Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቃሊቲ ብረታ ብረትን የገዛው ኩባንያ የተከፈለ ካፒታሉን ከ470 ሚሊዮን ብር በላይ አደረሰ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር (ከቀድሞው የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ) በ555 ሚሊዮን ብር ቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ፣ ፀሐይ ኢንዱስትሪያል አክሲዮን ማኅበር ለተሰኘው ኩባንያ በሽያጭ ከተዛወረ ከአምስት ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡

ወደ ግል ከተዛወሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለየት ባለ አኳኋን ፀሐይ ኢንዱስትሪያል ሠራተኞቹም ባለአክሲዮን እንደሆኑ በማድረግ የጀመረው አካሄድ ዕድገት እያሳየ እንደሆነም ሰኞ፣ ታኅሳስ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደው የኩባንያው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውና የሠራተኞች በዓል ላይ ተገልጿል፡፡ የፋብሪካውን ምርታማነት ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ የገለጹት የፋብሪካው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ማቴዎስ አሰሌ፣ በአክሲዮን ማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ባለአክሲዮኖቹ የድርጅቱን የተከፈለ ካፒታል በእጥፍ ለማሳደግ መወሰናቸው አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በባለአክሲዮኖቹ ውሳኔ መሠረት 439 ሚሊዮን ብር የነበረው የድርጅቱ የተከፈለ ካፒታል ከ478 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሆን ተስማምተዋል፡፡ በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥም ከ1.3 ቢሊዮን ብር ላይ ኢንቨስት በማድረግ፣ የፋብሪካውን እንቅስቃሴ የማስፋፋት ዕቅድ መቀመጡ ተብራርቷል፡፡

ፀሐይ ኢንዱስትሪያል፣ ቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካን በ2004 ዓ.ም. መጨረሻ ሲረከብ፣ በወቅቱ የነበረው የፋብሪካው የምርት መጠን 11,841 ቶን ነበር፡፡ በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ ግን ከ23,939 ቶን በላይ በመድረሱ ድርጅቱ በአምስት ዓመታት ውስጥ ከእጥፍ በላይ ማደጉን እንደሚያመላክት ተጠቅሷል፡፡ በ2004 ዓ.ም. 276.7 ሚሊዮን ብር የነበረው ዓመታዊ የሽያጭ መጠን፣ በ2009 ዓ.ም. በ130 በመቶ ጨምሮ 637.6 ሚሊዮን ብር መድረሱን የአክሲዮን ማኅበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ፈንቴ ገልጸዋል፡፡ የድርጅቱ የሀብት መጠንም በየዓመቱ እያደገ በመምጣቱ፣ በ2009 መጨረሻ 941.1 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉ ጠቅሰዋል፡፡ ፀሐይ ኢንዱስትሪያል ቃሊቲ ብረታ ብረትን ሲረከብ የነበረው የሀብት መጠን 303.5 ሚሊዮን ብር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የሀብት መጠን ዕድገቱ በ208 በመቶ እንደጨመረ ስለኩባንያው የቀረበው ዓመታዊ ሪፖርት አመላክቷል፡፡

በትርፍ ረገድም ዕድገት ሲመዘገብ መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን፣ የተጣራ ትርፉ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ እንደተመዘገበበት ተጠቅሷል፡፡ ‹‹ይህ የሥራ አመራር ቦርድ እዚህ የደረሰው ብዙ መሰናክሎችንና ውጣ ውረዶችን አልፎ ነው፤›› ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ በ2004 ዓ.ም. መጨረሻ የነበረውና በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ የተመዘገበው አፈጻጸም ሲነፃፀር በምርት የ102 በመቶ፣ በሽያጭ ገቢ የ130 በመቶ፣ በሀብት መጠን የ208 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ድርጅቱን ሊያሳድጉ በሚችሉ ሥራዎች ላይ 122 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡

አቶ ማቴዎስ በበኩላቸው፣ በ2009 ዓ.ም. የተሻለ ውጤት መመዝገቡን  በማብራራት፣ የተመዘገበው ክንውን ከ2008 ዓ.ም. አኳያ ሲታይ በምርት የ0.6 በመቶ፣ በሽያጭ የ11.3 በመቶና በትርፍ የ78.9 በመቶ ዕድገት እንደታየበት ተናግረዋል፡፡ የገበያውን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የተሳቢና የጭነት መኪኖችን አካላት  በስፋት በማምረት ወደ ገበያ የገባበት ዓመት እንደሆነ ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ፋብሪካውን ለማስፋፋት ከተያዘው ዕቅድ በመነሳት ትልቅ አቅም ያለው የቱቦ ማምረቻ መሣሪያ፣ ለቱቦ ማምረቻ ጥሬ ዕቃ የሚያዘጋጅ መሰንጠቂያ ማሽን፣ ባለጌጥና ባለቀለም ማምረቻ መሣሪያ፣ ትልቅ አቅም ያለው የብረት ማጠፊያ ማሽን፣ የተሳቢና የጭነት አካላትን በስፋት ለማምረት እንዲቻል የሁለት ትላልቅ ወርክሾፖች ሕንፃ ግንባታ ሥራዎች መካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ግንባታዎችንና ተያያዥ ሥራዎችን ለማከናወን ከ88 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንደወጣ ያስታወቁት አቶ ማቴዎስ፣ በ2009 ዓ.ም. የተሻለ ውጤት ቢገኝም፣ የውጭ ምንዛሪ በበቂ መጠን ባለመገኘቱ ችግር እንዳጋጠመ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ‹‹በተቻለ መጠን በነበረን ውስን ጥሬ ዕቃ በገበያው ተፈላጊ ምርቶችን በማምረትና በመሸጥ አፈጻጸማችን እንዳይጎዳ ለማድረግ ሞክረናል፤›› ብለዋል፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ወደፊትም ማነቆ ሆኖ ካልቀጠለ በቀር፣ የፋብሪካውን ምርታማነት በከፍተኛ መጠን ማሳደግ እንደሚቻል፣ በተለይም እየተተከሉ የሚገኙት ማምረቻ መሣሪያዎች ምርት ሲጀምሩ፣ የተወዳዳሪነትና የትርፋማነት አቅሙን ይበልጡን እንደሚጨምሩት ሥራ አስፈጻሚው አብራርተዋል፡፡

ፋብሪካው ወደ ግል ከዞረበት ጊዜ ጀምሮ ሁለት ጊዜ የደመወዝ ስኬል ማሻሻያ ጥናት ከማካሄዱን ባሻገር፣ በየዓመቱም ለሠራተኞችና ለሥራ መሪዎች የደመወዝ ጭማሪና ጉርሻ (ቦነስ) ሲሰጥ እንደቆየ የአክሲዮን ማኅበሩ ሪፖርት አመልክቷል፡፡ አቶ ማቴዎስ እንደገለጹትም፣ በ2009 ዓ.ም. ከተመዘገበው ውጤታማ አፈጻጸም የተነሳ፣ በድርጅቱና በሠራተኛው የኅብረት ስምምነትና የሥራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የሁለት እርከን ደመወዝ ጭማሪና የሁለት ወር ተኩል የደመወዝ ቦነስ ለሠራተኞችና ለሥራ መሪዎች ሰጥቷል፡፡

የሠራተኛ ማኅበሩ መሪ አቶ እድሪስ አወል በበኩላቸው፣ እንዲህ ያለው ማበረታቻ ሠራተኞች የበለጠ እንዲተጉ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

ፀሐይ ኢንዱስትሪያል አክሲዮን ማኅበር በጠቅላላ ጉባዔው ወቅት የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ ያካሄደ ሲሆን፣ ከጠቅላላ ጉባዔው አባላት ውስጥ ሁለት አዳዲስ የቦርድ አባላትን በማከል በሥራ ላይ የሚገኙት የቦርድ አባላትን በድጋሚ መርጧል፡፡ በቦርዱ ውስጥ ከተካተቱት ሁለቱ አባላት መካከል ፎርብስ መጽሔት ቢሊየነር ኢትዮጵያውያን በማለት ከጠቀሳቸው አምስት ባለሀብቶች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ በላይነህ ክንዴ ናቸው፡፡ ዘጠኝ የቦርድ አባላት ያሉት አዲሱ ቦርድ ለሦስት ዓመታት ያገለግላል፡፡

ከአክሲዮን ማኅበሩ ድርሻ ያላቸው ባለአክሲዮኖች ቁጥር 307 የደረሰ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በግላቸው አክሲዮን ከገዙ የድርጅቱ ሠራተኞች በተጨማሪ፣ ሁሉንም ሠራተኞች ባቀፈው የሸማቾች ማኅበር፣ የብድርና ቁጠባ ማኅበር በኩል የአክሲዮን ባለቤት የሚያደርጋቸውን ድርሻ ገዝተዋል፡፡ ቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ የተለያዩ የብረታ ብረት ውጤቶችን ከማምረት ባሻገር፣ በቅርቡ የተሽከርካሪ አካላትን ማምረት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች