ሠላሳ ቀኖች ብቻ ቀርተውታል፤ የሪዮ ኦሊምፒክ፡፡ በየአራት ዓመቱ የሚካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታ መላው ዓለምን ካላንዳች ልዩነት የሚያስተሳስር ስፖርታዊ መድረክ ብቻ ሳይሆን ባህላዊ መገለጫዎችንም የያዘ ነው፡፡
ከአራት ዓመት በፊት 30ኛውን ኦሊምፒያድ በድምቀት ካስተናገደችው ከእንግሊዟ ለንደን የተረከበችው የብራዚሏ ሪዮ መሰናዶዋን እያጠናቀቀች እንግዶቿንም እየጠበቀች ነው፡፡ ከስፖርታዊ ውድድሮች በተጓዳኝም ባህላዊ ትርዒቶችን የያዘ የባህል ኦሊምፒክ ዝግጅቷም አጠባቂ ሆኗል፡፡
ዘመናዊ ኦሊምፒክ ከ120 ዓመት በፊት በአቴንስ (ግሪክ) ከመጀመሩ በፊት ጥንታዊው የኦሊምፒክ ውድድር በተፈጠረበት ግሪክ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ776 ዓመት ጀምሮ እስከ ተቋረጠበት አራተኛው ምታመት ድረስ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡
ጥንታዊው ኦሊምፒክ በይፋ እንደሚታወቀው ከ2792 ዓመታት በፊት እንደተጀመረ ቢወሳም፣ ግሪካውያኑ ግን ዘመኑን ወደኋላ ያርቁታል፡፡ ስለአመጣጡም ልዩ ልዩ አፈታሪኮችን ያወጋሉ፡፡
ከእነዚህም አንዱ ከታላቁ ጀግና ከፔሎፕስ ጋር የተያያዘው ትረካ ነው፡፡ ክስተቱም ፔሎፕስ የፒሳ ግዛት ንጉሥ ኦኔማውስን ድል አድርጎ ሥልጣኑን ከነጠቀ ወዲህ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የፔሎፕስ አፈታሪክ እንደሚያመለክተው፣ በንጉሥ ኦኔማውስ ዘመን የንጉሡ ሴት ልጅ ሒፖዳሚያ በ13 ጎረምሶች ታፍና በሠረገላ ትወሰዳለች፡፡ ይህም በንጉሣውያን ቤተሰብ ውስጥ ድንጋጤንና ሽብርን ይፈጥራል፡፡ ነገር ግን በንጉሡ ሠረገላዎችና ፈጣን ፈረሶች አማካይነት በተደረገው ክትትል አሥራ ሦስቱም ይያዛሉ፡፡ ሒፖዳሚያም ነፃ ትወጣለች፡፡ በዘመናችን በምዕራባውያንም ዘንድ የዚህን የ13 ቁጥር ገደ ቢስነት ምልኪያ መንስዔ ከዚህ ጋር የሚያያይዙት እንዳሉ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡
ዳግመኛም ከዕለታቱ ባንዱ ቀን ፔሎፕስ የተባለ ወጣት ሲከሰትና ሊደርስ የሚችለውን ችግር በጥንቃቄ አጥንቶና ተዘጋጅቶ ሒፖዳሚያን ይዞ ይኮበልላል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የታፈነችበትን ልጁን ለማስለቀቅ ንጉሡ የጦር አበጋዞቹን አልላከም፡፡ ራሱ እየተከታተለ ቢያሳድደውም በጠላፊው ፔሎፕስ የተደለለው የንጉሡ ሾፌር ሰረገላውን ሆን ብሎ በማሰናከሉ ሊሳካለት አልቻለም፡፡ ፔሎፕስም በተገኘው አጋጣሚ ሒፖዳሚያን አግብቶ በመሞሸር ዙፋኑን ወረሰ፡፡ ለሥርዓተ ንጉሡም ክብር ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ጨዋታዎችን ያቀፈ ሃይማኖታዊ በዓልን በኤሊስ በምትገኘውና የአማልክቱ ቅድስት መሬት በምትባለው ‹‹ኦሊምፒያ›› አከናወነ፡፡ ይህ ታሪካዊ ሁነት የታየበት ዘመንም ከክርስቶስ ልደት በፊት 884 ዓመት ላይ ነበር፡፡
ሁለተኛውና ሌላው አፈታሪክ የኦሊምፒያ ጨዋታ መነሻን ከሔራክልስ ጋር ያያይዘዋል፡፡ በኤሊስ ዙሪያ የሚፈሱና የኦሊምፒያና ኮረብታ የከበቡ አልፌዎስና ከላውዴዎስ የሚሰኙ ሁለት ወንዞች ነበሩ፡፡ በኮረብታው ላይ መናፈሻውን የመሠረተው የኤሊስ ንጉሥ አውጊያስ አሽከሩ ሔራክልስ ላጠፋው ጥፋት መቀጣጫ የአምስት ሺሕ በሬዎቹን አዛባ ከበረቱ በፍጥነት እንዲያፀዳ ያዘዋል፡፡ ሔራክልስም ብልሃት ፈጥሮ ከበረቱ አጠገብ የሚወርደውን የአልፌዎሰ ወንዝ በመጥለፍና አቅጣጫውን በማስቀየር የጽዳት ተግባሩን ይወጣል፡፡ ጽዳቱን ካከናወነ ከንጉሡ ከብት ከአሥር አንድ እንደሚያገኝ ቃል ቢገባለትም የወንዙን አቅጣጫ አስቀይረህ ስላጠብህ አልሰጥህም ይለዋል፡፡ በዚህም የተናደደው ሎሌ ንጉሡን ገድሎ ንብረቱንና ዙፋኑን ይወርሳል፡፡ ወራሽነቱንም ለማስመስከር ከክርስቶስ ልደት በፊት 1253 ዓመት ላይ በኦሊምፒያ ኮረብታ ልዩ ልዩ ጨዋታዎችን ያካተተ ሃይማኖታዊ በዓልን ያከብራል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ለኦሊምፒክ ጨዋታዎች መሠረት የሆነው ይላል የግሪኩ አፈታሪክ፡፡
ከሦስት ሺሕ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ጥንታዊው ኦሊምፒክ በኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አማካይነት በየአራት ዓመቱ በዘመናዊነት ሲቀጥል ጠቅላላ ስፖርቶችን ባንድ መድረክ ማሰባሰብ ችሏል፡፡ ከስፖርት ማዕከልነት እስከ ባህላዊ የጥበብ ትዕይንት በማገናኘቱ ወደር ያልተገኘለት አቻ ያልተፈጠረለት ሰብዓዊ ክንዋኔ ነው – ኦሊምፒክ፡፡
የኦሊምፒክ ታሪክ ተንታኙ ዴቪድ ዎሊቺንስኪ፣ ኦሊምፒክ እንደተባበሩት መንግሥታት (ተመድ) ሸንጎ ሳይሆን እያንዳንዱን አገር ለዚያውም በተመድ አባልነት ያልታቀፉትን ጨምሮ በ205 ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎችን (አገሮች) ያቀፈ መሆኑን ይገልጻል፡፡ መድረኩም የየሀገሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከእጅግ ዝቅተኛው ነዋሪ እስከ ከፍተኞች የመንግሥት ሹማምንት ድረስ የሚሳተፉበት ነው፡፡
በግሪክ ትውፊት ኦሊምፒክ የሚካሄድባቸው ቀኖችና ወሮች እንደ ቅዱስ ስለሚቆጠሩ ውዝግቦች፣ ጦርነቶች፣ ግጭቶችም ጭምር እንዲቆሙ ይመከራል፡፡ በነሐሴ 2008 ዓ.ም. በሚካሔደው የሪዮው 31ኛው ኦሊምፒያድ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት የሚዘመረው ‹‹ብርሃንህ ይውረድ ያጥላ በእኛ ላይ›› የሚለው የኦሊምፒክ መዝሙር በእርግጥም በኦሊምፒክ ቡድኖችና በመላው ዓለም መስፈን አለበት፡፡ ከአራት ዓመት በፊት ለንደን ዝግጅቱን በድል አጠናቃ ዘንድሮ ለሪዮ ዲጄኔሮ አስረክባለች፡፡ ከአራት ዓመት በኋላ ቶኪዮ በሰላሙ ዐውድ ትደምቃለች፡፡