መንግሥት ያለግንባታ ፈቃድ በርካታ ፕሮጀክቶችን እየገነባ መሆኑ ተነቀፈ፡፡ የአዲስ አበባ መሪ ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሰኔ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ባቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ፣ መንግሥት ያለግንባታ ፈቃድ በርካታ ግንባታዎች እያካሄደ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡
መንግሥት ያለግንባታ ፈቃድ ገንብቷቸዋል ከተባሉት መካከል የመኖሪያ ቤቶች፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ግንባታዎች ለአብነት ቀርበዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የግንባታና የሳይት ፕላን ፈቃድ ሳይኖራቸው ከተገነቡት መካከል የእግረኛ መንገድ፣ ፓርኮች፣ የመንገድ አካፋዮችና የወንዝ ዳርቻዎች ተጠቃሾች ሆነዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚካሄዱ ግንባታዎች በሙሉ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ፈቃድ ሊያገኙ እንደሚገባ ተደንግጓል፡፡
ነገር ግን በመንግሥት ተቋማት እየተካሄዱ ያሉ ፕሮጀክቶች፣ ያለባለሥልጣኑ እውቅና መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ከመንግሥት በተጨማሪም የእምነት ተቋማትም እንዲሁ ያለግንባታ ፈቃድ ግንባታ እንደሚያካሂዱ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የእምነት ተቋማት መገንባት ያለባቸው ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለሕፃናትና ለአዛውንቶች መርጃ የሚሆኑ ግንባታዎች ቢሆንም፣ እየገነቡ ያሉት ግን ከዚህ የተለየ መሆኑ በወቅቱ በተካሄደ ውይይት ላይ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሪ ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የመዋቅራዊ ፕላን ቡድን መሪ አቶ ታምራት እሸቱ፣ እንደማንኛውም ግንባታ የእምነት ተቋማቱም ከተመደበላቸው አገልግሎት ውጪ መገንባት የለባቸውም ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አባተ ስጦታው፣ መንግሥት የግንባታ ፈቃድ ሳይኖረው በምን ምክንያት እንደሚገነባ ከሪፖርተር ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ሳይመልሱ አልፈዋል፡፡
በአዲስ አበባ በርካታ ግንባታዎች የሚካሄዱት በመንግሥት ቢሆንም፣ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን የማያውቃቸው በመሆኑ ከጥራት ጋር በተገናኘ በርካታ ጥያቄዎች በመነሳት ላይ ይገኛሉ፡፡