Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየምርቃቱ ሰሞን

የምርቃቱ ሰሞን

ቀን:

‹‹እንኳን ደስ ያላችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ…›› የሚለውን የምርቃት ሥነ ሥርዓት ዜማ ስትሰማ ምንም ዓይነት ስሜት እንዳልነበራት ታስታውሳለች፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በያዘችበት ወቅት የምርቃት ቀን ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውት እንኳን የመመረቅ የተለየ ስሜት እንዳላደረባት ማርታ ኃይሌ ትናገራለች፡፡ በመጨረሻው ሰዓት ላይ ግን መመረቅ ልዩ ስሜት እንደሚያሳድር ተረዳች፡፡

ቤተሰብ ልብስ እንድትገዛና ለምርቃቱ ዕለት የሚያስፈልጋትን እንድታሟላ አደረጋት፡፡ የምርቃታቸውን ዕለት ዋዜማ ዩኒቨርሲቲ ለማደር ከጓደኛዋ ጋር ተስማሙ፡፡ በዕለቱ ጠዋት ጋዋናቸውን አድርገው የምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ይካሔድ ወደነበረበት አዳራሽ ሲያመሩ ግቢው ውሰጥ ይመለከቱ የነበረው የተማሪ ሁኔታ፣ ተማሪዎች ገጽታ ላይ የሚነበበው ደስታና ተስፋ እሷም ላይ ልዩ ስሜት አጫረ፡፡ ‹‹በተለይ ደግሞ አዳራሽ ውስጥ ስገባ እዚያ ቦታ ላይ ቆሜ እንኳን ደስ ያላችሁ … የሚለውን ዜማ ስሰማ በጣም ደስ የሚል ስሜት ተሰማኝ›› በማለት የመጀመሪያ ዲግሪ ምርቃቷ ላይ የነበውን ሁኔታ ታስታውሰዋለች፡፡

ብዙዎች መመረቅን፣ (ዲግሪም ይሁን ዲፕሎማ) የምርቃት ዕለትንም ሲያስቡ በሐሴት ቢሞሉም እንደ ማርታ የመጨረሻው ሰዓት ድረስ ብዙም የተለየ ስሜት የማይሰማቸው አይጠፉም፡፡ ማርታ እንደምትለው የመጀመሪያ ዲግሪ ምርቃት በብዙ ምክንያት ልዩ ስሜት የሚያሳድር ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ቆይታ የአራት ወይም የአምስት ዓመት ውጤት ብቻ ሳይሆን ከታች ጀምሮ የረዥም ዓመታት ጥረት ውጤት ማግኛ  በጉዞው ደግሞ በእያንዳንዷ ደረጃ የቤተሰብ ጥረትና ተስፋ ያለበት መሆኑም የመጀመሪያ ዲግሪ ምርቃትን ልዩ ያደርገዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

2005 ዓ.ም. ላይ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በዲዛይን የሠራችው ማርታ ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ በሥነ ጥበብ ላይ ሠርታለች፡፡ ለመመረቅ ጥቂት ቀናት የቀሯት ማርታ በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት መምህርም ነች፡፡ ስለሁለተኛ ዲግሪዋ ምርቃትስ ምን እየተሰማት እንደሆነ ጥያቅ አቅርበንላት ነበር፡፡ ‹‹ይህ በሙያ ለማደግ ወደ ሌላ ደረጃ ለመሻገር የምሠራበት ጊዜ በመሆኑ እንደ መጀመሪያ ዲግሪ በደስታ ስሜት የምዋጥበት አይደለም›› በማለት በዚህ ደረጃ ብዙ የመመረቅ ጉጉትና ደስታ ይኖራል ብላ እንደማትጠብቅ ትናገራለች፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪ ምርቃት ጊዜ ወሳኝ ነው የምትለው ማርታ የተመራቂ ተማሪ ተስፋው፣ ደስታው፣ ጉጉቱ ይታያል እንጂ በጥቅሉ የሚያስበው ነገር ብዙም ጎልቶ እንደማይወጣ ትናገራለች፡፡ በተቃራኒው ሁለተኛ ዲግሪ ምርቃት ላይ ብዙ ጉጉትና ተስፋ ሳይሆን ተጨባጭ ነገሮች ላይ ቆሞ የማሰብ ነገር ያመዝናል የሚል እምነት አላት፡፡

‹‹እዚህ ደረጃ ላይ ምርጫው፣ ጊዜውና ገንዘቡ የኔ ነው፡፡ የቤተሰብ ተሳትፎ እስከዚህም ነው›› የምትለው ማርታ፣ የመጀመሪያ ዲግሪ ላይ የቤተሰብ ድጋፍ፣ ተስፋና የሚጠብቀው ነገር መኖር በተመራቂው ስሜት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖም ቀላል እንዳልሆነ ትገልጻለች፡፡ ከዚህ በመነሳት የመጀመሪያ ዲግሪ ምርቃት ብዙዎች በልዩ ስሜት ያለፉበት ልዩ የሕይወት አጋጣሚ እንደሆነ ይሰማታል፡፡

የምርቃት ዕለት በብዙዎች ዘንድ ትልቅ ቦታ ያለው ቀን ተደርጎ ይታያል፡፡ የተመረቁት ከኮሌጅም ይሁን ከዩኒቨርሲቲ አጋጣሚው ወሳኝ የሕይወት ክስተት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላኛው የሚሸጋገሩበት በተለይም ከትምህርት ወደ ሥራ ዓለም የሚሸጋገሩበት በመሆኑ ለብዙዎች የምርቃት ዕለት ብዙ ደስ የሚያሰኝ ስሜት የሚያስተናግዱበት ነው፡፡

ወቅቱ የምርቃት እንደመሆኑ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች በሚገኙባቸው አካባቢዎች በተለይ ሙሉ ልብስ ለብሰው ወዲያ ወዲህ የሚሉ ወንድ ተመራቂ ተማሪዎች በብዛት ይታያሉ፡፡ ስድስት ኪሎ፣ አምስት ኪሎና አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ወዲያ ወዲህ ከሚሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንቅስቃሴ የተለያዩ ነገሮችን በመመልከት የትኞቹ ተመራቂ ተማሪዎች እንደሆኑ መገመት ላይከብድ ይችላል፡፡ አለባበስ፣ ጥድፊያ፣ የደስታ ስሜትና ሌሎችም በተመራቂ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ላይ የሚስተዋሉ ናቸው፡፡ እንደ ጊዜው፣ የትምህርት ዘመን፣ የሥራ ዕድልና ሌሎችም ነገሮች በተመራቂ ተማሪዎች ላይ የተወሰነ የስሜት ልዩነት ሊያሳድሩ ቢችሉም የምርቃት ዕለት ለተመራቂዎች ልዩ ቀን መሆኑ አያከራክርም፡፡

በ1982 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በውጭ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ጥናት ነበር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያጠናቀቁት፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ከፍተኛ የደርግ ባለሥልጣናት በተገኙበት በልደት አዳራሽ የተካሄደውን የምርቃት ሥነ ሥርዓታቸውን ዛሬም በልዩ ስሜት ያስታውሱታል፡፡ በአዳራሹ የታደመው ተመራቂ በአንድ በኩል እያንዳንዱን ተመራቂ አጅቦ በአዳራሹ የተገኘው ቤተሰብ በሌላ በኩል፣ የእንኳን ደስ ያላችሁ ዜማ፣ በአዳራሹ፣ በቅጥር ጊቢው የሚታየው ነገር ሁሉ ‹‹ከምርቃት ይልቅ የትምህርት ቤት ቆይታዬ ያስደስተኝ ነበር›› የሚሉት አቶ አዲስ መኮንን፣ የማያውቁት አንዳች የደስታ ስሜት ውስጥ እንዲገቡ ግድ ብሎ ነበር፡፡

እሳቸው እንደሚያስታውሱት፣ ተማሪዎችን አጅበው በዩኒቨርሲቲው ቅጥር የተገኙ የተማሪ ቤተሰቦችና ወዳጆች ለተመራቂ ተማሪ ለዩኒቨርሲቲውም ያላቸውን ትልቅ ቦታ ይገልጹ የነበረበት መንገድ ተስተጋብቶ እንደ እሳቸው ያሉ ተመራቂዎች ላይ የሚያጭረው ስሜት የተለየ ነበር፡፡

‹‹ከትምህርት ጫና መላቀቅ፣ ወደ ሥራ ዓለም የመግባት ጉጉት ደስ የሚል ስሜት ያሳድር ነበር›› የሚሉት አቶ አዲስ፣ በጊዜው ለሕክምና ትምህርት ይሰጥ የነበረው ግምት ከፍተኛ ስለነበር ‹‹የሕክምና ተማሪዎች ተመርቃችኋል›› ሲባል በአዳራሹ የነበረው ጭብጨባ የምርቃት ቀናቸውን ሲያስታውሱ ወደ አዕምሯቸው የሚመጣ የመጀመሪያው ነገር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በእሳቸው ዘመን ሁሉም ተማሪ ሥራ ይመደብ ነበር፡፡ መመረቅ በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው፣ ከምሁራን ተርታ የሚያሰልፍ እንደ ለውጥ አጋፋሪ የሚያስቆጥር ነበር፡፡ በተቃራኒው ዛሬም የመመረቅ ደስታና ጉጉት በተመራቂዎች በቤተሰብ ዘንድ ያለ ቢሆንም፣ ከእነ አቶ አዲስ ምርቃት ዘመን ጋር ሲነፃፀር የተለወጡ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የተመራቂ መብዛት፣ ከምርቃት በኋላ ሥራ የማግኘት ያለማግኘት ጉዳይ፣ የኑሮ ውድነትና ሌሎችም፡፡

ያነጋገርናቸው የዘንድሮ ተመራቂዎች የመመረቅ ጉጉትና ደስታቸውን ተናግረው ሳይጨርሱ ሥራ ያለማግኘት ሥጋትና ፍርሃት ስሜታቸው ጭልጥ አድርጎ የሚወስዳቸው ናቸው፡፡ ከዚህ ሲያልፍም ሥራ ቢያገኙ እንኳ ሊቀጠሩ የሚችሉበት ደመወዝ ያለውን የኑሮ ውድነት አይሸከምም የሚል ሥጋት የተጫናቸውም ናቸው፡፡

የመመረቂያ ጥናቷን ባቀረበች ማግስት ነበር በስልክ ያናገርናት፡፡ አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው የ20 ዓመቷ ወጣት ሥነ ሕይወት በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ሆርቲካልቸር አጥንታለች፡፡ ከቤተሰብ መለየትን፣ የተለያየ አመለካከትና እምነት ካላቸው ተማሪዎች ጋር በአንድ ጣሪያ ስር መኖር መቻልን ተለማምዳ እንዲሁም ሌሎች ችግሮችን ተቋቁማ ለመመረቅ በመብቃቷ የምርቃታቸውን ዕለት (ሰኔ 25 ቀን 2008 ዓ.ም.) በጉጉት እንደምትጠብቀው ነግራን ነበር፡፡

አንደኛ ምርጫዋ ነርሲንግ የነበረ ሲሆን ሆርቲካልቸር አራተኛ ምርጫዋ ነበር፡፡ መጀመሪያ ላይ ምርጫዋ ያልሆነ ትምህርትን መቀበል፣ ከቤተሰብ ርቆ መኖር፣ ከማታውቃቸው ልጆች ጋር እንደ ቤተሰብ መኖር መቻል ሥነሕይትን ያሳሰቧት ጉዳዮች ነበሩ ቤተሰብ ግን ሞክራው ካልሆነ ሌላ አማራጭ እንደሚኖር ስላሳመናት በመጨረሻ ወደ መቐለ ሄደች፡፡

ኋላ ትምህርቱን ወደደችው፡፡ ይህ ማለት ግን ችግሮች አልነበሩባትም ማለት አይደለም፡፡ በውኃና በምግብ ትቸገር ነበር፡፡ በተደጋጋሚም ያማት ነበር፡፡ ሌሎች ችግሮችም ነበሩባት፡፡ ቢሆንም ግን ችግሮቹን ተቋቁማ ትምህርቷን ከዳር ለማድረስ ለራሷ ቃል በመግባቷ ለምርቃቷ ዕለት መድረሷ ትልቅ ደስታን እንደፈጠረባት ትናገራለች፡፡

የመመረቂያ ጽሑፏን ካቀረበች በኋላ ደስታዋ ሙሉ ሆኖ ተሰምቷታል፡፡ ምክንያቱም ያገኘችውም ውጤት ጥሩ የሚባል ነበርና፡፡ ቢሆንም ግን ደስታዋ የእውነት ሙሉ ሙሉ አይደለም፡፡ የሚያሳስባትም ነገር አለ፡፡ ‹‹ቀጣዩ ዕርምጃዬ ያሳስበኛል፡፡ ብዙ ተመራቂ ስላለ ሥራ ለማግኘት ውድድሩ ቀላል አይሆንም፡፡ ሥራ ባገኝም የደመወዝ ነገር ያሳስበኛል፡፡ ምክንያቱም የኑሮ ውድነቱ የታወቀ ነው›› ትላለች ሥነሕይወት፡፡

ይህም ቢሆን ግን እንደ አብዛኛው ተማሪ ሥራ አገኝ ይሆን አይሆን በሚለው ሐሳብ ከመጨነቅ ይልቅ ትምህርቷን ከዳር ማድረሷ የፈጠረላትን ደስታ ማጣጣምን የመረጠች ትመስላለች፡፡ ሦስት የቤተሰቧ አባላት በደስታዋ ዕለት ከጎኗ ለመሆን ወደ መቐለ እንደሚሄዱም ገልጻልናለች፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ያጠናችው የ21 ዓመቷ ወይንሸት ደጀኔ ደግሞ ምንም እንኳ ቤተሰቦቿ እሷን ለማስመረቅ ሽርጉድ እያሉ ቢሆንም፣ እሷ ያን ያህልም ደስታው እየተሰማት እንዳልሆነ ትናገራለች፡፡ የመረጠችውን ትምህርት አለማጥናቷ እንዲሁም ሥራ ባላገኝስ የሚለው ሥጋቷ የመመረቅን ስሜት እንዳታጣጥመው አድርጓት ሊሆን እንደሚችል ይሰማታል፡፡ ቀጣዩን ዕርምጃዋን ስታስብ ሥራ ከመፈለግ ይልቅ ወደ ንግድ የመግባት ሐሳብ እንደሚያይልባት ትናገራለች፡፡

ባንድም ይሁን በሌላ መንገድ የመጀመሪያ ዲግሪ ምርቃት ወሳኝ ጊዜ በመሆኑ ብዙዎች በተለያየ መልኩ የሚያስታውሱት ነው፡፡ ትውስታቸውንም በተለያየ መልክ ለማስቀረት ይጥራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...