ከግል ባንኮች ቀዳሚ በመሆን ላለፉት 22 ዓመታት በባንክ ኢንዱስትሪው ሲንቀሳቀስ የቆየው አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በተገባደደው በጀት ዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ያልተጣራ ትርፍ በማስመዝገብ ከግል ባንኮች ቀዳሚ የሚያደርገውን ሪከርድ መያዙ ታወቀ፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት ከሆነ፣ አዋሽ ባንክ በዓመቱ ያስመዘገበው ያልተጣራ የትርፍ መጠን 1,004,639,000 ብር በመሆን ከዚህ ቀደም በዳሸን ባንክ ተይዞ የነበረውን ከፍተኛ የትርፍ መጠን በልጧል፡፡ ባንኩ ባለፈው በጀት ዓመት ያስመዘገበው ያልተጣራ ትርፍ መጠን 869.8 ሚሊዮን ብር ገደማ በመሆኑ፣ የዘንድሮው ትርፍ የ134.8 ሚሊዮን ብር ያህል ብልጫ የታየበት አፈጻጸም ሆኗል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን አዋሽ ባንክ በበጀት ዓመቱ ማብቂያ የተከፈለ ካፒታሉ ከ2.3 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱም ታውቋል፡፡ ዓምና ካስመዘገበው 1.77 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል አኳያ ሲታይ ከ465.4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚደርስ ብልጫ ያለው እንደሆነ ከምንጮች ለመረዳት ተችሏል፡፡
ባንኩ በብድር አሰጣጥ ረገድ በጠቅላላው ከ15.4 ቢሊዮን ብር በላይ ያስመዘገበበትን እንቅስቃሴ በዚህ ዓመት እንዳከናወነ፣ ባለፈው ዓመት ከነበረው 12.5 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የብድር መጠን አኳያ ሲታይም ከ2.9 ቢሊዮን ብር በላይ ዕድገት በዚህ ዓመት ሊያስመዘግብ እንደቻለ ተጠቅሷል፡፡ ጠቅላላ ተቀማጭ ሒሳቡን በሚመለከት ለማወቅ እንደተቻለውም አዋሽ ባንክ በተገባደደው በጀት ዓመት ከ24.2 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ሒሳብ ለማስመዝገብ ችሏል፡፡ ባለፈው ዓመት ከ19. ቢሊዮን ብር በላይ የተቀማጭ ሒሳብ ቢያስመዘግብም፣ ዘንድሮ ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ ለውጥ ታይቷል፡፡
በአገሪቱ በብድር አሰጣጥ ረገድ በአማካይ ከፍተኛውን ደረጃ የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን፣ ዳሸንና አዋሽ ባንኮች ይከተላሉ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የነበረውን አኃዝ መነሻ አድርገው የተሠሩ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚያሳዩትም፣ ንግድ ባንክ በአማካይ 57 ቢሊዮን ብር ያህል በማበደር ቀዳሚ ነበር፡፡ ዳሸን ባንክ በአማካይ ያበደረው መጠን ስምንት ቢሊዮን ሲሆን፣ አዋሽ ባንክም ስድስት ቢሊዮን ብር ያህል በአማካይ በማበደር ተከታይ ሆኗል፡፡