ ሥርዓት መፈጠር  አለበት፡፡

የድህነት ቅነሳው ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል የመኖሪያ ቤት ችግር አንደኛው ነው፡፡ በጣም መሠረታዊ ከሚባሉ ፍላጎቶች መካከል ተጠቃሽ የሆነው የመኖሪያ ቤት እጥረት የብዙኃኑ የከተማ ነዋሪዎች ራስ ምታት ነው፡፡ ምንም እንኳ መንግሥት በቀጥታ በጀት መድቦለት የሚያንቀሳቅሰው መሆን አለበት ባይባልም፣ በተለይ የአገሪቱ ባንኮችና የተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በስፋት እንዲገቡበት አማራጮች መታየት አለባቸው፡፡ በተለያዩ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች መንግሥትና ቤት ፈላጊዎች በመቶኛ እየተሠላ የሚያቀርቡት ገንዘብ ለሚፈለግለት ዓላማ ይውል ዘንድ፣ በተጨማሪም በመንግሥት አማካይነት የመኖሪያ ቤት የሚገነቡ ኩባንያዎች ይዘው የሚመጡት ገንዘብም ሆነ ቁሳቁስና ዕውቀት ሥራ ላይ እንዲውል ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳ ይህ ተግባር በቀጥታ ከበጀት ጋር ቁርኝት ባይኖረውም፣ የድህነት ቅነሳ አካል በመሆኑና መንግሥትም ዋናው ተዋናይ ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በመኖሪያ ቤት ችግር የሚሰቃዩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ተስፋቸው በመንግሥት ላይ በመሆኑ አማራጮች ሁሉ ይታዩ፡፡ የመጠለያ ችግር ጊዜና ፋታ የማይሰጥ እየሆነ ነው፡፡

ሕዝብ በአገሩ ደስተኛ ሆኖ የሚኖረው፣ ስደት የሚቀንሰው፣ የሥራ ዕድሎች በብዛት የሚፈጠሩት፣ ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል የሚኖረው፣ ዴሞክራሲ የሚሰፍነው፣ የሕግ የበላይነት የሚረጋገጠውና ሰላምና ብልፅግና በአስተማማኝነት የሚገኙት በአገር ጉዳይ ብሔራዊ መግባባት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ የድህነት ቅነሳው ትግል የተሳካ እንዲሆንና በሁሉም መስኮች ስኬት መጎናፀፍ የሚቻለው በቃል የሚነገረውና በተግባር የሚታየው ሲጣጣሙ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደሚባለው በጀቱ የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል በማድረግ ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡ ድህነትም አስተማማኝ በሆነ መንገድ መቀረፍ አለበት፡፡ ወረቀት ላይ የሠፈሩ የሚያማልሉ ዕቅዶች ተግባራዊ ይደረጉ፡፡ ለዚህም ነው ድህነት ቅነሳ ላይ የሚያተኩረው በጀት የጎንዮሽ ችግሮችንም ማየት አለበት የሚባለው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው የውኃ ሀብት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዘመኑ በማይመጥን ዕሳቤ አገር ማተራመስ ይብቃ!

ዘመኑ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የሥልጣኔ ትሩፋቶችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች እያቋደሰ ነው፡፡ ለልማትና ለዕድገት የሚማስኑ የኑሮን ጫና ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በስፋት ሲጠቀሙ፣ ያላደላቸው ደግሞ እርስ...

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...