Friday, April 19, 2024

የኢትዮጵያና የግብፅ አዲሱ አሠላለፍ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ የህዳሴ ግድቡን አሞላልና አለቃቀቅ፣ እንዲሁም አካባቢያዊ ተፅዕኖ በተመለከተ የሦስትዮሽ ውይይት ማድረግ ከጀመሩ ከሁለት ዓመት በላይ ተቆጥሯል፡፡

ሦስቱ አገሮች የጋራ የአጥኚዎች ቡድን በማቋቋም የሦስትዮሽ ውይይት ሲያደርጉ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የህዳሴ ግድቡ የሚኖረውን ተፅዕኖ እንዲያጠና የቀጠሩት የፈረንሣዩ ‹‹ቢአርኤል›› የተሰኘው ተቋም የሚሠራበትን የመነሻ ሐሳብ ለማርቀቅ ብዙ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ቢሆንም ግን በውይይት መነሻ ሐሳቡ ላይ ግብፅና ኢትዮጵያ ስምምነት ላይ አለመድረሳቸው ይታወቃል፡፡

የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በቅርቡ፣ ‹‹የናይል ወንዝ ለግብፃውያን የሞትና የሽረት ጉዳይ ነው፤›› ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሰኞ ታኅሳስ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በግብፅ ካይሮ በተካሄደው አንድ ስብሰባ ላይ ደግሞ፣ ‹‹ግብፅ ውስጥ የውኃ ችግር እንዲፈጠር አልፈቅድም፤›› በማለት መናገራቸው እየተዘገበ ነው፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ ኢትዮጵያ መጥተው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት፣ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ በተመለከተ እየተደረገ ያለው ውይይት ከሱዳን ውጪ እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ውይይትና ድርድር የማደርገው ሱዳን ባለችበት በሦስትዮሽ መድረክ ላይ ብቻ ነው ብላለች፡፡

ሱዳን የግብፅ አምባሳደሯን ወደ አገሯ ጠርታ እንደነበር አህራም ኦንላይን የተሰኘው የግብፅ ሚዲያ ባለፈው ሳምንት ያስነበበ ሲሆን፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ መምጣቱን ሰሞኑን እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1958 ጀምሮ ሁለቱ አገሮች በመካከላቸው በሚገኘውና ‹‹ሃላያብ ትሪያንግል›› እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ሲወዛገቡ እንደቆዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 አወዛጋቢውን አካባቢ በተመለከተ ሱዳን በሁለትዮሽ ድርድር እንዲፈታ ወይም አደራዳሪ አካል ገብቶ እንዲያሸማግላቸው ብትጠይቅም ግብፅ ሳትቀበል ቀርታለች፡፡

 በሌላ በኩል ግብፅ ዳርፉር ውስጥ ላሉ አሸባሪ ኃይሎች ድጋፍ ታደርጋለች በሚል ከሱዳን ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብታ ቆይታለች፡፡

በሌላ በኩል ሱዳን ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ ድጋፏን በመስጠቷ ሳቢያ፣ ግብፅ ደስተኛ አለመሆኗን የፖለቲካ ተንታኞች ሲያወሱ ተደምጧል፡፡

‹‹ሃይላብ ትሪያንግል›› የተሰኘው ግዛት በግብፅና በሱዳን መካከል የይገባኛል ጥያቄ ቀርቦ ውዝግብ ውስጥ በመቆየታቸው ሳቢያ፣ ችግሩን ለመፍታት ሱዳን ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መውሰዷን የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ሱዳን በምሥራቅ በኩል ከኤርትራ ጋር የሚያገናኛትን ድንበር መዝጋቷን ሱና ኒውስ የተሰኘ የሱዳን ሚዲያ ዘግቧል፡፡ ሱዳን እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው ‹‹ካሳላ›› እየተባለ በሚጠራው ግዛት በተደጋጋሚ ጊዜ እየደረሰ ያለውን የአሸባሪዎች ጥቃት ለማስቆም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባወጀችበት ጊዜ መሆኑን የዜና አውታሩ አክሎ አብራርቷል፡፡ ሱዳን ካሳላ እየተባለ በሚጠራው ግዛቷ የስድስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማወጇ የተነገረ ሲሆን፣ ምንጮችን ጠቅሶ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው፣ በዚህ ግዛት አሸባሪ ቡድኖች ወደ ኤርትራ በመግባት፣ ወታደራዊ ሥልጠና ከተሰጣቸውና ከታጠቁ በኋላ ወደ አካባቢው በመግባት ጉዳት ያደርሳሉ፡፡

በሌላ በኩል የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ማክሰኞ ጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ግብፅ ካይሮ አቅንተው፣ ከግብፅ አቻቸው አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር እንደመከሩ ኢጅብት ቱዴይ የተሰኘው የመረጃ መረብ ዘግቧል፡፡ የግብፅና የኤርትራ ግንኙነት በተለይም ባለፉት 15 ዓመታት እየጠነከረ እንደመጣ፣ ግብፅ በቀጣናው በተለይም በቀይ ባህር ኃያል ሆና ለመታየት ሙከራ ስታደርግ መቆየቷን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ግብፅና ሱዳን በድንበርና በህዳሴ ግድቡ ምክንያት ያላቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየተቀዛቀዘ ከመምጣቱ ጋር ተያዞ፣ ግብፅ ከኤርትራ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደ አዲስ መጀመሯ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ሱዳን ደግሞ ከኤርትራ ጋር የሚያገናኛትን ድንበር መዝጋት፣ እንዲሁም ግብፅና ሱዳን በድንበር ይገባኛል ውዝግብ ውስጥ መግባት አገሮች የየራሳቸው የአሠላለፍ ጎራ እንዲኖራቸው እያደረገ መምጣቱን ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያና ሱዳን ያላቸውን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግንኙነት እያጎለበቱ መምጣታቸውን በሁለቱ መንግሥታት በኩል ሲገለጽ ተሰምቷል፡፡ ለአብነት ያህልም ሰሞኑን የሱዳን መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ወደ ኢትዮጵያ መምጣትና ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ተገኝተው መነጋገራቸው ይጠቀሳል፡፡ በግንኙነታቸው ወቅትም የመከላከያ ኤታ ማዦር ሹሙ ሌተና ጄኔራል ኢመድ አልዲን አዳዊን ከፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የተላከ መልዕክት ማድረሳቸው ተዘግቧል፡፡ ጄኔራሉ ኢትዮጵያ የሱዳን ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ከመጥቀሳቸው ባሻገር፣ በቀጣይ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል፡፡

የግብፅና የኤርትራ ግንኙነት በአንድ በኩል፣ የሱዳንና የኢትዮዮጵያ ግንኙነት በሌላ በኩል አዲስ ገጽታ እየያዘ መምጣት በቀጣናው ያሉ አገሮች የራሳቸውን አሠላለፍ እየያዘ መሆኑን እንደ ማሳያ ተደርጎ ሲጠቀስ እየተሰማ ነው፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁት አቶ ዳደ ደስታ፣ ይህ ያለየለት የጂኦ ፖለቲካ አሠላለፍና ያልተረጋጋ ሁኔታ እንዳለ የሚያሳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና የግብፅ፣ እንዲሁም የቱርክና ሌሎች ኃይሎች በቀይ ባህር አካባቢ የራሳቸው ተፅዕኖ እንዲኖራቸው በመሻት አዳዲስ የአሠላለፍ መስመሮች ውስጥ ከመግባት ባሻገር፣ የህዳሴ ግድቡ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለ ወዲህ የግብፅ ታሪካዊ መብቴ የምትለው የውኃ መጠን እንዳይነካባት የምታደርገው የማስፈራራትና የማንገራገር ጉዳይ ለዚህ አሠላለፍ አንዱ ማሳያ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ፣ የፖለቲካ ተንታኝና መምህሩ ንጋት አስፋው (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በዚህ ሐሳብ የጂኦ ፖለቲካ ተንታኙ አቶ ልዑልሰገድ ግርማ ይስማማሉ፡፡ ከግብፅ በቀጥታ እየታየ ያለው የማስፈራራትና የዲፕሎማሲ ሁኔታ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የግብፅ ጎራ ለይቶ አዲስ አሠላለፍ ማሳየት ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ እንድታቆም የምታደርገው ጥረት እንደሆነ አቶ ልዑልሰገድ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ልንመታችሁ ስለምንችል የምንላችሁን ስሙን ዓይነት የማስፈራራት ነገር ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ግን ሊሳካ እንደማይችልም አክለው ገልጸዋል፡፡ በግብፅ ምክንያት ቀጣናው በተለያዩ አሠላለፎች እንዲከፋፈል መደረጉን የጠቀሱት አቶ ዳደ፣ ለአሠላለፉ መፈጠር አንዱ ምክንያት ደግሞ የህዳሴ ግድቡ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ዶ/ር ንጋት በበኩላቸው፣ ‹‹ለዚህ ዓይነት አሠላለፍ መፈጠር ምክንያቱ ከዓባይ ወንዝ ጋር የተያያዘ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የግብፅ አቋም ኢትዮጵያ ማንኛውንም ዕርምጃ ከወሰደች ኃይል ከመጠቀም ሌላ አማራጭ አይኖረንም፤›› የሚል እንደሆነ ዶ/ር ንጋት ጠቁመዋል፡፡

ከኳታር ቀውስ ጋር ተያይዞ የዓረብ አገሮች የተለያየ አሠላለፍ መያዝ፣ ቱርክ ዓይኗን ሱዳን ላይ መጣልና በቀጣናው ድርሻ እንደኖራት መሻት፣ የግብፅ የስዊዝ ካናል ባለቤትነትና ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥታት ጋር በቀይ ባህር አካባቢ የጦር ሠፈር መመሥረት፣ እንዲሁም ግብፅና ኤርትራ በአንድ የአሠላለፍ መስመር ላይ መገኘት ለኢትዮጵያ ሥጋት ሊሆን እንደሚችል አቶ ልዑልሰገድ አስረድተዋል፡፡ አቶ ዳደ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ‹‹በአሠላለፉ ኢትዮጵያ ተጠቂ መሆኗ አይቀርም፤›› ይላሉ፡፡

የኤርትራ መንግሥት አካባቢው እንዲተራመስ ፍላጎት እንዳለውና ከዚህ በፊትም ልምድ እንደነበረው የጠቀሱት አቶ ዳደ፣ የኢትጵያና የኤርትራ መንግሥታት የቆየ የሻከረ ግንኙነት ለግብፅ የተመቸ ሆኖ እንደተገኘ ተናግረዋል፡፡ አሠላለፉ ግን በቀጣናው ያለውን የጂኦ ፖለቲካ አሠላለፍ በችግር የተተበተበ እንዲሆንና አገሮች በዓይነ ቁራኛ እንዲተያዩ እያደረገ መምጣቱን ተንታኞቹ ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን ካልፈታች ሥጋት ሊፈጥርባት እንደሚችል የጠቆሙት ደግሞ አቶ ልዑልሰገድ ናቸው፡፡ ‹‹የግብፅ እዚህም፣ እዚያም ማለት የኢትዮጵያን የተቃዋሚ ኃይሎች በማስታጠቅና በመደገፍ ማተራመስ ትችላለች እንጂ፣ በቀጥታ ልትወጋ አትችልም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ያም ሆነ ይህ እንቅስቃሴው ኢትዮጵያን ይጎዳታል፤›› ብለዋል፡፡

በቀጣናው ያለው አሠላለፍ በሁለት መልክ ሊታይ እንደሚችል አቶ ዳደ ይናገራሉ፡፡ የመጀመርያው አትዮጵያ ከግብፅ ጋር ያላት ግንኙነት ወዴት እየሄደ ነው? የሚለውን የሚያሳይ እንደሆነ፣ ሁለተኛ ደግሞ በቀጣናው ያለው የጂኦ ፖለቲካ ጉዳይ በተለይም የመክበብ፣ የመከበብ፣ የትርምስና ሌሎች የፖለቲካ ጨዋታዎች እየተጋጋሉ መምጣታቸውን እንደሚጠቁም ተናግረዋል፡፡

ግብፅና ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡም ሆነ በሌሎች መስኮች ውይይት ሲያደርጉና ወደ ፊትም በትብብር ለመሥራት በተለያዩ ጊዜያት ሲነጋገሩ ቢሰማም፣ መሬት እንዳልነካ የሚያሳይ እንደሆነ አቶ ዳደ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን የማስጨነቅና የማዋከብ ድርጊት እየታየ የመጣ ነው የሚመስለው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያና የግብፅን ግንኙነት ከአዎንታዊ መስመር ሊያስወጡ የሚችሉ ነገሮች እየታዩ መምጣታቸውን አቶ ዳደ ጠቁመዋል፡፡

የቀጣናው አሠላለፍ በግድ የመጣ እንደሚመስል፣ ግብፅ ኤርትራን ይዛ በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር መንቀሳቀስ፣ ሱዳን ከግብፅ ይልቅ ኢትዮጵያን ምርጫዋ በማድረግ በሌላ መስመር መሠለፍ በግድ እንዳመጣ እንደሚመስልና አገሮች አሁን ካለው የጂኦ ፖለቲካ ትኩሳት አኳያ ወደ አሠላለፉ ሳይወዱ በግድ እንዲገቡ መገደዳቸውን ተንታኞቹ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአሠላለፉ አሸናፊ ሆና እንድትወጣ ማድረግ ያለባትን ጉዳዮች እንዳሉ የፖለቲካ ተንታኞች ተናግረዋል፡፡ አቶ ልዑልሰገድ እንደተናገሩት፣ ‹‹በእነሱና በእኛ ሜዳ ስትጫወት ሕጉ የተለያየ ነው፡፡ የጨዋታው አሸናፊ ለመሆን የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች መቆም የለባቸውም፤›› ብለዋል፡፡ ሁለተኛ በአገር ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ትኩሳት በተገቢው መንገድ በመፍታት፣ ውስጣዊ ሰላምን በማረጋገጥ ለውጭ ኃይል የማይበገር አገር መገንባት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ እንዲሁም ከጂቡቲና ከሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

አቶ ዳደ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ በአገር ውስጥ ያለውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ መፍታት ካልተቻለ ለውጭ ኃይል በቀላሉ እንደሚያጋልጥ ጠቀመው፣ የውስጥ ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

ዶ/ር ንጋት አሁን ባለው አሠላለፍ አሸናፊ ሆኖ ለመገኘት ኢሕአዴግ የጀመራቸውን አዳዲስ ጉዳዮች ከግብ ማድረስ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ እንዳለው የታሰሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በመፍታትና ሌሎች የሕዝብ ጥያቄዎችን በተገቢው ሁኔታ በመመለስ አገራዊ መግባባት ከተፈጠረ፣ የሁሉም ነገር አሸናፊ መሆን ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

የጦር ቀጣና ለመመሥረት በቀይ ባህር አካባቢ ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየትና የግብፅ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ እንዲቆም መሻት፣ በቀጣናው ያለውን የጂኦ ፖለቲካ አሠላለፍ እየለወጠው እንደመጣ ተንታኞቹ አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችውን አሠላለፍ በመርህ ላይ የተመሠረተ ማድረግና ለውስጥ ችግሯ ቅድሚያ መስጠት ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ውጭ አገር በመሄዳቸው ምክንያት ሌሎች ኃላፊዎች በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተደረገው ሙከራ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አልተሳካም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -