Wednesday, October 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የአገር ሀብት የፈሰሰባቸው መንገዶች ለአደጋ ተጋልጠዋል!

የዘንድሮ ክረምት የተጠናከረ እንደሚሆን የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በሚቀጥሉት ሁለት ወራት መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ዝናብ ይኖራል ማለት ነው፡፡ የዝናቡ መጠን ሲጨምር ደግሞ የጠቀሜታውን ያህል ጉዳትም ያስከትላል፡፡ በመኖሪያ ቤቶች፣ በእርሻዎችና በተለያዩ ሥፍራዎች ከሚደርሰው ጉዳት በተጨማሪ ከፍተኛ የአገር ሀብት የፈሰሰባቸው መንገዶች ለጉዳት ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ የአገሪቱን ዋና ከተማ ከተለያዩ ከተሞች ጋር ከሚያገናኙ አውራ ጎዳናዎች በተጨማሪ፣ በከተሞች ውስጥ የተገነቡ መንገዶችም ለብልሸት ይዳረጋሉ፡፡ የክረምቱ ዝናብ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱ በፊት የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል፡፡

ባለፈው እሑድ ሰኔ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ሌሊት በአዳማ ከተማ በጣለው ከባድ ዝናብ ሳቢያ የደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት፣ የምንነጋገርበትን ርዕሰ ጉዳይ ያጠናክረዋል፡፡ በአዳማ የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ ከፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች አቅም በላይ በመሆኑ፣ በመንገዶች ላይ እየጋለበ በመኖሪያ ቤቶችና በሆቴሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ ለአንድ ሕፃን ሕይወት መጥፋትም ምክንያት ሆኗል፡፡ በከተማው ውስጥ የሚገኙ አምስት ቀበሌዎችን ያካለለው ከባድ ጎርፍ በርካታ ተሽከርካሪዎችንም ውጧቸው ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ክስተት በበርካታ የአገሪቱ ከተሞች ላይ አደጋ መደቀኑን ያመላክታል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ መንገዶች ተገንብተዋል፡፡ ዝናብ በዘነበ ቁጥር መንገዶቹ በጎርፍ ሲጥለቀለቁ ይታያል፡፡ የዘንድሮው የክረምት ዝናብ መጠን ሲጨምር ግን ከፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች አቅም በላይ የሆነ ጎርፍ መንገዶችን እያጥለቀለቀ የትራፊክ ፍሰቱን ከማስተጓጎሉም በላይ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ከፍተኛ የአገር ሀብት ያወጣባቸው መንገዶችም የአገልግሎት ጊዜያቸው ያጥራል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በጎርፍ በተደጋጋሚ የሚጠቁ መንገዶች ተገቢው ትኩረት ስለማይሰጣቸው እየፈራረሱ ሲሆን፣ ተገቢው ጥገና ስለማይደረግላቸውም ለተሽከርካሪ አደጋዎች ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአገር ሀብት ላይ ከፍተኛ ውድመት ይደርሳል፡፡

መንገዶች ሲገነቡ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች በልዩ ትኩረት መሠራት ሲኖርባቸው ችላ ስለሚባል፣ ብዙዎች መንገዶች የጎርፍ መጋለቢያ ሆነዋል፡፡ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ የተሠራላቸው መንገዶች በደረቅ ቆሻሻዎችና በባዕድ ነገሮች እየተዘጉ ፍሳሽ ማስተናገድ አልቻሉም፡፡ በቱቦዎቹ ላይ ቁጥጥር በማድረግ ዕርምጃ ባለመወሰዱ  ዝናብ ጠብ ሲል መንገዶቹ በጎርፍ ይወረራሉ፡፡ መንገዶቹ በርካታ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ ሲኖርባቸው፣ የአገልግሎት ጊዜያቸውም ከወጣባቸው ወጪ ጋር ተመጣጣኝ ካልሆነ ለአደጋ ይጋለጣሉ፡፡ አደጋው ከእነሱ አልፎ ለሕዝቡም ስለሚተርፍ ኪሳራው የከፋ ይሆናል፡፡

የመንገዶች በጥንቃቄ አለመያዝና ጎርፍን ከመሳሰሉ አደጋዎች አለመጠበቅ በተሽከርካሪዎችም ላይ መጠነ ሰፊ ችግር ይፈጥራል፡፡ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ተገዝተው ከውጭ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች በመንገዶቹ ምክንያት አደጋ ሲደርስባቸው፣ ለመለዋወጫ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ይጠይቃሉ፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አገር ድረስ አላስፈላጊ ለሆነ ወጪ መዳረግ ይከተላል፡፡ በተጨማሪም መንገዶቹ ያለጊዜያቸው ሲበላሹና ሲፈራርሱ ከግንባታ የማይተናነስ የጥገና ወጪ ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ሁሉ የአገር ሀብት ለክረምት ዝናብ ጥንቃቄ ባለመደረጉ ሲባክን ዝም መባል የለበትም፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የተገነቡ መንገዶችን ከጎርፍ አደጋ የመጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ በመሆኑም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በባለቤትነት ስሜት መንገዶቹን የመቆጣጠርና የማስተዳደር ኃላፊነት አለባቸው፡፡

የክረምቱ ዝናብ ከመጀመሩ በፊት መደረግ ያለባቸው ቅድመ ዝግጅቶች ካልተከናወኑና አደጋው ጉዳት ካስከተለ ተጠያቂነት መኖሩን መዘንጋት አይገባም፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለባቸው አሠራሮች በበርካታ መስኮች አገርን እየጎዱ መሆናቸው እየታወቀ፣ በመንገዶች ደኅንነት ዕጦት ምክንያት ሌላ ጥፋት ማስተናገድ በፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ በመንገዶች ላይ ከሚገለገሉ የተሽከርካሪ ባለቤቶች ጀምሮ እስከሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም ድረስ የሚከሰቱ አደጋዎችን ለማስቆም ርብርብ ማድረግ አለባቸው፡፡ ምክንያቶችን እየደረደሩ ኃላፊነትን አለመወጣት ማስጠየቅ አለበት፡፡ በየቦታው በጎርፍ ምክንያት የተጎሳቆሉ መንገዶችን መጠገን፣ አባጣ ጎርባጣዎችን ማስተካከል፣ የተደፈኑ የፍሳሽ ማስወገጃዎችን መክፈት፣ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ መንገዶችን በመለየት መላ መፈለግ፣ ወዘተ ሲገባ እጅን አጣጥፎ መመልከት ለማንም አይበጅም፡፡

ክረምቱ ከመደበኛው ለየት ያለ መጠኑ የጨመረ ዝናብ ያስተናግዳል ተብሎ ለጎርፍ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች ዜጎችን የማዘዋወር ተግባር መከናወኑ እየተነገረ፣ በከተሞችም የአደጋው ምልክት እየታየ፣ በመንገዶች ምክንያት የሚከሰተውን አደጋ ችላ ማለት ከፍተኛ ጥፋት ያስከትላል፡፡ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ አደጋውን ከመመከት ይልቅ፣ አደጋው ደርሶ ፋይዳ የሌለው መሯሯጥ ማድረግ ለማንም አይጠቅምም፡፡ የክረምቱ ዝናብ ከወትሮው ለየት ያለና ጠንካራ ይሆናል ሲባል፣ መንገዶችም ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...

የመከፋት ስሜት!

ከቤላ ወደ ጊዮርጊስ ልንጓዝ ነው፡፡ መውሊድና መስቀልን በተከታታይ ቀናት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግጭቶች በሙሉ ሁሉን አሳታፊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ተገቶ የተስፋ ጭላንጭል መታየት ሲጀምር፣ በአማራ ክልል ሌላ ዙር ዕልቂትና ውድመት ሊያደርስ የሚችል ግጭት መነሳቱ ብዙዎችን ያሳስባቸዋል፡፡ በአማራ...

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ የሚመሠርተው መንግሥት ከምንም ነገር በፊት ለሕግና ለሥርዓት መከበር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ የሚችለው ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...