Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርአዲሱ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት የሕወሓት ታጋይ አልነበሩም

አዲሱ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት የሕወሓት ታጋይ አልነበሩም

ቀን:

ሪፖርተር ጋዜጣ በእሑድ ሰኔ 19 ቀን 2008 ዕትሙ ‹‹አቶ ዳኜ መላኩ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ›› በሚለው የዜና ዝርዝር ውስጥ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት አቶ ፀጋይ አስማማው ነጋ የሕወሓት ታጋይ የነበሩ የሚለው ሐሳብ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው ፕሮፋይላቸው ላይ ያልተገለጸና ከእውነት የራቀ በመሆኑ ማስተካከያ ተደርጎ እንዲወጣልን እየጠየቅን፣ ኅብረተሰቡ ስለአዲሶቹ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የበላይ አመራር ተሿሚዎች ማንነትና የሥራ ልምድ የተመለከተ የተሟላ መረጃ እንዲኖረው የተሿሚዎችን ፕሮፋይል የያዘ ሰነድ ከዚህ ደብዳቤ ጋር አያይዘን የላክንላችሁ መሆኑን እገልጻለሁ፡፡

(አቶ ልዑል ሐጎስ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር) 

* * *

ለኋጂዬን መሬት ለመስጠት ሲባል ሜዳ ተጥለናል

ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ምክንያት ሕዝብ ያላግባብ እየተበደለ መሆኑንና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሕዝቡን እያስመረረና በሕዝብ መበደልና መጨነቅ እንዲሁም ለተለያየ ችግር መዳረግ የሚያስደስታቸው አመራሮች ያሉ ይመስላል፡፡

 የታደለ አገር ለሕዝቡ ቅድሚያ በመስጠት የሕዝቡን ችግር በአግባቡ ያስተናግዳል፡፡ በዚህ በእኛ ክፍለ ከተማ ግን ሕዝብና መንግሥትን የሚያጋጭ ኢሰብዓዊ ድርጊት እየተፈጸመ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት የነበሩ አመራሮች ሕዝቡን ሰብስበው በሚያነጋግሩበት ወቅት፣ አካባቢው ለቻይናው ኋጂዬን ጫማ ፋብሪካ የተሸጠ በመሆኑ እያንዳንዱ ነዋሪም ሆነ ገበሬ እንዲነሳ በአግባቡ ለነዋሪው 75 ካሬ ሜትር፣ ለገበሬም አስፈላጊው ግምትና ቦታ በመስጠት ነው ሕዝቡን የምናስነሳው በማለት ገልጸውልን ነበር፡፡ ነገር ግን የገቡትን ቃል ወደ ጐን በመተው ሕዝቡን በደሉት እንጂ ሕዝቡ ልማትን አልተቃወመም፡፡ ልማቱን እንደግፋለን ነዋሪውንና ገበሬውን በአግባቡ እስካነሳችሁት ምናለብን የምታነሱን ከሆነ በማለት በመግባባት የተደረገው ስብሰባ በ2004 ዓ.ም. በሰላም ተጠናቆ ነበር፡፡

ነገር ግን አሁን ያሉት አመራሮች በክፍለ ከተማ ደረጃ ሕዝቡ ምን እንደበደላቸው በማናውቅበት ሁኔታ፣ ሕዝብን ለማገልገል ከተመደቡ አመራሮች የማይጠበቅ ግፍና በደል እያደረሱ ነው፡፡ ቤታችንን በቤታችን ዕቃና ቁሳቁስ ላይ ግሬደር በመንዳት አፍርሰውብናል፡፡ ምንም ዓይነት መጠለያ ሳይሰጡን ሜዳ ላይ ወድቀን ከዛሬ ነገ ልጆቻችንን ጅብ ነጠቀን እያልን ለሊቱን በሥጋትና በሰቀቀን እያሳለፍን እንገኛለን፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከላይ ዝናቡ ከሥር የመሬቱ ቅዝቃዜ እየተፈራረቀብን ስድስትና ሰባት ቤተሰብ ይዘን በስቃይ ላይ እንገኛለን፡፡

ልጆቻችን ትምህርት ቤት ሄደው ሲመለሱ ቤታችን ፈርሶ ሲያዩት ድርቅ ብለው እንባቸው ሲወርድ ማየት እንዴት ከባድ ነው፡፡ የት ነው የምንገባው ትምህርት ልናቆም ነው በቃ በማለት አእምሮአቸው ተረብሾ በስቃይ ላይ እንገኛለን፡፡ እነዚህ ልጆች አገር ተረካቢዎች ናቸው፡፡ አእምሮአቸው ውስጥ ምን እንደሚቀረጽ አስቡት፡፡ ለድሃም እግዚአብሔር አለ፡፡ በእግዚአብሔር ቸርነት እስካሁን ባይተዋር ሆነን እዛው፣ እንዳለን አለን፡፡ ችግራችንን ለሕዝብና ለመንግሥት በማቅረብ መልሱንና መፍትሔውን  የሚያመጣልንን እንሻለን፡፡

በተጨማሪም የክፍለ ከተማችን አመራሮች ሕዝቡን የሚበድሉበት ምክንያት ምን እንደሆነ መንግሥት እንዲያጣራልን እንጠይቃለን፡፡ ምክንያቱም ማዘጋጃ ቤት ወይም ማዕከል ወስኖ ሕዝቡን አስተናግዱ በአግባቡ ምትክ ቦታ ስጡ ብሎ ወስኖ ካወረደ በኋላ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሕገወጦችን አላስተናግድም ያለበት ምክንያት ተገቢ ምላሽ አይደለም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ባወጣው መመርያ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ በይዞታው ላይ አጥርም ሆነ ቤት የሚያሳይ ነገር ካለ እንዲሁም ከሕጋዊው ግለሰብ ቆርሶ የገዛ ከሆነ ይስተናገዳል በማለት ያስቀመጠ ሲሆን፣ በዚህ ደንብና መመርያ የምንስተናገድ በቦታው ከ15 እስከ 19 ዓመት የኖርን እዛው አግብተን ወልደን ልጆቻችንም 17 እና 18 ዓመት የሞላቸውም ነዋሪዎቸ እንገኛለን፡፡ እንግዲህ ክፍለ ከተማው ሕዝብን ንቆ ከሕዝብ አካል እንዳልወጣ ሆና በማሰቃየት፣ ዜጋን በመግፋትና በአጠቃላይ መስተናገድ የሚገባንንም ሰዎች በግፍ ቤታችንን በማፍረስ በደል እየፈጸመብን ስለሆነ፣ ከአልሚዎቹ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንዳለው በማይገባን ሁኔታ ሰብዓዊ ርህራሄ የሚያሳዩ አመራቾችን አይተናል፡፡

ነግ በእኔ በማይሉ አመራሮች የእኛ የድሆቹ ልጆች ከትምህርት እየተፈናቀሉ የእነሱ ልጆች ግን ተንደላቀውና መኪና እየተላከላቸው ለዛውም የመንግሥትና የሕዝብ ገንዘብ ወጥቶ በተገዛ ንብረት እንዲህ እየሆኑ፣ ሕዝቡን ግን በአግባቡ አላስተናግድ ማለታቸው ተገቢ አይደለም፡፡

 እኛ ድሆቹ ለአገራዊ ጉዳይ ጥሪ የሚደረግልን፣ ዳር ድንበር የምናስከብረው እኛው፣ የእኛው የድሃው ልጅ ሆኖ ሳለ እንዲህ መገፋታችን ለምን ይሆን? ድሃው እየተበደለ ስለሆነ ችግራችንን አጣርቶ  ምላሽ የሚያሰጥልን አካል እንደሚኖር እናምናለን፡፡ የለቡ አካባቢ የቻይና ልማት ተነሺ የተባልን የአካባቢው ነዋሪዎች ቦታው ድረስ በመምጣት ማራጣት ለሚፈልግ አካል ሁኔታውን ለማሳየት ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን፡፡

በጠቅላላው

መንግሥት ፍትሕ አሰጣጤንና ሕዝብ አገልጋይነቴን አሻሽላለሁ ብሎ በሚሠራበት ወቅት ፍትሕ ማጠታችን እንዲታወቅልን እንፈልጋለን፡፡ ለቻይናው ኋጂዬን ቦታ የተሰጠበት አግባብ ሕዝቡን ግራ ያጋባ ነው፡፡ እንደ ድሮ አባቶቻችን በጋሻ ከዚህ መልስ እየተባለ መሬት የተሰጠው ይመስል አስቸጋሪ ሁኔታ ተከስቷል፡፡ ከዚህ በላይ ያላችሁ አትገቡም ባሉበት አፍታ፣ በመመርያው መሠረት ካርታ ይሰጣችኋል በማለት በተለያዩ ጊዜያት አራት ጊዜ ከወረዳው ሰነድ ተረክበናል፡፡ በመጨረሻ ግን ለልማቱ የሚሰጠውንና የሚቀረውን ቦታ እንኳ በአግባቡ ሳናውቅ ኋጂዬን የሚፈልገው የቦታ ስፋት ተሻሽሏል በማለት በግፍ ቤታችን ፈርሶብናል፡፡ ራሳቸው እንኳ በትክክል ሳያውቁት በዘመናዊ መንገድ ለተነሺዎች ግልጽ መረጃ ሳይሰጡን ተፈናቅለናል፡፡

አገራችን የኤርትራና ለተለያዩ አገሮች ስደተኞችን ተቀብላና ማረፊያ ሰጥታ እያስተናገደች ባለችበት ወቅት፣ መኖሪያ ተነፍገን ሜዳና ጫካ ሥር ላስቲክ በማንጠፍና በመከለል እየኖርን በችግር ላይ ስለምንገኝ የሚመለከታቸው ተጠይቀው አፋጣኝ ምላሽ ይስጡን፡፡ በኮሚቴ ቅሬታችንን አቅርበን ሊቀበሉ ስላልቻሉ የሚመለከተውን አካል አስፈቅደን የበደላችንን ማስረጃዎችና ቅሬታችንን ለሕዝቡ ለማሰማት በሰላማዊ ሠልፍ እንድንጠይቅ ይፈቀድልን ዘንድ እንማጸናለን፡፡

  • (የለቡ አካባቢ የኋጂዬን ተነሽ ነዋሪዎችና ገበሬዎች)
  • ኤጀንሲው ከቤቴ ለተባረርኩበት ምክንያት ምላሽ ይስጠኝ
  • ስሜ ከዚህ በታች የተገለጸው በቦሌ ክፍለ ከተማ በገርጂ አካባቢ ነዋሪ የሆንኩኝ ግለሰብ፣ ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ የተከራየሁትን ቤት ያውም ለአሥር ዓመት ተመዝግቤና ጠብቄ ያገኘሁትን ቤት ያላግባብ ከሰባት ቤተሰቦቼ ጋር አውጥቶ ጥሎኛል፡፡ በዚህም የተነሳ ከ25 ዓመት በላይ የኖርኩበትን ሠፈር ጭምር ከነእድሬ ሳይቀር እንድለቅ እያስገደደኝ ነው፡፡ ያላግባብ ከቤቴ መባረሬ አግባብ እንዳልሆነ የሚገልጹ የድጋፍ ደብዳቤዎች አያይዤ ባቀርብም ኤጀንሲው ችግሬን ሊፈታልኝ አልቻለም፡፡
  • ስለሆነም የደረሰብኝን የአስተዳደር በደል ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ አያሌ ንብረቶችን ወስዶ የት እንዳደረሳቸው ስለማይታወቅ በዚህ ነፃ ጋዜጣ (ፕሬስ) በኩል  እንዲጠየቅልኝ ስል፣ በተለይ ለኤጀንሲው ያቀረብኩት አቤቱታ ምንም ምላሽ ስላልተሰጠኝ፣ ጭራሽኑ ኃላፊዎቹ ቢሮዬ እንዳይገባ ስላሉ የድጋፍ ደብዳቤዎችና ሌሎች ሰነዶች የት እንደደረሱ እንኳ ሳይገልጽልኝ ስለቀረ ኤጀንሲው ለአቤቱታዬ መልስ መልስ እንዲሰጠኝ ሳሳስብ በታላቅ ትህትና ነው፡፡
  • (አሰፋ ተኮላ፣ ከአዲስ አበባ)  
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...