Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጨለማ ሲለመድ ብርሃን ይመስላል!

እነሆ መንገድ ከፒያሳ ወደ መገናኛ ልንጓዝ ቦታ ቦታ ይዘናል። ‹‹ኧረ ሞልቷል እንቀሳቀስ?›› ይላል መጨረሻ ወንበር ላይ የቸኮለ። ‹‹ማን ይሰማሃል? ወያላውም ሾፌሩም ወሬ እያዩ ነው፤›› አለ ሦስተኛው ረድፍ የተቀመጠ ጎልማሳ። ጉንጮቹና ግንባሩ ሽርክት በሽርክት ነው። ‹‹እኛ አገር ብቻ ነው እኮ ነው ወሬ የሚታየው። አይገርማችሁም? ሌላው ዓለም ቢለከፍ ቢለከፍ የወሬን የመወራት ተፈጥሯዊ ፀባይ ወደ መታየት አልቀየረውም። እኛ ከኋላቀርነት ወደ ሥልጣኔ ማማ እንደመሸጋገር ወሬን ከማውራት ወይም ከመስማት ወደ መታየት እናሻግራለን፤›› ይላል ከጎልማሳው አጠገብ ቀይ ጃኬት የለበሰ። ‹‹እውነት ብልሃል ጃል። ለዚያ ይሆን እንዴ የመተካካትና የሽግግር ዕቅዱ አየር ላይ የቀረው?›› ስትለው መጨረሻ ወንበር ሂጃብ የጠመጠመች ፀዳል፣ ‹‹እናንተ ሰዎች ምን ነክቷችኋል? ሮም እኮ በአንድ ጀንበር አልተገነባችም። ምነው ትዕግሥት ቢኖረን?›› ብሎ ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየመ ፀጉረ በራ ጎልማሳ ኮስተር አለ።

‹‹ምናለበት ግን አንዳንዱ ሰው ጨዋታ ካልቻለ ዝም ቢል? እኛ ተረቱና ታሪኩ ጠፋን እንዴ? ደርሶ የካድሬ ስብሰባ ያስመስልብናል፤›› ብሎ መጨረሻ ወንበር ከጓደኛው ጋር የተቀመጠ ልጅ እግር ሲንሾካሾክ ይሰማል። ‹‹ኧረ አደርን!›› አለ ደግሞ ጋቢና የተሰየመ ወጣት ለሾፌሩና ለወያላው እጁን እያውለበለበ። ‹‹ማደሬ ነው እኔስ ማደሬ ነው’ ብለህ መዝፈን ነዋ። የዘንድሮ ብሶትና ቅሬታ ወይ በዘፈን ወይ በስካር ካልሆነ አብራጅ የለውም፤›› አሉ አጠገቡ የተቀመጡ ተጨዋች አዛውንት። ‹‹ምን እያዩ ነው?›› ይጠይቃል አንዱ። አንድ ምስኪን መንገዱ ላይ ተንጋሎ ወድቆ ውኃ ይደፋበታል። ‹‹መኪና ገጭቶት ሄደ?›› ወያላው ከች አለ። ‹‹መኪናው ሰው አልባ ነው? እንዴት ገጭቶት ይሄዳል?›› ቢሉት አዛውንቱ ራሰ በራው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ዘንድሮ ሰውን የሚነዳ እንጂ ሰው የሚነዳው ነገር እኮ ተመናምኗል፤›› አላቸው። የሚነዳን ስሜትና ሐሳብ አልበዛም ግን?

ሾፌራችን ሞተር አስነስቶ መዘወር ጀምሯል። ቆይተው ቆይተው አዛውንቱ፣ ‹‹ለነገሩ ምን ሰው አለ?›› አሉ። ‹‹ምነው አባት? ይኼ ሁሉ የሚያዩት ሰው አይደለም እንዴ?›› አላቸው ከጎናቸው። ‹‹ታዲያ በተራመደ ነው አንዴ? ወይስ በተነፈሰ ብቻ ይመስልሃል? ዕፅዋትም እኮ ይተነፍሳሉ። ያውም ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ እያስገቡ ኦክስጂን እያስወጡ። ለመውጣት ለመውረድ አውሬውን ትተህ ሩቅ ሳትሄድ ሠፈር ያለ የጣራ ድመት ሲባክን ውሎ ሲያደር ማን ይደርስበታል? መጀመሪያ የሰው ሰው የመባሌ መለኪያው ምንድነው ብለህ ጠይቅ፤›› አሉት ቁጣ ቁጣ እያሉ። ‹‹ለምንስ መሥፈርት ይኖረዋል ቀድሞ ነገር ብዬ መጠየቅ እችላለሁ?›› አለ ወጣቱ ተለሳልሶ። ‹‹ይኼውልህ አሁን ልብህን አየሁት አየህ። ግድ የለም ጠይቅ። የተቸገርነው አንሻፎም አንጋዶም ቢሆን የሚጠይቀን ሰው ነው እኮ፤›› ብለው በረጂሙ ተነፈሱ።

ጥቂት አሰብ አደረጉና ‹‹ይኼውልህ ጉዳዩ የመሥፈሪያ መኖር አለመኖር አይደለም። ሰውን ሰው የሚያስብለው አንዱ ነገር መናገሩ፣ ማሰቡ፣ በእጆቹ ጥጥ ፈትሎ ሸማ መልበሱ አይደለም። እንዲያው በእሱ ብቻ ከሄድክ ሳይፈትሉ ሳይሸምኑ የምድር፣ የባህሩ ፍጥረታት ከእኛ በላይ የለበሱ ናቸው። ሰውን የሚለየው ጠያቂነቱ ነው። ለምን? የሚል እሱ ሰው ነው። ይኼው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ቲማቲም ከ16 ብር 28 ብር ገባ። ለምን ያለ አለ? ምናልባት አንተ አሁን ቲማቲም ብዙም ስለማንወድ ይሆናል? ትለኝ ይሆናል። የዚህ ትውልድ ትልቁ ችግሩ ውስጡ የሚብላላውን ጥያቄ በቅጡ ሳያዳምጥ ለመልስ መቻኮሉ ነው፤›› ብለው ዝም ሲሉ ከጎኔ የተሰየመው ራሰ በራ ጎልማሳ፣ ‹‹ስለ አንድ ኪሎ ቲማቲም ዋጋ ብቻ እያሰብ ከሆነ ወራጅ አለ ብትል ይሻልሃል፤›› ብሎኝ ይስቃል።

ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላው መሀለኛው ረድፍ ሦስተኛ ደርቦ ካስቀመጣት ጥቁር ሻርብ የተከናነበች ተሳፋሪ ጋር የሆነ ነገር ይባባላል።  ‹‹…  ለምን በሊሞዚን አትሄጂም ታዲያ? ሊሞዚን ላስመጣልሽ? ቁጥራቸው አለኝ እንኪ ሴቭ አድርጊው፤›› እያለ ብዙ የማይባል ነገር ሲላት ባለቀዩ ጃኬት፣ ‹‹ለምን ትሰድባታለህ? እኛ እኮ ታሪፉን ከፍለን ነው የምጓዘው። ገንዘባችንን ከፍለን ነው የምንሄደው። ገባህ? ቀስ ብሎ እንዲነዳ ሾፌሩን ንገረው አለችህ። ሌላ ምን አለችህ? ሊሞዚን ምናምን ምን ትርፍ ነገር ያስፈልጋል?›› አለው ግንፍል ብሎ። ‹‹ተረጋጋ። ሌላ ነገር ከፈለክ በግልጽ ተናገር። ደግሞ የምትጎዳው አንተ ነህ፤›› አለ ወያላው በተፈጥሮው የተቆጣጠረ ሉጫ ፀጉሩን እየፈታተለ። ‹‹ምን አልክ? ታውቀኛለህ?›› ቅብጥርሶ ግርግር ሲጀመር እንደ ወትሮው አንተም ተው አንተም ተው ባይ ጠፍቶ በስድብ ሲሞላለጩ እስከ ጥግ ሰማን።

ባለጃኬቱ ወጣት ከወያላው ይልቅ ዝም ባልነው ተሳፋሪዎች ተናደደ። ‹‹እናንተስ እንዲህ ያለ ብልግና ሲናገር ዝም የምትሉት ለምንድነው? ኢትዮጵያውያን አይደለንም እንዴ? ይኼኔ ፌስቡክ ላይ ሼር አድርጌው ቢሆን እዚሁ አጠገቤ ተቀምጣችሁ ቃል ያልተነፈሳችሁ በኮሜንት ታጨናንቁኝ ነበር፤›› ሲል ራሰ በራው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹በእንቁላሉ ጊዜ ያልተቆነጠጠን ምንም ብትለው ዋጋ የለው ብለን ነው ወንድሜ። አንዴ የተጣመመን ዛፍ  ምን ታደርገዋለህ?›› አለው። ‹‹ይህቺ እህታችን የማንኛችንም እህት ልትሆን ትችላለች፡፡ ያኔ ዝም አንልም አይደል? ኧረ ቆይ እንዲህ ሁሉን ነገር ፈርተን እጃችንን ጠምዝዘው የያዝነውን ሲነጥቁን እስካልነኩኝ ድረስ እስከ ማለት የደረስንበት ሚስጥር ምንድነው?›› ሲል አሁንም ታክሲዋ በዝምታ ተሞልታ ጉዞዋን ቀጠለች። አላስችል ቢለው ወጣቱ የጃኬቱን ቻርኔላ ሸምቅቆ ወራጅ ብሎ ወረደ። ምናልባት ወያላው ሲወርድ የሆነ አገር ኤምባሴ ደጃፍ ላይ ወርዶ ቢሆን ሁኔታው የቪዛ ማመልከቻ የሚያጽፍ ነበር። ‘አገሬን የአገሬ ሰው ካስለቀቀኝ ቆየሁ አለ’ ጉዱ ካሳ!

ወያላው ፀብ ፀብ ከሸተተው በኋላ እጁ ፀጉሩን ከመቆጣጠር አላረፈም። ምናምን የመሰለ ፀጉሩን በጎነጎነበት እጁ መልሳችንን መዳፋችን ላይ ይወረውራል። አዛውንቱ ከጋቢና ወርደው ከሕዝብ ጋር ልሙት እያሉ የሾፌሩን አነዳድ እያሽሟጠጡ አኩርፎ የወረደውን ወጣት ሥፍራ ያዙ። ወዲያው ታክሲያችን ቆማ በጎደለ ተካች። ተተኪው ጮክ ብሎ ስልክ ያወራል። ‹‹የግንባታ ፈቃድ ለማውጣት ይኸው ስምንት ወር ይፈጃል። ቆይ እኔን ምን አድርግ ትሉኛላችሁ? በዚያ ላይ ነጋ ጠባ ስብሰባ ነው። እኛም ማማረር አልሰለቸን እነሱም መሰብሰብ አልታከታቸውም፤›› ይላል።

ይኼን እየሰማ ተሳፋሪው እርስ በእርሱ ብሶቱን በተናጠል መንሾካሾክ ቀጠለ። አንዱ ይላል፣ ‹‹ጠዋት ከእንቅልፍህ ስትነሳ የሆነ ነገር ጠፍቶ ይጠብቅሃል። ወይ መብራት ወይ ውኃ ወይ ኮኔክሽን ወይ ታክሲ …›› እያለ ሲቆጥር፣ ‹‹ዋናው አንተ ጠፍተህ አለማደርህ ነው፤›› ይለዋል የእንስት ድምፅ። ‹‹የባሰ አታምጣ›› ብሎ ሳቀ። ወዲህ ራሰ በራው ጎልማሳ ደግሞ፣ ‹‹ሰው በሥራ ይዝላል እኛ በትችት ብቻ ጉልበታችን ያልቃል። ያደለው የበላውን ምግብ በላብ ያቃጥላል እኛ በሂስ እንመነምናለን፤›› ሲለኝ ከወደ ጋቢና ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም፤›› አለው። ‹‹በትግል መስሎኝ ቀን የወጣልን?›› ሲል ስልኩን ዘግቶ አጠገቡ የተቀመጠው፣ ‹‹ወንድሜ አንዳንዴ ውሸት ሲለመድ እውነት ይመስላል፤›› እያለ ቀልዱን ትቶ ማምረር ጀመረ። እንኳንም የቀንና ማታ ቆጣሪ በሰው እጅ አልሆነ እንጂ ዘንድሮ ጥላ ቢስ ሆነን ነበር አያስብልም ይኼ?

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። አዛውንቱ በተናጠል የሚሰሙትን ቅሬታና ብስጭት ለማጠቃለል ይመስላል፣ ‹‹ሁላችሁም አንድ ዓይነት ችግር ተቸግራችሁ አንድ ዓይነት ጉድለት ጐሏችሁ ለምንድነው በተናጠል የምትሾካሾኩት?›› ብለው ሲጠይቁ አንዱ፣ ‹‹ምን እናድርግ አባት ሰውን ማመን ቀብሮ ነው ብላችሁ ያስተማራችሁን እናንተ፤›› አላቸው። ይኼኔ አንድ ተረት አመጡ። ‹‹ሦስት የተላለየ ቀለም ያላቸው ላሞች ነበሩ። አንዱ ጥቁር ሌላው ነጭ አንዱ ደግሞ ቡናማ ነበሩ። እና አንድ ቀን አያ ጅቦ ከተፍ አለባቸው። ሦስቱም ላሞች አያ ጅቦን ከሩቅ እንዳዩት ተጠራሩና አንድ ዘዴ ካልዘየድን አያ ጅቦ ተራ በተራ እያንዳንዳችንን መብላቱ አይቀርም። ምን ይሻላል? ተባባሉ። ኋላም አንድ መላ መቱ። ሦስቱም ጭራቸውን ገጥመው በሦስት አቅጣጫ እርስ በእርስ አንዳቸው የሌላውን ጀርባ ለመጠበቅ ዘብ ቆሙ። አያ ጅቦ ይኼን እንዳየ እንግዲህ እንዴት አድርጌ እንደምለያያቸው ማሰብ አለብኝ ብሎ አወጣ አወረደና ቀስ ብሎ ቡናማና ጥቁሯን ላሞች ተጠግቶ ጠላት ከሩቅ አይቶ የሚያጠቃችሁ እኮ ነጩ ላም ከሩቅ ዓይን ውስጥ ስለሚገባ ነው። እሱን አባራችሁ ለእኔ ብትሰጡኝ እናንተን የሚነካችሁ የለም ሲላቸው ወዲያው እውነት መሰላቸው። ቀስ በቀስ ሁለቱን ደግሞ አጣልቶ ሦስቱንም አንክቶ በላቸው ይባላል። እና ምን ልላችሁ ነው ቅድም ይህቺን ልጅ ወያላው ሲሰድባት አንድ ሰው ብቻ አብሯት ቆመ። አሁንም እያንዳንዳችሁ በተናጠል ቢሮክራሲውን፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦቱን፣ ሙስናውንና ሌላውን ችግር ስታማርሩ የሚያገናኛችሁ አንድ መስመር የሌለ ትመስላላችሁ። ታዲያ አያ ጅቦ ዝም ብሎ የሚያይ ይመስላችኋል? እስከ መቼ የሴረኞች መጫወቻ ለመሆን ኅብረታችንን እናውካለን?›› ሲሉ ታክሲያችን ጥጓን ይዛ ቆማለች። ‹‹የተናጠል ጉዞና የአያጅቦ ፉጨት እስከ መቼ? ጨለማም ሲለመድ ብርሃን መምሰሉ እስከ መቼ? …›› የሚሉት አዛውንቱ ነበሩ፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት