የሰሜን ኮሪያው ፕሬዚዳንት ኪም ጆን ኡን የኑክሌር መሣሪያ ፕሮግራማቸውን የሚያዩት አገራቸውን ከአሜሪና ከደቡብ ኮሪያ ሊሰነዘር ከሚችል ጥቃት እንደ መከላከያ አድርገው ነው፡፡ ሁለቱ የሰሜን ኮሪያ ተቀናቃኞች ግን ይህን አይቀበሉትም፡፡ ሁሌም የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር ፕሮግራም እንደ ኮነኑ፣ በልሳነ ምድሩም የጋራ ወታደራዊ ልምምድ እንዳደረጉ ነው፡፡
የ34 ዓመቱ ኪም ምላሽ ደግሞ ረዥም ርቀት ሊጓዙ የሚችሉ የኑክሌር አረር ተሸካሚዎችን በመሞከር ያላቸውን ብቃት ማሳየት ነው፡፡ ታዲያ ይህንን የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ልቀት በሥልት መያዝ አልቻሉም የሚባሉት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላቸውን ቅራኔ በድርድር ከመፍታት ይልቅ የቃላት ጦርነት ውስጥ ነበር የገቡት፡፡ ኪምም በአሜሪካ ላይ ይዝታሉ፣ ትራምፕም እንዲሁ፡፡
ሰሜን ኮሪያ በሐምሌ 2009 ዓ.ም. አመርቂ የተባለና የአሜሪካን አብዛኞቹን ግዛቶች መምታት የሚችል የኑክሌር አረር ተሸካሚ ሚሳይል ሙከራ ማድረጓን ተከትሎም፣ ትራምፕ ሰሜን ክሪያን በዲፕሎማሲ ከማቅረብ ይልቅ አሜሪካም ከሰሜን ኮሪያ የተሻለ የኑክሌር ጦር መሣሪያ መታጠቋን ነበር የገለጹት፡፡ ‹‹ሰሜን ኮሪያ ላይ ‹‹(ፋየር ኤንድ ፊዩሪ) እሳትና ቁጣ ይወርድባታል፤›› ነበር ያሉት፡፡
በወቅቱ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ‹‹ፋየር ኤንድ ፊውሪ›› የሚለውን አባባላቸውን ሲያብጠለጥሉት፣ የፖለቲካ ተንታኞችም ሲተቹት ነበር፡፡ ትራምፕ እንደ ዋዛ በወቅቱ የተናገሩት ‹‹ፋየር ኤንድ ፊዩሪ›› ዛሬ ፊቱን በዋይት ሐውስ ላይ አዙሮ በመጽሐፍ መልክ ወጥቷል፡፡
ታዲያ መጽሐፉ ይዞ የወጣው እሳቸው ሰሜን ኮሪያን ድባቅ እመታበታለሁ ብለው እንዳስተላለፉት መልዕክት ሳይሆን፣ የእሳቸውን አሜሪካን የመምራት ብቃት ማነስና በዋይት ሐውስ ያለውን ውጥንቅጥ አካቶ ነው፡፡ መጽሐፉ ገበያ ላይ ከዋለ አምስት ቀናት ሲያስቆጥር፣ ሲኤንኤን፣ ቢቢሲንና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችንም ያነጋገረ ሆኗል፡፡
በማይክል ዎልፍ የተጻፈውና የትራምፕ አስተዳደር በዋይት ሐውስ ምን እንደሚመስል የገለጸው መጽሐፍ፣ በትራምፕ ጭምር ትችት ቢቀርብበትም፣ የአሜሪካውያን ብሎም የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
ዎልፍ በአሜሪካ ታሪክ አወዛጋቢ የተባለውን የትራምፕ ፕሬዚዳንትነት ሥልጣንና ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ የነበሩትን የዋይት ሐውስ ውጥንቅጦች ባሠፈረበት መጽሐፍ፣ በፕሬዚዳንቱ ቢሮ ያሉ አሠራሮችን በጥልቀት ማስፈሩን የተለያዩ ድረ ገጾች ስለመጽሐፉ ካስቀመጡት አጭር ፍሬ ነገር ማወቅ ይቻላል፡፡
‹‹ፋየር ኤንድ ፊዩሪ›› የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቢሮ ሠራተኞች ስለትራምፕ ስላላቸው አሉታዊ ምልከታ፣ ትራምፕ ኦባማ በመቅረፀ ድምፅ ቀድተውኛል ብለው ለመናገር ምን እንዳነሳሳቸው፣ የአሜሪካው ፌዴራል ምርመራ ቢሮ ዳይሬክተር ጀምስ ኮሚ ለምን ከሥራ እንደተባረሩ፣ የትራምፕ ልጅ ባለቤት ጄርድ ኩሽነርና ስትራቴጂስቱ ስቲቭ ባነን አብረው በአንድ ክፍል እንደማይሠሩ፣ ባነን ከተሰናበቱ በኋላ የትምራፕን የአስተዳደር ስትራቴጂ ማን እንደሚመራው፣ ከትራምፕ ጋር የመወያያት ሚስጥራዊነትንና ሌሎችንም ጉዳዩች የዳሰሰ መጽሐፍ ነው፡፡ የትራምፕ ፕሬዚዳንትነት ምን ያህል አሜሪካውያንን እንደከፋፈለና በአስተዳደሩም አለመስማማት መኖሩን ያተተ ነው፡፡
ይህ ታዲያ በሀብታቸው ምክንያት ስማቸውን ለሚሸጡት፣ በየሕንፃዎቹ፣ በየሆቴሎቹ፣ በጎልፍ መጫዎቻዎቹና በየቁማር ቤቶቹ ስማቸውን ለሚለጥፉት ትራምፕ ዝናቸውን አጠልሽቷል፡፡ ሲኤንኤን እንደሚለው፣ በተለይ ከማናቸውም ፖለቲከኞች ራሳቸውን ለየት አድርገው የሚመለከቱትን ትራምፕ መሳለቂያ ያደረጋቸው መጽሐፍ ከምንም በላይ የሚያሳዝናቸው ነው፡፡
ዎልፍ በመጽሐፉ እንዳሰፈረው፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በአሜሪካ ስላሉ ፖሊሲዎች ያለቸው ዕውቀት አናሳ ነው፡፡ አገሪቷ ለሰጠቻቸው ከባድ ኃላፊነትም ያላቸው ጥበቃ አናሳ ነው፡፡
ትራምፕ ለተሰጣቸው ኃላፊነት ግዴለሽ መሆናቸውም ስሜታዊና ሳያመዛዝኑ በችኮላ እንዲናገሩ ማድረጉ በዋይት ሐውስ ከጎናቸው ማንም እንደሌለና ብቸኛ እንደሆኑ ያሳያል ይላል፡፡ ዎልፍ እንደጻፈው፣ ትራምፕ ፕሬዚዳንት የመሆን ኃላፊነትንም መቼም ቢሆን ፈልገውት አያውቁም፡፡
በትራምፕ ላይ ባነጣጠረው፣ በትራምፕ አስተዳደር የዋይት ሐውስ አማካሪ በነበሩት ስቲቭ ባነን ንግግሮች በአብዛኛው የታጀበውና 200 ያህል የቃለ መጠይቅ ተሳታፊዎችን ያካተተው መጽሐፍ ለዋይት ሐውስ አስደንጋጭ ገጠመኝ ነው፡፡ ሆኖም አንዳንዶቹ የዎልፍ መረጃዎች በማስረጃ የተደገፉ ቢሆንም፣ በርካታ ስህተቶች መታየታቸውንም ሲኤንኤን አስፍሯል፡፡
በመጽሐፉ እንደ መረጃ ምንጭ በብዛት የተጠቀሱት ስቲቭ ባነንም፣ መጽሐፉ ገበያ ላይ ከዋለ ከቀናት በኋላ በሰጡት መረጃ መፀፀታቸውን ተናግረዋል፡፡ ይቅርታ በመጠየቅም፣ የትራምፕን አጀንዳ የሚደግፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ዋይት ሐውስን ላንቀጠቀጠው መጽሐፍ በሰጡት አስተያየት፣ ስለትራምፕ ልጅ ዶናልድ ጁኒየር የሰጡት አስተያየት ትክክለኛና ወቅቱን የጠበቀ እንዳልነበረ፣ ዶናልድ ጁኒየር አባቱን የሚያግዝና ለአሜሪካም የሚለፋ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ› እንዲሉ የባነን አስተያየቶች በመጽሐፉ መካተታቸው ትራምፕን ሆን ብለው ለመተንኮስ እንዳደረጉት ተመንዝሯል፡፡ ትራምፕም ባነን ‹‹አዕምሮውን አጥቷል›› እንዲሉ አድርጓል፡፡
ዘግይቶ ገበያ ላይ መዋል ከነበረበት ጊዜ ፈጥኖ ባለፈው ዓርብ ገበያ ላይ የዋለው ‹‹ፋየር ኤንድ ፊዩሪ›› መጽሐፍ፣ ትራምፕን እንደ ሕፃን የሚገልጽም ነበር፡፡ የአዕምሮ ዝግጁነታቸውንም ይጠይቃል፡፡ ትራምፕም አገርን ስለመምራትና ስለአዕምሮ ዝግጁነታቸው ስለተነሳባቸው ጥያቄ፣ ‹‹በዕድሜዬ ሙሉ ሁለት ቋሚ ሀብቶች አሉኝ፡፡ እነሱም የአዕምሮ መረጋጋትና ብልጠት ናቸው፤›› ሲሉ ትዊት አድርገዋል፡፡
‹‹ከውጤታማ ነጋዴነት የቲቪ ኮከብ፣ ከዚያም በመጀመርያ ሙከራዬ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኛለሁ፡፡ ይህም ብልጥ ብቻ ሳልሆን ተሰጥኦ እንዳለኝ ያሳያል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ በመጽሐፉ የትራምፕን ፕሬዚዳንትነት አጠልሽተዋል የተባሉትን ስቲቭ ባነንም ‹‹ስሜታዊ›› ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡
ትራምፕ እንደሚሉት፣ በሳቸውና በዋይት ሐውስ ዙሪያ አጠንጥኖ የታተመው መጽሐፍ ደራሲ ማይክል ዎልፍ ሁሉን ያጣ ነው፡፡ በመጽሐፉ ያካተታቸው ታሪኮችም አሰልቺና ከእውነት የራቁ ናቸው፡፡ መረጃ የሰጠው ስቲቭ ባነንም በሁሉም የተናቀ ሆኗል፡፡ ይህ በጣም መጥፎ ነው ብለዋል፡፡
በትራምፕና በሌሎች የፖለቲካ ተንታኞች ትችት የተሰነዘረበት ‹‹ፋየር ኤንድ ፊዩሪ›› መጽሐፍ በትራምፕ ነገረ ፈጅ አማካይነት ገበያ ላይ እንዳይውል ተጠይቆ የነበረ ቢሆንም፣ ከገበያ ያገደው የለም፡፡ መጽሐፉም በትራምፕና እሳቸውን በከበቡ ባለሥልጣናት ዙሪያ ያሉ ጉዳዮችን ይዞ ስለመውጣቱ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አሥፍረዋል፡፡ ገበያ ላይ ከዋለ አምስት ቀናት ያስቆጠረው መጽሐፍም የብዙዎችን ትኩረት በመሳብ መነጋሪያም ሆኗል፡፡
የመጸሐፉ ደራሲ ዎልፍ ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ትችቶችን አስመልክቶም ሲኤንኤን ለዎልፍ ቃለ መጠይቅ አድርጎ ነበር፡፡
ዎልፍ ለተነሱበት ጥያቄዎች በተለይም ትራምፕ አገሪቱን ለመምራት የአዕምሮ ዝግጁነት የላቸውም ማለቱ እውነት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ምንም እንኳን በመጽሐፉ የትራምፕን የካቢኔ አባላትና ምክትል ፕሬዚዳንቱን ማይክ ፔንስ ባያነጋግርም፣ በትራምፕ ዙሪያ ያሉ ሁሉ የትራምፕ የአዕምሮ ዝግጁነትና ብቃት እንደሚያሳስባቸው ተናግሯል፡፡ ‹‹በትራምፕ ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ስለትራምፕ የመምራት ብቃት ለማውራት መጠየቅ አያስፈልጋቸውም፡፡ ምክንያቱም ይህ ሳይጠየቅ የተመለሰ አጀንዳ ነው፤›› ብሏል፡፡
‹‹ተከታታይነት ያላቸውን ጉዳዮች አያነሱም፣ በአንድ ጭብጥ ላይም አያተኩሩም፤›› ሲል ትራምፕ ለአንድ ነገር ትኩረት የማይሰጡ ናቸው ሲል አክሏል፡፡
የመጽሐፉን ተዓማኒነት ያጣጣሉት ትራምፕ ራሳቸውን፣ ‹‹የተረጋጋና ተሰጥኦ ያለኝ አዋቂ ነኝ›› ሲሉ፣ የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ሳራ ሳንደርስ ደግሞ፣ ‹‹ከእውነት የራቀ መጽሐፍ›› ብለውታል፡፡
‹‹ፋየር ኤንድ ፊዩሪ›› በተንታኞችና በአንባቢዎች ዘንድ በትራምፕና በዋይት ሐውስ አስተዳደራቸው ላይ ውዥንብርን ቢፈጥርም፣ ሰዎች መጽሐፉን ለመግዛት እየተረባረቡና በመጻሕፍት መደብሮች እያማተሩ መሆኑን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡