Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምከ200 በላይ ሰዎች የሞቱበት የባግዳዱ ፍንዳታ

ከ200 በላይ ሰዎች የሞቱበት የባግዳዱ ፍንዳታ

ቀን:

በኢራቅ 2016 ከገባ ብቻ ከሰባት ያላነሱ በአጥፍቶ ጠፊዎችና በተሽከርካሪ ላይ በተጠመዱ ቦምቦች ፍንዳታ ምክንያት ከ300 በላይ ኢራቃውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ አብዛኞቹም ጥቃቶች የተፈጸሙት በአይኤስ ነው፡፡

በረመዳን ወር ማብቂያ እሑድ ሰኔ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ደግሞ፣ በባግዳድ ከ200 በላይ ሰዎችን የቀጠፈ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ በጥቃቱ ሕፃናትና ሴቶችም ሰለባ ሆነዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2007 ወዲህ በኢራቅ በአንድ ቦታ ብቻ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ ከ200 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ይህ የመጀመሪያው ነው፡፡

አልጄዚራ እንደዘገበው፣ ፍንዳታው የደረሰው የረመዳን ወቅት እየተገባደደ በመሆኑ በዓሉን ለማክበር በገበያ ቦታ በመገበያየት ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ ነው፡፡ በጥቃቱ ሙሉ ቤተሰብ ያላቸውን ጨምሮ ከ200 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ ብዙዎችም ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ‹‹አደጋውን የፈጸምኩት እኔ ነኝ፤›› ሲልም አይኤስ ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡

- Advertisement -

በአብዛኛው የሺዓ ሙስሊሞች በሚገኙበትና ፆሙን አፍጥረው ለገበያ በወጡበት ሰዓት በማዕከላዊ ባግዳድ ካራዳ በአይኤስ የተፈጸመውን ጥቃተ ተከትሎ፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና ነጋዴዎች መሪያቸውንና የፓርላማ አባላትን አውግዘዋል፡፡ ‹‹ጥበቃ አልተደረገልንም፣ በተደጋጋሚ የአይኤስ ሰለባ እየሆንን ነው፤›› ሲሉም መንግሥታቸውን ኮንነዋል፡፡

በባግዳድ ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲፈጽም የነበረው አይኤስ፣ በተለይ በሺዓ ሙስሊሞች ላይ የሚፈጽመው የአጥፍቶ መጥፋት አሊያም በመኪናና በጋሪዎች ላይ በተጠመዱ ቦምቦች የማጋየት ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የአሁኑ ጥቃትም የደረሰው በሺዓ ሙስሊሞች ላይ ሲሆን፣ በአብዛኛው የሞቱትም በገበያ ሥፍራው ውስጥ በነበረ የሕፃናት መጫወቻ ሲዝናኑ የነበሩ ሕፃናትና ለገበያ በወጡ እናቶቻቸው ላይ ነው፡፡

የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይደር አል አባዲ ጥቃቱ የደረሰበትን ሥፍራ ሲጎበኙ፣ ከነዋሪዎች መልካም አቀባበል ባይቸራቸውም በየአካባቢው የተጠናከረ ቁጥጥር እንደሚኖር ለነዋሪዎች አሳውቀዋል፡፡ ከቢሯቸው የወጣ መግለጫም ቦምብ የሚያነፈንፉ መሣሪያዎች ወደ አገሪቱ በብዛት እንደሚገቡ፣ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑትንና የውሸት የቦምብ መፈተሻ መሣሪያዎችንም ከአገሪቱ እንደሚያስወጡና ዕገዳ እንደሚጥሉ አትቷል፡፡ የደኅንነት ቁጥጥር የሚያደርጉ መኪኖች በብዛት እንደሚገቡና በየጎዳናው ቁጥጥሩ እንደሚጠናከርም ተነግሯል፡፡

በኢራቅ በሕገወጥ ነጋዴዎች የሚቀርቡት የቦምብ ማነፍነፊያ መሣሪያዎች የውሸት መሆናቸው እ.ኤ.አ. ከ2010 ጀምሮ ይፋ መውጣቱን፣ በዚህም አንዱን የውሸት መሣሪያ 40 ሺሕ ዶላር በማስከፈል ስድስት ሺሕ መሣሪያዎችን የሸጠ እንግሊዛዊ ነጋዴ በቁጥጥር ሥር ውሎ የአሥር ዓመት እስራት እንደተፈረደበት ቢቢሲ አስታውሷል፡፡ እንግሊዝም ወደ ኢራቅ በምትልካቸው የደኅንነት መሣሪያዎች ላይ በወቅቱ ዕገዳ ጥላለች፡፡ የኢራቅ የደኅንነት አካላት መሣሪያዎቹ እክል እንዳለባቸው ቢያውቁም፣ መሣሪያዎቹን ከመጠቀም አልተቆጠቡም ነበር፡፡ ሰሞኑን በካራዳ የመገበያያ ሥፍራ የደረሰውን የቦምብ ጥቃት ተከትሎ ግን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልአባዲ መሣሪያዎቹን ከአገልግሎት ውጪ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ የፍትሕ ሚኒስትሩ ደግሞ በሽብር ወንጀል እስር ቤት የሚገኙ በሙሉ በቅርቡ የሞት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አሳውቀዋል፡፡

የኢራቅ መከላከያ ሠራዊት በአይኤስ ቁጥጥር ሥር የነበረችውን ፉሉጃ ከተማ ባስለቀቀ ማግስት፣ በባግዳድ ካራዳ ከደረሰው ጥቃት በተጨማሪም በባግዳድ ሰሜናዊ ክፍል በሚኖሩ ሺዓዎች ላይ በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት አምስት ሰዎች መገደላቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

አይኤስ በድረ ገጽ በለቀቀው መረጃም የኢራቅ መከላከያ ኃይል በአይኤስ ላይ እየወሰደ ላለው ዘመቻ በኢራቃዊ የተፈጸመ አጸፋ መሆኑን አስፍሯል፡፡ አሜሪካ በኢራቅ የተፈጸመው ጥቃት ከኢራቅ ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ እንደሚያጠናክረው ስታሳውቅ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢራቅ ልዑክ ጃን ኩቢስ ደግሞ፣ ‹‹አይ ኤስ በጦር ሜዳ ሲሸነፍ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈጸመው ጥቃት የሽንፈቱ መገለጫ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ካራዳ በባግዳድ ማዕከላዊ ክፍል የሚገኝና የንግድ እንቅስቃሴ የሚበዛበት ስፍራ ነው፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ የሰው ፍሰት አለው፡፡ የ2016ን የአውሮፓ እግር ኳስ ጨዋታ ለማየትም ሰዎች በየካፌው የሚሰባሰቡበት ስፍራ ነው፡፡ ሆኖም ስፍራው ብዙም ጥበቃ እንደማይደረግለት የአካባቢው ነጋዴዎች ለአልጄዚራ ተናግረዋል፡፡ ነጋዴዎቹም ቢሆኑ በሰው ፍሰት የተሞላውን የገበያ ስፍራ ለማስጠበቅ አይችሉም፡፡ በመሆኑም እንዳሁኑ የከፋ ባይሆንም በአይኤስ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ይፈጸምባቸዋል፡፡

አብዛኞቹ ኢራቃውያንም በኢራቅ ለዓመታት የዘለቀው አለመረጋጋትና የአይኤስ ድርብ ጥቃት ከመንግሥታቸው ደካማነት የመጣ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በኢራቅ ያሉ ሁሉም ፖለቲከኞች ሚስተር አል  አባዲን ጨምሮ በሕዝቡ ላይ ለሚደርሰው በደልና ጥቃት ተጠያቂዎች ናቸው፣ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም፤›› ስትል አንዲት ሴት መናገሯን የአልጄዚራ ዘገባ ያሳያል፡፡

‹‹የኢራቅ ባለሥልጣናት በቤተ መንግሥታቸው ከፍተኛ ጥበቃ ሲያገኙ፣ ሕዝቡ ለአይኤስ ተላልፎ ተሰጥቷል፤›› ስትልም የአገሪቱን ፖለቲከኞች ኮንናለች፡፡

በኢራቅ 2016 ከገባ ወዲህ በየካቲት 70፣ በመጋቢት በተለያዩ ጊዜያት 47 እና 32 በተከታታይ፣ በግንቦት 33፣ 93 እና 69 በተከታታይ በሰኔ 30 እንዲሁም ከ200 በላይ ሰዎች በተከታትይ የአጥፍቶ መጥፋት ሰለባ ሆነዋል፡፡ አብዛኞቹ ጥቃቶች የደረሱትም በአይኤስ ሲሆን፣ ቡድኑም ለብዙዎቹ ኃላፊነቱን ወስዷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...