Sunday, September 24, 2023

የብሪታኒያ ውሳኔ ለኢትዮጵያ ምን ያጎድላል?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹ፀሐይ የማይጠልቅበት ግዛት›› የሚለው አገላለጽ ታላቋ ብሪታንያ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ ግዛቷን ያስፋፋችበት ዘመን የሚያስታውስ ነው፡፡ ዓለም ወደ አንድ መንደር እየተሰባሰበች ባለችበት በአሁኑ ዘመን ግን ብሪታኒያ ከአኅጉራዊው ድርጅት የሚያስወጣትን ሒደት ጀምራለች፡፡ የዓለም መሰባሰብ በቅኝ ግዛት፣ በቋንቋ መስፋፋትና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስፋፋት ከፍተኛ ሚና የነበራት ብሪታኒያ ግን፣ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ሁለት እንግዳ ውሳኔዎችን አሳልፋለች፡፡

መስከረም 2007 ዓ.ም. የዩናይትድ ኪንግደም አንድ አካል የሆነችው የስኮትላንድ ግዛት ራሷን ከታላቋ ብሪታንያ ለማውጣት የሕዝበ ውሳኔ ብያኔ ያካሄደች ሲሆን፣ በጠባብ ልዩነት (ማለትም 52 በመቶ) መራጮች በእንግሊዝ ለመቆየት መወሰናቸው ይታወሳል፡፡ ስኮትላንድ ጨርሳ ባትገነጠልም ስኮቲሾች ከሌሎች ብሪታኒያውያን የተለየ ማንነትና ምልከታ እንዳላቸው ይነገራል፡፡ ራሷን በራሷ የምታስተዳድር ግዛትም ነች፡፡

የዓለምን የዜና አውታሮች በርከት ላሉ ወሮች የተቆጣጠረው ይኼው የስኮትላንድ የመገንጠል ጥያቄ ሳይደርቅ ነበር ብሪታኒያ ከአውሮፓ ኅብረት ለመለየት የወሰነችው፡፡ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ብሪታኒያ በፊት አውራርነት ከመሠረተችው ከአውሮፓ ኅብረት ራሷን ለማስገለል በተደረገው እንቅስቃሴ ብሪታኒያውያን ከኅብረቱ ለመውጣት በድምፃቸው ሰሞኑን ወስነዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ከብሪታኒያ ለመለየት ያደረገው እንቅስቃሴ ያልተሳካለት የስኮትላንድ ክፍልም አገሪቱ በአውሮፓ ኅብረት ሥር ለመቆየት 62 በመቶ የወሰነ ሲሆን፣ በሌሎች አካባቢዎች ድምፅ ተበልጧል፡፡ ሆኖም የአብዛኛው ብሪታኒያውያንን ውሳኔ ተከትሎ የስኮትላንድ አስተዳደር ከብሪታኒያ የመገንጠል ሐሳቡ እንደገና ለማንሳት እንቅስቃሴ መጀመሩ እየተነገረ ነው፡፡ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ይህን ከኅብረቱ የመውጣት ውሳኔ የተቃወሙ ሲሆን፣ በራሳቸው ፍቃድ ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ ወስነዋል፡፡

28 አባል አገሮች ካሉት አውሮፓ ኅብረት ጠቅልላ ለመውጣት ሁለት ዓመት የሚፈጅ ሒደት የሚጠብቃት ታላቋ ብሪታንያ፣ አሁን በተወሰነው ከኅብረቱ የመውጣት እንቅስቃሴ ምክንያት ገና ለገና የዓለም የገንዘብ ግብይት በሁለት ትሪሊዮን ዶላር ተመቷል፡፡ ከዚሁ ውስጥ እጅግ የተጎዳው ኢኮኖሚ ደግሞ የራሷ የብሪታኒያ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በባንኮች የእንግሊዝ ቁጠባ 50 ቢሊዮን ዶላር መቀነሱን የተመዘገበ ሲሆን፣ እስካሁን የብሪታኒያ ፓውንድ ከአቻው የአሜሪካን ዶላር ባለፉት 30 ዓመታት ባልታየ ሁኔታ የ10 በመቶ ዋጋ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

   የብሪታኒያ ከኅብረቱ የመወጣት ውሳኔ በዚሁ ዘመን ዓለምን ካስደመመና ካነጋገረ ክስተት መካከል ሲሆን፣ በዚሁ ውሳኔ ምክንያት በብሪታኒያ ዜጎችና ባለሀብቶች ላይ ሊያስከትለው የሚችል የኢኮኖሚ ጫና በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ውሳኔው ሊቀለበስ ይችላል የሚሉ ትንታኔዎችም እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡

እንግሊዝና አፍሪካ

በተለይ በአፍሪካ ምድር ዛሬም ድረስ ‹‹አንግሎፎን›› በመባል የሚታወቀው ቀጣና በቅኝ ግዛት ዘመን የብሪታኒያ ግዛት ስፋት አስታዋሽ ሲሆን፣ ‹‹ፍራንክፎን›› ተብሎ ከሚታወቀው የፈረንሳይ ግዛት ከነበረው የአኅጉሩ ክልል ጋር ፖለቲካዊ ልዩነቶች አሉት፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ውሳኔዎችን ለሚከታተል የእነዚህ አካላት ልዩነት በውሳኔዎቹ መንፀባረቁን ማየት ይችላል፡፡

ቀደም ሲል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በካዛብላንካና ሞንሮቪያ ጎራዎች መካከል የተከሰተው አለመግባባት የድርጅቱ መቀጠል አደጋ ላይ ጥሎ የነበረ ሲሆን፣ ካዛብላንካ በመባል የሚታወቀው ጎራ ውስጥ የሚገኙት በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ምክንያት የፈረንሳይ ተፅዕኖ ያለባቸው ሲሆን፣ ሌላኛው ተቃራኒዋ ሞንሮቪያ ደግሞ የእንግሊዝ ሥርዓት ተፅዕኖ ያለባቸው ናቸው፡፡

ሁለቱም ጎራዎች በየፊናቸው የአፍሪካ የድርጅት መልክ ምን መምሰል እንዳለበትና አስፈላጊነቱ ላይ የራሳቸው ምልከታ አላቸው፡፡ ከሁለቱም ወገኖች ገለልተኛ ተደርጋ የምትታየው ኢትዮጵያና ንጉሷ አፄ ኃይለ ሥላሴ የአስታራቂነት ሚና እንዲጫወቱ አድርጓቸዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ቻርተርና የውስጥ አወቃቀርና አደረጃጀት በአብዛኛው የአውሮፓ ኅብረት መልክ የተከተለ ሲሆን፣ ከኅብረቱ የሚያገኘው ድጋፍ ደግሞ ቀላል አይባልም፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የፕሮግራም ወጪዎች ከ90 በመቶ በላይ ከለጋሽ አገሮች የሚገኝ ሲሆን፣ አውሮፓ ኅብረትና ብሪታኒያ እንደ አንድ አገር የአፍሪካ ኅብረትን በመደገፍ ቀዳሚነቱን ይይዛሉ፡፡

ብሪታኒያ በአፍሪካ ያላት ተፅዕኖ በዚሁ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ 19 የአፍሪካ አገሮች ‹‹ኮመንዌልዝ›› በመባል የሚታወቀው ኅብረት ያላቸው ሲሆን፣ ከእንግሊዝ የተለየ ጥቅምና ድጋፍ የሚያገኙ ናቸው፡፡ ለብዙዎቹ እንግሊዝኛ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ከብሪታኒያ ጋር የተለየ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ያላቸውና ከፍተኛ የቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት የሚፈስባቸው ናቸው፡፡ በብሪታኒያ የምትከሰት እያንዳንዷ ክንዋኔ የሚኖራት ተፅዕኖ በብሪታኒያ ዜጎች ብቻ የሚወሰን አይሆንም፡፡ በእነዚህ አገሮች ዜጎችና መንግሥታት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሒደቶች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡

ውሳኔው በአፍሪካ ኅብረት በአንግሎፎን የአፍሪካ ምድር እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊያስከትል እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል፡፡ በአፍሪካ የብሪታኒያ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተፅዕኖ ከፍተኛ በሆነባቸው በደቡብ አፍሪካና በኬንያ ያስከተለው አንዳንድ ክስተቶች አስደንጋጭ ሆኗል፡፡

በአፍሪካ ኢኮኖሚያቸው ከብሪታኒያ ጋር እጅግ ከተሳሰሩ አገሮች ግንባር ቀደም የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ውሳኔውን ተከትሎ እስካሁን የመገበያያ ገንዘብ የሆነው ራንድ በ21 በመቶ ዋጋው የወረደ ሲሆን፣ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠን 178 በመቶ የብሪታኒያ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይኼው ጫና በናይጄርያና በኬንያም እየተስተዋለ ነው፡፡ በተለይ የኬንያ ዋና የኢኮኖሚ የአጥንት ጀርባዋ የሆነውን የአበባ ምርት በ500 ሚሊዮን ፓውንድ የሚገመት ዋጋ ያለው ምርት በዓመት እንደምትልክ የኢትዮጵያ ሃይላንድ ፍሎራ ባለቤትና የቀድሞው የኢትዮጵያ የአበባ አምራቾች ኅብረት ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋዬ አበበ ለሪፖርተር ይገልጻሉ፡፡

የብሪታኒያ ከአውሮፓ ኅብረት መውጣት ከየትኛውም የዓለማችን ክፍል በበለጠ ተፅዕኖው በአፍሪካ እንደሚሆን ተንታኞች እየተናገሩ ሲሆን፣ በአራት ዋና ዋና ዘርፎች ላይ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በኦፊሴላዊ በዕርዳታ (ODA – ኦፊሻል ዴቨሎፕመንት አሲስታንስ) በፖለቲካና በፀጥታ ጉዳዮች ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡

ኢትዮጵያና ምሥራቅ አፍሪካ

የብሪታኒያ ውሳኔን ተከትሎ በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ተፅዕኖው ከፍተኛ የሚሆነው የኢትዮጵያ ጎረቤት በሆነችው በኬንያ እንደሚሆን አቶ ፀጋዬ ይናገራሉ፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት የብሪታኒያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኒክ ክሌማ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት እንዳረጋገጡት፣ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራት ግንኙነት ከፖለቲካም ይልቅ ወደ ኢኮኖሚ ሊያዘነብል እንደሚፈልግ የተናገሩ ቢሆንም፣ የእንግሊዝና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትስስር ግን እስካሁን እስከዚህም ነው፡፡

የኢትዮጵያ የአበባ አምራቾች በአውሮፓ የገበያ ዋና ማረፊያቸው ሆላንድ ስትሆን፣ በኬንያ የተስተዋለው የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ተፅዕኖ በኢትዮጵያና ሌሎች አጎራባች አገሮች የሚስተዋል እንደማይሆን ባለሙያው አቶ ፀጋዬ ይናገራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ በበኩላቸው፣ ከአቶ ፀጋዬ ጋር ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረትም ሆነ ከብሪታኒያ ጋር የገባባቸውን ስምምነቶች ላይ እምብዛም ለውጥ ለማስደረግ ክስተቱ ምክንያት አይሆንም ይላሉ፡፡

የፕሮፌሰር ዓለማየሁ ሥጋት የዕርዳታ ጉዳይ ነው፡፡ ብሪታኒያ ከአሜሪካ ቀጥላ ለኢትዮጵያ ዕርዳታ በመለገስ ትቀመጣለች፡፡ ከጠቅላላ ገቢዋ ለድሃ አገሮች የምትለግሰው ገንዘብ ከዓመታዊ የኢኮኖሚ ገቢዋ 0.7 በመቶ ነው፡፡ ይህም ተመድ ያስቀመጠውን ደረጃ ያሟላል፡፡ በአኃዝ ሲገለጽ 12.2 ቢሊዮን ፓውንድ ይሆናል፡፡ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብሪታኒያ ለአፍሪካ 2.54 ቢሊዮን ፓውንድ የሰጠች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ 334 ሚሊዮን ፓውንድ በመውሰድ ቀዳሚ ነች፡፡ በእርግጥ ብሪታኒያ ከምትረዳቸው አገሮች ኢትዮጵያ ትልቁን ዕርዳታ ተቀባይ ነች፡፡ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ እንደሚሉት የአገሪቱ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ተከትሎ ለዕርዳታ የምታውለው የገንዘብ መጠን ሊቀንስ ይችላል፡፡ ኢትዮጵያም እንደ ዋና ተቀባይ ልትጎዳ ትችል ይሆናል፡፡

ይኼም ብቻ ሳይሆን ብሪታኒያ ለምሥራቅ አፍሪካ መልካም ዕይታ ካላቸው የኅብረቱ አገሮች ግንባር ቀደም ከመሆኗ ተነስቶ ከአውሮፓ ኅብረት ውስጥ ከዕርዳታና ከስደተኞች ጋር ተያይዞ አንዳንድ ለውጦች እንደሚኖሩ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡ ገና ከወዲሁ ብሪታኒያ ፓውንድ ላይ የታየው የዋጋ ምንዛሪ ማሽቆልቆል በዕርዳታው መጠን ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ግልጽ እንደሆነ የሚናገሩት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ፣ ይህንን ውሳኔ ያራገቡ ሰዎች የኮንዘርቫቲቭ ፓርቲ አመራሮች መሆናቸውን ደግሞ ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ የኮንዘርቫቲቭ ፓርቲ አመራሮች ለውጭ ዕርዳታ ያላቸው አመለካከት አሉታዊ መሆኑን በማስረዳት፡፡

ዶ/ር መሐሪ ታደለ ግን የብሪታኒያ ከኅብረቱ መውጣት በዚሁ በምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካና የፀጥታ ጉዳዮች እስከዚህም ነው ይላሉ፡፡ በጊዜው የብሪታኒያ የኢኮኖሚ መንገጫገጭ መጠነኛ ጉዳት ቢኖረውም፣ ብሪታኒያ ከቀጠናው ካላት የታሪክ ግንኙነት የተነሳ ከፍተኛ የፖለቲካ ፍላጎት እንዳላት ያስረዳሉ፡፡ በእርግጥም ከብሪታኒያ ጋር የነበረው የድርድርና ግንኙነት መልክ ይቀያየራል እንጂ፣ ብሪታኒያ በራሷ በተናጠል የምታደርጋቸው ድጋፎች አጠናክራና አብልጣ ልትሄድበት እንደምትችል ያምናሉ፡፡ በተለይ ደግሞ በቀጥታ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ አገሪቱ በዋናነት ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራት ግንኙነት ወደ ንግድና ኢንቨስትመንት የሚያዘነብል እንደሆነ መወሰኗ የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ እንደሚጠናከር ይናገራሉ፡፡

ለዶ/ር መሐሪ አሳሳቢ ጉዳይ የሰብዓዊ መብቶችና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ሲሆኑ፣ ምናልባት ብሪታኒያ ታደርግ የነበረው ለኢትዮጵያ ያደላ ተፅዕኖ ስለማይቀጥል የኅብረቱ ጫና ሊበረታ ይችላል፡፡ በኅብረቱ ውስጥ እነዚህ ጉዳዮች አጀንዳ እንዲሆኑ በር ሊከፍት ይችላል ይላሉ፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ በተለይ ከደኅንነትና ከመረጋጋት ጋር ተያይዞ የሶማሊያና የደቡብ ሱዳን ቀውሶች ዋና ትኩረት የሚሰጣቸው ሲሆኑ፣ ብሪታኒያ ትኩረቷ እንደማይቀንስ ያስረዳሉ፡፡ ባለፈው ዓመት የሶማሊያ ጉባዔ የተካሄደው በለንደን ሲሆን፣ አልሸባብን እየተዋጋ ያለው አሚሶም (የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል) የገንዘብ ድጋፍ ከአውሮፓ ኅብረት ይደረግለታል፡፡

ከኅብረቱ ጋር የሚደረገው ቀጣይ ውይይት ከብሪታኒያ መውጣት በኋላ መልኩ ሊቀይር የሚችል ቢሆንም፣ እምብዛም አይለወጥም ብለው ያምናሉ፡፡ የብሪታኒያ ድጋፍ በተናጠል እንደሚቀጥልም እመነታቸው ነው፡፡

በደቡብ ሱዳንም በቅርቡ የተቋቋመውና ገና በሁለት እግሩ ያልቆመው የጋራ መንግሥት ለመደገፍ ከሚንቀሳቀሱ ትሮይካ በመባል የሚታወቁ ሦስት አገሮች ብሪታኒያ ዋነኛዋ ስትሆን፣ ሌሎቹ አሜሪካና ኖርዌይ ናቸው፡፡ እዚህም ላይ በአካባቢው ካለው ነዳጅ ጋር ተያይዞ የብሪታኒያ ጥቅም ከፍተኛ ሲሆን፣ አገሪቱ በተናጠል የምታደርገው ድጋፍ እንደሚጎለብት የዶ/ር መሐሪ እምነት ነው፡፡ እንዲሁም ለምሥራቅ አፍሪካ በጎ አቋም አላት ያሏት ብሪታኒያ፣ ከአውሮፓ ኅብረት መውጣት የኅብረቱ ትኩረት ወደ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የአፍሪካ አገሮች (በተለይ ማሊ) ሊሆን እንደሚችልም ገምተዋል፡፡

በአፍሪካ ፈረንሳይና ብሪታኒያ ባላቸው ተፎካካሪ ፍላጎቶች የተነሳ በፈረንሳይ ጉትጎታ የአውሮፓ ኅብረት በቅርቡ ለአሚሶም የሚሰጠው ዕርዳታ የቀነሰ ሲሆን፣ ይህም ኡጋንዳ ወታደሮችዋን ከአካባቢው ለማስወጣት ምክንያት ሆኗል፡፡ ይኼ የቀጣዩ የሶማሊያ ዕጣ አመላካች መሆኑ ደግሞ የሚገልጹት የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ አቶ ልዑልሰገድ ግርማ ናቸው፡፡ እንዲሁም ደግሞ የብሪታኒያ የአውሮፓ ኅብረት አባልነት መቋረጥ ተከትሎ ኅብረቱ በደቡብ ሱዳን ለሰላም ማስከበርና ለአጣሪው ኮሚቴ (JMEC) ለመስጠት ያቀደው ድጋፍ ሊቋረጥ እንደሚችል ሥጋት አላቸው፡፡

የፖለቲካ ተንታኞች የታላቁ ብሪታንያ ከአውሮፓ ኅብረት መለየት በኢኮኖሚ ፖለቲካና የፀጥታ ጉዳዮች በአፍሪካ በተለይ ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን ተፅዕኖ በተለያዩ መንገዶች የተመለከቱት ሲሆን፣ የአውሮፓ ኅብረት አወቃቀር መሠረት ያደረገው ለአፍሪካ ኅብረት መልካም ዜና እንዳልሆነ ሌሎች ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

የብሪታኒያ ኤምባሲ ለሪፖርተር በኢሜይል የላከው ምላሽ ግን እንዲህ ይነበባል፡፡ ‹‹ብሪታኒያ ከአፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ታሪካዊና ጠንካራ ነው፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ከብሪታኒያ ጋር ያላቸው የቋንቋ፣ የሙዚቃና የባህል ትስስሮች የጠበቀ ነው፡፡ እንግሊዝም ለአኅጉሩም ሆነ ለምሥራቅ አፍሪካ ማድረግ ያለባትን ድጋፍ አጠናክራ የምትቀጥል ይሆናል፤›› ይላል፡፡

 

   

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -