Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲሱ የውጭ ምንዛሪ አሠራር ጉዳት እያስከተለ መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ላይ እየተሠራበት ያለው አዲስ አሠራር አገሪቱን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገና ኩባንያዎችንም አላስፈላጊ ወጪ እያስወጣ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ከውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ጎን ለጎን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠመው ነው የተባለው ችግር ኩባንያዎች ከውጭ የተለያዩ ምርቶችን ገዝተው ለመግባት ሌተር ኦፍ ክሬዲት (ኤልሲ) ሲከፍቱ ግዥውን ለመፈጸም መጀመርያ ኢንቮይሱ ከተያያዘለት ኩባንያ ውጭ ግዥ መፈጸም አይቻልም ከመባሉ ጋር የተያያዘ ነው፡፡  

ከጥቂት  ወራት በፊት በተጀመረው በዚህ አሠራር ጉዳት እየደረሰብ ነው ያሉ ኩባንያዎች እንደቀድሞ ኤልሲው በሚፈቀድበት ወቅት ከሌሎች ኩባንያዎች  ዋጋ በማወዳደር ለመግዛት ይቻል የነበረውን ዕድል አሳጥቶናል ይላሉ፡፡ አንድ ውጭ ምንዛሪ የጠየቀ ኩባንያ መግዛት ያለበት የውጭ ምንዛሪውን ለማግኘት ኤልሲ ሲከፍት ምርቱን ለመግዛት መጀመርያ ካስመዘገበውና ኢንቮይሱን ከሰጠው ኩባንያ ብቻ ነው የሚል ግዴታ መጣሉ አግባብ እንዳልነበርም ያስረዳሉ፡፡ ቀድሞ ከሚሠራበት አሠራር ውጭ ከሌላ ኩባንያ የተሻለ ዋጋ ቢገኝ እንኳን መጀመርያ ኢንቮይሱ ከገባለት ኩባንያ ብቻ መሆን አለበት የሚለው አሠራር ዕቃ አቅራቢዎቹን የበለጠ እየጠቀመና ዋጋ እንዲያንሩም ዕድል የሰጣቸው በመሆኑ መቸገራቸውን ይገልጻሉ፡፡

በዚህ አሠራር ተጎጂ መሆናቸውን የገለጹ አንድ ባለኢንዱስትሪ እንዳመለከቱትም ለኢንዱስትሪያቸው የጥሬ ዕቃ ለመግዛት መጀመርያ ኢንቮይሱ የገባለት የውጭ ኩባንያ መለወጥ አይችልም የሚለው አሠራር በተሻለ ዋጋ ከሌላ ኩባንያ ለመግዛት የነበራቸውን ዕድል አሳጥቷቸዋል፡፡ ምርጫ ስላልነበራቸውም ጥሬ ዕቃውን በውድ ዋጋ ለመግዛት መገደዳቸውን በመጥቀስ መንግሥት ይህንን አሠራር ማስተካከል እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡

ባለኢንዱትሪው ኤልሲውን ከፍቶ የውጭ ምንዛሪውን ለማግኘት ከሦስት እስከ ስድስት ወሮች ስለሚፈጅ አቅራቢዎቹ ቀድመው ከሰጡት ዋጋ በላይ ዋጋ እየጠየቁበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ገዢ ኩባንያዎች ግን ዋጋው ቢለወጥም እንኳን ምርቱን ሊያስገቡ የሚችሉት በተፈቀደላቸው የውጭ ምንዛሪ መጠን ብቻ በመሆኑ በዋጋ ለውጡ ምክንያት የምርት መጠኑን ቀንሰው እንዲገዙ እያስገደዳቸው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በተሻለው ዋጋ እንግዛ ቢሉ ደግሞ እንደገና ወረፋ መጠበቅ ስለሚኖርባቸው በውድ ዋጋ መግዛት እንደመረጡ አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ዘግይቶ መፈቀዱና አዲሱ አሠራር ያስከተለባቸውን ችግር ያብራሩት ሌላ ነጋዴ ደግሞ የውጭ ምንዛሪው ከመፈቀዱ ከ20 ቀን በፊት ኩባንያው ዋጋውን ያስወድዱብናል ብለው በመፍራት ዋጋውን እንዲያስተካክልላቸው ሲጠይቁ  ዋጋው እንደጨመረ ይገለጽላቸዋል፡፡

ኤልሲ ሲከፍቱ ከውጭ ለማስገባት ያቀዱትን ጥሬ ዕቃ አቅራቢው ኩባንያ በወቅቱ ተሰጥቷቸው የነበረው ዋጋ በአንድ ቶን 1,190 ዶላር ነበር፡፡ የውጭ ምንዛሪው ሲፈቀድ ግን ዋጋው 1,310 ዶላር እንደደረሰ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በዚህ ዋጋ መግዛት ባያወጣም መግዛት ግድ ነበር፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹በወቅቱ ግን የተሻለ ዋጋ የሚያቀርብልን ሌላ ኩባንያ ብናገኝም ከሌላ ኩባንያ ለመግዛት አዲሱ አሠራር የሚከለከል በመሆኑ በተወደደ ዋጋ ገዝተናል፤›› ብለዋል፡፡  ኤልሲው ተከፍቶ እስከተከፈቀደበት ጊዜ ድረስ ዋጋው በዚህን ያህል ልዩነት ማሳየቱም በአንድ ቶን ተጨማሪ ወደ 120 ዶላር መክፈላቸውንና ከአጠቃላይ ግዥውም ተጨማሪ 79,360 ዶላር መክፈላቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህ አሠራር ባይኖር ግን ኩባንያዎች ይህንን ያህል ወጪ ሳያወጡ በተሻለ ዋጋ ምርቱን ይገዙ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመንግሥትም ጭምር አመልክተን መፍትሔ አላገኘንም የሚሉት እኚሁ ነጋዴ ኤልሲ በተፈቀደበት ወቅት ያገኘነው አነስተኛ ዋጋ ከቀድሞው ኢንቮይስ ጋር በማያያዝ በተሻለው ዋጋ እንድንገዛ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አለማግኘቱን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ይህም በመሆኑ በአንድ ዙር ግዥ ብቻ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ወጪ አስወጥቶናል፡፡ አገሪቱም ያላግባብ የውጭ ምንዛሪ እንዲባክን አድርጓል፤›› በማለት ችግራቸውን አስረድተዋል፡፡ ይህ ችግር የብዙዎች ቢሆንም የኢትዮጵያ ኬሚካል ውጤቶች አምራቾች ዘርፍ ማኅበር የችግሩን አሳሳቢነት በመጠቀስ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ለብሔራዊ ባንክ አቤት ብሏል፡፡ ማኅበሩ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የላከው ደብዳቤ በውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ላይ ስላጋጠመ ችግር መፍትሔ ሊሰጥበት እንደሚገባም አመልክቷል፡፡ እንደ ማኅበሩ ደብዳቤ በሚፈቀደው የውጭ ምንዛሪ አፈጻጸም ላይ ሁለት ፈታኝ ጉዳዮች የማኅበሩን አባላት እያጋጠማቸው ነው፡፡ ያለውን ችግር የሚያሳይ አባሪም አያይዟል፡፡

በደብዳቤው የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ቀደም ሲል በንግድ ባንኮች ተራ ለመጠበቅ ከሚገባው ዋጋ ማቅረቢያ ኢንቮይስ በስተቀር ምንዛሪው በሚፈቀድበት ወቅት ከአዲስ አቅራቢ (ዝቅተኛ ዋጋ) ኢንቮይስ ማቅረብ ተቀባይነት ማግኘት አለመቻሉ አንዱ ችግር መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ሁለተኛው ችግር ደግሞ ተራ ለመያዝ ባንክ ከገቡት የጥሬ ዕቃ ዝርዝር ውስጥ እንደወቅታዊነቱና እንዳስፈላጊነቱ አቀያይሮ ለመጠቀም የሚያስችል አሠራር መመርያ ለንግድ ባንክ መድረስ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ አላስፈላጊ ወጪና አገሪቱ አግባብ ያልሆነ የውጭ ምንዛሪ ወጪ እንድታወጣ እያደረገ መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡

አሁን ባለው ተጨባጥ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄው መቼ እንደሚፈቀድ ስለማይታወቅና በሚፈቀድበት ወቅት ደግሞ የጥሬ ዕቃው ዋጋ ሊጨምር ወይም ሊቀንስ የሚችል በመሆኑ አስቀድሞ በአቅራቢዎች መካከል ተገቢን ውድድር በማድረግ አሸናፊውን ድርጅት መርጦ ከአቅራቢዎች ጋር ውል ለመግባት እንዳልተቻለም የማኅበሩ ደብዳቤ ያመለክታል፡፡ ምክንያቱም ቀድሞ የሚደረገው ውል ቢበዛ ከአንድ ወር በላይ ስለማይሠራ ኤልሲው ዘግይቶ በሚፈቀድበት ወቅት ብዙ አቅራቢዎች ቀድሞ የሰጡትን ዋጋ ስለሚጨምሩ ነው፡፡ ማኅበሩ የዋጋ ውድድሩ የውጭ ምንዛሪው ሲፈቀድና ለግዥ ሲወሰን ቢካሄድ ችግሩ እንደሚፈታ እምነቱንም ገልጿል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የባንክ የሥራ ኃላፊዎች የብሔራዊ ባንክን መመርያ እያስፈጸሙ ቢሆንም፣ አሠራሩ ነጋዴዎች ላይ ችግር መፍጠሩን ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ በሌላ በኩል ግን አሠራሩ የተለወጠው ማጭበርበሮችን ለመቀነስ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች