በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚኘው የጎንደር ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለኩላሊት ሕክምና የሚያስፈልጉ የዘመናዊ መሣሪያዎች ባለቤት መሆን ቢችልም፣ መሣሪያዎችን በሥራ ላይ ለማዋል የኃይል እጥረት እንዳጋጠመው አስታወቀ፡፡
መሣሪያዎቹንም መጠቀም ባለመቻሉ የኩላሊት ሕመምተኞች ለሕክምና ባህር ዳርና አዲስ አበባ ድረስ ለመሄድ እየተገደዱ መሆኑን፣ የሆስፒታሉ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሆስፒታሉ የሲቲ ስካንና በርከት ያለ የኤምአርአይ መሣሪያዎች ቢኖሩትም፣ ከፍተኛ ኃይል ማስተላለፍ የሚችል ትራንስፎርመር ካልተገኘ ማሽኖቹን መጠቀም አይቻልም፡፡
ነገር ግን አነስተኛ ኃይል የሚፈልጉ የሦስት ኤምአርአይ መሣሪያዎች ተከላ የተጠናቀቀ በመሆኑ፣ በእነሱ አገልግሎቱ በቅርቡ ይጀመራል ብለዋል፡፡
መሣሪያዎችን ሙሉ ለሙሉ መጠቀም አንዲቻል ለመንግሥት የኃይል አቅርቦት ጥያቄ መቅረቡን፣ ሌሎች አማራጮችን ለማየትም እየተጠና መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ሆስፒታሉ መሣሪያዎችን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አማካይነት ያገኛቸው በመሆኑ በጎንደርና አካባቢው ለሚገኝ ሕዝብ የኩላሊት ንቅለ ተከላ፣ የዲያሌሲስና ተያያዥ ሕክምናዎች ለማድረግ ታስቦ እንደነበርም ዶ/ር ደሳለኝ አስረድተዋል፡፡
የሆስፒታሉ ኃላፊዎች የሚያስፈልገውን ኃይል መንግሥት እንዲያቀርብላቸው፣ ሕሙማኑም ወደ ሌሎች ቦታዎች በመጓዝ የሚደርስባቸውን እንግልት ለመቀነስ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሆስፒታሉ በጎንደርና በአካባቢው የጤና አገልግሎቶችን ማስፋፋት የሚያስችለውን ስምምነት ባለፈው ሳምንት ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ኮሌጅ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ፈርሟል፡፡ በሁለቱ ሆስፒታሎች የመግባቢያ ስምምነት መሠረት በጋራ የኩላሊት የዲያሌሲስ ሕክምና፣ የንቅለ ተከላና የባዮ ሜዲካል ምሕንድስና በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡
እንዲሁም በተመሳሳይ ሁኔታ ከአሜሪካ የሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ጋር በሥነ ተዋልዶ ላይ በጋራ ለመሥራትና ዩኒቨርሲቲው ሊጠቀምበት የሚችል የልህቀት ማዕከል ለመገንባትም ስምምነት መደረጉ ታውቋል፡፡