Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የተቀመጠው ሳይነሳ የቆመው እንዴት ይቀመጣል?

እነሆ መንገድ። ዛሬ የምንጓዘው ከጀሞ ወደ ሜክሲኮ ነው። ከመንጋቱ ነዋሪው ከቤቱ ነቅሎ ወጥቷል። እንቅልፍና ሰላም ያልጠገቡ ፊቶች አባብጠው በይስሙላ ፈገግታ እየተያዩ የውሸት ሰላምታ ይለዋወጣሉ። ሲታሹ ያደሩ ደም የመሰሉ ዓይኖች እያጨነቆሩ ርቀት ያያሉ። ግርግሩ ጦፏል። ምድር ተሸብሯል። ተማሪው ይሮጣል። ሠራተኛው በፍጥነትና በችኮላ ይራመዳል። አሽከርካሪው ከእነ ተሽከርካሪው ይራኮታል። ይኼ ሁሉ ግርግር አንዳች ነገር መጥቶብን ከተማ ለቃችሁ ውጡ የተባለ ያስመስለዋል። ታክሲ ጥበቃ ሠልፍ ከያዝነው መሀል አንድ መንገደኛ፣ “ይገርማል እኮ። አሁን ይኼ ሁላ ሰው ዕውን ሲሠራ ነው የሚውለው? እንደዚህ ጥድፊያ እንደዚህ ሩጫ ከሆነ አይደለም ስምንት አሥር ሰዓት ሦስትና አራት ሰዓት በቅጡ ተሠርቶ አገር የትና የት አይሽቀነጠርም ነበር? የምን ቻይና? የምን አሜሪካ? ማለት አልነበረብንም እንደ አሯሯጣችን?” እያለ ይለፈልፋል።

እና ከኋላው ያለች ጠይም ሎጋ ወጣት፣ “ታዲያ ምን ስንሠራ ነው የምንውለው? ሥራ ካልሆነ ምንድነው እንዲህ የሚያስሮጠን?” አለችው። “ወሬ ነዋ። ወሬና ሴራ ነው የምናውቀው። መሥሪያ ቤት ደርሼ ስለእከሌ ምን አውርቼ? ምን ሰምቼ? እከሌን እንዴት ብዬ አስጠምጄ? አስገምግሜ? ሌላ ምን ሥራ አለን? ሥራ እንዲህ ነው እንዴ? አላየሽም አውሮፓን? አላየሽም ኤዢያን?” አላት። ይኼኔ ሎጋዋን ማባበል የፈለገ ልጅ እግር አጋጣሚውን ለመጠቀም አላመነታም። “የዘንድሮ ሰው እኮ ሲገርም? እንደምንም ወሬ ጠምዝዞ ቪቫውን ካላስቆጠረ  አይሆንለትም። አሁን ይኼ እንኳን አውሮፓንና ኤዢያን ያየ ሊመስል አሜሪካ ግቢን የሚያውቅ ይመስልሻል?” ሲላት ልጅት ፈገግ ብላ፣ “ለዛሬ አልተሳካልህም። አርፈህ ተቀመጥ፤” አለችው። “ወንበር ማን ለቆለት ነው አርፎ የሚቀመጠው? የተቀመጡት ሳይነሱ የቆሙት ጭራሽ ለመቀመጥ ያስባሉ?” ይላል ያም ያም። ለከፋና ልክፍቱ በዝቶ ይኼው ከጎሳና ከጎጥ አልፈን ደግሞ በመልክና በፆታም ቆመንም ተቀምጠንም መጠማመድ ልንጀምር ነው። ምን ይለናል አትሉም?

“የት አሉና ነው ታክሲዎቹ የምሠለፈው?” አንዱ መንገደኛ ይነጫነጫል። “ይመጣሉ ነዳጅ ሊቀዱ ተሠልፈው ነው። እናንተም ተሠልፋችሁ ጠብቁ። አይዟችሁ የታክሲ ሠልፍ ነው ሰላማዊ ሠልፍ አይደለም የምናሠልፋችሁ፤” ይላል አንድ ቀልቃላ ወያላ። ሁኑ፣ ተናገሩ፣ ሥሩ ከተባሉት ውልፍት ማለት እያስከተለ ያለው ጣጣ ነዋሪን ስላሰለቸው ይመስላል፣ በዝምታ ላይጓዝ በሠልፍ መስመር ውስጥ ይገተራል። “እነሆ በመጨረሻው ዘመን ነዳጅ በሌላው ዓለም ሲረክስ በኢትዮጵያ ጠፍቶ መኪኖች እንደ ታክሲ ሠልፈኞች ሠልፍ ይጀምራሉ’ የሚል ትንቢት ተጽፎ ሳናነበው ቀርተን ይሆን ጎበዝ? እስኪ እናጣራ!” ብላ አንዲት ወይዘሮ በአካባቢዋ ያለውን ሰው በጨዋታዋ ታዝናናለች። “አዳሜ በቃ ማዕከላዊ ሊዘጋ ነው ሲባል የፌስቡክ ፔጁን በየመንገዱ በአፉ መክፈት ጀመረ አይደል?” ይላል አንድ ጎልማሳ። ትንሽ እልፍ ብሎ ደግሞ ማልዶ የተከፈተ ሙዚቃ ቤት ጥዑም ዜማ ይልክልናል። “ተው ማነህ ተው ማነህ የተኛውን ልቤን ትቀሰቅሳለህ… መንደርተኛው ሁሉ እሳት ጫሪ ነው… ያንን ገል አደራ ሰው እንዳይነካው…” ስትል እንሰማለን ዘፋኟ።

‹‹አይ ግጥም? አይ ጥበብ? እኔ ምለው ለምንድነው ጥበብም እንደ ዴሞክራሲ አንድ ዘመን ላይ ብልጭ ብሎ የጠፋብን?” ስትል አንዲት ሠልፈኛ እሳት ትለኩሳለች። “እሱን ስንገረፍ እናወጣዋለን። አንድ ቀን አይቀርልን?” ይላል አንድ ጎረምሳ። “ዴሞክራሲ ደግሞ መቼ ጠፋብን? እኛ ነን እንጂ የጠፋንበት። በሰው አገር ልክ የተሰፋ ርዕዮት ዓለም ለእኛ ካልሆነ ስንል እየተደነቃቀፍን፣ ለልማት ተባበሩ ሲባል እኛ የመልሶ መገንባትን ጽንሰ ሐሳብ ሙዚቃው ውስጥ ሳይቀር ደንጉረን፣ በሰው ወርቅ መድመቅ ስንጀምር ነው ነገሩ ሁሉ እንዳይሆን የሆነው፤” ይላታል ጎልማሳው። ይኼ ጨዋታ ሳይገባዳድ ደግሞ እዚያ ማዶ ከሠልፉ ጫፍ አካባቢ ፌዘኛ ወጣቶች፣ “መቆማችን ካልቀረ ለምን ብሔራዊ መዝሙር አታዘምሩንም? ተማሪ ብቻ ነው ባንዲራ መስቀል ያለበት ያለው ማን ነው? አይደል እንዴ ሰዎች? ሠልፉ ካልቀረልን የዜግነት ክብሩስ ለምን ይለፈን?” ሲባባሉ ተራ አስከባሪዎቹ፣ “ለዛሬ አልተሳካላችሁም፤” እያሉ ያፌዛሉ። ማን ይሆን ዘንድሮ የሚሳካለት?

ጉዟችን ተጀምሯል። “ቆይ ግን ታክሲዎቹ ነዳጅ ከሱዳን ነው ወይስ ከማደያ ነው የሚቀዱት?” ተሳፋሪው ወያላውን ሊበላው አሰፍስፏል። “ኧረ ተውን እስኪ! አሁንማ ብለን ብለን ሳናጣ የሚቸግረን ይዘን የሚርበን ሆንን እኮ!” ይላል ከፊት ያለው። የተሳፈርንባት ታክሲ ከየዘርፉ ከየዕድሜ እርከኑ ከየኑሮ ደረጃው መራርጣ አሳፍራን ወዲያው መክነፍ ጀመረች። “እሁሁ!” መሀል መቀመጫ ላይ አንዲት አዛውንት በረጅሙ ይተነፍሳሉ። አጠገባቸው የተመቀጠ ወጣት፣ “ምነው እማማ አመመዎ?” ይጠይቃቸዋል። “እ! ይህችን ያህል ቆምሽ ብሎ ይኼውልህ ይኼ እግሬ ማበጥ ጀመረ። ስቅስቃቱ ደግሞ አይጣል ነው! ልደቱን እርፍ ብዬ ውዬ ነበር። ይኼው ማግሥቱን ጀመረ…” ሲሉት “አይዘዎት! ትንሽ ጊዜ ነው። በቅርቡ በባቡር አልጋ ተከራይተን ተሳፍረን ከዚህ ከተማ የምንጠፋበት ጊዜ እየመጣ ነው። ድሬና ጂቡቲ ሄደን አዲስ ጎጆ አዲስ ዓለም እንጀምራለን። አዲስ አበባ ከሽፋለች። አውቶቡሱም ታክሲውም በቁጥራችን ልክ ይደረግላችኋል እያሉ ስንት ዓመት ሸወዱን። እነሱማ ምን አለባቸው በቪኤት እየተንፈላሰሱ። ሥራ የሚያውቁ ይመስላሉ ወሬ ሲያወሩ። ወሬኞች፤” እያለ ተንተከተከ።

አዛውንቷ ታዝበውት ሽራፊ ፈገግታ ገጻቸው ላይ ተሥሎ፣ “ኧረ እባክህ ልጄ እንኑርበት። አንተም ብትሰነብት አይሻልህም? ከሰነበትክ እንደምንም ብለህ እዚያ የፈረደበት አሜሪካ መሄድህ አይቀርም። ስንቱ ሄዷል። ምን በወጣህ በገዛ አፍህ ዕድልህን የምታበላሸው፡፡ ይኼ ማዕከላዊ የሚሉት ይዘጋል፣ ያሰርናቸውን እንፈታለን ምናምን ሲሉ አምነሃቸው ነው? ዝንጀሮ ዛፍ ስትወጣ መጀመርያ ምኗ እንደሚታይ አታውቅም? ቂጧ እኮ ነው። ለራሳችሁ ማወቅ አለባችሁ እናንተ ወጣቶች፤” ብለው ምክር ጀመሩ። “አይ እማማ! ማወቅ ምን ዋጋ አለው? ማመን ነው እንጂ! ማወቅ ብቻውንማ መቼ በጀን? ይኼው እርስ በእርሳችን እያደናቆረ ያስቸገረን አወቅኩ ባይነት አይደል?” ብሎ ያልተጠየቀውን መለሰላቸው። እሳቸውም ሰምና ወርቁ ገብቷቸው፣ “አሃ! ሳያዩ የሚያምኑ ልማታዊ ናቸው እያልከኝ ነው?” ሲሉት ገሚሱ ተሳፋሪ ሳቀ። ‘ከመፈከር መፈተል ‘ቦነስ’ ዕድሜ ሳያስጨምረን አይቀርም’ ያለ ይመስላል መንገደኛው!

መንገዱ በብዙ ፀጥታ ተገባደደ። ተሳፋሪ መጣ ተሳፈሪ ሄደ። ወረደ፣ ወጣ። ያው የወትሮው የኑሮ ሰርክ በበዓል ማግሥት ቀጠለ። ወሬ ግን የለም። ሰው ፊቱ ላይ ይዞ የሚዞረው መሰልቸት ብቻ ነው። ያለወትሮው ተሳፋሪው ሳይነጋገር አንድ የሚያግባባው ቋንቋ ያለ ሳይመስል ‹ወራጅ› እያለ ይወርዳል። ሜክሲኮ ከመድረሳችን በፊት ግን፣ “አይ አዲስ አበባ?” አለ ሳር ቤት የተሳፈረ ወጣት ለጓደኛው። “አስበኸዋል በእኛ ጊዜ ምን ያህል ለዛ ያላት ከተማ እንደነበረች?” ሲለው ያኛው “ቀላል? በዓሉ በዓል ነበር። ዎክ ስታደርግ ራሱ የሚሰማህ ስሜት። ምቾቱ። ሰው አይጎረብጥህ። ምን ዓይቶብኝ ነው የገላመጠኝ? የት አውቆኝ ነው ያጉረጠረጠብኝ? ሳትል ዘና ብለህ ወጥተህ ትገባለህ። አሁን ፋራው በዝቷል፡፡ ከፋራም ደግሞ የዚህ ፋራ (ጭንቅላቱን እየጠቆመ) የት ያላውስሃል ባለፈው አንዱ ነግሬሃለሁ አይደል? መንገድ ጠፍቶብኝ ቫቲካን አካባቢ ስጠይቀው፣ “አይ ካንት ስፒክ አምሃሪክ፤” አለኝ። ከዚያ ሰውዬውን የት ባየው ጥሩ ነው? እናቴ የገና ዕለት ጠዋት አብረን ቤተ ክርስቲያን ደርሰን ካልመጣን ብላኝ ስንሄድ፣ በዚያ ማለዳ ተንበርክኮ መሬት እየሳመ ሲፀልይ አየሁት። አልረሳሁትም። እና ይኼን ምን ትለዋለህ? በሰላሳ ሰባት ዓመቴ ሰማንያ ዓመት የሞላኝ ያህል የሚመሰማኝ የእርጅና ስሜት በጣም እየደበረኝ ነው፤” ሲለው ተሳፋሪው እየተያየ አጉረመረመ።

ጥጋቸውን ይዘው የተቀመጡ አዛውንት ይኼንን ሲታዘቡ ከቀዩ በኋላ፣ “እነዚህ ልጆች ነፍስ አውቀው ሳያድጉ ገና አረጀን እስኪሉ ድረስ ይኼን ያህል ሰው አገሩ ላይ የቁጭት ታሪክ ይጽፋል? በታሪክ ስንቆጭ መስከረም ጠብቶ መሸ። በቋንቋ ስንቆጭ ደመራ ተለኩሶ አመድ ሆነ። በነፃነት፣ በፍትሕና በዴሞክራሲ ስንቆጭ ብዙ ልደት አከበርን። በአንዱም ዳግም ሳንወለድ፡፡ ተቀጭተን ሳናድግ አረጀን። እኔ ምለው ግን እስከ መቼ ድረስ ነው የቁጭት ታሪክ ስንጽፍ የምንኖረው? ከቁጭት በፊት የምንኖረው መቼ ነው?” ሲሉን ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ከፍቶታል። የተቀመጠው ሳይነሳ የቆመው እንዴት መቀመጫ ያገኛል የሚለው አባባል የገባን ይኼኔ ነው፡፡ መልካም ጉዞ!

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት