ናኖ ቴክኖሎጂን የሚያጠኑ ተመራማሪዎች፣ ቴክኖሎጂው ድህነትን ከመቅረፍ ባሻገር፣ ሞትን እስከማስቀረት የሚደርሱ ጠቀሜታዎች እንደሚያስገኝ ይገልጻሉ፡፡ ቴክኖሎጂው ተቀባይነት ሲያገኝና በስፋት ተግባር ላይ ሲውል፣ የሰዎችን ሕይወትና አኗኗር ሙሉ ለሙሉ የመለወጥ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
ናኖ ቴክኖሎጂ (ናኖ) በአንፃራዊነት ዕይታ ሲቃኝ አዲስ የምርምር ዘርፍ እንደሆነ ይገለጻል፡፡ በመሆኑም የዘርፉ ተመራማሪዎችም ሆኑ ሌሎች ባለሙያዎችን የሚያስማማ ትርጓሜ ሊገኝለት አልቻለም፡፡ የዘርፉ ተመራማሪዎች ናኖ ቴክኖሎጂ በአጠቃላይ ከአንድ እስከ መቶ ናኖ ሜትር መጠን ባለው ደረጃ የሚደረጉ ምርምሮችን ለመግለጽ የሚውል መጠሪያ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ከመጠናቸው ይልቅ በተጠቀሱት አኃዞች ደረጃ የሚገኙ ቁሶች የሚያሳዩዋቸው ባህርያት እጅግ ጠቃሚ ናቸው የሚሉም አሉ፡፡
ስለጉዳዩ መጽሐፍ የጻፉትና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂው የሕግ ተመራማሪ ኃይለ ሚካኤል ተሾመ (ዶ/ር)፣ ቁሶች በዚህ መጠን የሚያሳዩዋቸው ባህርያት አስደናቂ እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ በተፈጥሮው ቢጫ ቀለም ያለው ወርቅ በናኖ መጠን የአተሞቹን (‹‹አተም›› ወይም ‹‹አቶም›› ሁሉም ቁስ የተገነባበት መሠረታዊ እኑስ ነው። እንደ ግዝፈታቸው፣ መጠናቸው የተያየ ስም ያላቸው ልዩ ልዩ ዓይነት አተሞች አሉ። እነዚህ የተለያዩ ዓይነት አተሞች የኬሚካል ንጥር ይባላሉ)፣ ቦታ በመለዋወጥ የተለያዩ ቀለማትንና የጥንካሬ ደረጃን እንዲያመጣ ማድረግ ይቻላል ይላሉ፡፡
‹‹ቫዝሊን ለስላሳና ስንነካውም ምንም የመቆርቆር ስሜት አያሳይም፡፡ ነገር ግን በናኖ መጠን ላይ ምርምር ሲደረግ፣ መንኮራኩርን ወደ ጠፈር ተሸክሞ ሊያወጣ የሚችል አሳንሰር ለመሥራት የሚያስችል ጥንካሬን ያሳያል፡፡ ይህም በውስጡ ያሉትን አተሞችና ሞለኪዩሎች ቦታ በመቀያየር የሚሠራ ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡
ይህ የቴክኖሎጂው አቅም፣ የወቅቱ የዓለም ሥጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቀልበስ የሚያስችል አቅም እንዳለው ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ለዚህም ነው ‹‹አተሞችንና ሞለኪዩሎችን ቦታ በመቀያየር የሚገኝ ከፍተኛ አቅምን ለሰው ልጆች ያጎናጸፈ ቴክኖሎጂ፤›› የሚባልለት፡፡
ቴክኖሎጂው ምንም እንኳ አዲስ ቢሆንም፣ በተመራማሪዎችና በአካባቢ ተቆርቋሪዎች መካከል ከፍተኛ ክርክር ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ ስለቴክኖሎጂው ጠቀሜታ የሚያቀነቅኑ አካላት፣ በናኖ ቴክኖሎጂ ምክንያት ለሰው ልጆች የሚያገኛቸው ጥቅሞች በርካታ በመሆናቸው፣ በምድር የሚገኙ ሕይወት ያላቸውም የሌላቸውም ነገሮች ላይ የሚከሰቱ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን እጅጉን ሊያሻሽል እንደሚችል ይናገሩለታል፡፡ በአንፃሩ በቴክኖሎጂው አማካይነት ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶች አካባቢን በመበከል ረገድ ተፅዕኖ ያሳድራሉ የሚሉ ድምፆች በሌላ ወገን ይስተጋባሉ፡፡
በተጨማሪም ቴክኖሎጂው እንደ ሕክምና ያሉ ዘርፎችን በእጅጉ ሊያሻሽል የሚችል እንደሚሆንና ያለ ቀዶ ጥገና የውስጥ በሽታን ለማከም የሚያገለግሉ ናኖ ቦት በመጠቀም የተዋጣለት ሕክምና ለመስጠት ያገለግላል ይላሉ፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ እነዚህ ናኖ ቦትስ የማይታዩ ሊሆኑ ስለሚችሉ ከቤተ ሙከራ ቢያመልጡና በትንፋሽ መልኩ የሰው አካል ውስጥ ቢገቡ ከፍተኛ ጉዳትን ያስከትላሉ የሚሉ ተከራካሪዎችም አሉ፡፡
‹‹ሥጋት አልባ አኗኗር ግን ሊኖር አይችልም፣ መታሰብም የለበትም፤›› በማለት መከራከሪያ የሚያቀርቡት ኃይለ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ በናኖ ቴክኖሎጂ ላይ የሚደረገው ምርምርና የሚደግነው ሥጋት መንገድ ላይ መኪና በመንዳት ከሚመጣው ሥጋት አይበልጥም ሲሉ ያነፃፅሩታል፡፡
በተፈጥሮው ትልልቅ ቁሳቁሶችን ማጓጓዝ ስለማይጠይቅና በትንንሽ የቁስ አካላት ላይ የሚደረግ ምርምር ስለሆነ፣ አካባቢ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ብክለት እምብዛም አሳሳቢ እንዳልሆነ ኃይለ ሚካኤል (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡ ይልቁንም ከጉዳቱ በላይ ጥቅሙ እንደሚያመዝን ይሞግታሉ፡፡ ይህንን ሲያስረዱ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የተጋረጠባቸው የመፍረስ ሥጋትን ለመቀልበስ ቴክኖሎጂው ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚችል በማብራራት ይጀምራሉ፡፡ የአብያተ ክርስቲያናቱ ገጽታ ሳይቀየር፣ በዓይን የማይታዩ የናኖ ቀለሞችን በመቀባት የመፍረስ አደጋ የተጋረጠባቸውን ብርቅዬ ቅርሶችን ቢያንስ እስከ ሁለት ክፍለ ዘመናት ማቆየት እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡
ከመላምት በሚመነጩ ሥጋቶች ሳቢያ ቴክኖሎጂው የሚሰጣቸው ጥቅሞች በባዮ ቴክኖሎጂ ላይ እንደታየው ሁሉ እምብዛም አገልግሎት ሳይሰጥ እንዳይቀር ኃይለ ሚካኤል (ዶ/ር) ያሳስባሉ፡፡ የባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፉ፣ በተለይም የዘረ መል ምሕንድስና፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፉ የመጡት የጂኖም ኤዲቲንግ ወይም የዘረ መል ማደት ተግባራት በባዮ ቴክኖሎጂ መስክ የሚጠቀሱና ሰፊ ተቀባይነት እያገኙ የመጡ ቴክሎጂዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ቴክሎጂዎች ሊያስገኟቸው የሚችሏቸው ሰፊ ጠቀሜታዎች በተለያዩ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖዎች እንደሚፈለገው ጥቅም ላይ ሳይውሉ መቅረታቸውን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ ቴክኖሎጂው ሥነ ምኅዳርን ከመጠበቅ አኳያ ያለው ሰፊ ጠቀሜታ ከሳይንስ ይልቅ በሚራብበት ቅስቀሳ ሳቢያ ሰዎች ሥጋት ላይ በመውደቃቸው ቴክኖሎጂውን ለመሸሽ እንደሚገደዱ ኃይለ ሚካኤል (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡ ነገር ግን ጠቀሜታውን በመረዳታቸው በተለይ የጥቅሙ ተካፋይ ሳይሆኑ የቀሩ የአፍሪካ አገሮች በዘረ መል ምሕንድስና መስክ የተገኙ የሰብል ዝርያዎችን ወደ እርሻ ማሳያዎቻቸው ሲያስገቡ እየታየ ነው፡፡
ይሁንና የቱንም ያህል ጥቅም የሚያስገኝ የምርምር ውጤት ነው ቢባልለትም፣ በናኖ ቴክኖሎጂ ላይ የምርምር ተቋማትን ማደራጀት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ይጠይቃል፡፡ ተቋም ከማደራጀት ባለፈም ምርምሩ የሚጠይቀው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 በመላው ዓለም በዘርፉ ለሚደረግ ምርምር 400 ቢሊዮን ዶላር እንደወጣ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ መንግሥት ለናኖ ቴክኖሎጂ ምርምር የሚያውለው በጀት ከ12 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነም ይታወቃል፡፡
ይህን ያህል ከፍተኛ በጀት በሚጠይቅ የምርምር ዘርፍ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገሮች አቅማቸው ስለማይፈቅድ፣ የተሻለው አማራጭ አካባቢያዊ ትብብር በመፍጠርና የቤተ ሙከራዎችን ግንኙነት በማዳበር፣ በጎ ፈቃደኛ ተመራማሪዎችን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በማምጣት መሥራቱ ተመራጭ መፍትሔ እንደሆነ ኃይለ ሚካኤል (ዶ/ር) ያሳስባሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘውና ‹‹ኢቴምባ›› የተሰኘው ቤተ ሙከራ፣ የአፍሪካ ተመራማሪዎች እንዲጠቀሙበት የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ክፍት እንዳደረገውና ይህንን አካሄድ ሌሎቹም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች እንዲጠቀሙበት ባለሙያው ይመክራሉ፡፡
ይህንን ያህል መዋዕለ ንዋይ የሚፈስበት ዘርፍ አስፈላጊውን ጥቅም ለኅብረተሰቡ ይሰጥ ዘንድ ቁጥጥር እንደሚያስፈልገው ግን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ አስፈላጊውን ቁጥጥር ለማድረግ ደግሞ ዘርፉን በሚመለከት ያለው የሕግ አቅምና ዕውቀት ውስን ስለሆነ የሥነ ምግባር ጉዳዮች ላይ በትኩረት መሥራት በአብላጫው እንደሚጠቅም በዘርፉ የሕግ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ፡፡
ሕጉ በዋናነት ከዘርፉ የሚመነጩ ጥቅሞች ላይ ማተኮር እንዳለበትና ተፅዕኖዎችን በሚመለከት ግን ለሥነ ምግባር ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱ የተሻለ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ ኃይለ ሚካኤል (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡ በእያንዳንዱ የናኖ ቴክኖሎጂ ምርምር ላይ የሚያደርግ የቤተ ሙከራ ሥራ ውስጥ የሥነ ምግባር ባለሙያዎችና የሕግ ባለሙያዎች ከሳይንቲስቶች ጋር በመሆን አብረው እንዲሠሩ እየተደረገ መመራት እንደሚኖርበት ይመከራል፡፡
ይህ ሲደረግ በውስን ሀብት ላይ የሚደረጉ ሽሚያዎችን ለማስቀረት እንደሚያግዝ ይታመናል፡፡ ግብፅ በዓባይ ውኃ ላይ ጥገኛ ከመሆን በመላቀቅ፣ ጨዋማውን የባህር ውኃ አጣርታ መጠቀም የሚያስችላትን አቅም ማግኘት ከምትችልባቸው አማራጮች ውስጥ የናኖ ቴክኖሎጂ በግንባር ቀደምትነት እንደሚጠቀስ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡