በያመቱ በቋሚነት እንደሚካሄድ የተገለጸው የሪል ስቴት ዓውደ ርዕይ፣ ዘንድሮ በጅማሬው በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ እንዲዘጋጅ መታቀዱንና በንግድ ትርዒቱም አምስት ባንኮችን ጨምሮ 22 የሪል ስቴት አልሚዎች እንዲሳተፉ መጋበዙን የዓውደ ርዕዩ አዘጋጅ 251 ኮሙዩኒኬሽንስ ኩባንያ አስታውቋል፡፡
ኩባንያው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ይፋ እንዳደረገው፣ በመጪው መስከረም ወር ሊካሄድ የታቀደው የሪል ስቴት ዓውደ ርዕይ በዳያስፖራው ማኅበረሰብ ዘንድ ትልቅ ጥያቄ ለሆነው የቤት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መድረክ እንዲፈጥር ለማስቻል ታስቦ መዘጋጀቱን የ251 ኮሚዩኒኬሽንስ መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አዲስ ዓለማየሁ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
አቶ አዲስ እንዳብራሩት፣ በያመቱ እንዲካሄድ የታሰበው የሪል ስቴት ዓውደ ርዕይ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት በብዛት በሚገኙባቸው አገሮች ተዘዋውሮ የሚካሄድ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የዋሺንግተኑ መሥራችና የሁለት ቀናት ዓውደ ርዕይ ላይ ለመሳተፍ ከኢትዮጵያ የሚያቀኑት ባንኮችና ሪል ስቴቶችን ጨምሮ እስከ አምስት ሺሕ የሚደርሱ የዋሺንግተንና የአጎራባች ከተሞች ነዋሪዎች እንደሚገኙበት አቶ አዲስ ገልጸዋል፡፡
በአሜሪካው የዓውደ ርዕይ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው የተጠቀሱት አምስቱ ባንኮች ዘመን፣ ዓባይ፣ ቡና፣ አዋሽ እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆናቸውን አቶ አዲስ ጠቅሰዋል፡፡ በዓውደ ርዕዩ የሚሳተፉት የሪል ስቴት አልሚዎችም እስካሁን ካሳዩት የሥራ አፈጻጸም አኳያ ተመርጠው ለጉዞ መጋበዛቸውን ተናግረዋል፡፡ የባንኮቹ ተሳታፊነት ሁለት ገጽታ እንደሚኖረው የጠቀሱት አቶ አዲስ፣ አንደኛው ባንኮቹ በብድር አቅርቦት እንዲሳተፉ የሚያስችላቸውን ዕድል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል፡፡
በዚህም ባንኮቹ ብድራቸው እስኪመለስ ድረስ የቤት ገዥዎችን ቤቶች በእኩል ባለቤትነት በመያዝ ለብድሩ ማስያዣነት እንደሚያውሉት፣ ይህም በቤት ገዥዎችና በአልሚዎች መካከል መተማመንን ለመፍጠር እንደሚያግዝ አብራርተዋል፡፡ በሁለተኛነትም ባንኮቹ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ስለሚሆናቸው ጭምር በዓውደ ርዕዩ ለመሳተፍ መሻታቸው ከዚህም አኳያ ጠቀሜታ ስላለው መሆኑም ተብራርቷል፡፡
ይሁንና በአገሪቱ በሪል ስቴት ግንባታ ዘርፍ እየተሳተፉ ከሚገኙት ኩባንያዎች ውስጥ በርካቶቹ በተለያዩ ምክንያቶች ለቤት ገዥዎች ቤት ማስረከብ ተስኗቸው ቆይተዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉትም ከቤት ገዥዎች የሰበሰቡትን ገንዘብ ይዘው የጠፉና የፈረሱ ኩባንያዎች ሆነዋል፡፡ በዚህ ሰበብ ጉዳት ከደረሰባቸውና ገንዘባቸውን ውኃ ከበላባቸው መካከል አብዛኞቹ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ናቸው፡፡
ይህ መሆኑ ከሪል ስቴት አልሚዎችና ገንቢዎች ባሻገር መንግሥትን በተጠያቂነት የሚተቹም አሉ፡፡ ምክያቱም መንግሥት የሪል ስቴት ዘርፉን በአግባቡ መቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘጋ ልቅ ስለተወው፣ ገንዘብ ሳይኖራቸው ከገዥዎች ገንዘብ ሰብስበው እልም የሚሉ፣ መሬት ሳይኖራቸው በጨበጣ የሚንቀሳቀሱ በርካታ ሪል ስቴት አልሚዎች ታይተዋል፡፡
እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ የሚገኘውን የቤት ልማት ዘርፍ ማስተዋወቁ ለምን እንዳስፈለገና ተዓማኒነትስ ይኖረዋል ወይ ተብለው ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አዲስ፣ ምንም እንኳ የሪል ስቴት ዘርፍ የሚገኝበት ሁኔታ ብዙም አስደሳች ባይሆንም በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለው የቤት ፍላጎት ግን ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን ፍላጎት ለማስተናገድ የሚያስችል ሥራ መሥራት ግድ እንደሚል አብራርተዋል፡፡
በዚህ መነሻነትም እስካሁን ከሚንቀሳቀሱ የሪል ስቴት አልሚዎችና ገንቢዎች ውስጥ በታማኝነት ቤት መገንባት የቻሉና ያስረከቡ፣ እየዘገቡም ጭምር ቢሆን እየሠሩ ያሉ ኩባንያዎች በዓውደ ርዕዩ ተሳታፊ እንደሚደረጉ ገልጸዋል፡፡ ለተሳትፎ የምርጫ መሥፈርት መሆኑም የተገለጸው ይኸው መሆኑን የተናገሩት አቶ አዲስ፣ እንደ ከዚህ በፊቱ እንዲሁ ልንገነባ ነው ልንሠራ ነው ስላሉ ሳይሆን መሬት ላይ የሚታይ ሥራ የሠሩት ኩባንያዎች ብቻ እንዲሳተፉ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
በያመቱ እንደሚሰናዳ የተገለጸው የሪል ስቴት ዓውደ ርዕይ፣ የጀመሪያውን በአሜሪካ ለማካሄድ የተቆረጡት ቀናት ከመስከረም 7 እስከ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ያሉት ናቸው፡፡ ከአሜሪካው ዓውደ ርዕይ ቀጥሎ በካናዳ፣ በእንግሊዝና በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች እንዲሁም በእሥራኤል እንደሚካሄድ አቶ አዲስ ገልጸዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ከናይጄሪያ በመቀጠል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በአሜሪካ ይኖራሉ፡፡ በጠቅላላው ከሁለት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በመላው ዓለም እንደሚኖሩ ሲገመት ከዚህ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚቆጠሩት በሰሜን አሜሪካ እንደሚገኙ ይገመታል፡፡