Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኢትዮጵያና ግብፅ በየራሳቸው ፖለቲካዊ ቅርቃር ውስጥ

ኢትዮጵያና ግብፅ በየራሳቸው ፖለቲካዊ ቅርቃር ውስጥ

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው  

ኢትዮጵያና ሰሜን አፍሪካዊቷ ግብፅ የሚያስተሳሷራቸውና የሚያመሳሳሏቸው ጉዳዮች በርከት ያሉ ናቸው፡፡ ቀዳሚው ጉዳይ ሁለቱም የታሪክና የቅድመ ሥልጣኔ ባለቤት መሆናቸው ነው፡፡ ምናልባትም ብቸኛ የአራት ሺሕና የአምስት ሺሕ ዓመታት ዕድሜ ጠገብ የአፍሪካ አገሮች መሆናቸውንም ታሪክ ዘክሮት ይገኛል፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ በሰው ልጅ መገኛነቷ ጥንታዊነቷን የሚተካካል አለ ባይባልም፣ በእኛ የአክሱም ሥነ ሕንፃዎችና በካይሮ ፒራሚዶች የአገሮቹን ቀደምትነት በግርድፉ መጥቀስ ይቻላል፡፡

       አገሮቹ የኦርቶዶክስና ኮፕቲክ ክርስትና ሃይማኖትን ከዘመናት በፊት የተቀበሉ፣ በተለይ የግብፅ ጳጳሳትና የሃይማኖት አባቶችን በኢትዮጵያ እስከ መሰየምና መሾም ይደርሱ የነበሩ፣ አሁንም ድረስ የሁለቱ ቤተ ክርስቲያኖች ትስስር ጠንካራ ሆኖ መቆየቱ  በተመሳስሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል በሁሉቱም አገሮች የሚገኙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እምነቱን የተቀበሉበትም ሆነ ያስፋፉበት ዘመን ተቀራራቢ ከመሆኑ ባሻገር፣ በየአገሮቹ ነበራዊ ሁኔታ ልክ ሃይማኖታዊ አስተምሯቸውን ያሳደጉበት ታሪክም አላቸው፡፡

       ከዚህ ሁሉ በላይ ሁለቱ አገሮች የድንበር ወሰንተኛ ባይሆኑም ተፈጥሮ በጥብቅ ያስተሳሰረቻቸው ናቸው፡፡ የዓለማችን ረጅሙና ጥንታዊው ወንዝ ዓባይ (ናይል) ሁለቱን አገሮች ከአንድ ምንጭ የሚጠጡ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ ለዘመናት አንዱ አመንጪ ሌላው ጠጪ ሆነው መቆየታቸውም አይዘነጋም፡፡ ይህን ትስስር ‹የአፍሪካ ሶሳይቲ› በሚል ስያሜ የሚታወቀው የግብፅ ተቋም ዳይሬክተር እ.ኤ.አ. በየካቲት ወር 2015 ግብፅን ለጎበኘው የአፍሪካ ጋዜጠኞች ቡድን ሲያብራሩ፣  “ዓባይ ሥሩ ኢትዮጵያ ፍሬው ግብፅ ነው፤” ማለታቸው  ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል፡፡

        ያም  ሆኖ እነዚህ ቀደምት አገሮች ያላቸውን ትስስር ያህል የጠበቀ ወዳጅነት የገነቡ  ናቸው ሊባሉ አይችሉም፡፡ ይልቁንም ከቀደመው ዘመን አንስቶ የግብፅ ነገሥታትና መሪዎች የናይልን የውኃ ምንጭ ለመቆጣጠርና አገራችንም ተጠናክራ ከውኃ ሀብቷ መጠቀም እንዳትጀምር ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ ጦር መዘው፣ ጋማ ከብት ጭነው፣ አልፈው ባህርም ተሻግረው እስከ መዋጋት የደረሱበት ጊዜም ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል፡፡ በአባቶቻችን ፅኑ ተጋድሎ አፍረው ተመለሱ እንጂ፡፡

         በእጅ አዙር ከውጭ ወራሪዎች (ከሶማሊያው  ዚያድ ባሬና ከኤርትራው ሻዕቢያ ወራራ) በስተጀርባ መኖራቸው፣ የድህነትና ኋላቀርነት አዙሪታችን እንዳይበጠስ፣ ብሎም በአገር ውስጥ የእርስ በርሳችን ግንኙነት በኋላቀርነቶቹ የጠባብነትና የብሔርተኝነት አስተሳሳብ እንዲናጋ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተፋልመውናል፡፡ እየተፋለሙን እንደሆነም ጥርጥር የለውም፡፡

        እንደዚህም ሆኖ ኢትዮጵያና ግብፅ በቡድን ደረጃም ሆነ በሁለትዮሽ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ውስጥ የቆዩ አገሮች መሆናቸው ሊካድ አይችልም፡፡ ቢያንስ በአፍሪካ አንድነት (ኅብረት) ምሥረታ፣ የተጠናከረ ሒደት ውስጥ ሁለቱም የጎላ ቦታ ነበራቸው፡፡ በአፍሪካ ስፖርት ውድድር መሥራችነትም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በናይል ተፋሰስ አገሮች የምክክር መድረክ በኩል ምንም እንኳን የግብፅ ፍላጎት ባያሳካም፣ ከ13 ዓመታት በኋላ ለታችኛዎቹ ብዙዎቹ አገሮች ጠቃሚ የሚባል ስምምነት ላይ ሲደረስም በጋራ መድረኩ ውስጥ ነበሩ ፡፡  

        ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ለመገንባት፣ መላውን ሕዝብ ያሳተፍ ጥረት በማድረግ ላይ ነች፡፡ እነሆ ከስድስት ዓመታት በኋላ ከ62 በመቶ በላይ ግንባታው መከናወኑም እየተነገረ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ኢትዮጵያና ግብፅ “በሒደት መጣ” መልካም ቢሆን የውኃ አጠቃቀም ድርድራቸውን ቀጥለዋል፡፡

        እንግዲህ  የዚህ ጽሑፍ መሠረታዊ አትኩሮት የሚሆነው እነዚህ አገሮች ከዚህ በኋላስ እንዴት ነው ተግባብተውና ተረዳዳተው ሊሠሩ የሚገባቸው፣ በተለይ ሁለቱ አገሮች በውስጣቸው ያለውን የፖለቲካ ቀውስና ወቅታዊ ፈተና እንዴት እያለፉ፣ ከሴራና የመጠላላፍ ፖለቲካ የፀዳ ብሎም በመተማማን ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን ለማዳበር ይችላሉ የሚለው ነጥብ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የጋራ ጉዳያቸው የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብም ተጠናቆ በቀዳሚነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በመቀጠል ለቀጣናው ሕዝቦች ጥቅም እንዲሰጥ መልዕክት ለማስተላላፍ ይሞክራል፡፡

የግብፅ ወቅታዊ ፈተናዎች

       የግብፅ ሕዝብ አገሩን የሚወድ ቢሆንም በጣም ለውጥ ፈላጊና በመተባባርና በስሜት ከተነሳ ወደ ኋላ የማይል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የዓረቦች መጽሐፍ ደራሲ ዴቪድ ላምብም ይህን ነጥብ አንስቶታል፡፡ ለነገሩ እ.ኤ.አ በ2011 የፀደይ አብዮት ወቅት እንደታየውም ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ ምድረ ፈርኦንን ቀጥቅጦ የገዛውን የሙባረክ አስተዳዳር፣ ከታንክ ጋር ተፋጥጦ የገነደሰው የሕዝብ ማዕበል ነበር፡፡ የግብፅ ሕዝብ የእንቢተኝነት ችቦውን የለኮሰበት የካይሮውን ታህሪር አደባባይ፣ በነውጡ የተቃጠሉት ሐውልቶችና የገዥው የፓርቲ ጽሕፈት ቤት ገና ጥላሸታቸው ሳይረግፍ በቦታው ተገኝቼ ስጎበኝ የተገነዘብኩት፣ ሕዝብ ከተማረረ ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል እንደማያቆመው ነው፡፡

       በእርግጥ በዚያ አብዮት ውስጥ በአንድ በኩል ረጅም ዕድሜና በርካታ ደጋፊ አለው የሚባለው፣ በሌላ በኩል በሃይማኖት አክራሪነትና ጽንፈኝነት የሚታማው ሙስሊም ወንድማማቾች የተሰኘው የፖለቲካ ማኅበር የነቃ ተሳትፎ ነበረው፡፡ ከአብዮቱ በኋላም በተካሄደ ሕዝባዊ ምርጫ መሐመድ ሙርሲን በግብፅ ፕሬዚደንትነት እስከ ማስመረጥ ደርሶ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በኋላ በወታደራዊው ክንፍ ተጠልፎ የቀድሞውን ከፍተኛ መኮንን አብዱልፈታህ አልሲሲንና ባልደረቦቻቸውን ወደ ሥልጣን ያመጣ ዕርምጃ  ቢወሰድም፡፡

       አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት ከዚያን ጊዜ ወዲህ ግብፅ ምንም እንኳን እንደ ሊቢያ በአብዮትና ለውጥ መሻት ስም የመፍረስ አደጋ ባይገጥማትም፣ በሕዝቡ ውስጥ አለመተማመን ተፈጥሯል፣ ደጋግማ ለግብረ ሽብር ስትጋለጥም ታይታለች፡፡ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት በአይኤስ በሊቢያ በረሃ ከተሰየፉ ንፁኃን ግብፃዊያን ጀምሮ፣ በመስጊዶችና አብያተ ክርስቲያኖች ውስጥ፣ በተለያዩ የፖሊስ የጥበቃ ቦታዎችና  ሻርም አል ሼክን በመሰሉ የቱሪስት ሥፍራዎች ላይ ሳይቀር በተፈጸመ የሽብር ጥቃት ብዙዎች የአገሪቱ ሰዎችና የውጭ ዜጎች አልቀዋል፡፡ አካል ጎድሏል፣ ንብረት ወድሟል፡፡

      የአገሪቱ መንግሥትም ከእነዚህ ጥቃቶች ጀርባ በውጭ ካሉ ዓለም አቀፍ ሽብርተኞች ባሻገር በአገር ውስጥ ሙስሊም ወንድማማቾችና ሌሎች ፅንፈኛ ቡድኖች እንዳሉ ደጋግሞ ሲገልጽ ተደምጧል፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ስለሙስሊም ወንድማማቾችና የግብፅ ውስጣዊ ፖለቲካ የተፍታታ አለመሆን (በነገራችን ላይ የግብፅ መንግሥት ጋዜጠኞችን በማሰርና በማሳደድ፣ በዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራስዊ መብቶች አከባባር ጉድለትም የሚወቅሱት እንዳሉ ይታወቃል) አንዳንድ ነገሮችን መጥቀስ የሚያስፈልገው፣ ጉዳዩ የግብፅ ወቅታዊው የፖለቲካ ቅርቃር መሆኑንም ማየት የሚበጀው፡፡

       ሙስሊም ወንድማማችነት እ.ኤ.አ. በ1928 የተመሠረተ የ90 ዓመት ዕድሜ ያለው የእስልምና ሃይማኖትን፣ ፖለቲካንና ማኅበራዊ ሥርዓትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ መሥራትን ዓላማ አድርጐ የተነሳ ፓርቲ ነው፡፡ የሙስሊም ወንድማማችነትን የመሠረተው በወቅቱ (በ1928) የአንድ መደበኛ ትምህርት ቤት መምህር የነበረ ‹ሐሰን አል ባና› የተባለ ሰው ነበር፡፡

       ይህ የፖለቲካ ማኅበር በሌሎች ሙስሊም አገሮችና ሙስሊሞች በርከት ባሉበት ማንኛውም አገር፣ በአንድ ወይም በሌላ እግሩን የዘረጋ ቢሆንም ዋነኛ ጠቅላይ መምርያውና መንቀሳቀሻው ግብፅ ውስጥ ነው፡፡ ለማንኛውም የሽብር ተግባር ‹ሆ› ብለው የሚነሱ 600 ሺሕ አክራሪ አባላትና በርካታ ደጋፊዎች እንዳሉትና የእስልምናን ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ እጁን የማያስገባበት ቦታ እንደሌለም ይነገራል፡፡ ይሁንና አብዛኛው የግብፅ ለዘብተኛ ዜጋ፣  በተለይ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ኃይልና የኮፕቲክ ክርስትና እምነት ተከታዩ ሕዝብ የዚህን ኃይል ወደ ሥልጣን መምጣት ሊቀበሉ አይችሉምና እሱም ፍጥጫውን ከማጠናከር የሚቦዝን አይደለም፡፡

       ለምሳሌ ይህ ኃይል እ.ኤ.አ. በ1948፣ በ1954 እና በ1965 የግብፅን መንግሥት ለመገልበጥና መሪዎችን ለመግደል ባደረጋቸው ሙከራዎቹ የተነሳ፣ መንግሥት በወሰደው ዕርምጃ እስከ መፈረካከስ የደረሰ ቢሆንም ዛሬም ድረስ ከሽብርተኝነቱ ሊታቀብ አለመቻሉን የግብፅ መንግሥት ይገልጻል፡፡ ድርጅቱ ለበርካታ ዓመታት በይፋ እንዳይንቀሳቀስ ታግዶ ከኖረ በኋላ እ.ኤ.አ. በ2011 የግብፅ አብዮት ሙባረክን ሲያስወግድ በይፋ እንዲንቀሳቀስ እንደተፈቀደለትም የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ ዕድል ተጠቅሞ ከሙባረክ በኋላ ላለው ምርጫ ራሱን ለማዘጋጀት ሲል ‹‹የነፃነትና የፍትሕ ፓርቲ›› (Freedom and Justice Party) የተባለ አዲስ ክንፍ አቋቋሞ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

       አዲሱ ፓርቲ ከስም ለውጥ በስተቀር አቋሙ በሙሉ የሙስሊም ወንድማማችነት የማይለወጥ አቋም ነው፡፡ ፓርቲው በዚህ የሽፋን መጠሪያ ተጠቅሞ ለምርጫ ተወዳዳረ፡፡ ፓርቲውን ወክለው ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደሩት መሐመድ ሙርሲ በምርጫ አሸንፈው ገማል አብደል ናስር እ.ኤ.አ. በ1952 ከገለበጣቸው የግብፅ ንጉሥ በኋላ የመጀመሪያው በምርጫ ያሸነፉ ሲቪል ፕሬዚዳንት ሆነውም ነበር፡፡ ሥልጣን ከያዙ  አንድ ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ. በ2013 በተቃዋሚዎቹ ጩኸትና ሠልፍ በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ከሥልጣናቸው ወርደው በወታደራዊ የማቆያ ሥፍራ እንዲያርፍ ተደረጉ፡፡ ዛሬም በዕድሜ ልክ ፍርድ ከነጋሻ ጃግሬዎቻቸው ወህኒ ወርደው ቢገኙም፡፡   

       ሙስሊም ወንድማማቾች ታሪኩ እንደሚያስረዳው የሰላማዊ ትግል፣ የሰብዓዊ መብት፣ የንግግርና የመሰብሰብ ነፃነት መርሆዎችን ‹‹አከብራለሁ›› ቢልም፣ ከአክራሪነትና ከፅንፈኝነት የሚወጣ እንዳልሆነ የሚናገሩ ብዙዎቸ ናቸው፡፡ ፓርቲው በሰላማዊ ትግልና በድርድር ፈጽሞ አያምንም፡፡ እ.ኤ.አ. በ1952 ፓርቲው የግብፅን ለዘብተኛ ተራማጅና የሥልጣኔ ዘመን ማክተሚያ የሆነ ድርጊት መፈጸሙ በጥቁር መዝገብ ተከትቦ ይገኛል፡፡

       በካይሮ ከተማ ውስጥ ብቻ ከ750 በላይ የሆኑ ሕንፃዎችን በእሳት አቃጥሎ አውድሟል፡፡ እነዚህ ሕንፃዎች አብዛኞቹ የምሽት ክበባት፣ ቴአትር ቤቶች፣ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ሲሆኑ፣ የእንግሊዝና ሌሎች የውጭ አገሮች ቱሪስቶች የሚያዘወትሩባቸው ነበሩ፡፡ ያለቁት ሰዎች በሙሉ ሲቪሎችና ሴቶች ነበሩ፡፡ ናፖሊዮን የምዕራቡን ዓለም ቴክኖሎጂና ባህል እ.ኤ.አ. በ1798 ወደ ግብፅ ምድር አምጥቶ፣ ፈረንሣዊው ፈርዲናንድ ደሎሴፕስ የስዊዝ ቦይን ሠርቶ የካይሮን ዝና የገነባውን ያህል፣ ያ ድርጊት አገሪቱን ቅስሟን ሰብሮት እንደነበር ይነገራል፡፡ ዛሬም ድረስ የግብፅ ፖለቲካ የውስጥ ሙግት እየመነጨ ያለው፣ ከዘመናዊው የምዕራቡ ዓለም ሰፊ ልምድ በወሰደችው ግብፅና ፅንፈኝነት ሊወልዳት በሚፈልጋት ግብፅ መሀል በመሆኑ፣ ብሎም ካይሮ ከምትገኝበት ቀጣና አኳያ የአገሪቱ የውስጥ ፖለቲካ በፈተና ውስጥ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ 

       ይኼው ድርጅት በሰላም ጉዳይ ላይም እምነት የለውም፡፡ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት እ.ኤ.አ. በ1979 ከእስራኤል ጋር የሰላም ውል በመፈራረማቸው ብቻ ጠላት ሆኖባቸው ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1981 ኦክቶበር 6 ቀን ‹ታንዚም አል ጅሃድ› ከተባለ ሌላ ሽብርተኛ ቡድን ጋር በመተባበርም አደባባይ ላይ አንዋር ሳዳት እንዲገደሉ ያደረገ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ኃይል ሥልጣን ቢይዝም፣ ባይዝም ለግብፅ ዋነኛው የውስጥ እንቅፋት እንደሆነ ማስተባባል አዳጋች ነው የሚባለው ከዚሁ እውነታ በመነሳት ነው፡፡

        ከእኛም ጋር ባለው የዓባይ ዲፕሎማሲ ወቅት፣ በተለይም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመርን ተከትሎ የታየው የግብፃዊያን አንዳንድ ዝንባሌ ከሙስሊም ወንድማማቾች ድርጅት ተፅዕኖ ጋር የተያያዘ እንደሆነ የሚገልጹ አሉ፡፡ ራሳቸው መሐመድ ሙርሲ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት “በተሳሳተ” የቴሌቨዥን ሥርጭት ስም ባለሥልጣኖቻቸውን ሰብስበው “ኢትዮጵያን እንውረር? እናበጣብጥ? ወይስ እንደብድብ?” እስከማለት የደረሰ ኋላቀርነት የተሞላበት ፕሮፓጋንዳ መሥራታቸው አይዘነጋም፡፡ ከዚያም ወዲህ በሕገ መንግሥቱ ረቂቅ ወቅት በአንቀጽ 44 የናይል ውኃ አጠቃቃም ጉዳይ (በእጃቸው በሌለው ሀብት) እንዲካተት መደረጉ፣ የሕዝቡንና የነውጠኛውን የፖለቲካ ማኅበር ቁጣ ለማብረድ ቢመስልም ለትውልድ ጭቅጭቅን ከማጋባት ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው ብዙዎች ተናግረዋል፡፡ በዚህ ላይ መጪው የግብፅ ምርጫም ፍጥቻ እንደማያጣውና የዓባይ ጉዳይም የድምፅ ማሰባሰቢያው አንዱ ነቁጥ እንደሚሆን መገንዘብ ተገቢ ይሆናል፡፡

       በድምሩ ሙስሊም ወንድማማቾችና ሌሎች ፅንፈኛ ቡኖች የግብፅን ውስጣዊ ፖለቲካ ከመፈተን ባሻገር፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ላላት ሁለንተናዊ ግንኙነት እንቅፋት እየሆኑ መምጣታቸውም አይቀርም፡፡ ከዚህ አንፃር የግብፅ መንግሥትና ሕዝብ በአገራቸው ልማትና ዴሞክራሲን ከማስፈን ባሻገር በትብብርና በመተማማን ላይ ለተመሠረተ የአገሮች ግንኙነት፣ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ካሉት ጋርም በሰጥቶ መቀበል ላይ ለተመሠረተ ሀቀኛ ወዳጅነት መዘጋጀት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህን አለማድረግ ግን በችግር ላይ ሌላ ችግር እንደ መፍጠር የሚቆጠር ነው፡፡ ስለግብፅ ይህን ካልኩ ወደ ራሳችን ጉዳይ በመግባት አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳት ልሞክር፡፡

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፈተና

       ኢትዮጵያ ከቅድመ ሥልጣኔ ተገፍትራ በኋላቀርነት፣ በድህነትና የእርስ በርስ ጦርነት ያባከነችው ጊዜ የሚያስቆጭና የሚያሳዝን የዘመን ውድቀት ነው፡፡ ካለፉት 27 ዓመታት ወዲህ ግን ተስፋ ሰጪ ሰላምና ልማት ከመታየቱ ባሻገር፣ የዴሞክራሲ ጅምርም መፍካቱ መልካም ነበር፡፡ እዚህ ላይ በአንድ በኩል ካላፈው የተዛባ ታሪክ በመውጣት የብሔሮች ማንነትና ጥቅም መከበር መጀመሩ፣ በሌላ በኩል ቀላል በማይባል ደረጃ ከገጠር እስከ ከተማ የልማትና ዕድገት መነሳሳት መፈጠሩን በኩራት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ራሱ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በድፍረት በማከናወን መጪውን ጊዜ ብሩህ ሊያደርጉ የሚችሉ መንግሥታዊና የሕዝብ መነቃቃቶች መታየታቸውም አይካድም፡፡

       ከላይ በተጠቀሰው የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ በአገራችን ለታዩት ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ደግሞ ሕዝቡ (የገጠርና የከተማ ነዋሪው)፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞችና አጋር አካላት የየራሳቸው ድርሻ ቢኖራቸውም፣ ለሦስት አሥርት ዓመታት ጥቂት ጉዳይ አገሪቱን የመራት ኢሕአዴግና መንግሥት ግን የአንበሳውን ድርሻ ቢወስዱ ክፋት የለውም፡፡ መውሰድም አለባቸው፡፡

       ይሁንና ኢሕአዴግ የሚታወቅባቸው መልካም ተሞክሮዎች ያሉትን ያህል፣  በዴሞክራሲው መስክ ክፉኛ እየታማ መምጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በሙስና፣ በመልካም አስተዳዳር ዕጦት፣ በኔትወርክ በመሳሳብና የሕግ የበላይነት በማጓደል በኩል ያለው ክፍተት ብዙዎችን የሚያስማማ ነው። በልማት ረገድ የተመዘገቡ ተስፋዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ከፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ሥርጭት አንፃር ያለው የሕዝብ ጉምጉምታም ቀላል አይደለም፡፡ “ጥቅሜ ተነካ”፣ “ተበደልኩ” ፣ “የበይ ተመልካች ሆኛለሁ”  የሚለው ወገንም መጠኑ ትንሽ አይመስለኝም፡፡

        ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሥርዓቱ ውስጥ በመሥራችነት የሚታወቁትን የብሔር ፓርቲዎች ጭምር ውዝግብ ውስጥ የከተተ የወሰን፣ የማንነት፣ የፍትሐዊ ሀብትና ሥልጣን ክፍፍል ጥያቄ የታጨቀበት ሕዝባዊ መከፋት ተደጋግሞ እየተነሳ ነው፡፡ በዚህ ላይ የሕግ በላይነት መላላት፣ የዴሞክራሲው መቀጨጭና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ አለመጠናከር አገሪቱን እያናወዛት የሚገኝ ወቅታዊ ፈተና ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህም በላይ ተስፋ ሰጪውን ፌዴራላዊ ሥርዓትና ሕገ መንግሥቱን በአግባቡና በመርህ ላይ ተመሥርቶ መተግበር ባለመቻሉ ምክንያት የሕዝብ ለሕዝብ ግጭቶችና መገፋፋቶች ጎልተው ታይተዋል፡፡

       በዚህ መዘዝ  የዜጎች ስደት፣ መፈናቀልና እንግልት ብቻ ሳይሆን አሳፋሪ በሚባል ደረጃ የእርስ በርስ ግድያና ዘረፋ ተፈጽሟል፡፡ ይህ ሁኔታም በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ ጥያቄ ለሚያነሱ ኃይሎች ምቹ የመከራከሪያ አጋጣሚ ከመፍጠሩ በላይ፣ ዜጎች በመንግሥትና በሥርዓቱ ላይ ያላቸው መተማማን እንዲሸረሽር በማድረግ ላይ ነው፡፡ በሁሉም መስክ የተጀመሩ ፈጣን ለውጦችን ለማስቀጠልም እንደ ቀዳሚ አገራዊ እንቅፋት ተቆጥሮ እርምት ሊደረግለት የሚገባው ዛሬውኑ መሆን አለበት፡፡

        አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለአገራችን ተጠናክሮ መውጣት (ሕገ መንግሥቱን አክብሮ ለማስከበር) የኢሕአዴግ መጠናከርና ሕገ መንግሥቱን በብቃት ተግብሮ፣ ማስተግበር ወሳኝ ጉዳይ  ነው፡፡  ይሁንና ቢያንስ ግንባሩ የሚታወቅበትን ውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲያዊነት፣ ለመርህ ተገዥነትና ሚስጥራዊነት እየሸረሸረ መምጣቱ  አሳሳቢ እየሆነ ይገኛል፡፡ በተለይ የድርጅቱን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰው (አቶ መለስን) በሞት ካጣ ወዲህ ማዕካላዊነት ከመላላቱ ባሻገር፣ ወሳኝ የፖለቲካውን የአመራር ሥራ  የተረከበና ሕዝቡን ለመምራት ቀድሞ የተገኘ ሰው በግንባሩ ያለ አለመምሰሉ አገራዊ መተማማኑን ክፉኛ ጎድቶታል የሚሉ ወገኖች ተበራክተዋል፡፡  

        ብዙ ጊዜ  እንደሚባለው  እስካሁን  ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማምጣት  ብርቱ ሥራ እያከናወነ መምጣቱ ሊካድ አይችልም፡፡ አምባገኑን ወታደራዊ ሥርዓት ከማፈራረስ ጀምሮ በምትኩ ሕዝባዊ መንግሥት ለመመሥረትም ሆነ ከነጉድለቱም መላው የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችን ያማከለ ሕገ መንግሥት በማፅደቅ ረገድ ከፍተኛውን ድርሻ ተጫውቷል፡፡  ያ በፓርቲው ውስጥ የተገነባው ሕዝባዊ ባህሪ  ግን እያደገና ሁሉን አሳታፊ እየሆነ ብቻ ሳይሆን፣ እየጎመራ መሄድ ሲገባው ቀስ በቀስ እየተሸረሸረና ፀረ ዴሞክራሲያዊነት (መርህ አልባነት፣ መንደርተኝነት፣ አድርባይነትና አምባገነነት…)  እንዲሁም  የጥላቻ  ፖለቲካ  አስተምህሮ  እንደ ጥንጣን እየበላው ሲመጣ፣ ይመለከተኛል የሚል አካልን ሁሉ ሊያስጨንቅ ይገባል፡፡ ለህዳሴው ፕሮጀክትና እንደ አገር ተጠናክሮ ለመቀጠልም ተግዳሮት ሆኖ መታየት አለበት፡፡

        በመሠረቱ በተለያዩ የዓለም የፓርቲዎች ታሪክ ውስጥ እንደሚታየው የፖለቲካ ፍፁምነት የሚባል ነገር የለም፡፡  የአብዛኛውን ሕዝብ ይሆን እንጂ የምልዓተ ሕዝብን እርካታ በአጭር ጊዜ ከዳር ዳር ለማሟላትም የሚቻል አይሆንም። ተደጋግሞ እንደሚባለው ኢሕአዴግም ቢሆን የሰው እንጂ የመላዕክት ስብስብ ባለመሆኑ ይህ ተፈጥሮዊ ጫና ይኖርበታል። ነገር ግን  ሲሠራ እንደሚሳሳት የምድር፣ ያውም ብዙ ፍላጎቶችና ድህነት በተንሰራፋበት ምድር እንደሚመራ ኃይል ራሱን በሆደ ሰፊነትና  የአብዛኛውን ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ባቀራረበ መንገድ፣ ዓለምም በደረሰበት የአስተሳሳብ ደረጃ ልክ መምራት አለበት። ስለሆነም በየጊዜው ችግሮችን እየፈተሹና እየተከታተሉ ማፅዳትና የእርምት ዕርምጃም መውሰድ ተገቢነት ያለው አሠራር ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠልም ወሳኝ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። 

       በሌላ በኩል አሁንም መንግሥት ትኩረት መስጠት ያለበት የፌዴራል ሥርዓቱ ለሕዝቦች እኩል ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ያበረከተውን አስተዋጽኦ በመፈተሽ፣ ለሕዝቦች ኅብረ ብሔራዊ አንድነት መጠናከር የጎላ ሚና እንዲጫወት ሳያሰልስ መታገል ላይ  ሊሆን ይገባል፡፡   ለዚህ ደግሞ  ባለፉት  ጊዜያት  ሲቀነቀን የነበረውን ልዩነትን የማጉላት (የውጭ ኃይሎች የማደከሚያ ሥልት እንደ መሆኑ ተግባሩ በሌሎች ድጋፍ እንዳለው ይታወቃል) እና የታሪክ ውዝግብን የማጫር ትርፍ የለሽ አካሄድን በመተው  በአንድ በኩል የሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኛነት እንዲጠናከር፣ በሌላ ወገንና በዋናነት ግን አገራዊ የጋራ እሴቶችና የአንድነት መልህቆች ሥር እንዲሰዱ በትኩረት መሥራትና ሕዝቡንም ማነሳሳት ያስፈልጋል፡፡  ከጥላቻ ፖለቲካና ከዜሮ ድምር ጨዋታ በመውጣት ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በአገራቸው ጉዳይ የየድርሻቸውን ሚና እንዲጫወቱ የማድረግ ታሪካዊ  ኃላፊነትም ተጥሎበታል፡፡

        እዚህ ላይ ኢትዮጵያ የሁላችንም ቤት መሆኗን ተገንዝቦ ለሚታዩ ችግሮች የጋራ መፍትሔ መፈለግ ግን ከሁሉም ወገኖች የሚጠበቅ ነው፡፡ ስለሆነም የአገሪቱን ወቅታዊ  ችግር ሁሉ በኢሕአዴግ ላይ መጫን ብቻ ሳይሆን፣ ይመለከታቸዋል የሚባሉ ባለሀብቶች፣ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ምሁራንና አክቲቪስቶችም በቅንነትና በአገራዊ ስሜት መሳተፍና ለመጭው የአገሪቱ ህዳሴ የሚረዳ ዕርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይጠበቅብናል፡፡ 

       ለዚህም ሁሉም ወገኖች በቅንነትና ሕዝባዊነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ መስተጋብር መፍጠርን ቀዳሚ ተግባር ማድረግ አለባቸው፡፡ ይህን ማድረግ ሲቻል ነው እንደ አገር የምንቀጥለው፣ ብንናገር የምንደመጠው፣ ከጎረቤትም ሆነ ከወዲያ ማዶ የሚመጣን ማንኛውም ተፅዕኖ ለመመከት የምንበቃው፡፡ በታላቁ የህዳሴ ግድብም ሆነ በሌሎች ግዙፍ ተግባራትና ፕሮጀክቶች ላይ ዘላቂ ውጤት ማስመዝገብ የሚቻለውም በዚሁ መንገድ ብቻ ነው፡፡

ለኢትዮ ግብፅ ትብብር የሚበጀው

       ተቀምጦ መምከር ያውም የግል ዕይታን በአገራዊ ጉዳይ ላይ እንደ ልብ መሰንዘር ቀላል፣ በጣም ቀላል ሥራ እንደሆነ ይገባኛል፡፡ “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ” እንዲሉ፡፡  ያም ሆኖ ለኢትዮጵያና ለግብፅ መንግሥታት (ሕዝቦች) አሁንም በቀዳሚነት የሚበጀው የውስጥ ሰላማቸውን፣ ልማታቸውንና ዴሞክራሲያዊ ምኅዳራቸውን ማጠናከርና እንደ ደረሱበት የኑሮ ደረጃ የሕዝብ ጥያቄን የመመለስ ብቃትን ማሳደግ መሆን እንዳለበት ማስገንዘብ ከገራገር ምክርም በላይ ነው፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ከዚህ ቀደምም በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብታችን እንዳይከበር ካስገደዱን ምክንያቶች መካከል ዋነኛው፣ ድህነታችንና ኋላቀርነታችን እንደነበር ማስታወስ ያስፈልገናል። ይህ ትናንት ነው። ዛሬም ቢሆን ግን አያገረሽም ብሎ መደምደም  አይቻልም፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን እየታየ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ አለመተማማንና የብሔረሰቦች ግጭት የሕዝቡንና የባለሀብቱን ተደፋፍሮ ወደ ሥራ መግባት ሊያወክ የሚችል ነው፡፡ የኑሮ ውድነትንና ሥራ አጥነትንም ያባብሳል፡፡ አገርንም ወደ ቀውስ የሚገፋ መሆኑን ሳይዘናጉ ማጤን ያስፈልጋል፡፡

        አገራችን የምትከበረውም ሆነ እያደገ የመጣውን በጎ ተፅዕኖ የመፍጠር ሚናዋን የምታስቀጥለው እንደ ወትሮው ሁሉ ሰላሟን ጠብቃ፣  ለቀጣናው ሰላምም ዘብ ስትቆም፣ ልማቱና ዕድገቱም ሳይስተጎጎል ሲቀጥል፣ እንዲሁም በሰብዓዊና በዴሞክራሲያዊ የዜጎች መብት አጠባባቅ አገሪቱ ከመወቀስ ስትድን ብቻ ነው፡፡ በየቦታው መለስ ቀለስ በሚል ነውጥ ዜጎች እየሞቱ፣ ሀብት እየወደመና አገራዊ ዋስትና እየተዳከመ ሁነኛ አጋር ማግኘት አሁን ባለችው ዓለም መክበዱ አይቀሬ ነው፡፡

        ከግብፅ ጋር ባለው የሁለትዮሽ ግንኙነትም ቢሆን ከኖረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባሻገር (በተለይ የግብፅ ፖለቲከኞች ከጭቃ እሾካዊ አካሄድ ወጥተው) በሰጥቶ መቀበልና በመተማማን ላይ ያተኮረ ሁሉ አቀፍ መስተጋብር መገንባት አስፈላጊ ነው፡፡ ስምምነቱ ሁሉ አቀፍ መሆኑ መረጋጋጥ ያለበትም አንዱ በሌላው የውስጥ ጉዳይ እስካለመግባትና አንዱ ለሌላው መሻሻል ጠጠር እስከማቀበል መድረስ ባለበት ደረጃ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም “አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ” ሳይሆን፣ ከሁሉም የተፋሰስ አገሮችና ጎረቤቶች ጋር ታስቦበት እንዲፈጸም በፖሊሲ ሊደገፍ ይገባዋል፡፡  

        እስካሁን ኢትዮጵያ የግብፅን ፍትሐዊ የውኃ ጥቅም እንደማትነካ ግድቡ ኃይል አመንጭቶ ተገቢው መጠን ያለው ውኃ እንደሚለቀቅ አረጋግጣለች፡፡ ኃይል ሲመነጭም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መድረስ የሚችል መሆኑም የሚታወቅ ነው፡፡  ኢትዮጵያ አሁን ለሱዳን፣ ለጂቡቲና ለኬኒያ ከምታቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ ለሩዋንዳና ለየመን ለማቅረብ በድርድር ላይ እንደምትገኝ ሲገለጽ፣ በብዙዎች ዘንድ ግርምትን አጭሮ እንደ ነበር አይዘነጋም፡፡ ይህ ሐሳብ ዕውን መሆን የሚችለው ግን ታላቁ ፕሮጀክት ተጠናቆ ኃይል ሲያመነጭ ብቻ እንደመሆኑ፣ እዚህ ላይ አተኩሮ መረባረብ ለአፍታም ያህል ሊዘነጋ አይገባውም፡፡

       በዚህ ረገድ  ከሁለት ወራት በፊት የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ የውኃ ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ 16ኛው መድረክ ላይ ምክክር ማድረጋቸው ተደምጧል፡፡ ከሳምንታት በኋላም 17ኛው የምክክር መድረክ በግብፅ ካይሮ ተካሄዷል፡፡ ይሁንና ውይይቱም  አሁንም ድረስ ታላቁ ህዳሴ ግድብ በታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ላይ ስለሚያደርሰው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና አካባቢዊ ተፅዕኖ፣ እንዲሁም የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ ተፅዕኖ ጥናት ቢያወሳም እዚህ ግባ የሚባል ስምምነት ላይ ስለመደረሱ የተገኘ ፍንጭ የለም፡፡

       እንዲያውም በሒደቱ መሀል የግብፅ ፕሬዚደንት አብዱልፈታህ አልሲሲ “ጠብታ ውኃን ለማንም አሳልፈን አንሰጥም” የሚለው ንግግርና የካይሮ ሚዲያዎች ጉሰማ ዳግም ጉዳዮን አንሮት ሰንብቷል፡፡ እነሆ አሁን በመሪዎች ደረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በካይሮ መገኘትና ገንቢ ምክክር ማድረግ ግን ሌላ በጎ ተስፋ የሚያጭር ነው፡፡ እንግዲህ መጭውን ጊዜ በአዲስ ተስፋ ስንጠብቅ፣ ለሁሉቱም አገሮች የሚጠቅመው የውስጥ ችግርን ፈጥነው እያስተካካሉ፣ ከፖለቲካዊ ቅርቃር ውስጥ በመውጣት  በትብብር መቆም ብቻ እንደሆነ በመጠቆም  ነው፡፡ ሰላም!!

    ከአዘጋጁጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...