Sunday, June 23, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ግልጽነት የጎደለው የዳኞች ምልመላ

በኃይለገብርኤል ሠዐረ

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሕገ መንግሥቱና ሌሎች የአገሪቱን ሕጎች መሠረት አድርገው በሰዎች መካከል ባሉ ግንኙነቶች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ይፈታሉ፣ መብትን ያስከብራሉ፣ በአጥፊ ላይ ቅጣት ይጥላሉ፡፡ ፍትሕን ፈልገው ወደ ፍርድ ቤት ለሚመጡ ባለጉዳዮች ፍላጎት መሳካት የፍርድ ቤቶቹ ዳኞች፣ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችና የበላይ ኃላፊዎች የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ሰሞኑን ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች (ለመጀመሪያና ከፍተኛ) የተከናወነው የዳኞች የምልመላና የሹመት ክንውን እንዲሁም በቀጣዩ ሳምንት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሹመት በሚቀርቡ ዳኞች አመላመል ሒደት ፍትሐዊነት ምን ይመስላል የሚለውን በመጠኑ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡

የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በአዋጅ ቁጥር 684/2002 በአዲስ መልክ ሲቋቋም ከተሰጡት ኃላፊነቶች አንዱ ዕጩ ዳኞችን መመልመልና መለየት በመሆኑ፣ ጉባዔው ባለፉት ስድስት ዓመታት ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞችን መልምሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሾሙ አድርጓል፡፡

ለበርካታ ዓመታት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ያለውን የዳኞች የብሔር ተዋጽኦ ለማመጣጠን በሚልና መሰል ምክንያቶች ለበርካታ ዓመታት ዳኞች ይመለመሉ የነበረው ከክልሎች የነበረ ሲሆን፣ ይህም በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ አባላትና የጉባዔውን አባላት በሚያውቁ ግለሰቦች ጥቆማ የሚከናወን ግልጽነት የጎደለው ስለነበረ ውጤታማ ሆኖ ባለመገኘቱ ዕጩ ዳኞች ማስታወቂያ ወጥቶ ፈተና ተሰጥቶ ለሕዝብ አስተያየት ቀርበው የመሾም ሒደት ከአዋጅ ቁጥር 684/2002 መውጣት በኋላ ተጀምሯል፡፡

ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥገኝነት እስካሁን ያልወጣው የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቤትም ኃላፊ ለመመደብ በርካታ ወራት ፈጅቶ ኃላፊውም በመልቀቃቸው አሁን የሚገኙት ኃላፊ ተመድበው መደበኛው ሥራ ከሞላ ጎደል እየተሠራ ነው፡፡

በፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቤትና በጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ላይ ከዳኞች በርካታ ቅሬታዎች የሚቀርቡ ሲሆን፣ ባለፉት አምስት ዓመታት የጉባዔው አባላት ከዳኞች ጋር የተገናኙት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በዳኞች ጥቅማ ጥቅምና ደመወዝ፣ በሚወሰዱ የዲሲፕሊን ዕርምጃዎች ላይ ግልጽ የሆነ አሠራር እየታየ አይደለም፡፡

የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ሰሞኑን ተመልምለው በተሾሙ ዳኞች የፌዴራል የመጀመሪያና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች የምልመላና የመረጣ ሒደት እንዲሁም ሰሞኑን በተዘጋጁ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዕጩ ዳኞች የምልመላ ሒደት ላይ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮችን ለመዳሰስ ነው፡፡

ለፌዴራል የመጀመሪያና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስለተሾሙ ዳኞች ምልመላ

የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቤት በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. ለፌዴራል የመጀመሪያና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ዕጩ ዳኞችን ለመመልመልና ለማሾም ማስታወቂያ በማውጣቱ፣ ከመላው የአገሪቱ ክልሎች መመዘኛውን እናሟላለን የሚሉ በሺሕ የሚቆጠሩ ተመዝጋቢዎች ተመዝግበው የመጀመሪያውን መመዘኛ አሟልተዋል ተብለው የተመረጡ ተፈታኞች በሐምሌ ወር 2007 ዓ.ም. የጽሑፍ ፈተና ተሰጣቸው፡፡

የጽሑፍ ፈተናውን በተመለከተ ከ700 በላይ ተፈታኞች በአንድ አዳራሽ ውስጥ ሆነው በቂ ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግ የፈተናው ዓይነት የሕግ መጻሕፍትና ሌሎች ሰነዶች ተይዞ የሚገባበት (ግልጽ ይሁን ዝግ) መሆኑ ሳይታወቅ የተወሰነው ተፈታች መጻሕፍትና ሰነዶች ይዞ ሌላው ሳይኖረው አብዛኛው ተፈታኝ መልስ እየተኮራረጀ፣ በስልክ እዚያው አዳራሽ ውስጥ መልስ እየተነጋገረ እየወጣ እየገባ ፈተና የሚመስል ‹‹ፈተና›› ተሰጠ፡፡

ወትሮም ዘገምተኛ የሆነው የጉባዔው ጽሕፈት ቤት የዚህን የጽሑፍ ፈተና ውጤት ለማሳወቅ አራት ወራት ፈጅቶበት በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. የጽሑፍ ፈተና ውጤትን አሳውቆ በዚሁ ወር ቃለ መጠይቅ በጉባዔው አባላት ተደርጎ በታኅሳስ ወር 2008 ዓ.ም. 39 ዕጩ ዳኞች ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ 121 ዕጩ ዳኞች ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተወዳዳሪ ባለሙያዎች መሆናቸው ተገልጾ ሕዝቡ አስተያየቱን ለአሥር ቀናት በአካል፣ በስልክ፣ በድረ ገጽ እንዲገልጽ ጥሪ አደረገ፡፡

ከሰባት ወራት በኋላ ባለፈው ሳምንት የጉባዔው ጽሕፈት ቤት ስማቸው ለሕዝብ አስተያየት ከቀረበው ዕጩዎች መካከል ለተወሰኑት እየደወለ ለመሾም ዝግጁ መሆናቸውን ከጠየቀ በኋላ፣ ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው ቃለ መሐላ ፈጽመው ተሹመዋል፡፡

ግልጽነት የሚባለውን መርህ ከቃሉ በቀር የማያውቀው የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ከጽሑፍ ፈተና ውጪ፣ በቃለ መጠይቅ ተፈታኞች ያገኙት ውጤት፣ ከሕዝብ በተሰበሰበ አስተያየት ቅሬታ የቀረበባቸውም ካሉ ቅሬታውን በትክክል አጣርቶ ምን እንደሆነ ሳያመለክት ሹመቱ ተከናውኗል፡፡

ከተሾሙት ዳኞች መካከል ብቃት የነበራቸው ያሉ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ በጽሑፍ ፈተና ዝቅተኛ ውጤት አምጥተው ከአንዳንድ ኃላፊዎች ጋር በነበራቸው ቅርበት የተሾሙ መሆኑ ቅሬታ እየተሰማበት ነው፡፡ በተለይ በፍርድ ቤቶቹ በዳኝነትና በረዳት ዳኝነት ይህ ቢስተካከል እያሉ አስተያየት ይሰጡ ከነበሩት መካከል ሳይሾሙ የቀሩ ይገኙበታል፡፡

የዳኝነት መመዘኛ መስፈርት የዳኛው ችሎቱን የመምራት ብቃት፣ ለጉዳዩ አግባብነት ባለው ሕግ ዙሪያ ያለው ዕውቀት፣ የሙግቱን ሒደት በሥነ ሥርዓት ሕጎች የመምራት፣ ለሚይዘው መዝገብ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ በችሎት መገኘት፣ በሚሰጠው ፍርድ ማስረጃውን አግባብነት ካለው ሕግ ጋር ማገናዘብ መመዘንና መተንተን፣ ጭብጥ የመለየት ብቃት፣ ከአድልዎ በፀዳ መልኩ ክርክርን የመምራትና   ፍርድና ውሳኔ መስጠት ሊሆን ይገባዋል እንጂ ሌላ መመዘኛ ከሆነ መንግሥትም ሕዝብም ይጎዳሉ፡፡

ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስለተመለመሉ ዕጩ ዳኞች

ጉባዔው የራሱ ጽሕፈት ቤት ኖሮት ሥራውን ከጀመረበት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችን ያሾመው በ2005 እና በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ነው፡፡ በእነዚህ የመመልመያ ወቅቶች በተሰጠው የጽሑፍና የቃለ መጠይቅ  መመዘኛ ውጤታቸው ከፍ ካለ ዳኞች መካከል ያልተሾሙ በፌዴራል የመጀመሪያና ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚገኙ ዳኞች ምስክር ናቸው፡፡

ለወትሮው ዳኞችን ለማሾም በርካታ ወራት የሚወስድበት የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በግንቦት ወር 2008 ዓ.ም. የመጨረሻ ቀናት ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዕጩ ዳኞችን መልምሎ ለማሾም እንደሚፈልግ ባወጣው ማስታወቂያ፣ ለተመዘገቡት ባለፈው ሳምንት ሐሙስና ዓርብ ከጉባዔው ጽሕፈት ቤት ተደውሎላቸው ቅዳሜ ሰኔ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፈተና እንዲቀርቡ ተነግሮ የጽሑፍ ፈተና ጠዋት ቃለ መጠይቅ ከቀትር በኋላ ተደርጎላቸዋል፡፡

በዚህ የጽሑፍ ፈተና ላይ እጅግ የሚገርመው ነገር ለጽሑፍ ፈተና ተፈታኞች ከተቀመጡ በኋላ በ2007 ዓ.ም. ተፈትነው ለነበሩት ‹‹እናንተ ባለፈው ዙር የወሰዳችሁት የጽሑፍና የቃል ፈተና በቂ ስለሆነ ተመለሱ እኛ እንደውልላችኋለን፤›› ተብለው ፈተናውን ሳይወስዱ ቀርተዋል፡፡ እነዚህና ሌሎችን ጨምሮ 41 ዕጩ ዳኞች አስተያየት እንዲሰጥባቸው የስም ዝርዝራቸው በያዝነው ሳምንት መግቢያ ላይ በፍርድ ቤቱ የፌስቡክ ገጽ ላይ ወጥቷል፡፡

የጉባዔውንና የጉባዔውን ጽሕፈት ቤት አሠራር እጅግ አሳዛኝ የሚያደርገው ከአንድ ዓመት በፊት የጽሑፍ ፈተና ወስደው ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸው ከእነርሱ የተሻለ ተመርጠው ተሹመዋል ከተባለ በኋላ፣ ለእነዚሁ ዳኞች ያለፈው ዓመት ፈተና ውጤት ለዚህ ዙር እንደመመዘኛ መወሰዱ ነው፡፡ በተጨማሪም በፍርድ ቤቱ የፌስቡክ ገጽ ላይ ዝርዝራቸው የወጣው ዳኞች በፌዴራል ፍርድ ቤቶችና በክልል ፍርድ ቤቶች የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ የእነዚሁ ዳኞች ስም በፌስቡክ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በአራት ቀናት ውስጥ (ከሰኔ 21 እስከ 24 ቀን 2008 ዓ.ም.) በዕጩዎች ላይ አስተያየት ስጡ መባሉ አድርገናል ለማለት ካልሆነ በቀር ጊዜውና ተደራሽነቱ ምን ያህል በቂ ነው?

የዚህ ዓመት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን ከመጠናቀቁ በፊት በአሥር ቀናት ውስጥ የጽሑፍ ፈተና ሰጥቶ፣ ቃለ መጠይቅ አድርጎ፣ የተፈታኞችን የተለያየ ጊዜ የፈተና ውጤት ወስዶ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል ለምክር ቤቱ አቅርቦ ለማሾም እየተደረጉ ያለው ዝርክርክ አሠራር የመንግሥት ያለህ የሚያሰኝ ነው፡፡

ለጉባዔው ጽሕፈት ቤት ቅሬታ ለማቅረብ ቢሞከርም ቅሬታ ተቀባዩም፣ አጣሪውም፣ መልስ ሰጪውም የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቤት በመሆኑ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡

ስለሆነም የጉባዔው አባላትም ሆነ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የበላይ አመራሮች በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ ማብራሪያ ሊሰጡ ቅሬታዎችንም ሊያስተናግዱ የጽሕፈት ቤቱን አሠራርም የመንግሥት የሚመለከተው አካል በቅርብ ሊከታተል ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles