Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊትውስታ

ትውስታ

ቀን:

ሰአሊቷ የአጥንት ካንሰር እንዳለባት ያወቀችው ከስምንት ዓመት በፊት ነበር፡፡ ለዓመታት ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ብትዋጥም ከበሽታዋ ለመፈወስ ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም፡፡ ከዘመናዊ ዶክተሮች እስከ ባህላዊ ሕክምና ሰጪዎች የሁሉንም በር አንኳኳች፡፡ መዳን ግን አልቻለችም፡፡ እስትንፋሷ የሚያቆምበት ቀን እየተቃረበ እንደሆነ ማሰብ ሰላም ነሳት፡፡ ቀሪ ሕይወቷን በደስታ ለማሰለፍ፣ ባለፉት ዓመታት ያሳለፈቻቸውን መልካም ጊዜያት በሥነ ጥበብ ማስታወስ የተሻለ እንደሆነ ስታምን ግን መረጋጋት ጀመረች፡፡ ከካንሰር ጋር ያደረገችውን ትግል የሚያሳዩ ፎቶግራፎችና ረቂቅ (አብስትራክት) ስዕሎች፣ እንደመስታወቷ ያሉ ቁሳቁሶች፣ ቅርጻ ቅርጾች እንዲሁም የፀጉሯን ቁርጥራጮች በተለያዩ ቁሳቁሶች ውስጥ አድርጋ ትልቅ ዐውደ ርዕይ አዘጋጀች፡፡

ሰአሊቷ ካይሊን አንደርስ ትባላለች፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኒውዮርክ ውስጥ ያሳየችው ዐውደ ርዕይ የዓለም መገናኛ ብዙኃንና የሥነ ጥበብ አፍቃሪዎችን ቀልብ ስቧል፡፡ ካንሰር እንዳለባት ከማወቋ በፊትና በኋላም ያለፈችበትን፣ አመለካከቷንና ትውስታዎቿን ለዓለም እነሆ ያለችው ሰአሊት፣ ሕይወቷ ቢያልፍ እንኳን አሻራዋ እንደሚቀር በማመን ነው፡፡

ሰዎች በዚህ ምድር ላይ ሳሉ የሚያሳልፏቸውን በጎም ይሁን መጥፎ ጊዜያት ወደኋላ መለስ ብለው ማስታወሳቸው አይቀርም፡፡ አንዳንዶች እንደ ሰአሊቷ በዚህ ምድር ላይ የነበራቸውን ጊዜ ለማስታወስ ዘወትር የሚገለገሉባቸውን ቁሳቁሶች አልያም አንድ ወቅትን ያስታውሰናል የሚሉትን ማንኛውም ነገር ያስቀምጣሉ፡፡ ወደኋላ እየተመለሱም ሕይወት ያስረገጠቻቸውን ቦታዎች ዳግም ይቃኛሉ፡፡

የብዙዎች ምርጫ የሆነው ፎቶግራፍ በትውስታ ዘመናትን ከሚያሻግሩ መንገዶች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ቪዲዮ፣ የውሎ ማስታወሻ (ዲያሪ)፣ ቁሳቁስና አልባሳትም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከግል ትዝታዎች ጀምሮ የቤተሰብ፣ የአካባቢንና የአገርንም ታሪክ በመመዝገብ ትውስታዎቻቸውን ለማቆየት የሚጣጣሩ ሰዎች መኖራቸው ባያጠያይቅም፣ ያለፈን ለማስታወስ አንዳች ሙከራ የማያደርጉም ይኖራሉ፡፡

የፀጉር ቁራጭና ጥፍርን የመሳሰሉ የሰውነት ክፍሎቻቸውን ወይም የሌላ ሰውን በማቆየት ማስታወስ ወደሚፈልጉት ዘመን እንደ መጓጓዣ የሚጠቀሙባቸው ገጥመውናል፡፡ እግራቸው የረገጠውን አካባቢና በተለያየ ወቅት ያገኟቸው ሰዎችን ማስታወሻ ይሆናል ያሉትን ማንኛውም ነገር የሚሰበሰቡት አቶ ገናና ካሳ፣ ‹‹ያለፍኩባቸውን ነገሮች በአጠቃላይ መዘንጋት ስለማልፈልግ የምጥለው ዕቃ የለም፤›› ይላሉ፡፡

በሕይወታቸው የሚገጥሟቸውን ጉልህ ነገሮች ለማስታወስ ትልቁን ድርሻ የሚሰጡት ለፎቶና የጽሑፍ መዝገቦቻቸው ነው፡፡ የመጀመሪያ ፎቷቸውን የተነሱት የ13 ዓመት ልጅ ሳሉ ሲሆን፣ እስካሁን ማለትም 65 ዓመታቸው ድረስ ፎቶ መነሳት በሚችሉበት ቦታ ሁሉ ይነሳሉ፡፡ በትምህርት፣ በሥራና ማኅበራዊ መስተጋብር ከሚያገኟቸው ሰዎች ጋር ፎቶ አላቸው፡፡ ቦታዎችና የቤት እንስሳዎቻቸውን ሳይቀር በካሜራቸው ያስቀራሉ፡፡ ፎቶ ማንሳት ብቻውን በቂ ስለማይመስላቸው የየዕለት ውሏቸውንም በጽሑፍ ያስቀምጣሉ፡፡

ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ መጻሕፍት፣ ስብሰባዎች ላይ የሚሰጧቸው ማስታወሻ ደብተሮችና እስኪርቢቶ ሳይጻፍባቸው፣ ደብዳቤዎች፣ ፖስተሮች፣ ሳንቲሞች፣ የብር ኖቶች፣ የተለያየ ድርጅት አርማ የሰፈረባቸው ቲሸርቶችና ኮፍያዎች፣ የሠርግና ተስካር ወረቀት ያስቀምጣሉ፡፡ ‹‹በመጀመሪያ ደመወዜ የገዛሁት ሬዲዮ፣ የሠርግ ልብሴ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች የሰበሰብኳቸው የእጽዋት ዓይነቶችና ብዙ ነገሮችም አስቀምጣለሁ፡፡ ትውስታዬን የማቆይባቸው ቢሆኑም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቤት እያጣበቡ ስለመጡ ባለቤቴ ደስተኛ አይደለችም፤›› ይላሉ፡፡

በሕይወታቸው የሚገጥሟቸውን መልካምም ይሁን መጥፎ ጊዜዎች በሚያስቀምጧቸው ነገሮች ያስታውሳሉ፡፡ ልጆቻቸው ሲነጋገሩ በካሴት ይቀዳሉ፡፡ እህታቸው ሲያርፉ የነበረው የለቅሶ ሥነ ሥርዓት በቪዲዮ አላቸው፡፡ ቤታቸው ለሚሄድ እንግዳ፣ ‹‹ይኼ የአፋር ቅጠል ይኼ ከምፅዋ ያመጣሁት ሼል ነው፤›› እያሉ ያሳዩና ታሪኩን ያወሳሉ፡፡ የወጣትነት ዘመናቸውን ማስታወስ እንደሚያስደስታቸው የሚናገሩት አቶ ገናና፣ ትውስታን ለማቆየት የሚደረግን ጥረት ለልጆቻቸውም እንዳወረሱ ይገልጻሉ፡፡ ልጆቻቸው የተማሩበትን ደብተር፣ ዩኒፎርምና ሌሎችም ቁሳቁሶች እንዲያስቀምጡ ያበረታታሉ፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ በዘመነ ደርግና ኢሕአዴግ ያሉ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለምን የሚያሳዩ መጻሕፍትና ጽሑፎች፣ ለእሳቸው ዘመንን ማያ ናቸው፡፡

‹‹ሕይወት ከምንገምተው በላይ አጭር ነው፡፡ በሕይወት ሳለን ለሚገጥሙን ነገሮች ቦታ መስጠት ካለፉም በኋላ ማስታወስ አለብን፤›› ይላሉ፡፡ ከሚያስቀሯቸው ትውስታዎች በተጨማሪ፣ በሚሄዱባቸው ቦታዎችም ትዝታቸውን ለማቆየት ይሞክራሉ፡፡ ብዙ ጊዜ የማይሄዱባቸው አገሮች ሲሄዱ፣ እንጨት ወይም የቤት ግድግዳ ላይ ስማቸውን ይቀርጻሉ፡፡

እንዳሻው በኃይሉ የየዘመኑን ታሪክ ለማስታወስ የሙዚቃ አልሞችን ይሰበስባል፡፡ አልበሞቹ የወጡበት ትዝታ ጥሎበት ካለፈው ሁነት በፊትም ይሁን በኋላ አልበሞቹን አፈላልጎ ያስቀምጣል፡፡ ያደገበት ሰፈር ጠላ ቤት የነበራቸው ሴት ዘወትር የዚነት ሙሀባን አንድ አልበም ይከፍቱ ነበርና ካደገ በኋላ ወቅቱን ለማስታወስ ሲል አልበሙን ገዝቶታል፡፡ የቅርብ ጓደኛው የሞተበት ወቅት የተሰማውን ሐዘን ታሳቢ በማድረግ ከንዋይ ደበበ አልበሞች በወቅቱ የወጣውን ገዝቶም ቤቱ አስቀምጧል፡፡ በደርግ ወቅት በጦርነት ሳቢያ እግራቸውን ያጡ አንድ ሰው ሁልጊዜ የሒሩት በቀለ፣ ቴዎድሮስ ታደሰና ኩኩ ሰብስቤ አልበሞች ይሰሙ ነበር፡፡ ሰውየው የሚኖሩበት አካባቢ እየሄደ ያዋራቸው ነበር፡፡ የእነዚህን ዘፋኞች አልበም የገዛውም ከእሳቸው ጋር የነበረውን ጭውውቶች ለማስታወስ ነው፡፡ የሙዚቃዎቹ የጥራት ደረጃ የእሱ ጥያቄ አይደለም፡፡ አልበሞቹ የሕይወቱ ነፀብራቅ እንደሆኑ ያምናል እንጂ፡፡

ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ አልበሞችን በማሰባሰብ ሥራ የተጠመደው እንዳሻው፣ ‹‹በተለይ በልጅነቴ የነበሩኝን ትዝታዎች የማስታውሰው ከሙዚቃ ጋር አገናኝቼ ነው፡፡ አንዳንዶቹን አልበሞች ለማግኘት ከባድ ቢሆንም ትውስታዬን ለማቆየት ስል እንደምንም ለማግኘት እሞክራለሁ፤›› ይላል፡፡ ልጅ ሳለ ይወዳት የነበረችውና ከብዙ ትውስታዎቹ ጋር የሚያያይዛት ድምጻዊት ንግስት አበበ የሞተችው አንድ ካሴት ለቃ ነበር፡፡ ይህንን ካሴት ማግኘትም በጣም አስቸጋሪ እንደነበር ይናገራል፡፡

በእሱ እምነት፣ ሰዎች በሕይወታቸው ቦታ የሚሰጧቸው ሁነቶችና ሰዎች ትውስታ ጥለውባቸው ያልፋሉ፡፡ በወቅቱ የተሰማቸውን ስሜት መልሶ ማግኘት ባይቻልም እንኳን ቅጽበቱን ለማስታወስ የሚረዷቸውን ነገሮች ቢይዙ መልካም ነው፡፡ አያቱ በወጣትነታቸው ለየት ያለ ነገር ሲገጥማቸው ልብስ ይገዙና ሳይለብሱ ያስቀምጡ ነበር፡፡ ያልተለበሱ አዳዲስ አልባሳቶቻቸውን እያወጡም ትዝታቸውን ይተርካሉ፡፡ እናቱ ደግሞ የጥንት የቤት ውስጥ መገልገያዎቻቸውን አይጥሉም፡፡

የሰዎች ትውስታ በህሊና ውስጥ ህያው ሆኖ የሚኖር እንጂ በግዑዝ ነገር ላይ የሚያጠነጥን ባይሆንም፣ ቁሳቁሶች ትዝታን ማጫራቸው እንደማይቀር ይገልጻል፡፡ ዘመን ያመጣቸው የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ትውስታን ለማቆየት የሚደረገውን ጥረት ቅርፁን እንደለወጡትም ይናገራል፡፡ ‹‹ዛሬ ትዝታዎች የሚቀመጡት በዕቃ ሳይሆን በሶፍትዌር ነው፤›› ይላል፡፡

ብዙዎች የሚያሳልፉትን ጊዜ፣ ስሜታቸውንና አስተያየታቸውን በማኅበረሰብ ድረገጽ ያሰፍራሉ፡፡ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ትዊተርና ሌሎችም የማኅበረሰብ ድረ ገጾች፣ ላይ ውሎዋን የምታሰፍረው ምልእቲ ግርማ፣ ‹‹በየቀኑ የማደርጋቸው ነገሮች ሲደማመሩ የሕይወቴን አንዱ ክፍል ያሳያሉ፡፡ እነዚህን በፎቶ፣ በቪዲዮ ወይም በጽሑፍ ገጾቼ ላይ የማሰፍረው አንድም ከጓደኞቼ ጋር ለመጋራት ሲሆን፣ ከጊዜ በኋላ ተመልሼ ማየት ብፈልግም በቀላሉ ይገኛሉ፤›› ትላለች፡፡

ምልእቲ 34 ዓመቷ ሲሆን፣ ላለፉት ስምንት ዓመታት በማኅበረሰብ ድረገጽ የልደት፣ የሠርግ፣ የበዓላት እንዲሁም መንገድ ላይ ያየቻቸው አስገራሚ ነገሮችን ፎቶ ትለቃለች፡፡ ስለግላዊ ጉዳዮቿ እንዲሁም በአካባቢዋ ስለምታያቸው ነገሮች ደስታዋንና ሐዘኗን ለመግለጽም ይህንን መንገድ ትመርጣለች፡፡ ትውስታዎቿን ከማስቀመጥ ባለፈ ለማታገኛቸው ወዳጆቿ ስላለችበት ሁኔታ የምትገልጽበት መንገድ እንደሆነ ትገልጻለች፡፡

በገጾቿ ላይ በምትለቃቸው መረጃዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የአመለካከቷን ለውጥ ታያለች፡፡ መረጃዎቿ የሚደርሷቸው ሰዎች የሚሰጧትን አስተያየት ለማስታወስም ተመራጭ መንገድ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ‹‹ለዓመታት ከተለያዩ የወንድ ጓደኞቼ ጋር የነበረኝን ጊዜ ለማስታወስ የፊልም ትኬት፣ የቸኮሌት ልጣጭ፣ የዲዮድራንት ዕቃ፣ የጥርስ ብሩሽ፣ ጠጠር ሁሉ አስቀምጣለሁ፤ እጮኛዬ ግን ያለፉ ግንኙነቶችሽን ሙሉ በሙሉ አልረሳሻቸውም ማለት ነው ብሎ እንድጥላቸው ጠይቆኛል፤›› ትላለች፡፡ ለእሷ ግን እያንዳንዱ ዕቃ በየወቅቱ ምን ዓይነት ሰው እንደነበረች የምታይበት መነጽር ስለሆነ አትጥላቸውም፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ትርሲት ሲሳይ ያለፈን ለማስታወስ ምንም ዓይነት ጥረት እንደማታደርግ ትናገራለች፡፡ ‹‹ባለሁበት ቅጽበት መኖር እንጂ ዛሬን ነገ ተመልሼ እንዳስታውሰው ብዬ ማስታወሻ አልሰበስብም፤›› በማለት ትገልጻለች፡፡ ሰዎች ፎቶ በማንሳት፣ ዕቃ በመሰብሰብ ወይም ስላሳለፉት ጊዜ በመጻፍ ትውስታቸውን ለማቆየት ሲጣጣሩ፣ በቅጽበቱ መኖርን የሚረሱበትም ጊዜ አለ ብላ ታምናለች፡፡

ስለገጠማት አሳዛኝ ነገር ወይም ስላሳለፈችው ጥሩ ጊዜ የሚያስታውሱ ነገሮች ማስቀመጡ፣ በወቅቱ የነበረውን ስሜት መልሶ ስለማያመጣ ትርጉም አለው ብላ አታስብም፡፡ ‹‹ነገሮችን የማስታውሰው በራሳቸው ወደ አዕምሮዬ ሲመጡ እንጂ ላስታውሳቸው ብዬ በመጣጣር አይደለም፤›› ትላለች፡፡ ከብዙ ትዝታዎቿ መካከል የማትረሳው ተፈጥሯዊ አካባቢዎችን የጎበኘችባቸውን ጊዜዎች በመሆኑ ወደቦታዎቹ በመመለስ ዳግም ሐሴት ታገኛለች፡፡

አምና ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ልትመረቅ ሳምንታት ሲቀሯት፣ ግሬዷ ስላልተሟላ እንደማትመረቅ መምህራኗ ይነግሯታል፡፡ በጣም ባዘነችበት በዚያ ወቅት ከጓደኞቿ ጋር መቐለ የሚገኝ ተራራ ለመውጣት ዕቅድ ያወጣሉ፡፡ ጉዞ ላይ ሳሉ ባልተጠበቀ ሁኔታ መምህራኗ ውጤቷ እንደተስተካከለ እንደምትመረቅም ደውለው ይነግሯታል፡፡ ልትገልጸው የማትችለው ደስታ እየተሰማት ተራራውን ይወጣሉ፡፡

ተራራው ጫፍ ላይ ጥርት ባለሰማይ ጸሐይ ስትጠልቅ ያየችበትን ቅጽበት ያህል ተደስታ ባታውቅም፣ በምንም መንገድ ትውስታውን ለማስቀረት አልሞከረችም፡፡ ‹‹በሕይወቴ አስደሳች ዜና የሰማሁበት ቀን ነበር፡፡ እንደዚህ ያሉ ቅጽበቶችን በፎቶ ወይም በጽሑፍ ማስቀረት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ወደ ቦታው ተመልሼ መሄድን እመርጣለሁ፤›› ትላለች፡፡ መመለስ የማትችልባቸው አካባቢዎች ላይ ያሉ ትዝታዎቿን በህሊናዋ ከማስቀመጥ ሌላ አማራጭ አትወስድም፡፡

ለብዙዎች፣ ቅጽበቶችን ለማስታወስ የሚቀመጡ ነገሮች በሕይወታቸው ያሉ ለውጦችን የሚያዩባቸው ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ትውስታዎችን ለማስቀረት ከሚደረገው ጥረት ይልቅ በቅጽበት መኖርን የሚመርጡም አሉ፡፡ ትውስታዎችን በቦታዎች፣ በሰው ወይም የሽቶ ጠረን፣ በተፈጥሯዊ ወቅቶችና ሌሎችም ከሰው ቁጥጥር ውጪ በሆኑ መንገዶች የሚያቆዩም አሉ፡፡ ያለፈ ታሪካቸው ለዛሬ ማንነታቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የሚያምኑ ሰዎች፣ ለልጆቻቸው በሚሰጡት ስም፣ በንቅሳትና መሰል መንገዶች ትዝታን ለማቆየት ይሞክራሉ፡፡

ሪፖርተር በአንድ ወቅት ያነጋገረው ወጣት፣ ያለፈ ታሪኩን መርሳት ስለማይፈልግ ሰውነቱ ላይ በንቅሳት አስፍሮታል፡፡ በስደት ወደ አሜሪካ ከሄደ በኋላ ሕይወት ፈታኝ ነበረ፡፡ እሱና ጓደኞቹ በጥቁርነታቸው የሚደርስባቸውን መገለልና የኑሮን ውጣ ውረድ ለመቋቋም በጋራ መኖር ጀመሩ፡፡ አንድ ቀን በሚኖሩበት አካባቢ በተነሳ ግጭት ከጓደኞቹ አንዱ ሕይወቱ ያልፋል፡፡ ሐዘኑ ሊቀልለት አልቻለም፡፡ የጓደኛውን ሞትና ያሳለፉትን ሕይወት እንደማይረሳው ለማሳየት ዓይኑ ጠርዝ ላይ የእንባ ዘለላ ስዕል ተነቀሰ፡፡ ለእሱና የሚያዩት ሰዎችም ግልጽ ቦታ ስለተቀመጠ ሐዘኑን ዘወትር እንደማይረሳው ይናገራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...