Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርታላቋ ብሪታንያ ወደ ታናሽ እንግሊዝነቷ ስትመለስ

ታላቋ ብሪታንያ ወደ ታናሽ እንግሊዝነቷ ስትመለስ

ቀን:

በአሰፋ እንደሻው (ዶ/ር)፣ ለንደን

ሰኔ 16 ቀን 2008 ) ዓ.ም. (በአውሮፓውያን አቆጣጠር ሰኔ 23 ቀን 2016) አብዛኛው የብሪትን ሕዝብ ከአውሮፓ ኅብረት አባልነት ለመውጣት የሰጠው ድምፅ በጣም አስገራሚ ነው። በትልልቆቹ ከተሞች የሚኖረው ሕዝብ (ጥቁሮችን ጨምሮ) ከአውሮፓ ጋር ለመቀጠል ፍላጎቱን ቢገልጽም ብዙኃኑ አሻፈረኝ ብሏል። ክርክሩ ከላይ ከላይ ራሳችንን በነፃነት መምራት ይገባናል፣ የአውሮፓ ማኅበር እየተጫነን እስከመቼ እንኖራለን የሚል ሆኖ በውስጡ ግን ሥር የሰደዱ ሌሎች ነገሮች አሉት (ነበሩት)።

የታላቋ ብሪታንያ አነሳስ

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንግሊዞች ደሴት ላይ በመኖራቸው ከጥንት ጀምሮ ሁልጊዜ በውጭ ኃይሎች እንወረራለን፣ እንጠፋለን፣ እንዋጣለን የሚል ሰቀቀን አዕምሯቸው ውስጥ ሰርጿል። አገሪቱን ወረው የተቆጣጠሯት የሰሜን አውሮፓ ጎሳዎች በፊት የሰፈሩትን የኬልት

ሕዝቦች (ዌልስ፣አይሮችና ስኮቶች)  አሽንፈው ስለነበር ሌላ ባለተራ ይመጣብናል የሚል ፍራቻቸው በተደጋጋሚ በተከስቱ ድርጊቶች ሥር ሰዶ ኖሯል። ሮማውያን አስቀድመው፣ ከዚያ ከሰሜን ፈረንሣይ (ኖርማንዲ) እኤአ በ1066 የተሻገረው ወራሪ፣ ስፓኞች በባህር ኃይላቸው፣ ናፖሊዮንና ሂትለር በተጠናከሩ ዘመናዊ ጦር ሠራዊቶቻቸው አማካይነት ብሪትንን ለማንበርከክ ሞክረዋል። በምላሹ ብሪትኖች ከተከታተለው የውጭ አደጋ ለመከላከል ሲሉም የባህር ኃይላቸውን ገንብተው ጭራሽ ባካባቢያቸው ብሎም ዓለም ላይ ገናና ሆኑ። በብሪትን ግዛት ፀሐይ አትጠልቅም እስከ ማለት ደረሱ።

የብሪትን  የባህር ኃይል ባለቤትነት ቅኝ ግዛቶችን ለማብጀት ከነሱም ስፍር ቁጥር የሌለው ጥሬ ሀብትና ባሪያ ወደ ደሴቲቱ ለማጋዝ፣ በእነሱም  አማካይነት ከግብርና ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ኃያልነት ለመሸጋገር በቃች። አፍሪካውያንን በተለይ በቅኝ ግዛትነት ጥሬ ሀብታቸውን ለማጋበስ ከመቻሏም በላይ ነዋሪዎቿን በባርነት እየፈነገለች ዛሬ አሜሪካ ወደ ሚባለው አገር  እያጓጓዘች ጉልበታቸውን ለጥጥና ሌላም ምርት በማዋል ውጤቱን ለራሷ ደሴት ማበልጸጊያ አድርጋለች። ከሷ ቀደም ብለው ቅኝ ግዛት ለማቋቋምና የሌሎች ሕዝቦችን ሀብት  ለመዝረፍ የሞከሩትን ስፔንና ፖርቱጋልን በልጣና ወደ ጎን ገፍትራ ፈረንሣይ እግር እግሯን እየተከተለቻት በዓለም ደረጃ የኢንዱስትሪያዊ ሽግግር ያከናወነች አገር ሆነች። ናፖሊዮን በንቀት ዓይን “የሱቅ ጠባቂዎች አገር” እንዳላት ተሸብባ ሳትቀር በንግድ መተዳደሩን አልፋ የኢንዱስትሩ አብዮት ባለቤት ሆነች። (ሟቹ አለሜ እሸቴ የመጀመርያውን አብዮት ማለትም እሳትን መጠቀም የቻሉት የኢትዮጵያውያን ቅድም አያቶቻችን ናቸው ያለውን ልብ ይሏል። ለምን ሁለተኛውን አብዮትም ከብሪትን ይልቅ እኛ ማድረግ እንደተሳነን በዚያው ማሰላሰል ይገባል።)

ብሪትን ከፈረንሣይ ጋር የነበራት ፉክክር ቀጥሎ በቅኝ ግዛት ማስፋፋቱም ሆነ በጥሬ ሀብት ማጋበሱ በኩል ግን ይበልጥ ተሳካላት። ሰሜን አሜሪካ ላይ የሃይማኖት ጭቆናን ሸሽተው የተሰደዱትንና የሰፈሩትን ዜጎቿን መረማመጃ አድርጋ ዝርያዎቿን በብዛት አጎረፈች፣ አሰማራች። ቀይ ህንድ ብለው የሰየሟቸውን ያካባቢውን ሕዝቦች እያስጨፈጨፈችም ዘሮቿን ማለትም አንግሎ ሳክሰኖችን አባዛች። ከሌሎች አውሮፓ አገሮች ሰፋሪዎች እየፈለሱ ወደ ሰሜን አሜሪካ ቢጎርፉም በብዛታቸውና የተቋቋመውን አገዛዝ እንዲሁም ሀብት በጃቸው ያስገቡት አንግሎ ሳክሰኖች ስለነበሩ፣ ሰሜን አሜሪክ እስካሁን ድረስ የእንግሊዝ ቁራሽ አካል ሆኖ ቀጥሏል። በኋላ ላይ በአውስትራሊያ፣ በኒውዚላንድ ተመሳሳይ የአንግሎ ሳክሶን ወረራና ሰፈራ ሲከናወንም የእንግሊዝ ቁራጭ አካሎች መብዛት በዓለም ላይ የአንግሎ ሳክሶንን ግዛት የቆዳ ስፋትና አቅም ከፍተኛ አደረገው። በደቡብ አፍሪካ በአጠቃላይና በሌሎች ቅኝ ግዛቶች የተደረገው ተመሳሳይ የሕዝብ ማስፈር ሙከራ ግን ሙሉ በሙሉ አልተሳካም።

ይሁንና ብሪትን በእንግሊዝ መሪነት በሄደችበትና በረገጠችበት አካባቢ ሁሉ የጥሬ ሀብት ዘረፋ ከማካሄዷ ውጪ፣ የለም መሬት ቅሚያ፣ የከተማ ርስት ግንባታ ተያይዛ ስለነበረ ቅኝ ግዛቶቹ ነፃ ከወጡም በኋላ እነዚያን ይዞታዋቿን ሳታስነካ እስካሁን ድረስ ዘልቃለች። በኬንያ፣ በዚምባብዌ፣ በዩጋንዳ፣ በሆንግ ኮንግ፣ በሲንጋፖር ስንቱ አገር ተዘርዝሮ ያልቃል ሰፋፊ ለም መሬትና የከተማ ርስት ከቅኝ ግዛትነት ዘመን ጀምሮ በብሪትን ዜጎች እጅ እንዳለ አለ። በቅኝ ግዛቶች ውስጥ በተከፈቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ተቋማት ውስጥም የብሪትን (በይበልጥም የእንግሊዝ) ዜጎች የዳጎሰ ድርሻ ነበራቸው፣ እስከዛሬም እየተንከባለለ መጥቷል፡፡

ብሪትን የባህር ኃይል አቅሟን ገንብታና በዓለም ዙሪያ አሰማርታ፣ የባዕድ (ውጭ) ሕዝቦችን ጥሪቶችና ሀብቶች በቅሚያና በንግድ እያግበሰበሰች በመሄዷ ከግብርናና ንግዳዊ ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪያዊ ኃያልነት መሸጋገሯ ለተወሰኑ ዓመቶች ከፈረንሣይ በስተቀር ተፎካካሪ የሌላት ብቸኛ የዓለም ልዕለ ኃያል እንድትመስል አድርጓት ነበር፡፡ ነገር ግን ከእንግሊዝና ከፈረንሣይ ወደ ኢንዱስትሪ መግባት ተከትለው በሁለተኛ ደረጃ ብቅ ያሉት አሜሪካ፣ ጀርመንና ሩሲያ የዓለምን የኃይል ሚዛን ከ19ኛው መቶ ዓመት ማብቂያ ወዲህ መለወጥ ተያያዙ። የእንግሊዝና የፈረንሣይ ገናናነት በአዲሶቹ የኢንዱስትሪያዊ አገሮች መፈታተንና መፎካከር ሲደርስበት ሰላማዊ ሽግሽግ ከማድረግ ይልቅ በጦርነት መጋጠምን አዘወተሩ። በፊት በፊት አንድ ለአንድ ይደረግ የነበረው የገናናዎቹ ጦርነት (እንግሊዝ ከአሜሪካ፣ ከሩሲያ፣ ከኦቶማን ቱርኮች፣ ከሰፔን እንዲሁም ከፈረንሣይ)፣ በጅ አዙርና በተዘዋዋሪ መልክ የሚከናወነውን ጨምሮ እያደር እየቀረ በቡድን መልክ ተደራጅተው ወደመጋጠም ላይ ደረሱ። ቀደም ያሉትን አናሳ መቧደኖች ትተን የመጀመርያውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተሰኙት ትንቅንቆች በዚህ አኳኋን የተከሰቱ ነበሩ። የጦርነቶቹ ቀስቃሾች (ከሞላ ጎደል አዳዲሶቹ የኢንዱስትሪ ኃያላን) ፈረንሣይና እንግሊዝ በዓለም ላይ ገንብተው ያቆዩትን የባላይነት ሽረው፣ ከሁለተኛ ደረጃነት ወጥተው ከፍ እንዲሉ፣ የእነሱንም ጥቅም የሚያስጠብቅ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ለመፍጠርና በመካከላቸው አቻነትን ለማስፈን ያለሙ ነበሩ።

የታላቋ ብሪታንያ ኃይል ማሸቆልቆል

በመጀመርያውም ሆነ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከብሪትንና አባሪዎቿ (በይበልጥ ሩሲያ፣ ፈረንሣይና አሜሪካ) ጋር የተፋለሙት ኦስትሪያ ሃንጋሪ፣ ጀርመን፣ የኦቶማን አገዛዝና በኋላም ጃፓን ከፍተኛ ወድቀትና መፈረካከስ ቢደርስባቸውም፣ ብሪትን ይኼ ነው የማይባል ኪሳራ (ዕዳ) ውሰጥ ገብታ ቀዳሚ የዓለም ኃያልነቷ ተናግቷል፡፡ ከዓመት ገቢዋ በአንደኛው ዓለም ጦርነት 150 ከመቶ በሁለኛው ዓለም ጦርነት ደግሞ 200 ከመቶ ደርሶ ስለነበር፡፡ በሌላም በኩል ከመጀመርያው የዓለም ጦርነት በኋላ ባላንጣዎቿ አሜሪካና ሩሲያ በይዞታቸው ላይ መሠረታዊ ለውጥ ተከሰተባቸው፡፡ አሜረካ በባህር ኃይሏና በኢኮኖሚዋ ከሁሉም ኢንዱስትሪያዊ አገሮች ልቃ ስትገኝ ሩሲያ በአብየት እሳት ተበልታ ወደ ሶሻሊዝም አምርታ በርካታ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮችንና ቻይናን አጋር አድርጋ፣ ከምዕራባውያን ኃያላን ጋር ታይቶ ለማይታወቅ ግብግብ ተዘጋጀች፡፡ አሜሪካ (በፕሬዚዳንት ውድሮው ዊልሰን መሪነት) የእንግሊዝና የፈረንሣይን የቅኝ ግዛቶች ወደ ነፃነት እንዲያመሩ በሰጠችው ፍንጭና ግፊት የኢንዱስትሪና የወታደራዊ ጡንቻዎቿን ተመክታ ጥላዋን በያቅጣጫው ስትዘረጋ የብሪትንን የበላይነት ሰፍራ ያላንዳች ጦርነት ለመረከብ በቃች፡፡ የግብፁ ናስር የስዊዝን ቦይ እ.ኤ.አ. በ1956 በቁጥጥር ሥር ሲያደርግ አሜሪካዎች የብሪትንና የፈረንሣይን መልሶ ማጥቃት ሙከራና መሸነፍ ሲኮንኑ በብሪትን ግዛት ፀሐይ እንደጠለቀ አበሰሩ፡፡ ጥቂት ቆይቶም የብሪትኑ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃሮልድ ማክሚላን የለውጥ ንፋስ እንደመጣ እ.ኤ.አ. በ1960 በይፋ ባወጀበት ወቅት ይኼን የብሪትንን ቦታ መነጠቅ ማወጁ ነበር፡፡

ለ400 ዓመታት በብሪትን ሲዘረፍና ሲቀጠቀጥ የኖረው የህንድ ሕዝብ ትግል አስቀድሞ ድል መቶ እ.ኤ.አ. በ1947 ነፃ ሲሆን ብሪትን እንዳለቀላት በቂ ምልክት ቢሆንም፣ ስትንገታገት በኬንያ የማኦ ማኦን እንቅስቃሴ፣ በማላያም የፋኖ ጦርነት ገጠማት፡፡ ፈረንሣይም ብትሆን በአልጄሪያው የነፃነት ትግል ተለብልባለች፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሳይቀር (እ.ኤ.አ. በ1960 ላይ) ቅኝ የሆኑ አገሮች በሙሉ ነፃ እንዲወጡ ታወጀላቸው፡፡ ሶቭየት ኅብረትና ቻይና የሚደግፏቸው የነፃነት እንቅስቃሴዎች በዓለም ዳር እስከዳር ይንፈቀፈቁ ገባ፡፡ የባሰ ሳይመጣ በሚል ብሪትንና የፈረንሣይ ቅኝ ግዛቶቻቸውን አንድ ባንድ ነፃ ለቀቁ፡፡ ብሪትን በምንተፍረት የዱሮ ቅኝ ግዛቶቿን በወዳጅነት አብረው እንዲቆዩ ተማጽና እስከዛሬ ያልፈረሰ የጋራ ጥቅም ኅብረት አቆመች፡፡

ሄዶ ሄዶ ብሪትን የዱሮውን ክብሯንና አቅሟን አጥታ እንደሌሎች የአውሮፓ አገሮችና ጃፓን ከአሜሪካ ሥር መግባቷ አልቀረም። ሁለታችንም የአንግሎ ሳክሶን ዝርያ ነን የሚለውን ትረካ ተገን አድርጋ ልዩ ዝምድና መሥርተናል እያሰኘች ብታንቧርቅም፡፡ ይኸው ዝምድና በብዙ መልክ እየተተረጎመ ውሉ የጠፋ ቢሆንም፣ አስተሳሰቡ የበላይና የበታች የሌለበት ባልደረባነት እንደሆነ ያህል ያስመስሉታል፡፡ በውስጠ ታዋቂነት ግን እንግሊዝ በዓለም ዙሪያ በነበራት ገዥነት ያካበተችው ልምድ (እና የቀበረቸው ፈንጂ!) ስላለ የአሜሪካውን ጥሬ ኃይል በማለስለስና በመሞረድ ለጋራ ጥቅማቸው አብረው መንቀሰቀስ እንዳለባቸው የመስበኪያ መሣሪያ ነው፡፡ ብሪትን ከአሜሪካ ጋር በበርካታ የዓለም አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ የወሰደቻቸውን አቋሞች ልዩነት በዚህ መሣሪያ አማካይነት እየተነተነች የአሜሪካኖችን መሳሳት፣ ችኩልነትና ልምድ ማነስ ብሎም ጥሬ ጉልበተኛነት እንደሚያመለክት አድርጋ ስታስተጋባ ኖራለች፡፡ በሚስጢር የሚባባሉትን የመስሚያ ቀዳዳ በተፈጠሩ ወቅቶች በተገኙት መረጃዎች መሠረት፡፡

የብሪትን የአውሮፓ የጋራ ገበያ አባልነት

አሜሪካና ሶቭየት ኅብረት (ከነጋሻ ጃግሬዎቻቸው) በሚተናነቁበት ዘመን ብሪትን ታላቅነቷ እያቆለቆለ የአሜሪካም ቡችላ እየሆነች ስትሄድ፣ ኢኮኖሚያዋም ሲወዳድቅ፣ ከአውሮፓ ጋር የጋራ ገበያ ለመፍጠር እንድትስማማ የአሜሪካ መንግሥት ተፅዕኖ አርፎባት እስከ እ.ኤ.አ. 1972 ድረስ ለ20 ዓመታት ያህል ስታቅማማ ቆይታ ጥልቅ አለች። (የአሜሪካ ስለላ ድርጅት ይኼንን ልዩ ተልዕኮ አድርጎ ሲሠራ እንደነበር በቅርቡ ይፋ ወጥቷል፡፡) በውስጧ ግን ከአሜሪካ ላይ ተንጠላጥላ ወይም ብቻዋን ሆና እንደ ታላቅ ኃይል ለመቀጠል መጓጓቷ አልጠፋም ነበር። ምንም ብንቀጥን ጠጅ ነን ዓይነት። ብሪትን ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ዓለምን ስትገዛ ኖራ ከማንም ትንንሽ አገር ጋር እንዴት በእኩልነት ቆማ ልትታይ ይሁንና የፈሩት ይደርሳል ሆነና የኢኮኖሚያዊ አጋርነቱን አስፈላጊነት ተቀብላ በወግ አጥባቂው ፓርቲ በኤድዋርድ ሂት ጠቅላይ ሚኒስቴርነት መሪነት የአውሮፓ የጋራ ገበያ ማኅበር አባል ሆነች፡፡

የአውሮፓ የጋራ ገበያ መነሻ አስተሳሰቡ በተደጋጋሚ ጦርነት የዳሸቁትን አገሮች አንድ ላይ በሰላማዊ መንገድ አስተባበሮ በመያዝ ወደፊት ከሚመጣ ተመሳሳይ አደጋ ለማዳን ነበር፡፡ በተለይ በጀርመንና በፈረንሣይ መካከል የማይበርድ መነቋቆርና መናናቅ በታሪካቸው ሥር ስለሰደደ ከዚያ ችግር ለመውጣት አዲስ ጎዳና መከተላቸው ይበጃቸዋል የሚል ግምት ነበር፡፡ የጋራ ገበያ ዕቅዱ ቀስ በቀስ በስምምነት እየተለወጠ ወደ አውሮፓ ማኅበርነት ከፍ ሲልና የአውሮፓ ፖለቲካዊ ሥርዓት ወደ መፍጠር ጥድፊያው ሲሸጋገር፣ ብሪታንያ  በውጭ ኃይሎች የመዋጡ የቆየ ፍራቻ በሽታ አገርሽቶባት ሁሌ የርስ በርስ መነታረክ አመንጪ ሆነች። በሟችቷ ታቸር ዘመን ጭቅጭቁ አይሎ እኛ የጋራ ገበያ እንጂ ፌዴራል መንግሥት አንፈልግም የሚለው መፈክር ዘወትር ይሰማ ነበር።

ከዚያ ወዲህ ግን የዓለም ኢኮኖሚ እየተገለባበጠ፣ ከዳር እስከዳር መጠቃለሉ እየፈጠነ ከአሜሪካው ግዛታዊ መንግሥት በስተቀር ነፃ የሚባል አገር እየጠፋ ሲሄድ የብሪትን መወራጨት ቅጥ አጣ። ሶቭየት ኅብረት ተፈረካክሳ ጀርመኖች ተዋህደው፣ የአውሮፓው ኅብረት በብዙ አቅጣጫዎች መጠነኛ ስምምነቶች እየፈጠረ እንደ አንድ የዓለም ልእለ ኃያል ብቅ ማለቱን እያየች እንኳን፣ ብሪትን በአውሮፓውያን መካከል እያደር እንደ በጥባጭና አደናቃፊ መታየቷን አላቆም አለች፡፡ እንዲያውም ከአውሮፓ ውጪ ራሳችንን ችለን ታላቅ ሆነን እንቀጥላለን የሚለው ፉከራ ከንቱ መሆኑ በታሪክ ቀብረው እንደተሰናበቱት ማመን አቅቷቸው፣ ይኸውና ገዥዎቿ ለውሳኔ ሕዝብ አቅርበውት ቅዠት ይሁን ሕልም በማይለይ አኳኋን የብሪትንን ዕድል፣ የሕዝቧን ዕጣ ፋንታ ሜዳ ላይ ዘረሩት።

የብሪትን ከአውሮፓ ኅብረት መውጣት መዘዝ

የብሪትን ከአውሮፓ መውጣት መዘዙ ባብዛኛው ለራሷ ነው። ኦኮኖሚዋ ጭራሽ ያሽቆለቁላል። ብዙ ሰው የማያስተውለው እነሱም ሽፋፍነው የሚይዙት ግን የብሪትን አቅም ቁልቁል ከወረደ 30 እስከ 40 ዓመታት አድርጓል። ዛሬ ከአውሮፓ ኃያላን ከጀርመን፣ ከፈረንሣይና ከሩሲያ በታች ወርዳ ከጣሊያንና ከስፔን እኩያ አካባቢ ናት። የማሽን ፋብሪካዎቿ ከፊሎቹ ከስመዋል ሌሎቹ ተነቃቅለው ወደ ቻይናና መሰል አገሮች ሸሽተዋል። የዕቃ ማምረቻዎች ክፉኛ ተንደው ቻይናና ሌሎች አዳጊ ኢኮኖሚዎች ጋ ገብተዋል። የከተማ ርስቶችና ታላላቅና ዕውቅ ሕንፃዎች ሳይቀሩ በውጭ ባለ ሀብቶች እጅ ገብተዋል፡፡ ዝነኛው በለንደን መሀል ላይ ያለው የቢቢሲ መናኸሪያ ሕንፃ (ቡሽ ሃውስ የሚሉት) ባለቤትነት ወደ ጃፓኖች ከዞረ ስንት ዓመታት አልፈዋል!

በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍም ቢሆን ማሽቆልቆሏ ያለቀለት ጉዳይ ነው። ለትምህርትና ለምርምር የምትመድበው ከቅርቡ (እ.ኤ.አ. 2008) ቀውስ ወዲህ መሬት ወርዷል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተፎካካሪዎቿ አውሮፓውያን በሙሉ እንደ ኢኮኖሚያቸው ማንሰራሪያ ከማድረግ ይልቅ በገቢ መልቀሚያነት ስለመደበችው፣ የሚያስፈልጋትን የሠለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት እየተሳናት ነው፡፡ ወደ መረጃ አኪኖሚ ለመሸጋገር የሚያሰችለውን ሥልጡን ሠራተኛ ካላፈራች በተለይ በዓለም መጠቃለል ሒደት ራሷም እየተሸመለለች የዱሮውን ዝና መቸብቸቡ ምን ፋይዳ ይኖረዋል? በኢንዱስትሪ አብዮቱ ቀዳሚ የሆነችበት ወቅትና ምክንያቶች ሁሉ ስለጠፉ ከሌሎች መካከለኛ ደረጃ ያሉ ኢንዱስትሪያዊ አገሮች ጎን ተሰልፋ የሚደርሳትን ዕጣ በጥሞና እንደመከታተል ቡራ ከረዩ ውስጥ ገብታ ስትዋኝ ሕዝቧን ለመከራና ለባሰ ውድቀት ልትዳርገው ነው፡፡

እስከዛሬ ድረስ የብሪትን አስተማማኝና ታላቁ የገቢ ምንጯ የገንዘብ ተቋሞቿ ነበሩ። የካፒታል ገበያዋ ከኒውዮርክ ቀጥሎ የዓለም ማዕከል ነው፡፡ በቁጥጥሯ ሥር ባሉ አሁንም ነፃ ባልወጡ ቀኝ ግዛቶችና ጥገኛ ደሴቶች አማካይነት በስውር የገንዘብ መሸሸጊያ ጓዳዎችም አብጅታ በሰፊው ትገለገላለች፡፡ በአደባባይ ላይ እነስዊስና ሌሎችን ስትወነጅል የሷን ጓዳ ሚስጢር ግን በጥብቅ ታስጠብቃለች፡፡ ከአውሮፓ በመውጣቷ ግን ፍራንክፈርት (ጀርመን) ለንደንን አሽቀንጥሮ የአውሮፓን የገንዘብ ታላቅ መናኸሪያነት ማዕረግ መረከቡ አይቀርም። ቻይና በቅርቡ ያገሯን የውጭ ገንዘብ (ዩዋን የሚባለውን) ለንደን ላይ በነፃ እንዲሸጥ እንዲለወጥ ለማድረግ ውስጥ ለውስጥ ከብሪትን ጋር ስትስማማ፣ የአውሮፓ አባልነቷን እንደምትቀጥል ገምታ ስለነበር አዲሱ ይዞታዋ ግን ያንን እንድታጣ ያደርጋታል፡፡ ይባስ ብሎም በየሱቆቿ የተደረደሩት የቻይናና የመሰል አገሮች ውጤቶች ፓውንዱን ወደ ውጭ የሚመዙ እንጂ ያገሪቱን ገቢ የሚያግዙ አይደሉም። የብሪትን ዕዳ ከዓመት ምርቷ ወደ 820 በመቶ አካባቢ መድረሱም የተሳካ ጎዳና ላይ አለመሆኗን ያስረዳል፡፡

ሲጠቃለል የዱሮው የብሪትን ታላቅነት ጉራ የሕዝቧን ጭንቅላት አሳብጦት አሁንም ለምታመርታቸው ዕቃዎች የአውሮፓ ገበያ የሚሰጣትን ጥቅም ብሎም በኅብረቱ አማካይነት የሚደርሷትን ልዩ ልዩ ዕድሎች አሽቀንጥራ ጥላ ለመውጣት በቃች። ብሪትን የቀራት ብቸኛ ችሎታና አቅም ከአሜሪካ ሥር ተሸጉጣ ሌሎችን አገሮች ማተራመስ ብቻ ይሆናል። (ቶኒ ብሌር ለጆርጅ ቡሽ ልጅየው በሰጠው የመካከለኛውን ምሥራቅ የማፈራረስ ግልጋሎት ዓይነት፡፡) ያም ቢሆን ከአሜሪካ የኢኮኖሚና ወታደራዊ አቅም እያደር መኮሰስ አንፃር ብዙም የሚያወላዳት አይሆንም፡፡ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ በተለይም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እ.ኤ.አ. በ1976 ዓ.ም. ብሪትን ብድር ከተቀበለች በኋላ፣ ስትፈራና ስትከበር የኖረችበት ዘመን ማክተሙ ሁሉም ያወቀው ጉዳይ ሆኖ ለራሷ ጆሮ ግን ሳይደርስ ዘገየ፡፡

የብሪትን ከአውሮፓ ማኅበር መውጣት በሌላ በኩል ሲታይ የብሪትን እንቅፋትነት ስለተወገደ አውሮፓ በፍጥነት ወደ ፌዴራላዊ መንግሥት መገስገሱ ይቀጥላል። በአንፃሩም ብሪትን በአሜሪካ 53ኛ ያካባቢ መንግሥትነት ደረጃ ተዋውላ እንድትገባ ትገደድ ይሆናል። እናት ለጡረታ ወደ ልጅ ቤት እንደምትገባው ዓይነት። ስኮትላንድ በበኩሏ ያለ ጥርጥር ከብሪትን ተገንጥላ ወደ አውሮፓ መመለሷ የማይቀር ይመስላል። ሰሜን አይርም እንደዚሁ፡፡

አንዳንዶች የብሪትን ከአውሮፓ መውጣት ሌሎች አገሮችን ለተመሳሳይ ዕርምጃ ይገፋፋል ይላሉ፡፡ ነገር ግን መሀል፣ ምሥራቅና ደቡብ አውሮፓ ያሉ ትንንሽ አገሮች ሕዝቦች እንደ እንግሊዙ የተወሰሰበና የተመሰቃቀለ የነፃነት ታሪክ ስለሌላቸው፣ የአውሮፓን ልዕለ መንግሥት መፈጠር በብርቱ የሚቃወሙ ግዙፍ ንቅናቄዎች የሚወለዱ አይመሰልም። እንዲያውም የውህደቱን ፍጥነት ጨምረው ከጭቅጭቅ ለመገላገል ሳይቸኩሉ ይቀራሉ? የአውሮፓ ትላልቅ ኩባንያዎች ትስስርና የጀርመን ኢንዱስትሪ ተፅዕኖ ከአሜሪካኖች ዳተኝነት ጋር ተዳምረው ቢያንስ ቢያንስ የጠነከረ ኅብረት እንዲቀጥል ማድረግ ይሳናቸዋል? አሜሪካኖች ፌዴራል አውሮፓን ባይወዱም የእንግሊዞች ሰንካላ ብሔረተኝነት የከፈተውን ቀዳዳ ለመድፈን ሳይተጉ ይቀራሉ? የኦባማ ጥረት ለሱ እንደነበር፣ አለመሳካቱም ብዙ ብሽቀትንና ብሶትን በአሜሪካውያን በኩል መፍጠሩ ይኼን ይጠቁማል።

በእርግጥ አሜሪካ የአውሮፓን ኅብረት በምትፈለገው ፍጥነት፣ መልክና አቅጣጫ እንዲገሰግስ ለመቆጣጠር ከውስጥ ሆኖ የሚያግዛት ሌላ ተተኪ አገር ወይም አገሮች ላታጣ ትችላለች፡፡ ካሁን በፊት በተለያዩ ዘርፎች ለአሜሪካ በመላላክ ያግዙ የነበሩት የስካንዲኔቪያ አገሮች (በተለይ ዴንማርክ) የብሪትንን ቦታ ተክተው የጋራ የውጭ መመርያና የመከላከያ ጉዳይን ለመሸበብ ይተጉ ይሆናል፡፡ ቢሳካላቸውም ባይሳካላቸውም፡፡ ነገር ግን የአውሮፓም ሆነ የዓለም ኢኮኖሚ መዘውር እንደ ዱሮው በአሜሪካና በጥቂት አባሪዎቿ እጅ መሆኑ እየቀነሰ ስለሆነ፣ ብሪትን ባካሄደችው የቅርቡ ሕዝበ ውሳኔ ዋና ምክንያት በአዲስ ሁኔታ እየተዘጋጀ ላለው የሰንጠረዥ ጨዋታ ተጋባዥ የመሆን ዕድል ማጣቷ እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ የቀበጡ ዕለት…

 

ከአዘጋጁ፡- ዶ/ር አሰፋ እንደሻው ቦረና ትምህርት ቤት፣ ጄኔራል ዊንጌት፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ለንደን ዩኒቨርሲቲ ተምረው ሲንጋፖርና ኢንግላንግ ዩኒቨርሲቲዎች በፕሮፌሰርነት ሕግ ያስተማሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...