Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበገርጂ ሰንሻይን ኮንዶሚኒየም የሚኖሩ 547 አባወራዎች በውኃ ችግር እየተሰቃዩ መሆኑን ገለጹ

በገርጂ ሰንሻይን ኮንዶሚኒየም የሚኖሩ 547 አባወራዎች በውኃ ችግር እየተሰቃዩ መሆኑን ገለጹ

ቀን:

ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ገርጂ የገነባቸውን 547 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ገዝተው በመኖር ላይ ያሉ አባወራዎች፣ የውኃ መስመራቸው በመቆረጡ በከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን ገለጹ፡፡

በጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ላይ የሚኖሩ ከሦስት ሺሕ በላይ ቤተሰቦች እንደሚገኙ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ የሕንፃው የውኃ ፍሳሽ ማስወገጃ፣ በአካባቢው ከሚገኘው ሴፕቲክ ታንክ ጋር የተገናኘው በሕገወጥ መንገድ መሆኑን በመግለጽ፣ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ከ15 ቀናት በፊት መስመሩና እንደቆረጠባቸው ተናግረዋል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው መታፈሪያ፣ መንግሥት ለዜጎቹ ማቅረብ ካለበት መሠረታዊ ነገሮች አንዱ ውኃ መሆኑን ጠቁመው፣ የአገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው የሪል ስቴት ግንባታ መሠረት፣ ሕንፃዎቹ ሲገነቡ ቁጥጥር በማድረግ ችግሮቹን መቅረፍ ሲገባው፣ እነሱ እንዲጠሙና ውኃን ተከትለው ሊመጡ ለሚችሉ በሽታዎች ሥጋት ውስጥ ማስገባት እንዳልነበረበት አስረድተዋል፡፡

ሕግን ተከትለውና መኖሪያ ቤቶችን ገዝተው ለዓመታት ከኖሩ በኋላ፣ ፍሳሽ ማስገወጃው በሕገወጥ መንገድ ባለሥልጣኑ ከዘረጋው የፍሳሽ ማስወገጃ ጋር እንደተገናኘ በመግለጽ፣ ውኃ ማቋረጥ ሕዝብና መንግሥትን ለማጋጨት የታሰበ ካልሆነ በስተቀር፣ ሌላ ዓላማ እንደሌለው ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት (ባለሥልጣኑ) የቆፈረውን ሴፕቲክ ታንክ መጠቀም እንደማይችሉ የባለሥልጣኑ ሠራተኞች እንደገለጹላቸው የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፣ አዲስ ሴፕቲክ ታንክ ለማስቆፈር የግዴታ ውል እንዲገቡ እየተገፉ ቢሆንም፣ ዋጋው ከፍተኛ በመሆኑ ነዋሪው አቅም እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ የከተማውን ጽዳትና የነዋሪውን ደኅንነት መጠበቅ ሲገባው፣ ውኃ እያቋረጠ ለአጣዳፊና ተቅማጥ በሽታ (አተት) እንዲሁም ለሌሎች በሽታዎች በሚያጋልጥ ሥራ ይሠራል የሚል እምነት እንደሌላቸው የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ኃላፊዎችን ለማግኘት ሪፖርተር ያደረገው ጥረት ባይሳካም፣ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የባለሥልጣኑ ሠራተኛ ስለችግሩ አስረድተዋል፡፡ ሠራተኛው እንደገለጹት፣ ችግሩን ሁሉም ኃላፊዎች ያውቁታል፡፡ ነዋሪዎቹ ቤቱን ገዝተው ሲገቡ ሁሉን ነገር አረጋግጠው መረከብ የነበረባቸው ቢሆንም፣ ተቋሙ ግን የባሰ ችግር ከመፍጠር ሌላ አማራጭ መውሰድ ይገባው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ በወቅቱ የፍሳሽ ማስወገጃው የተገናኘው በብልሹ አሠራር (ሙስና) ሊሆን እንደሚችል የገመቱት ሠራተኛው፣ የባለሥልጣኑ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች በየክፍለ ከተማ የነበረ በመሆኑ፣ በወቅቱ የነበሩ የክፍለ ከተማው ኃላፊዎችና ግንባታውን ያከናወነው አካል ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ ነዋሪዎቹ ለከፋ ችግር ከመጋለጣቸው በፊት ባለሥልጣኑም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካሎች መፍትሔ እንዲያገኙ ቢያደርጉ የተሻለ እንደሚሆን አሳስበዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...