Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እጃችን ከሚቆረጥ ከገቢያችን ሁለቴ ቫት ይቆረጥ

ሰላም! ሰላም! በአሉና ተባለ የተገነባው ነሲባችን ዛሬም አዲስ ወሬ አግኝቶ ይሄው በየሰፈሩ ቡና ያስወቅጣል አሉ። ምን ተገኘ እንዲሉ አሉባልተኞች አገራችን የፀጥታው ምክር ቤት ተጠባባቂ ምናምን ነገር ሆና ተመረጠች ተብሎ ነው አሉ። እኔ ዝርዝር ሐሳብና ብር ስላስጠላኝ ብዙም ጆሮ አልሰጠሁም። ብቻ ነገር መምዘዝ የማይሳናቸው የነሲባዊ ወሬ ሞገድ አሠራጮች ለተጠባባቂ ለተጠባባቂነትም ታኬታና ገምባሌ ያጠለቀ ሁሉ እኮ ኳስ ተጫዋች ነው ሲሉ ሰማሁ። መቼም እኛ በማካፈልና በማቃለል የሚደርስብን የለም። እንዲሁ ከዓመት ዓመት በፀጉር ስንጠቃ ስንጠዛጠዝ ይሄው መገንዱን መላጣ በመላጣ ሆነ ያለኝ ማን ነበር? እንግዲህ ነገርን ነገር ካነሳው አይቀር አብረን ተነስተን እንፍረጣ እኛም። ይሄውላችሁ ደርሶ ዝቅ ዝቅ ደርሶ ኮሰስ ኮሰስ መደራረግ ብሶብናል። ይሄን ለመታዘብ መቼም በመልሶ ማልማት ሰበብ ጉራንጉር ሰፈር አጣሁ፤ የት ሄጄ ላመሳክር የሚል ካለ ፓርላማውን መጠቆም ነው። ነፍሳቸውን ይማረውና አቶ መለስ ዜናዊ ያኔ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር ሶማሊያ መግባት አለበት ሲሉ በማን ቆዳ ማን ሊቀበር? ምን አገባን? የራሳቸው ጉዳይ ያሉ ብዙ ሩቅ አሳቢ የመሰሉን ሰዎችን አስታውሳለሁ። እኔ ብቻ ሳልሆን እናንተም የአንድ ፖለቲከኛ ዋነኛ መገለጫው ሁሉም ሰው ሊያየው ከሚችለው ባሻገር ነገን የመመተን ተስጦው ነው በሚለው ትስማማላችሁ። ታዲያ ዛሬ አገራችን በዓለም ዙሪያ ሰላም ለሰው ልጆች እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ካደረጉ አገሮች ሁለተኛ ወጥታ ስትወደስ ሰላማዊነት በወሬ፣ በዘፈን አልያም በፕሮፓጋንዳ ብቻ ሳይሆን ዋጋ በመክፈል ጭምር እንደሆነ ስታዩ ያ ቅድም ያልኳችሁ ደርሶ የሰው ሐሳብ (ምናልባት የእኛ ስላልሆነ ብቻ ይሆናል እኮ) የማጣጣል ፖለቲካዊ ኑሯችን ስንት ክብርና ሽልማት እንዳስመለጠን ቁጭ ብላችሁ መቁጠር ነው። ዘመኑ የቁጥር ነው ብዬ እኮ ነው!

እናላችሁ በቀደም ከባሻዬ ልጅ ጋር ስናወጋ ይሄን አሁን ያልኳችሁን ነገርኩት። እኔ የምለው ሰላም በሙዚቃ በፕሮፓጋንዳ አልያም በወሬ ብቻ ሰፍና አታሸልምም ካልከኝ የጋሽ ኦባማ የሰላም ኖቤል ተሸላሚነትን ምን ልትለው ነው? አለኝ። በእሱ ቤት አፋጦኝ ሞቷል። አላወቀም ጠዋት ማታ አምላኬን ከአወዳደቄ ቀድሞ የዘመኑ ፈጣጣና አፋጣጭ ሳይደፋኝ አይቀርም እያልኩ አፈጣጠሬን አሳምረው ብዬ እንደምለምነው። አምላኬም ሲመለስ (መቼም እሱ ሲመለስ ግዑዝ ያናግር አይደል?) አንድ ድንገት በእጄ የገላለጥኳት ጋዜጣ ጳውሎስ ኞኞ ከአራተኛ ክፍል ትምህርቱን ቢያቋርጥም መፀዳጃ ቤት የወደቀ ጽሑፍ ያለበት ወረቀት ሳይቀር አንሥቶ በማንበብ ሙሉ ሰው መሆኑን አጫወተችኝ። እኔ ደግሞ የፀሎቴ መልስ ነው ብዬ ፈለጉን ስከተል ይሄው መንፈቅ ሆነኝ። ፈለጋቸውን አንከተል ብለን እንጂ የአጥቢያ ኮከቦች ነበሩን። ግን ሰው ሲባል የሚያለማውን ሳይሆን የሚማግደውን መከተል ይወዳል። በእኛ ደግሞ ይብሳል። በሌላው የማይብስ እንዳየ ሳወራ እየታዘባችሁኝ ነው? ይሄን ሁሉ ምን አዘባዘበህ እንደምትሉኝ ይገባኛል። ኧረ ከዛም በላይ ይገባኛል።  ጊዜው ለጠየቅነው ጥያቄ ወደኋላ ያጠነጠነ በታሪክ ምስክር የዳበረ አመጣጡ የሚታወቅ ሐሳብ ላይ የተመረኮዘ መልስ ሰልቺዎች እንዳደረገን ይገባኛል። ምናልባት አንዳንዴ ነገር አርዛሚዎች በመሆናችን ብቻ የተጎዳነውን እንደተጎዳን አስበን ብዙ ነገር እያሳጠርን ያለነውም ለዚያ ሳይሆን አይቀርም። ነገራ ነገሩን ትታችሁ ሱሪውን፣ ቀሚሱን፣ ጫማውን፣ ኮቱን፣ ቲሸርቱን ማየት ብቻ ይበቃል። በበኩሌ ሰላም አይጠርብን እንጂ ሌላው ከአቅም በላይ ነው። እና ለባሻዬ ልጅ ስመልስለት ምን አልኩት አንተ ንገረኝ እስኪ ማንዴላን ሸልሞ ጋንዲን የነፈገው የኖቤል ሽልማት ተጠሪ ኮሚቴ ከሰላም ነው ከነገር? አልኩታ። የደህና ሰው ፈለግ መከተል ጥቅሙን ታዩልኛላችሁ?!

በተያያዘ ሀሜት ሁለት መቶ ካሬ ላይ ያረፈ ቪላ ቤት ወደዚህ ወደ ሰሚት አካባቢ ላሻሽጥ የቤቱ ባለቤት ቁልፍ ይዞ እስኪደርስ ከገዥዎች ጋር ሻይ ቡና እያልኩ ተቀምጫለሁ። ፊፍቲ ሴንትን በጀርባም በፊቱም የታተመበት ቲሸርት በካኪ ቁምጣ ያደረገ ሞጋጋ መጽሐፍ ሻጭ አዲስ መጽሐፍ። በቃ አዳም ከዚህ ወዲያ አያወጣም እያለ ወርዱና ቁመቱ ከኮንዶሚኒየም መታጠቢያ ቤት መስኮት የማይተናነስ የደለበ መጽሐፍ ማሳየት ጀመረ። አለፍ ብሎ ብቻውን የተቀመጠ ወጣት እስኪ አምጣው ብሎ ተቀበለው። በስመ አብ ሰውዬው ሥራ የለውም እንዴ? ዘጠኝ መቶ ገጽ ልብ ወለድ ይጽፋል? ብሎ እየሳቀ ወደ እኛ ተመለከተ። ደንበኞቼ በዕድሜ ጠና ጠና ያሉ ናቸው። ሳይስቁ ሳያዝኑ ሳይተቹ ሳይደግፉ ስሜት ድራሹ በጠፋበት አተኩሮት ያዩታል። ሻጩ ኧረ ምርጥ ጸሐፊ ነው። ይሄው ከወጣ ስንት ቀኑ ግን አታገኘውም አልቋል ይላል መጤነቱ ባልተለመደ የአነጋገር ዘይቤው ይታወቃል። ስንት ነው ለመሆኑ ብሎ የመጽሐፉን ጀርባ ሲገለብጠው ከእጁ አምልጦ ወደቀ። ደንግጦ ሲያነሳው ዘግይቶ ነበር። የመጽሐፉ ርዕስ በጭቃ ቀለም ቀልሟል። ባለ ቁምጣው መጽሐፍ ነጋዴ ሦስት ዕርምጃ ወደኋላ እያፈገፈገ እሱን መጽሐፍ መልሼ እንደማልቀበልህ እወቅ ሲለው ልጁ 350 ብር ዋጋው እንደሆነ ሲያይ አንድ ሆነ። ያለችውን አውጥቶ፣ ግማሹን ሲከፍል ግማሹን ከግማሽ ሰዓት በኋላ ጓደኛው መጥቶ ከፈለ። ይሄኔ አጠገቤ ወንበረኞች በሹክሹክታ ይሄን መጽሐፍ ዛሬ ባይጨርሰው ምን አለ በለን እያሉኝ ስንስቅ ቆየን። ከሳቁ ባሻገር መልዕክቱ በአሳር ዘርተን በመከራ ካላጨድን የማይሆንልን እስከ መቼ ነው? የሚል ነው። ባላነበውም ሲወድቅ ያየሁት መጽሐፍ ዘጠኝ መቶ ገጽ የፈጀው እንዲያ ለማለት መሰለኝ!

ደንበኞቼ ቤቱን ጊዜ ወስደው ካዩትና ከተማከሩ በኋላ እንደሚያስቀሩት ሲያበስሩ ወዲያው አንዳንድ ነገር ለማጻፍ አጠገባችን ያገኘው ኢንተርኔት ቤት ገባን። ኢተርኔት ቤት መሆኑን የምታውቁት ኮምፒውተር ስታዩ እንጂ ውስጡ ያለው ሰልፍAnchor ዳቦ ቤት ወይንም ታክሲ ተራ  . . . . እእ . .  እናንተ ሠልፍ የሌለበት ስለሌለ እኮ አንዱን መጥራት የጨነቀኝ። ደንበኛዬ አንድ ወረቀት ከዶሴው መዞ አገልግሎት ሰጪውን ታታሪ ወጣት ኮፒ እንዲያደርግልን ሲጠይቀው አያይዞ ዲቪ ወጣ እንዴ? አለው። አይ የሲሪን ፊልም እያስጫኑ ነው ብሎ መለሰ። ምንድነው ሲሪ? ጠየኩ እኔ። ተከታታይ ፊልም። ይሄው ይሄ ሁሉ ተከታታይ ፊልም ነውብሎ ዙሪያውን ግድግዳ ላይ የተለጠፉትን ከተዋጊ እስከ መልከኛና ጨዋ አክተሮች ተደርድረው አሳየኝ። ይሄን በተከታታይ ፊልም ያበደ የትውልዱን ግርግር ካየሁ በኋላ፣ ከባሻዬ ልጅ ጋር ስንጫወት በመሠረቱ ዕድሜ እዚህ ውስጥ ቦታ የለውም። ደግሞም ፊልም ለምን አያችሁ አይባልም እያለ ትዝብቴን ማጣጣል ጀመረ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ አንዳንዴ ትላንት የተናገረውን ዛሬ የሚረሳው ነገር አለ። ቀለብ አድርጌ አንተ አይደለህም እንዴ በቀደም የዚህ አገር መፃኢ ፋንታ በሚቀጥሉት 20 እና 25 ዓመታት ይወሰናል። አሁን የምታየው የካፒታል ወደተወሰኑ ሰዎችና ቦታዎች መከማቸት እየቀጠለ ሲሄድ ብለህ ፍሬድሪክ ኤንግልስ በእንግሊዝ የታዘበውን የወዝ አደሮች ሁኔታ አስታውሰህ፣ ሕዝብ በተወሰኑ ስፍራዎች ስለሚከማች ወዝ አደርና ቡርዧ በሚባሉ ሁለት መደቦች (ያለ ምንም ተላላፊ መደብ) ኅብረተሰብ ታቁሮ ይቀራል። ስለዚህ ከተሠራ አሁን ነው። ከታደገ አሁን ነው። ስትል የነበረው? ታዲያ በማያልቅ የሲሪ ግርግር ዕድሜ ተቃጥሎ ወጣቱ ሕይወቱን መቼ ሊያሻሽል ነው? ስለው ዝም አለ ብላችሁ ታምኑኛላችሁ? አንዳንዴ እኮ ከአጉል ሙግቴ መፍትሔው የትላንቱን ጨዋታ ማስታወስ በቂ ነው። የትላንቱን ስላችሁ ለሠራተኛው መደብ የቆመውን ፍልስፍናም ጭምር ነው እሺ!

በሉ እንሰነባበት። ማንጠግቦሽ አትክልት ተራዋ ውላ መግባቷ ነበር። የምትይዘው የምትጨብጠው አጥታ ዝም አልክ? ብላ ወደ እኔ ዞረች። ምን ተፈጠረ? ብዬ ሳልጨርስ እንዳለ የአትክልት ዘር በአምስት በስድስት ብር መጨመሩን ነገረችኝ። በተለይ የቲማቲም ነገር አንገብግቧታል። አንዳንዴ ማንጠግቦሽ እንዲህ ስትንገበገብ ይገርመኛል። የማወጣው እኔ የምትገዛው እሷ። ይሄን ያህል ምን ያንገበግባል የዋጋ ቅጥ ማጣት? ስል ከየት መጣ ሳልለው አላየሃቸውማ! አላየሃቸውም! ይለኛል የባሻዬ ልጅ። ገብቷችኋል መሰለለኝ። እናላችሁ የማንጠግቦሽን ንዴት ለመሸሽ በቀን ወደማዘወትራት ግሮሠሪ ስሄድ እዛም ወሬው የአትክልት ተራ ወሬ ነጋዴዎች ጉዳይ ነው። ቫት ተመዝገቡ ሲሏቸው እኮ ነው ብን ብለው ጠፍተው፣ ገበያውን ጭር አርገውት ሁሉ ነገር የተወደደው ሲል አንዱ፣ እና ምን ያደርጉ? እስከ ዛሬ የት ነበሩ እነሱስ? ብሎ በደምሳሳው ያወራል። መጀመሪያ የተሰበሰበው የቫት ገንዘብ ምን ተሠራበት? የት ደረሰ? የሚለው ላይ ሳንስማማ እስኪ አሁን ደህና ሠርተው የሚያድሩትን ሰዎች ማስበርገግ ምን ይረባል? የጠፉት የቁጠባ ቤት ብሎኮች ጉዳይ በጥያቄ ብቻ ነው እንዴ መቅረት ያለበት? የስኳሩስ በቃ ዝም ዝም ነው? ሲል ወዲያ ማዶ አጠገቤ ያሉት ኧረ ባክህ በቃህ። ነገር ሊያመጣብን ነው እንዴ? እያሉ የጀመሩትን ሳይጨርሱ ሒሳብ ከፍለው ወጡ። ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ አይወጣም ሲባል ሰምታችኋል፤ ታዲያ ዛሬ ሁለት እጅ አለኝ ተብሎ ሁለቴ ቫት ይቆረጣል? ብለን ብንሰነባበትስ? እጃችን ከመቆረጡ በፊት ማለቴ ነው። መልካም ሰንበት!

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት