Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በአዲስ አበባ

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ በአዲስ አበባ

ቀን:

ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኙት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ፣ በመጀመሪያ ቀን ውሏቸው ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በብሔራዊ ቤተመንግሥት ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ባጋጣሚው በቀድሞው ኢዮቤልዩ ቤተመንግሥት የሚገኙትን አንበሶችንም ቃኝተዋል፡፡

ውሸት ከየት መጣ?

የዋሾ ሰው ውሸት የመጣበት አገር

 

ከየት ስፍራ ይሆን ከየትኛው መንደር

ከመጽሐፍ ገላጮች ከጠንቋዮች አምባ

ይሆን ዋሾ ሰው ቤት ዘው ብሎ የገባ?

ዋሾና ሌባ ሰው ይመሳሰላሉ

ጠብና ችግርን ለሰው ያተርፋሉ

ዋሾ ውሸት ሲያድል መንደር እየዞረ

ስንቱን ሰው በደለ ስንቱን አቃቃረ?

ዋሽቶ ሌላውን ሰው ለመጉዳት ካሰበ

ውሸታም ገላውን በውሸት ካጠበ

በገዛ ውሸቱ እስከ ተደበበ

የዋሾ ሰው ኑሮ መላ ቅጡን ያጣል

እንደ ተረገመ ኑሮውን ይገፋል፡፡

  • ታደለ ብጡል ክብረት፣ ሦስትዮሽ እና ሌሎች ግጥሞች፣ 1997 ዓ.ም.

****************

ሊዮኔል ሜሲ በስፔን በታክስ ማጭበርበር የ21 ወራት እስራት ተፈረደበት

ስፔን ውስጥ ለባርሴሎና ክለብ የሚጫወተው አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ በስፔን በታክስ ማጭበርበር ወንጀል የ21 ወራት እስራት እንደተፈረደበት ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

አባቱ ጆርጅ ሜሲም በስፔን ከ2007 እስከ 2009 ባሉት ዓመታት 4.5 ሚሊዮን ዶላር ታክስ በማጭበርበር እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡

እንደ ዘገባው፣ በስፔን ከሁለት ዓመት በታች የሆነ የእስር ፍርድ በገደብ ይካካሳል፡፡ በመሆኑም ሜሲም ሆነ አባቱ የእስር ፍርዱ በገደብ ሊቀየርላቸው ይችላል፡፡

ሜሲና አባቱ በባርሴሎና ፍርድ ቤት በሦስት የታክስ ጉዳዮች ነበር የተከሰሱት፡፡ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸውም ከእስር ፍርዱ በተጨማሪ ሜሲ ሁለት ሚሊዮን ዩሮ አባቱ 1.5 ሚሊዮን ዩሮ ቅጣት እንዲከፍሉ ተወስኖባቸዋል፡፡ ስህተታቸውን ለማረምም ሁለቱም በፈቃደኝነት ተጨማሪ አምስት ሚሊዮን ዩሮ ለመክፈል የተስማሙ ሲሆን፣ ይህም መክፈል ይገባቸው የነበረውን ታክስ ከነወለዱ ይሸፍናል ተብሏል፡፡

****************

ያመለጠው እስረኛ ከ37 ዓመት በኋላ ተያዘ

ከእስር አምልጦ የሞተ ዘመዱን ስምና ማንነት በመጠቀም በአንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ አገልጋይ ሆኖ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቢል በርችፊልድ ከ37 ዓመት በኋላ መያዙ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ትኩረት ሆኗል፡፡ የ67 ዓመቱ ቢል በርችፊልድ፣ በሚኖርበት ኬንታኪ በቤተክርስቲያን አካባቢም የሚታወቀው ሀሮልድ አርኖልድ በመባል ሲሆን፣ ከዚህ ሁሉ ዓመት የተሳካ ከእስር ማምለጥ በኋላ በኬንታኪ ፖሊስ ሲያዝ በክርስትና ሕይወቱና በመልካም ሥነ ምግባሩ የሚያውቁት የኬንታኪ ኗሪዎች እንዲለቀቅ ፊርማ ማሰባሰብ ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ኗሪዎች ቢልን የሚገልጹት፣ ‹‹መልካም ሰው፣ የተቸገሩን የሚመግብ›› በማለት ነው፡፡ ከግድያ ጋር በተያያዘ፣ እ.ኤ.አ. በ1979 ላይ 15 ዓመት እስርና የጉልበት ሥራ ተፈርዶበት የነበረው ቢል፣ በሁለት አጋጣሚዎች የማምለጥ ሙከራ አድርጐ እንደነበር የዘ ኢኮኖሚስት ዘገባ ያመለክታል፡፡ በመጀመሪያ ከጃክሰን ካውንቲ ማረሚያ ቤት ካመለጠ በኋላ ወዲያው ተይዞ እሥራቱም 16 ዓመት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ከአራት ዓመት በኋላ ከመስክ ሥራ ላይ ያመለጠ ሲሆን፣ በዚህኛው ስኬታማ ሆኖ እስከተያዘበት ዕለት ድረስ በተረጋጋ ሁኔታ መኖር ችሏል፡፡

****************

አባጋር

አባጋር፤ በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች ረጅም ታሪክ፣ ገናና ስምና ሰፊ ሕዝባዊ ተቀባይነት ያለው የግጭት ማስወገጃ ተቋም ነው፡፡ አባጋር የሚለው ቃል ‹‹አብ›› እና ‹‹አገር›› የሚሉትን ቃላት በማጣመር የተበጀ ሲሆን፣ ትርጉሙም ‹‹የአገር አባት›› ማለት ነው፡፡ አባጋር የሚለው ስያሜ፣ የአገር ሽማግሌ ወይም የመሪ የማዕረግ ስም ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሕግ፣ ደንብ፣ ልማድና ባህል ማለት ሊሆን ይችላል፡፡

አባጋርነት ከአባት ወደ ልጅ በሚተላለፍ መንፈሳዊ ብቃተ ወግ የሚገኝ ሥልጣን ነው፡፡ በደቡብና ሰሜን ወሎ በሚገኙት አብዛኞቹ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የየራሳቸው አባጋር አላቸው፡፡ ይህ አባጋርም የተጣላን ያስታርቃል፣ የተበደለን ያስክሳል፣ በድብቅ የተሠራ ወንጀልን ያወጣል፤ ደም ያደርቃል፡፡ አባጋር በአጭሩ እንደዛሬው ወንጀልን የሚከላከልና የሚመረምር ፖሊስ በሌለበት ሕግና ሥርዓት እንዲከበር፣ ወንጀለኛ ስለወንጀሉ በአገር ልማድና ሕግ እንዲጠየቅ፣ ቂም በቀል ያለባቸው እርስ በእርስ እንዳይጠቃቁ ዋስትና ይሆን ዘንድ የአገሬው ሰዎች የፈጠሩት ነባር አገር በቀል ተቋም ነው፡፡ አባጋር በማኅበረሰቡ ውስጥ ባለው ተቀባይነት፣ ታማኝነትና ክብር ምክንያት ቀደም ሲል የነበሩት መንግሥታትም ሆነ አሁን አገሪቷን በሚያስተዳድረው ሥርዓት ዕውቅና የተሰጠው አገር በቀል የግጭት መከላከያና መፍቻ ተቋም ነው፡፡ ስለዚህም አባጋሮች ወንጀልን በመከላከልና ወንጀለኛን በማውጣት፣ እንዲሁም ሰላምን በማስፈን ረገድ ከቀበሌ መስተዳድር አካላትና ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት ይሠራሉ፡፡ አባጋሮች ሕግን የሚያስከብሩበት እርቅ የሚያወርዱበት ወይም ወንጀለኛን የሚያወጡበት መንፈሳዊ ሥልጣን ወይም አሠራር ‹‹ቆቲ›› በመባል ይታወቃል፡፡ ‹‹ቆቲ›› ወንጀል በተፈጸመበት አንድ አካባቢ የሚኖር ማኅበረሰብ በነቂስ ወጥቶ ወንጀሉን ራሱ/ራሷ ላለመሥራቱ/ቷ ወይም ወንጀሉ በሌላ ሰው ሲፈጸም አለማየቱን/ቷን በመሃላ የሚያረጋግጥበት ሥርዓት ነው፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ የአማራ ሕዝብ ባህልና ተቋም፣ 2001 ዓ.ም.

 

 

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...