Friday, February 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየማስተር ፕላን ጽሕፈት ቤት የሊዝ አዋጁ እንዲሻሻል ምክረ ሐሳብ አቀረበ

የማስተር ፕላን ጽሕፈት ቤት የሊዝ አዋጁ እንዲሻሻል ምክረ ሐሳብ አቀረበ

ቀን:

  • በርካታ ኩባንያዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቤቱታ እያቀረቡ ነው

በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀውን የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን የሚመራው ጽሕፈት ቤት፣ የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 እንዲሻሻል ምክረ ሐሳብ አቀረበ፡፡

ለአዲስ አበባ ከተማ ዕድገት መሠረታዊ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው በማዕከል ደረጃ የተዘጋጁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ለማድረግ፣ የአዋጅ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መሪ ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የመዋቅራዊ ፕላን ቡድን መሪ አቶ ታምራት እሸቱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለአዲስ አበባ ከተማ ቀጣይ ዕድገት አስፈላጊ በመሆናቸው ከሊዝ አዋጅ ወጣ ተደርጎ ሊታሰብ ይገባል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተለይ አዲስ አበባ ከሌሎች ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች፣ የገበያ ማዕከላትና የመዝናኛ ማዕከላት መገንባት እንዳለባቸው በረቂቅ ማስተር ፕላኑ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

ነገር ግን የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 7 ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በግል ለማካሄድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ሆስፒታሎች፣ የጤናና የምርምር ተቋማት፣ ከአራት ኮከብ በላይ የሆኑ ሆቴሎችና ግዙፍ ሪል ስቴቶች የሚስተናገዱት በጨረታ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡

አዋጁን ለማስፈጸም የወጣው መመርያ ቁጥር 11/2004 አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 2 የአገልግሎት መስጫ ዘርፎች የሚስተናገዱት በልዩ ጨረታ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

ነገር ግን የማስተር ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ለከተማው ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ በማለት ያዘጋጃቸውን ፕሮጀክቶች በሊዝ ጨረታ ማልማት ውጤታማ አያደርግም ተብሏል፡፡

‹‹የተዘጋጁት ፕሮጀክቶች ከሊዝ አዋጅ ወጣ ያሉ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቶቹ ለከተማው እጅግ አስፈላጊ በመሆናቸው የሊዝ አዋጅ መሻሻል እንዳለበት ሐሳብ አቅርበናል፤›› በማለት አቶ ታምራት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አዲስ አበባ ዕድገቷን ለማረጋገጥ ደረጃቸውን የጠበቁ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ስለሚያስፈልጉ፣ በአሁኑ ወቅት እነዚህን ፕሮጀክቶች ዕውን ለማድረግ በርካታ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ቦታ እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡

ነገር ግን በሊዝ አዋጁ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለማሰተናገድ ልዩ ጨረታ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ በማቅረቡ፣ የኩባንያዎቹን ጥያቄ ማስተናገድ አለመቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

አቶ ታምራት እንደሚናገሩት፣ የማዕከላቱን አጠቃላይ የመሠረተ ልማት ግንባታ መንግሥት ያካሂዳል፡፡ ነገር ግን የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ ግን በግል ኩባንያዎች መካሄድ ይኖርበታል፡፡

ፕሮጀክቶቹ የሚፈልጉት ቦታ ከ5,000 ካሬ ሜትር በላይ ስለሆነና የመሬት ጥያቄው በሊዝ አዋጅ ላይ በተቀመጠው መሠረት ለማስተናገድ የሚያስቸግር በመሆኑ፣ መንግሥት ሌሎች አማራጮችን ማየት ይኖርበታል በማለት አቶ ታምራት ገልጸዋል፡፡

‹‹ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በጨረታ በሚገኝ መሬት ማልማት አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም ጨረታ ውድድር በመሆኑ አልሚው ከፍተኛ ዋጋ ለመሬቱ የሚመድብ ስለሆነ ለግንባታ የሚሆን ገንዘብ በመሬት ግብይት ላይ እንዲፈስ ያደርጋል፡፡ ይህም የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፤›› በማለት አቶ ታምራት ተናግረዋል፡፡ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ለመገንባት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ጥያቄ ያቀረቡ፣ ነገር ግን በሊዝ አዋጅ ምክንያት መስተናገድ ያልቻሉ ኩባንያዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቤቱታ እያቀረቡ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ኩባንያዎቹ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦታ እንደሚሰጣቸው ገልጾላቸው፣ ነገር ግን ረዥም ርቀት ከሄዱ በኋላ በሊዝ አዋጅ ምክንያት በድርድር ቦታ እንደማይሰጣቸው ማስታወቁን ተቃውመዋል፡፡

ከተለያዩ አቅጣጫዎች ቅሬታ እየቀረበለት የሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ የሊዝ አዋጁን ለማሻሻል እንቅስቃሴ መጀመሩ እየተገለጸ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...