Monday, May 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባለሥልጣኑ በበጀት ዓመቱ ከአዲስ አበባ ግብር ከፋዩ 26 ቢሊዮን ብር እሰበስባለሁ አለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በከተማው ከ360 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች እንዳሉ ጠቁሟል

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ለአራት ወራት በሚያካሂደው የ2008 በጀት ዓመት የገቢ ማሳወቂያ ወቅት፣ በ2009 በጀት ዓመት ከአዲስ አበባ ከተማ ግብር ከፋዮች 26 ቢሊዮን ብር እሰበስባለሁ አለ፡፡

በባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት የአዲስ አበባ ከተማ ታክስ ፕሮግራም ልማት ሥራዎች ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ነፃነት አበራ፣ ሰኔ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደገለጹት፣ በበጀት ዓመቱ ቀጥተኛ ከሆነና ቀጥተኛ ካልሆነ ታክስ ከሚሰበስበው 26 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ 53 በመቶ የሚሆነው የሚሰበሰበው በገቢ ማስታወቂያ ነው፡፡

ከሐምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ባሉት አራት ወራቶች፣ በከተማው የሚገኙት ከ360 ሺሕ በላይ ግብር ከፋዮች፣ የ2008 በጀት ዓመት ያገኙትን ገቢ በየደረጃቸው እንደሚያሳውቁ ወ/ሮ ነፃነት ተናግረዋል፡፡

ከ360 ሺሕ ግብር ከፋዮች ውስጥ 60 በመቶ የሚሆኑት በደረጃ ‹‹ሐ›› ውስጥ የሚካተቱ መሆናቸውን የጠቆሙት ወ/ሮ ነፃነት፣ ከሐምሌ 1 እስከ ሐምሌ 30 ቀን  2008 ዓ.ም. የሚስተናገዱ ናቸው ብለዋል፡፡ ዓመታዊ የሽያጭ ገቢያቸው 100 ሺሕ ብር የሆኑ ግብር ከፋዮች ደረጃ ‹‹ለ›› መሆናቸውንና ከሐምሌ 1 እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሚስተናገዱ፣ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ማለትም ደረጃ ‹‹ሀ›› ግብር ከፋዮች ደግሞ፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. የሚስተናገዱ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በዘርፉ ቀልጣፋና አስተዳደራዊ ችግር የሌለበት መስተንግዶ ለማካሄድ ሰፊ ዝግጅት አድርጐ ማጠናቀቁን የጠቆሙት ወ/ሮ ነፃነት፣ በሁሉም ማስተናገጃ ጣቢያዎች የተሟላ የሰው ኃይልና ሲስተም መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ለአቅመ ደካሞች፣ መጻፍና ማንበብ ለማይችሉ ግብር ከፋዮችም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንና መስተንግዶን በሚመለከት በተለይ ለአቅመ ደካሞቹ ግብር ከፋዮች ማኅበረሰብ ቅድሚያ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ክፍተቶች ቢፈጠሩ በሚል ለማስተካከያ የሚሆኑ ባለሥልጣኑ በ114 ግብር መክፈያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን፣ 116 ማይክሮ ግብር መክፈያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችንና በመርካቶ በሚገኙ ስምንት የታክስ ማዕከላትን ዝግጁ በማድረግ ለማስተካከል መዘጋጀቱን ወ/ሮ ነፃነት አስረድተዋል፡፡

ግብር ከፋዩ የመክፈያ ጊዜውን አውቆና ከመጀመሪያዋ ቀን ማለትም ከሐምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ዓመታዊ የሽያጭ ገቢውን የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት የገለጹት ወ/ሮ ነፃነት፣ በመጨረሻዎቹ 28ኛ፣ 29ኛ እና 30ኛው ቀን እየሄዱ ቢሠለፉ፣ ያንን የሚያስተናግድ የሰው ኃይል፣ ሲስተምና ቦታ ስለማይኖር መጨናነቅና እንግልት ስለሚያመጣ ከዚያ መጠንቀቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ባለፈው በጀት ዓመት ከከተማው ግብር ከፋዮች ሊሰበስብ ያቀደው 22.8 ቢሊዮን ብር እንደነበር ያስታወሱት ወ/ሮ ነፃነት፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. 21 ቢሊዮን ብር እንደሚሰበሰብና የዕቅዱን 92 በመቶ እንደሚያሳካ ተናግረዋል፡፡

በ2009 በጀት ዓመት ደግሞ 14 በመቶ አድጐ 26 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን አክለዋል፡፡

በመርካቶ ዓመታዊ የሽያጭ ገቢ ላይ ስለሚነሳው ችግር ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፣ የመርካቶ ችግር የከተማው ብቻ ሳይሆን የአገር ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም የመርካቶን ችግር በተለየ መንገድ ለመፍታት በ2004 ዕቅድ ወጥቶ ከዚያ በኋላ ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ፣ ከባለሥልጣኑ የሚመለከታቸው አካላትና ከሌሎችም የተውጣጣ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ እልባት ለመስጠት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ክልሎችም ድርሻ እንዲኖራቸው እየተደረገ መሆኑን አክለዋል፡፡   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች