Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  በድጋሚ ለጨረታ የቀረበው የከብቶች ሀሞት ጠጠር ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣቱ ተሰማ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በቁጥጥር ሥር ያዋለውና 11 ኪሎ ግራም የሚመዝን የከብቶች የሀሞት ጠጠር፣ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት በጨረታ መሸጡ ተሰማ፡፡

  ጨረታው ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፣ ገዥውም የኤክስፖርት ፈቃድ በማውጣት የሀሞት ጠጠር ወደ ቻይና ለመላክ እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ ሁለት ግለሰቦች መካከል አቶ ሔኖክ ተሾመ ጨረታውን ማሸነፋቸው ታውቋል፡፡ 

  ወደ ውጭ ኤክስፖርት ስለመደረጉም ሆነ የቱን ያህል ዋጋ እንደሚያወጣ መንግሥት ሳያውቀው የቆየው የእንስሳት የሀሞት ጠጠር (ወርቅ) የሚያስገኘውን አገራዊ ጠቀሜታ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ በመሄድ ማስረዳታቸውንና መንግሥት እንዲያውቀው ማድረጋቸው የሚነገርላቸው እኚሁ ግለሰብ፣ በዓለም አቀፍ ገበያዎች የእንስሳት ሀሞት ጠጠር ያለውን የገበያ ድርሻ በተለይም በቻይና ያለውን ሰፊ ተቀባይነት ለመንግሥት በማሳወቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

  ከከብቶች ሀሞት ውስጥ የሚገኘውንና ውድ ዋጋ እንደሚያወጣ የሚነገርለትን ጠጠር በድብቅ ከአገር ሊያስወጡ የሞከሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ሰሞኑን ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በጨረታ የሸጠው 11 ኪሎ ግራም የሀሞት ጠጠር፣ በጥራት ደረጃው መሠረት በሁለት መደብ ተከፍሎ በጨረታ መሸጡ ታውቋል፡፡

  ቀና በሆኑ ግለሰቦች ጥቆማ አማካይነት እንደተደረሰበት የተገለጸው የሀሞት ጠጠር፣ ዲኤችኤልን ጨምሮ በተለያዩ ዘዴዎች ከአገር በድብቅ ሊወጣ ሲል መያዙን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ እንደ ምንጮች ማብራሪያ፣ አገሪቱ ከከብቶች የሚገኘውን የሀሞት ጠጠር የሚመለከት ምንም ዓይነት ገዥ ሕግ የሌላት በመሆኑ እስካሁን ድረስ ጥቅሙ ሳይታወቅ ነበር፡፡ ይሁንና አንድ ግራም የሀሞት ጠጠር እስከ 25 ዶላር በማውጣት በዓለም ገበያ ሲሸጥ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ገበያው ተቀዛቅዞ ወደ 15 ዶላር ዝቅ ማለቱን ምንጮች አብራርተዋል፡፡

  በግራም ይህንን ያህል የሚያወጣው የሀሞት ጠጠር፣ በተለያዩ መንገዶች ከአገር ሲወጣ ቆይቶ በቅርቡ በተደረገ የሕግ ማስከበር ክትትል ግን በአንድ ቻይናዊና በኢትዮጵያውያን አማካይነት በስውር እንዲወጣ ሊደረግ ሲል ተይዟል፡፡ ከተያዘው የሀሞት ጠጠር ውስጥ 11 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ግንቦት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. በቦሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አማካይነት ለጨረታ ቀርቦ ነበር፡፡ በመሆኑም አራት ያህል ተጫራቾች በተሳተፉበት ጨረታ ከ14 ዶላር ጀምሮ እስከ 16 ዶላር የሚደርስ ዋጋ ሊቀርብ መቻሉ ታውቋል፡፡ ይሁንና በዚህ የመጀመሪያው ዙር ጨረታ የተሰጡ ዋጋዎችና ገዥዎች ሊቀርቡ ባለመቻላቸው በድጋሚ ጨረታ ሊወጣ መቻሉ ተሰምቷል፡፡

  በቦሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሥራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ገብረ ሕይወት ገብረ ሥላሴ ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት፣ ለጨረታ በቀረበው የከብቶች ሀሞት ጠጠር ተወዳዳሪዎች ቀርበው ተጫርተዋል፡፡ ይህም ሆኖ እስካሁን በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የታወቁና ፈቃድ ኖሯቸው ወደ ውጭ ኤክስፖርት የሚያደርጉ ሁለት ድርጅቶች ብቻ መሆናቸውን አቶ ገብረ ሕይወት ገልጸዋል፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ስለሀሞት ጠጠር ያን ያህል ግንዛቤ እንዳልነበረና የኤክስፖርት ጥቅሙም ብዙ የታወቀ እንዳልነበር አልሸሸጉም፡፡

  ከከብቶች የሀሞት ከረጢት ውስጥ የሚገኘው ጠጠር በአብዛኛው የዱቄት ወርቅ ባህርይ እንዳለው ይነገርለታል፡፡ ከወርቅነቱ ባሻገር ግን የተለያዩ ውድ ጌጣጌጦችን ለመሥራት፣ እንዲሁም ለባህላዊ መድኃኒት መቀመሚያነት የሚያገለግል የማዕድን ይዘት ያለው ነው፡፡

  በዓለም ገበያ በሰፊው ግብይት የሚፈጸምበት የሀሞት ጠጠር፣ በተለይ በቻይናውያን የባህል ሕክምና መስክ ሰፊ ተፈላጊነት ያለው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት  ተከትሎም ከፍተኛ መጠን ያለው የከብቶች የሀሞት ጠጠር ወደ ቻይና ከተለያዩ አገሮች እየተላከ ይገኛል፡፡

  ከፍተኛ የጥራት ደረጃ እንዳለው የሚነገርለት ከቀንድ ከብቶች በተለይ ከበሬና ከላም የሚገኘው የሀሞት ጠጠር ሲሆን፣ በቻይና የሚገኙ ቄራዎች ሠራተኞቻቸው የሀሞት ጠጠር እንዳይሰርቋቸው በማሰብ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርጉበት ሀብት መሆኑም ይነገራል፡፡

  መንግሥት ግንዛቤው እንዲኖረውና ሕጋዊ ግብይት እንዲካሄድበት መንገዱን የጠረጉ ግለሰቦች ባደረጉት አስተዋጽኦ፣ ከአገር ሊወጣ ሲል የተያዘውን የሀሞት ጠጠር ደብቀው ሊያስወጡ ነበር ባላቸው ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ የመሠረተው ዓቃቤ ሕግ፣ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶታል፡፡ የተያዙት ተጠርጣሪዎችም በመጪው ሐምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በከፍተኛው ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት እንዲቀርቡ ቀጠሮ መሰጠቱ ታውቋል፡፡

   
   

   

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች