Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፓርላማው የካርቱምን የንግድና ኢንቨስትመንት የትብብር ስምምነት አፀደቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ስምምነቱ ከሱዳን ጋር የባቡር ኔትወርክ ዝርጋታና የ230 ኪሎ ቮልት የኃይል ትስስር ያካትታል

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና በሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር በ2006 ዓ.ም. በካርቱም ተደርጎ የነበረውን የንግድ፣ የኢኮኖሚና የቴክኒክ ዘርፍ የትብብር ስምምነት ሰኔ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. አፀደቀ፡፡

ኢትዮጵያና ሱዳን ለበርካታ ዓመታት የነበራቸውን የኢኮኖሚ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ቁርጠኝነታቸው ያሳዩበት ነው የተባለው ስምምነት፣ በንግድና በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመተባበር እንዲችሉና መሰናክሎችን በማስወገድ ሕዝቦቻቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ከማፅደቂያው ረቂቅ አዋጅ ጋር ተያይዞ የቀረበው አባሪ ሰነድ ያስረዳል፡፡

በስምምነቱ የመጀመሪያ አንቀጽ መሠረት በሁለቱ አገሮች ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማጠናከር የተለየ ቦታ የተሰጣቸው አራት ዋና ዋና ዘርፎች ተለይተው ተቀምጠዋል፡፡ እነዚህም የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም፣ የአዕምሮ ንብረት መብቶች፣ የኃይል መሠረተ ልማት፣ የማዕድንና የውኃ እንዲሁም የግብርና፣ የአየር ንብረትና የደን የሚሉ ዘርፎች ተብለው ተዘርዝረዋል፡፡

በእያንዳንዳቸው ዘርፎችም በርከት ያሉና ሁለቱ አገሮች በጋራ የሚተገብሯቸው ንዑስ ዘርፎችም ተዘርዝረዋል፡፡

የሁለትዮሽ ንግዱ እንዲጠናከርም አገሮቹ በጋራና ንግድ ማኅበራቸው አማካይነት የንግድ ሚሲዮኖች ማቋቋም እንዳለባቸው በስምምነቱ ተገልጿል፡፡

ምርቶችን መለዋወጥን በሚመለከትም የዕውቀት ልውውጥ እንደሚከናወንና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው የጉምሩክ ኮዶችን በመጠቀም፣ የዕቃዎች ስያሜና የቀረጥ አመዳደብ ላይ የተሻለ ስምምነት እንደሚኖርም ተመልክቷል፡፡

ከንግድ ልውውጡ ጋር በተገናኘም አንድ የድንበር ማቆሚያ ሥፍራ በመፍጠር የሰዎች፣ የሸቀጦችና የአገልግሎቶች እንቅስቃሴዎች ማሳለጫ ስልት ማመቻቸት እንደሚያስፈልግም በስምምነቱ ተጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም ባለቤትነታቸው አገር በቀል የሆኑ የንግድ ባንኮችን በመምራት በሁለቱ አገሮች መካከል ግንኙነት መፍጠርን የተመለከቱ ድንጋጌዎች በስምምነቱ ሰፍረዋል፡፡

ከንግዱ ግንኙነት ባሻገር ተዋዋይ ወገኖች ባላቸው የውስጥ ሕግ መሠረት አፋጣኝ የአዕምሮ ንብረት መብቶችን ማጠናከሪያና መቆጣጠሪያ ማዕቀፎችን በመፍጠር፣ በስምምነቱ ውስጥ የተዘረዘሩ የትብብር ዘርፎችን በሚመለከት የአዕምሮ ንብረት መብቶችን ማስፈጸም እንዳለባቸው በስምምነቱ አንቀጽ 4 ተደንግጓል፡፡

በዚሁ ስምምነት አንቀጽ 5 ውስጥ በኢነርጂ፣ በመሠረተ ልማት፣ በማዕድንና ውኃ ዘርፎች ሁለቱ በጋራ የተስማሙባቸው የትብብር ሥራዎች የተደነገጉ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ከአየር ንብረት ጋር ተስማሚ የሆነ ተተኪ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል የልምምድ ልውውጥ ማድረግ አንዱ ነው፡፡ ከግንባታ ስምምነት ጋር የተያያዙ የሕግ ጭብጦችን በመፍታት ሁለቱ አገሮች የ230 ኪሎ ቮልት የኃይል ትስስር ለማድረግ የደረሱበትን ስምምነት ተግባራዊ ማድረግም የስምምነቱ አካል ነው፡፡

ስምምነቱ ሁለቱን አገሮች በባቡር ለማስተሳሰር በጋራ እንደሚሠሩና የሱዳንን ወደብ ለመጠቀም የሚቻልበትን ሁኔታ በተመለከተም አካቷል፡፡

በቱሪዝም ዘርፎች በጋራ የማስተዋወቅ ሥራዎች፣ የዘርፉን ኢንቨስትመንት ማሳለጥ፣ የሥልጠናና የአቅም ግንባታ ልውውጥ ስለማጠናከር፣ አገሮች ባላቸው የውስጥ ሕጎች መሠረት የቱሪስት መኪኖች ወደ ቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ያለገደብ እንዲንቀሳቀሱ ስለመፍቀድና ድንበር ተሻጋሪ ብሔራዊ ፓርኮችን መጠበቅና መከላከል የመሳሰሉ የትብብር ንዑስ ዘርፎችም ተካተዋል፡፡

ቀደም ብሎ በዝርዝር ዕይታ ረቂቅ አዋጁ የተመራላቸው የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አዋጁ የሁለቱን አገሮችና ሕዝቦቻቸውን የሚጠቅምና ግንኙነታቸው እንደሚጠናከር በማመናቸው ኮሚቴዎቹ ሙሉ ድጋፍ እንደሰጡት ተገልጿል፡፡ ይህንን ከግንዛቤ ያስገባው ፓርላማ ረቂቅ አዋጁን በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች