Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህልክረምትን በንባብ

  ክረምትን በንባብ

  ቀን:

  የዘንድሮ ‹‹ሰኔ 30 ብሔራዊ የንባብ ቀን›› ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር (ኢደማ) አስታውቋል፡፡ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ የሚከበረው የንባብ ቀን፣ በአዲስ አበባ፣ ባህርዳር፣ መቐለ፣ ጐንደርና ደሴ ይካሄዳል፡፡ በአዲስ አበባው የንባብ ቀን ከግዮን ሆቴል ፊት ለፊት በሚገኘውና በተለምዶ ሲ ሜዳ ተብሎ በሚታወቀው ስፍራ የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ ይካሄዳል፡፡ በዐውደ ርዕዩ ከ40 በላይ የመጻሕፍት ሻጮች፣ አሳታሚዎችና አታሚዎች ይሳተፋሉ፡፡

  የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዐውደ ርዕዩ የመጻሕፍት አዝዋሪዎችም ይገኛሉ፡፡ አዝዋሪዎቹ ከመጻሕፍት ጀርባ የተጻፈ ዋጋ ፍቆ ከትክክለኛው ዋጋ ጨምሮ በማስፈር ሕገወጥ ተግባር ያልተሰማሩ መሆናቸው ተረጋግጦ በዐውደ ርዕዩ እንዲሳተፉ ቦታ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ፡፡ የመጻሕፍትን ትክክለኛ ዋጋ በመፋቅ ያለአግባብ የሚነግዱ ለዘርፉ እንቅፋት ከሆኑ መካከል እንደሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩትን ማበረታታትም ለችግሩ እንደመፍትሔ ሐሳብ ይቀርባል፡፡

  የንባብ ቀን በሚከበርባቸው አምስቱ ቀናት፣ ከዐውደ ርዕዩ በተጨማሪ የወግ፣ የቅኔ፣ የዲስኩር፣ የግጥም፣ የሕፃናት ንባብና ሽልማት እንዲሁም የሥነ ጽሑፍ ምሁራን የመጻሕፍት ዳሰሳ የሚያቀርቡባቸው መርሀ ግብሮች ተዘጋጅተዋል፡፡ መርሀ ግብሮቹ ዐውደ ርዕዩ በሚካሄድበት ቦታ ምሽት ላይ የሚቀርቡ ሲሆን፣ በወግ ምሽት ፍቃዱ ከበደና እንዳለጌታ ከበደ፣ በቅኔ ምሽት አበረ አዳሙና መዝገበቃል አየለ፣ በዲስኩር ምሽት መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ፣ በሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ዳሰሳ ምሽት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ መምህራን፣ በግጥም ምሽት አላዛር ሳሙኤልና ስዩም ተፈራ እንዲሁም ሌሎችም ሥራዎቻቸውን ያቅርባሉ፡፡

  እንደ ዶ/ር ሙሴ ገለጻ፣ ሰኔ 30 የትምህርት ተቋሞች የሚዘጉበት ቀን በመሆኑ፣ ከሰኔ 30 በኋላ ባሉት ቀናት ትምህርት ነክና ሌሎችም መጻሕፍት የማንበብ ፍላጎት ሲቀንስ ይስተዋላል፡፡ ‹‹ክረምት ላይ ትምህርት ቤት ሲዘጋ ወጣቱ ከንባብ ይርቃል፡፡ በሰኔ 30 የንባብ ቀን ወጣቶች ለጠቅላላ ዕውቀት የሚረዱ መጻሕፍትን እንዲያነቡ እንቀሰቅሳለን፡፡ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በመሆን የሚያነቡበት ወቅት እንዲሆንም ማድረግ እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡

  የንባብ ባህልን ለማዳበር አንድ ዕለት መርጦ የንባብ ቀን ማድረግ ብቻውን በቂ ባይሆንም፣ ተነሳሽነት ለመፍጠር እንደሚረዳ ግን ገልጸዋል፡፡ የንባብ ቀን ሲከበር፣ በማኅበሩ ተነሳሽነት ከሚከናወኑ ተግባሮች ባሻገር አገር አቀፍ በዓል እንዲሆንና ተደራሽነቱ እንዲሰፋ ጥረት እያደረጉ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ሰኔ 30 በአገር አቀፍ ደረጃ የንባብ ቀን እንዲሆን በሚያደርጉት ጥረት ዘንድሮ በዓሉ በክልል ከተሞችም እንዲከበር ማድረግ መቻላቸውን ይናገራሉ፡፡ አሁን ካለበት በሰፋ ደረጃ እንዲካሄድ የመንግሥት እገዛ ስለሚያስፈልግም፣ ከባህልና ቱሪዝምና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በዓሉ አገር አቀፍ እንዲሆን ለማድረግ ማኅበሩ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

  ዐውደ ርዕዩ መጻሕፍት የመግዛት እንዲሁም የማንበብ ልማድን ከማዳበር ባሻገር፣ ወጣት ደራሲያንን ማበረታታትንም ያለመ ነው፡፡ ታዳጊዎችን የሚያሳትፉት መርሀ ግብሮች ታዳጊዎቹ በክረምት ወቅት በተለያየ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥኑ መጻሕፍት የማንበብ ልማድ እንዲያዳብሩ ማድረግን ያለሙ ናቸው፡፡ የመጻሕፍት ሽያጭን አስፋፋቶ ደራሲያንን በማበረታታት ደራሲያኑን ለተጨማሪ ሥራዎች ማነሳሳትም ከግቦቹ መካከል ይጠቀሳል፡፡ ሻጮች፣ አሳታሚዎች፣ አታሚዎች፣ ደራሲያንና አንባቢው የሚገናኙበትም መርሀ ግብር ይሆናል፡፡

  የማኅበሩ ፕሬዚዳንት እንደተናገሩት፣ የንባብ ባህልን በማዳበር ረገድ በተለያዩ ክልል ከተሞች የንባብ ክበባት መቋቋማቸው፣ የመጻሕፍት ዐውደ ርዕዮችና ሌሎችም ንባብ ነክ እንቅስቃሴዎች መበራከታቸው አበረታች ጅማሮ ነው፡፡ እንደ ሰኔ 30 የንባብ ቀን ያሉ ክንውኖችም በንባብ ባህል ለውጥ ለማምጣት አጋዥ ይሆናሉ ይላሉ፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...