Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየኢትዮጵያ እግር ኳስ ፊት የተደቀኑት ተግዳሮቶች

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፊት የተደቀኑት ተግዳሮቶች

ቀን:

በዶ/ር ኤልያስ አቢ ሻክራ

የአገራችን እግር ኳስ ልክ እንደ መኪና ፍሬቻ አንዴ ብልጭ አንዴ ድርግም እያለ ይጓዛል፡፡ በኦኑራ የሚሠለጥነው ቡድናችን ሌጎስ ሄዶ 3 ለ 0 ተሸንፎ በቶም ሴንፊት አዲስ አበባ ላይ 2 ለ 2 ወጣ፡፡ በናይጄሪያ ከአምስት ቀን በፊት አርጀንቲናን 4 ለ 0 አሸንፎ ነበር፡፡ የ29ኛው አፍሪካ ዋንጫ የመጀመርያ ግጥሚያ ከዓመት በፊት ዋንጫ ካሸነፈው ዛምቢያ 1 ለ 1 ወጥቶ አድናቆትን ተጎናፀፈ፡፡ ሆኖም ከአራት ቀን በኋላ በሚያስደነግጥ ሁኔታ በቡርኪና ፋሶ 4 ለ 0 ተሸነፈ፡፡ የሚገርመው ከዛምቢያ ጋር ስንጫወት በአሥር ተጫዋቾች ተአምር ሠራን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ቡርኪና ፋሶ ከኛ ጋር በአሥር ሰው ተጫውቶ ያልታሰበና የሚገርም ውጤት አስመዘገበ፡፡ ብራዚል በምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ለመግባት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምርጥ አሥር ቡድኖች ውስጥ ተቀላቅሎ በናይጄሪያ በማያሳፍር ሁኔታ ቢሸነፍም ከሦስት ወር በኋላ በደቡብ አፍሪካው ቻን ደግሞ ቡድናችን አንድም ጎል ሳያገባ ሦስቴ አከታትሎ ተሸንፎ የመጨረሻ ቦታ ይዞ ውድድሩን አጠናቀቀ፡፡ ማሪያኖ ባሬቶ የያዘው ቡድን በማሊ አዲስ አበባ ላይ 2 ለ 0 ተሸንፎ ባልተጠበቀ ሁኔታ ባማኮ ላይ 2 ለ 1 አሸነፈ፡፡ በመጨረሻም ዘንድሮ አልጄርስ ሄዶ በአስደንጋጭ ሁኔታ 7 ለ 1 የተሸነፈው በድናችን አዲስ አበባ በሚገርምና ከዚህ በፊት ባልታየ ሁኔታ 3 ለ 3 ተለያየ፡፡ ወይንም ጠፍቶ አልጠፋ ወይንም በርቶ አልበራ አንድያውን ብቅ ጥልቅ፣ ብልጭ ድርግም እያለ ነው እግር ኳሳችን የሚጓዘው፡፡ ሆኖም የዛሬው ሁኔታ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ከነበረው ሁኔታ የተሻለ መሆኑ ምንም አያጠራጥርም፡፡ ለ31 ዓመታት ከታላቁ አኅጉራዊ ድግስ የተገለለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተካፈለ፡፡ አልፎ ተርፎም በአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው የተመራው ቡድን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ አሥሩ ምርጥ የአኅጉሩ ቡድኖች ውስጥ ተካተተ፡፡ ለዚህ ውጤት ከፍተኛ ምሥጋና ለአሠልጣኙና ለተጨዋቾቹም ይገባቸዋል፡፡ ዓለም ዋንጫ ለመካፈል ገነት በራፍ ደርሶ ሳይሳካለት በናይጄሪያ ተሸንፎ ቀረ፡፡

ሆኖም አንድ መስቀል ወፍ ስለታየች መስከረም ጠብቶ ፀደይ ወቅት ገባ እንደማይባል ሁሉ በታየው ጊዜያዊ ለውጥ እግር ኳሳችን ተሻሻለ፣ ተለወጠ ለማለት አያስደፍርም፡፡ አዲስ የውጭ ዜጋ አሠልጣኝ በብዙ ሺሕ ዶላር ተቀጥሮ ከአንድ ያልተጠበቀ ውጤት በስተቀር (ማሊን ባማኮ ማሸነፍ) ምንም ለውጥ ሳያመጣ አገር ለቆ ሄደ፡፡ አንድ ጥሩ ነገር ሠራ ቢባል አሠልጣኝ ባሬቶ ወጣቶችን ቡድኑ ውስጥ ለማሠለፍ መሞከሩ ነው፡፡ አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንዲያሠለጥን ተመረጠ፡፡ እንደጀመረ ብሔራዊ ቡድናችንን ለቻን ተሳታፊ እንዲሆን አበቃው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሴካፋ ተሳትፎ ሳይሳካለት ወደ ሩዋንዳ አቅንቶ ሁለት ጨዋታዎች ተሸንፎ አንድ አቻ ወጥቶ ለመጀመርያ ጊዜ በቻን ውድድሩ አንድ ግብ አግብቶ ተመለሰ፡፡ በነገራችን ላይ አንድ የሚገርም ክስተት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ማጣሪያ አልፎ በአኅጉራዊ ውድድር በተካፈለ ቁጥር የሚመደበው ከዋንጫው አሸናፊ ጋር ነው፡፡ ለአፍሪካ ዋንጫ ናይጄሪያ፣ ለቻን ሊቢያና ኮንጎ ዲአርሲ፡፡  ለመሆኑ የአገራችን እግር ኳስ ለምንድነው ከተዘፈቀበት ማጥ መውጣት ያልቻለው?  የቻን መሥራች አገር ሆና ሳለ እንደ ግብፅና እንደ ቱኒዚያ እግር ኳሷ አያብለጨልጭም፡፡ የአገራችን ቡድኖች ደካማ በመሆናቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አዳክሞታል፡፡ በአፍሪካ ቻምፕዮንስ ሊግ ሆነ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፏችን በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ብቻ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ ዙር ማለፍ ሳይሳካለት ቀርቶ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ የመጨረሻ ደረጃ ይዞ ጨረሰ፡፡ ደካማ ቡድኖች ደካማ ብሔራዊ ቡድን መፍጠራቸው አያስገርምም፡፡ ነገር  ግን ይህ ክስተት ለምን ተፈጠረ ብሎ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡

በእኔ አመለካከት ያሉትን ችግሮች ተራ በተራ አንስቼ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ ይኼን አምድ ለመጻፍ የፈለኩት በራሴ ተነሳሽነት እንጂ ለማንም ቃል አቀባይ ሆኖ ለማገልገል አይደለም፡፡ የአገሬ እግር ኳስ ውስጥ ስሳተፍ ሰንበት ብሏል፡፡ በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ኮርሶችን በአካል ብቃት ዙሪያ ሰጥቻለሁ፡፡ ከአንድ ሁለት ሦስቴም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሲሰበሰብ የአካል ብቃቱን ገምግሚያለሁ፡፡ ደግሞም ካለፈው ዓመት ጀምሮ በዘመናዊ የመለኪያ መሣሪያዎች የተለያዩ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቡድኖችን ከነምንዝራቸው ለክቼ ተጨባጭ ማስረጃ እጄ ውስጥ ሳለለ ነው ደፍሬ ይኼን ርዕሰ ለመጻፍ የተነሳሳሁት፡፡ አብዛኞቹ የአገራችን እግር ኳስ ተቺዎች በኔ ግምት ስሜታዊ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ምንም ተጨባጭ ማስረጃ ሳይዙ ለመተቸት ይቸኩላሉ፡፡ ስለባርሳ ሲያወሩ ግማሹን እውነት ብቻ ነው የሚያቀርቡት፡፡ ቀሪውን ማስረጃ አስተሳሰባቸውን ስለሚያፈርሰው ይደብቁታል፡፡ ታዲያ የምሁር ሀቀኝነት የሚባል ቃል እንዳለ እስከ ዛሬ ሰምተው አያውቁም እንዴ? የአገራችን ተጫዋቾች በጉልበት፣ ጀፍጥነትና ጀኃይል እንደነ ናይጄሪያ፣ ካሜሩን፣ ኮትዲቯር ስለማይሆኑ ለአካል ብቃት ትኩረት መስጠት አያስፈልግም፣ ጊዜና ጉልበት በከንቱ ማባከን ነው እያሉ ይናገራሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ተጠጋግታችሁ ተጫወቱ የሚባለው የጨዋታ ፍልስፍናና ሥልት ተፈጠረ፣ እንዲስፋፋም ከፍተኛ ቅስቀሳና ግፊት ተደረገ፡፡ ለተወሰነ ጊዜ የእግር ኳስ ኅብረተሰቡን እንዳነጋገረ አያጠራጥርም፡፡ ሆኖም ፈጣሪዎቹ እንዳሰቡት ፍልስፍናቸው ሥር ሰዶ አልያዘላቸውም፡፡ አካልን ወደ ጎን ጥለው ቴክኒክን ወደ ማምለክ ተዳርሰው ነበር፡፡ የባርሴሎናም ቲክታክ አጨዋወት እንደምሳሌ እየተወሰደ ስህተቱ ቀጠለ፡፡ አካል ብቃት እንደማይሠራ አድርገው ያወሩ ጀመር፡፡ ጋርዲዮላ ያስቀመጠውን ወርቃማ ሕግ ማለት እንደ ባርሳ ተጫዋች ኳስ በተጋጣሚው ተጫዋች በተቀማ በአምስት ሴኮንድ ውስጥ መልሶ መንጠቅ እንዳለበት ደብቀው ቴክኒክ ብቻ ይበቃል ብለው ወሰኑ፡፡ ጋርዲዮላ ያስቀመጠው ሕግ ከፍተኛ አካል ብቃት እንደሚያስፈልገው ረሱት፡፡ ባርሳ ለአካል ብቃት ምን ያህል ትኩረት እንደሰጠ የአካል ብቃት አሠልጣኙን ሆዜ ቱስ ድረ ገጽ ገብተው ቢያዩ ከማይሆን ቅዥት ይላቀቁ ነበር፡፡

  1. የአገራችን እግር ኳስ ደረጃ ዝቅተኛ ስለመሆኑ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደረጃ የሚለካው የአገራችን ጋዜጠኞች ወይንም አሠልጣኞች ወይንም ስሜታዊ ደጋፊዎች ባወጡት መስፈርት ሳይሆን የዓለም እግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪና ተቆጣጠሪው በሆነው በፊፋ ብቻ ነው፡፡ ይኼ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ከዓለም አልፎ በአኅጉር ደረጃ ለወኪሎቹ ስፖርቱን እንዲቆጣጠሩ ሥልጣን አሳልፎ ሰጥቷቸዋል፡፡ በየወሩ እያንዳንዱ አገር ስንተኛ ደረጃ እንደተመደበ በዓለም ቀጥሎም በአኅጉር ያወጣል፡፡ ሆኖም ከትላልቅ ውድድሮች የተሻለ መለኪያ አለ ብዬ አልገምትም፡፡ ለኛ በአኅጉር ደረጃ የአፍሪካ ዋንጫ ጥሩ የአቋም መለኪያ ሲሆን፣ ወደ ዓለም ከተሻገርን ደግሞ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እንዲሁም በመጨረሻ ትልቁና ዋና መለኪያ የዓለም ዋንጫ ተቀምጠውልናል፡፡ በአኅጉር ደረጃ አጀማመራችን ጥሩ ሆኖ ሳለ ቀስ በቀስ እየተንሸራተትን ከመድረኩ ተሰወርን፡፡ አንድ ትውልድ ካለፈ በኋላ አገራችን ብቅ ብላ ለጥቂት ጊዜ ታየች፡፡ በኦሊምፒክ ውድድር የዛሬ 48 ዓመት በራፉ ደርሰን በናይጄሪያ ተሸንፈን ሳንካፈል ቀረን፡፡ ከብራዚሉ 2014 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በስተቀር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንዴም የመሳተፍ ዕድል አግኝቶም አያውቅም፡፡ እዚህ ውድድር ብቻ ነው ለመጀመርያ ጊዜ ቡድናችን አሥር ምርጡ ውስጥ ለመግባት የቻለው፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ልዩ መለኪያ መፍጠር አስፈለገ? የአገራችን አትሌቲክስ በሁሉም ኩነቶች ባይሆን እንኳን በሚሳተፍበት ውድድሮች ማንነቱን ማሳወቅና ማሳየት ከተያያዘው ሰንበት ብሏል፡፡ የአገራችን እግር ኳስ ሙያተኞች ስኪዞፍሬኒያ ወይንም የተሰነጠቀ ባህሪ በሚባል ችግር የተያዙ ይመስላሉ፡፡ በአንድ በኩል የዓለም ምርጥ እግር ኳስ ቡድኖችን አድናቂ መሆናቸውን በግልጽ ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እዛ ለመድረስ የማይፈለጉና በተቃራኒው መንገድ እንደሚጓዙ በግልጽ ባያወሩም በተግባር ያሳያሉ፡፡ ልቀጥልና የአካል  ብቃት ልምምድ ያስፈልጋል ወይ ተብለው ሲጠይቁ ያላንዳች ጥርጣሬ ጮክ ብለው ዕምነታቸውን ይገልጣሉ፡፡ ሆኖም ሲሠሩ አይታይም፣ አያሠሩም፣ የሚያሠራ አያስጠጉም፡፡ ውጤታቸው እንደተሳሳቱ በግልጽ ቢያሳያቸውም፣ የኦርጅናሉን ጉድፍ (ድሮ የሠለጠኑበት መንገድ) ደጋግሞ እንደሚያበዛ የፎቶኮፒ መሣሪያ እነሱም ስህተታቸውን ሳያርሙ ዓመት አልፎ በዓመት ሲተካ ይደጋግሙታል፡፡ ባለመድፈራቸው ለመቀየር ፈጽሞ አይሞክሩም፡፡ በአገራችን አባባል ከሚያውቁት መላክ የማያወቁት ሰይጣን ይሻላል ተብሎ ይነገራል፡፡ የአገራችን አሠልጣኞች ደግሞ ከማያውቀት ለውጥና መሻሻል የሚያውቁት ኋላ ቀርነት ይሻላል ብለው ሙጥኝ ብለው ተጣብቀዋል፡፡ የወጣላቸው አሉታዊ ወግ አጥባቂዎች ሆነው ተቀምጠዋል፡፡ ውጤታማ አሠልጣኝ በራሱ የሚተማመን ደፋር፣ የመንደር ወሬ የማይሰማ አወንታዊ ወግ አጥባቂ ነው፡፡ ለውጥ ያመጣልኛል ብሎ ተመራምሮ ያመነበትን አዲስ ግኝት የዕምነቱንና እውቀቱን በር ሳይዘጋ በደስታ ይቀበላል፡፡ ልምምዱን ያስተካክላል፡፡

የሚገርመው በ1966 ዓ.ም. በአገራችን አብዮት ሲፈነዳና የመንግሥት ለውጥ ሲያካሄድ በዚያኑ ተመሳሳይ ወቅት ደግሞ የዓለምም እግር ኳስ ከፍተኛ አብዮት አካሂዶ ነበር፡፡ ዋና አምባሳደሩ የሆነው በቅርቡ ያረፈው ዮሃን ክሮይፍ ከሆላንድ ብሔራዊ ቡድን ጋር አጠቃላይ እግር ኳስ የሚባል አዲስ የአጨዋወት ሥልት አመጣ፡፡ ከመጠን በላይ በቴክኒክ የሚተማመነውን የደቡብ አሜሪካንን እግር ኳስ አፈኑት፣ ገደሉት፡፡ ቴክኒክ ብቻውን የትም እንደማያደርስ በግልጽ ለዓለም የእግር ኳስ ሙያተኛና አፍቃሪ አሳዩ፡፡ የተጫዋቹ ሰውነት ወደ መሣሪያነት እንዲቀየር አደረጉት፡፡ ሁሉም አጥቂ ሁሉም ተከላካይ መሆን አለበት ብለው ካወጁ በኋላ በአንዴ በ90 ደቂቃ ጨዋታ የሚሸፈነው ርቀት ከሰባት ኪሎ ሜትር ወደ 11 እና 12 ኪሎ ሜትር ተሸጋገረ፡፡ እየተራመዱ መጫወት አበቃ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1974 የጀርመኑ ዓለም ዋንጫ ወዲህ ነገሮች ጭራሽ እየከረሩ መጡ፡፡ ስፖርት ሳይንስም በግልጽ ጣልቃ በመግባት የለውጥ ዋና ተዋናይ ሆነ፡፡ ኳስ ለመጫወት ስጦታ ብቻውን እንደማይበቃ በግልጽ ታየ፡፡ የደቡብ አሜሪካ ተጫዋቾች በፈጠሯቸው በቴክኒክ ስጦታ የታደሉ፣ ከአውሮፓውያን ተጫዋቾች የሚበልጡ ስለነበር በቀላሉ የበላይነቱን ይዘው ነግሰው ነበር፡፡ ይኼ አብዮት ከተጀመረ ወዲህ ብራዚል 20 ዓመት ጠብቃ ነው የዓለም ዋንጫ እንደገና ማንሳት የቻለችው፡፡ ከዛም ስምንት ዓመት ጠብቃ ዋንጫ ደግማ ወሰደች (ከዛ በፊት ከ1958 እስከ 1970 በ12 ዓመት ሦስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ ወስዳለች)፡፡ በመጨረሻ አገሯ ላይ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅታ ከፍተኛ ውርደት ነው የተላበሰችው፡፡ ወደ ተራ ቡድን ደረጃ እየወረደች ነው፡፡ አርጀንቲናም እነሆ 30 ዓመት ሆናት የዓለም ዋንጫ ሳታነሳ፡፡ በነገራችን ላይ የዓለም እግር ኳስ ግራቪቲ ማዕከል ከደቡብ አሜሪካ ወደ አውሮፓ የተገለበጠው ከዛን ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ የደቡብ አሜሪካ ተጫዋቾች አልተበተኑም፡፡ የአገራችን አሠልጣኞች ምን ነክቷቸው ነው ታዲያ መላው ዓለም ከተቀበለው ለውጥ ጋር ተቃርነው ወደ ኋላ የቀሩት? የኢቢሲ ጋዜጠኞች የሌላው እግር ኳስ በሩጫ ሲከናወን የኛ ማርሽ መቀየር አቅቶት ከመራመድ አላለፈም ብለው ሲተነትኑ ተሰምተዋል፡፡ ከእውነት የራቀ አነጋገር አይደለም፡፡ ለዚህም ነው የአገራችን ቡድኖች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጭምር ከውጭ ቡድናችን ጋር ሲጋጠሙ ከ70 ደቂቃ በላይ መጫወት የማይችሉት፡፡ በፌዴሬሽኑ ዙሪያ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ አሠልጣኞች፣ እግር ኳስ አካባቢ የሚያንዣብቡ ሙያተኞች፣ ይህን ችግር አለማየታቸው በጣም የሚያስገርምና የሚያስደነግጥ ነው፡፡ ማየት ከማይፈልግ የባሰ ዓይነ ሥውር የለም የሚባለው ለዚህ ነው ለካ፡፡   

  1. የአሠልጣኞቻችን ችሎታ ውስንነት

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የአኅጉሩ ኳስ ዋና አስተዳዳሪ ካፍ ባወጣው መስፈርት የአገራችን አሠልጣኞች የላይሰንሲንግ ሥርዓት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይኼ አካሄድ ጥሩ ጅምር ሆኖ ሳለ እንደሚመስለኝ የሚሰጠው የብቃት ማረጋገጫ (C-B-A ሳይንስ) በሥራ ሲተረጎም አልታየም፡፡ እንደተለመደሙ ዲፕሎማው ከተያዘ በኋላ እንደ በፊቱ ማሠልጠኑን ይቀጠሉበታል፡፡ “Business as usual” ይላሉ ምዕራባውያን፡፡ እነሆ ይኼ አካሄድ ከተቀየሰ ጀምሮ ስድስት ዓመታትን ሆነው፡፡ በዚህን ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ አራት ጊዜ በውጭ አሠልጣኞች ዋንጫ ሲወስድ፣ የኢትዮጵያ ቡና በአሥልጣኝ ውበቱ አባተ፣ ደደቢት ደግሞ ሦስት አሠልጣኞች ተፈራርቀውበት አንድ ጊዜ ሻምፒዮን ሆነዋል፡፡ በአኅጉሩ የክለቦች ውድደር ከቅዱስ ጊዮርጊስ በስተቀር ማንም ሁለተኛው ዙር የገባ የአገራችን ክለብ የለም፡፡ ከዚህ በላይ ማስረጃ ማምጣት የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ከአሠልጠኝ ሚቾ ጀምሮ አስካሁን ድረስ በውጭ አሠልጣኝ ነው ሥልጠናውን የሚያካሂደው፡፡ ሆኖም ከአንዳንድ ትልልቅ የአኅጉሪቱ ክለባት ጋር ተጫውቶ ያስመዘገበው ጥቂት  ጥሩ ውጤቶች በስተቀር የትልቁ ድግስ ተካፋይ ለመሆን አልቻለም፡፡ ይህም የሚያሳየው የአገራችን አሠልጣኞች ከእነዚህ መለስተኛ ችሎታ ካላቸው የውጭ አሠልጣኞች ጋር እንኳን መፎካከር ወይም መወዳዳር አለመቻላቸውን ነው፡፡ እዚህ አገር መጥተው አሠልጥነው ከተመለሱት የውጭ አሠልጣኞች ከተናቀው፣ ከተሰደበው ከዲያጎ ጋርዜቶ በስተቀር ሌሎቹ ደብዛቸው ፈጽሞ እንደ ውኃ ሽታ ጠፍቷል፡፡ ቴፔ ማዜምቤን ይዞ ማሠልጠን በጀመረበት ዓመት ጋርዜቶ ለኮንጎ ዲአርሲ ሻምፕዮንነት አበቃው፣ በዓመቱም ድሉን ደገመው፡፡ በተጨማሪም የአፍሪካ የክለብ ሻምፒዮን ሆነ፡፡

ለመሆኑ ስንቱ አሠልጣኝ ነው በሰውነት መለካት የሚያምነው? በዓመት ስንት ጊዜ የአካል ብቃት ይለካል? ለማስመሰል የአገራችን አሠልጣኞች ዓመቱ መጀመርያ ላይ በአካል ብቃት ግምገማ ይቀድሱና ልምምድ ይጀመራል፡፡ ነገር ግን ሁለተኛ ግምገማ ቢያንስ ከስድስት ሳምንት በኋላ መደረግ ሲገባቸው (ሥልጠናው ለውጥ እንዳመጣ ለማረጋገጥ) ደግመው አያደርጉም፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መጀመርያ ዙር እንደተለመደው አንዳንድ ክለቦች ይከንፋሉ፣ ይበራሉ፡፡ ከዛ ሁለተኛው ዙር ገና ሲጀመር ወገቤን ማለት ይጀምራሉ፡፡ ወራጅ ቀጣና የሚደርሱም ታይተዋል፡፡ እንደተለመደው ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱ ይረከብና ጉዞውን ይጨርስና ሻምፒዮን ይሆናል፡፡

ከጥቂት አሠልጣኞች በስተቀር እንግሊዝኛ የሚናገርና የሚያነብ የለም፡፡ በአማርኛ የተጻፉ መጽሐፍት ስለሌሉ የአገራችን አሠልጣኞች ዕውቀት በጣም ውስን ነው፡፡ ዕውቀታቸውን ለማሻሻል አጋጣሚው በጣም ውስን ነው፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት  ከአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር አንድ አሠልጣኝ መጥቶ ኮርሱ መጨረሻ ላይ ነጭ ወረቅት እንዲዞርና ተሳታፊዎች ስማቸውንና  ኢሜይል አድራሻችሁን እንዲጽፉ ጠየቀ፡፡ ወረቀቱ ዞሮ ወደሱ ሲመለስ ሦስት ስም ብቻ ተጽፎ አገኘ፡፡ ይኼን አይቶ ‹‹አሁን ገባኝ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ለምን እንደወደቀ፡፡ ኢሜይል ከሌላችሁ ኢንተርኔት ከፍታችሁ አትጠቀሙም ማለት ነው፡፡ ያለ ኢንተርኔት ዕውቀታችሁ ላይ ወቅታዊ ማሻሻል አታደርጉም ማለት ነው፤›› ብሎ ነገራቸው፡፡ በኢንተርኔት አማካይነት ሌሎች ውጭ አገር ያሉት አሠልጣኞች የደረሱበት ደረጃ ላይ እስከ 70 እና 80 በመቶ ለመጠጋት ይችላሉ፡፡ ከማንም አስመሳይ አካል ብቃት ሙያተኛ ጥገኝነት መላቀቅ ይችላሉ፡፡ በክፍያም አዲስ ግኝቶችን አውጥተው መጠቀም ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ትልቅ አሠልጣኝ ለመሆን ከፈለጉ ቋንቋ መማር እንዲሁም አይቲ መጠቀም የግድ ነው፡፡ አቶ መላኩ ጴጥሮስ ከሲዲኒ ኦሊምፒክ መልስ ብዙ ጥሩ መጽሐፍትን ገዝቶ ነበር፡፡ ድሮ አራት ኪሎ መጽሐፍት ቤት ተቀምጠው ኃላፊዋ እንደነገረችኝ ከሦስትና አራት ሰዎች በስተቀር ማንም አሠልጣኝ መጥቶ አያነባቸውም፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የብዙ ግሩም መጽሐፍት ባለቤት ነው፡፡ ከፈለጉ እዛም ሄደው 9ውቀታቸውን ለማሻሻል ጥሩ አጋጣሚ ያገኛሉ፡፡ ይኼን ለማድረግ ግን ያላንዳች ማንገራገር እንግሊዝኛ ማንበብ የግድ ያስፈልጋል፡፡    

  1. አሠልጣኞቻችንን ስለአካል ብቃት ያላቸው የተሳተተ ግንዛቤ

አሠልጣኞቻችን ስለአካል  ብቃት ያላቸው ዕውቀት ግንዛቤ በጣም የወረደ ነው፡፡ በክለብም ይሁን ብሔራዊ ቡድን ደረጃ የውጭ ውድድር ስንካፈል ተጫዋቾቻችን ትንፋሽ አጥሯቸው ከ70 ደቂቃ በኋላ ሜዳ ውስጥ ነፍሳቸው እንጂ ሥጋቸው በድን ሆኖ ነው ጨዋታውን በስለት የሚጨርሱት፡፡  በዓባይ ቁጭት ወገኖቼ የዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው እያሉ ሲተርቱ ከርመው ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ተረቱ ውድቅ ሆኖ መደ መቅረት ላይ ነው፡፡ ታዲያ ስንት የረጅም ሩጫ ንጉሥ፣ ንግሥት፣ ንጉሠ ነገሥት፣ ንግሥት ነገሥታት ያፈራች ድንቅ አገር እንዴት ትንፋሸ ቢስ ተጨዋቾች ለማፍራት በቃች? ከውጭ አገር የሚመጡት ቡድኖች እነሱ አገራችን ተራሮች ላይ ተወልደው ያደጉ፣ እኛ ደግሞ በራሳችን አገር ባይተዋር መስለን ቁጭ አልን፡፡ ከባህር ወለል አንድ ሺሕ ሜትር ከፍ ብሎ ወደ ላይ ሲወጣ የጽናት ብቃት በአሥር በመቶ ይቀንሳል፡፡ የሚገርመው አዲስ አበባ ሲመጡ ቢያንስ 25 በመቶ የጽናት ችሎታቸው ወርዶ እንኳን እንደፈለጋቸው ይጫወቱብናል፡፡ በአብዛኛው የውጭ  ቡድኖች በአማካይ 17 ኪሎ ሜትር በሰዓት መሮጥ ሲችሉ በአንፃሩ የአገራችን ቡድኖች 13 አያልፉም፡፡ ታዲያ በአበበ ቢቂላ አገር የአበበን ልጆች ትንፋሽ አጠራቸው ብሎ ሊተረትብን ነው? የዛሬ 15 ዓመት ለሁሉም የፕሪሚየር ሊግ አሠልጣኞች አካል ብቃትን በተመለከተ ሥልጠና ሰጥቼ የቱ አካል ብቃት ወሳኝ ነው ብዬ ብጠይቃቸው ሁሉም በአንድ ጽምፅ ጽናት ብለው መለሱልኝ፡፡ ይግረማችሁ አሁንም ቢሆን ይኼን እንደሚመልሱ አትጠራጠሩ፡፡ ታዲያ ካመኑበት ለምን የሚያሠለጥኑትን ቡድን 60 ወይንም 70 ደቂቃ ብቻ እንዲጫወቱ ሳይሆን 90 ደቂቃ እንዲጫወቱ አያዘጋጁትም? ይኼ እንቆቅልሽ መቼ እንደሚፈታ እግዚአብሔር ይወቀው፡፡ የሚገርመውና የሚያስደንቀው ከባህር ወለል የሚመጡት ቡድኖች አዲስ አበባ መጥተው ይፈነጥዙብናል፡፡ ቦሊቪያ ዋና ከተማ ላፓዝ (3,600 ሜትር ከፍታ አላት፡፡ አዲስ አበባ 2,400 ሜትር ከፍታ አላት)፡፡ የሚመጡት እነ ብራዚልና አርጀንቲና ሽንፈትና ውርደትን ተከናንበው ነው የሚመለሱት፡፡ አንድ ጊዜ የፊፋ ኮርስ ላይ እንደታዛቢ ተጋብዤ ዶ/ር ኢስማኢል ጣሀ የሚባሉ ግብፃዊ የካፍ ከፍተኛ ሙያተኛ  (ሦስተኛ አፍሪካ ዋንጫ አዲስ አበባ ላይ የተጫወቱ) ሲያጫውቱኝ ‹‹የሦስተኛው አፍሪካ ዋንጫ ፍጻሜ ዕለት ገና ስንሟሟቅ በኦክስሲጂን ዕጥረት ከጅምሩ ተዳክመን ነበር፡፡ እኩል ለኩል ሆነን 30 ደቂቃ ሲጨመር ድራሻችን ነው የጠፋው፡፡ ለስሙ ነው የቀጠልነው፤›› አሉኝ፡፡ ‹‹ታዲያ እንዴት የናንተ ቡድኖች ተፈጥሮ ያደላቸውን ብልጫ መጠቀም አቃታቸው?›› ብለው በአግራሞት ጠየቁኝ፡፡ ለማታውቁት ሁሉ አንድ የ14 ዓመት ዕድሜ ላይ ያለ የአውሮፓ እግር ኳስ አካዳሚ ወጣት በሰዓት 17 ኪሎ ሜትር ይሮጣል፡፡

የዛሬ 15 ዓመት ጂም በጣም  ብርቅ ነበርና አሠልጣኞቻችን ስንፍናቸውንና አለማወቃቸውን ለመሸፈን ጥሩ ምክንያት ነበራቸው፡፡ አሁን ግን ጂሞች ከዝናብ በኋላ እንደሚበቅል እንጉዳይ በየቦታው ብቅ ብቅ ይላሉ፡፡ ኩባ የተለያዩ ፍርደ ገምድል የአሜሪካን አስተዳሮች በጣሉባት ማዕቀብ ምንም የማሠልጠኛ መሣሪያ ማስገባት ሳትችል ቀርታ ተስፋ ሳትቆርጥ በተገኙት የተለያዩ ቁሳቁሶች (ያረጁ ጎማዎች፣ ከባድ መዶሻዎች ወዘተ) እየተጠቀመች በተለያዩ ስፖርቶች ስንት ድንቅ ስፖርተኞች አፍርታለች፡፡ ሚስጥሩ የአሠልጣኞቿ ከፍተኛ የዕውቀትና ክህሎት ደረጃ ብቻ ነው፡፡ የስፖርት ሳይንስ ዕውቀታቸው ከማንም የምዕራብ ምርጥ አሠልጣኝ የሚወዳደር ነው፡፡ በተለይ የጉልበት ልምምድ አጠቃቀም ከሶቪዬት ኅብረት ተምራ በየስፖርቱ በአግባቡ ትጠቀማለች፡፡ እዚህም አገር አግዳሚ ወንበር፣ የስታዲየም ደረጃ፣ የተለያዩ የጎማ ዓይነቶች፣ ገመዶች፣ መንጠልጠያዎች ያረጁ የመኪና ዲስኮች ወዘተ አልጠፉም፡፡ የጠፋው የስፖርት ሳይንስ ዕወቁቱ ብቻ ነው፡፡ ኢንተርኔት ከፍተው በአሮጌ ትራክተርና ከባድ ተሽከርካሪ ጎማ ምን መሥራት እንደሚቻል ቢያዩ ይገረሙና ይደነቁ ነበር፡፡ እዚህ አገር ክብደት ማንሳት እንደ ኤቦላ ወረርሽን እስከተፈራና እስከተሸሸ ድረስ የአገራችን ስፖርት እዛው እንደቀጨጨ፣ እንደቆረቆዘ ይቀራል፡፡ በአሁኑ ወቅት የጥንካሬ ልምምድ መርሐ ግብር በአብዛኛው ስፖርት ከፍተኛ ቦታ ይዟል፡፡ የዛሬ አምስት ዓመት አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ፕሮፌሰር ፒትሳላዲ የሚባል ከፍተኛ የስፖርት ሳይንስ ተማራማሪ ለታላቁ ሩጫ አስመጥቶ ነበር፡፡ አንድ ጥናት አቅርበው ‹‹ማራቶን ከሁለት ሰዓት በታች መሮጥ ይቻላል ወይ?›› የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ተማራማሪው አስፋልት ላይ  ብቻ መሮጥ ከሁለት ሰዓት በታች መውረድ እንደማይቻልና ማራቶኑ እየፈጠነ ሲሄዱ ወደ ሁለት ሰዓት የጊዜ ወሰን ሲጠጋ የጥንካሬ ልምምድ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የፍጥነትና የጉልበት ጥንካሬ መቀራረብ በደምብ ጠቁመዋል፡፡ ጥንካሬ ለረዥም ሩጫ ካለገለገ ለእግር ኳስ እንዴት አያገለግልም? እዚህ ስለጥንካሬ የሚወራው በጣም የሚገርም ነው፡፡ ያሳጥራል፣ ያደርቃል፣ ይወጥራል፣ መጋጠሚያ ያስራል፣ ባጭሩ ይጎዳል ይባላል፡፡ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በየቀኑ ከኳስ ልምምድ በኋላ ሁሌ ጂም ገብቶ ብረት ይገፋል፡፡ ታዲያ እሱን ካልጎዳው ለምን የኛን ተጫዋች ለይቶ ይጎዳዋል? ሳይንስ ሳይሆን የሰው ልጅ ነው ዘረኛ፡፡ በሙያተኛ የተቀየሰ የጥንካሬ መርሐ ግብር የማንን ጉልበት ይጎዳል? ጥንካሬ ላይ ያለው አሉታዊ አስተሳሰብ ስሰማ የኛ የአፄ ምንሊክ ታሪክ ትዝ  ይለኛል፡፡ ሚስተር ቤንትሊ የሚባል የእንግሊዝ ዜጋ ከጓደኛው ጋር የመጀመርያዋን ተሽከርካሪ መኪና ይዞ አገራችን መጥቶ አዲስ አበባ ገባ፡፡ ንጉሡ ከሹማምንቶቻቸው ጋር ተሰብስበው ትርኢቱን ካዩ በኋላ መኪናዋን ለመንዳት እንደሚፈልጉ ገለጡለት፡፡ እሱም ፈቃደኛ ሆኖ ሊያስነዳቸው ሲፈልግ እቴጌ ጣይቱ፣ ጳጳሱ፣ ካህናቱ፣ እንዲሁም ሹማምንቶቻቸው በአንድነት ‹‹ይቅርቦት ትገለብጦታለች››  ሲሏቸው ደፋሩ ንጉሥ ‹‹እሱን ካልገለበጠችው ለምን እኔን ለይታ ትገለብጠኛለች?››  ብለው ሄደው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መኪና አሽከርካሪ ሆነው ታሪክ ሠሩ፡፡  

  1. የአገራችን ተጫዋቾች ዝቅተኛ የንቃት ደረጃ

የአገራችን እግር ኳስ ተጨዋቾች ስለሙያቸው ያላቸው ግንዛቤ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ስንት ድንቅ ለአብነት የሚጠቀሱ ታላላቅ አትሌቶች ያሏት አገር ነች፡፡ ኳስ ተጨዋቾቻችን ከነዚህ ስፖርተኞች ስንት ነገር መማር በቻሉ ነበር፡፡ አትሌቲክስ ያፈራቸው ጀግኖቻችን ለሙያቸው ያላቸው አክብሮት በጣም የሚያስደንቅ ነበር፡፡ አትሌቶቻችን የልምምድ ሰዓት ማክበር፣ በትክክል መሟሟቅ፣ ከልብ መለማመድ፣ በትክክል መመገብ፣ የሚጠቅማቸውን ተጓዳኝ ልምምዶች በራሳቸው ወጪ (ጂም) በአግባቡ መሥራት፣ በመጨረሻም የእረፍት ጊዜያቸውን በደንብ ማክበር በጣም የሚገርም ነው፡፡ ደንበኛ ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች መሆናቸውን በተግባር ያሳያሉ፡፡ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ለሁለት አሥርት ትልቅ ሯጭ ሆኖ የቆየው ሩጫውን እንደሙያ በደንብ ስላከበረ ብቻ ነው፡፡ በዓለም ደረጃ ፉክክሩ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ለሙያቸው ያላቸው አክብሮት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል፡፡ ችላ ቢሉ በአንዴ ከታላቁ መድረክ ተንሸራተው እንደሚጠፉ አጥብቀው ያውቁታል፡፡ ስንቱ ብቅ ብሎ እንደበራሪ ኮከብ በአንዴ የጠፋው ሙያውን ትኩረት ስላልሰጠው ብቻ ነው፡፡ ከፍተኛ የፕሮፌሽናል ስሜት ተላብሰው ነው የሚሠሩት የሚኖሩት፡፡ የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ከፍተኛ መስዕዋትነት ከፍለዋል፡፡ የተሳካላቸውና ውጤታማ የሆኑት አትሌቶች ከነሱ የሚጠበቅባቸውን ሁሉንም ነገር በጥብቅ ያከብራሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉት አትሌቶች ብዙ ጊዜ ባለማወቅ ወይም በመቸኮል ከመጠን በላይ በመለማመድ የመጠን አለፍ ልምምድ ሰለባ ይሆናሉ፡፡ የአገራችን እግር ኳስ ተጨዋቾች የመጠን አለፍ ልምምድ ሰለባ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ ዓባይ ወደ ግብፅ ማፍሰሱን አቁሞ ፍሰቱ ወደ ደቡብ አፍሪካ ቀየረ እንደማለት ይሆናል፡፡ ከአትሌቶቻችን የእግር ኳስ አሠልጣኞችም ሆኑ ተጨዋቾች ብዙ ሊማሩ ይችላሉ፡፡ ቻምፒዮን ስፖርት የተጋበዘው ፊሊፕ ዳውዝ፣ የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ልምምድ ላይ መጨከን ስለማይፈልጉ ስንፍና እንደሚያጠቃቸው ተናግሯል፡፡ ከባድ ልምምድ ካደረጉ በማግሥቱ አሠልጣኙን ሳይጠይቁ በራሳቸው ፈቃድ ዕረፍት ይወስዳሉ ብሎም ተናግሯል፡፡ የአሜሪካ አሠልጣኞች አንድ ዝነኛ ያደረጋቸው ፍልስፍና ለዓለም ስፖርት ኅብረተሰብ አውርሰዋል፡፡ እሱም ያለ ሕመም/ስቃይ ውጤት አይመጣም የሚል ነው፡፡ የእኛ አትሌቶች ደም እምባ አልቅሰው፣ ነጭ ላብ አፍስሰው፣ ሰውነታቸው ደቅቆ ነው የዓለም ምርጥ ሯጮች ለመሆን የቻሉት፡፡ አንዳንድ የመንደር ኤክስፐርቶች እንዲሁም ስፖርት ሳይሠሩ በስሜት ተነሳስተው የሚያወሩ ሯጮቻችን በተፈጥሮ የታደሉ፣ አሠልጣኝ የማያስፈልጋቸውና በገዛ ጥረታቸው የነገሡ ነው ብለው ይናገራሉ፡፡ እንደዚህ ቀላል ቢሆን ኖሮ በተሳተፍንበት የኦሊምፒክ ማራቶን ወርቅ ባገኘን ነበር፡፡ ለማስታወስ ያህል ከሜክሲኮ ኦሊምፒክ 32 ዓመት በኋላ ጠብቀን ነው ሲድኒ እንደገና ማራቶን ወርቅ ያገኘነው፡፡ የአገራችን አትሌቶች ከባድ ልምምድም እያደረጉ በሮጡበት አጋጣሚ አያሸንፉም እኮ፡፡ በትውልዱ ኬንያዊ ነገር ግን ለአሜሪካ የሚሮጠው በርናርድ ላጋት በበርሊን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአምስት ሺሕ ሜትር ፍጻሜ ውድድር ሳያስበው በቀነኒሳ በቀለ ተበልጦ ከሩጫው በኋላ በሰጠው ቃለ ምልልስ ‹‹እርግጥ ቀነኒሳ በተፈጥሮ የታደለና አስደናቂ አትሌት ነው፣ ነገር ግን የበላይነቱን የያዘው ጨክኖና ያለ ርህራሄ በመለማመዱ ብቻ ነው፤›› ብሎ መለሰ፡፡ የፕሮፌሽናሊዝም አስተሳሰብ ሯጮቻችን በደምብ የተቀበሉት ሲሆን፣ እግር ኳስ ተጫዎቻችን ግን ግቢው አጥር ገና አልደረሱም፡፡ አትሌቲክስ በሁለቱም ፆታዎች ለአብነት የሚጠቀሱ ብዙ ምርጥ አትሌቶች አሉ፡፡ እግር ኳስ ስንሄድ ግን አንድም ሰው የለም፡፡ ምዕራብ አፍሪካ ብንሄድ ስንት የአውሮፓ ሊግ ገብተው ክብር፣ ዝናና ሀብት ያተረፉ ምርጥ ተጫዋቾች አፍርተዋል፡፡ እርግጠኛ ነኝ አንድ ቀን አንድ የአገራችን ተጨዋች አንድ ትልቅ የአውሮፓ ክለብ ገብቶ ተጫውቶ ስም፣ ዝናና ሀብት ቢያገኝ ብዙ ተከታዮች እንደሚያፈራ አትጠራጠሩ፡፡ አንድ ሌላ ጥሩ የአሜሪካኖች አባባል አለ፡፡ ይኼውም ‹‹አስተሳሰብህ ትልቅ ይሁን›› የሚል ነው፡፡ የአገራችን ተጨዋቾች የአስተሳሰባቸው አድማስ ከኢትዮጵያ የማያልፍ ከሆነ ያው የመንደር ሻምፒዮን ሆነው ይቀራሉ፡፡ ሯጮቻችን አድማሳቸውን አስፍተው ኦሊምፒክና ዓለም ሻምፒዮና ነው ምኞታቸው፡፡ ክርስቲያኖ ሮናልዶ አንድ ዕርምጃ ብቻ ሲራመድ 25 ብር ያገኛል፣ ቀጥሎ አንድ ደቂቃ ሲራመድ 1,400 ብር፣ 60 ደቂቃ ከሄደ 84,000 ብር፣ በመጨረሻም በ24 ሰዓት ሁለት ሚሊዮን ብር ያገኛል (በማስታወቂያና ሌሎች የገቢ ምንጮቹን ወደ ጎን አስቀምጠን)፡፡ አንድ ምርጥ የሚባል የአገራችን ተጨዋች ደመወዝ መከፈል ከመጀመሩ በፊት ለሁለት ዓመት 1.6 ሚሊዮን ብር ነበር በፊርማ የሚያገኘው፡፡ ዘንድሮ ደመወዝ መከፈል ከተጀመረ ወዲህ ከፍተኛ ክፍያ 120 ሺሕ ብር በወር ደርሷል፡፡ ሮናልዶ በአንድ ቀን የሚያገኘው የአገራችን ምርጥ ተጨዋች አሁን በአንድ ዓመት ከሚያገኘው በ600 ሺሕ ብር ይበልጣል፡፡ የዘንድሮውን የዱባይ ማራቶን ያሸነፉት ወንዱም ሴቷም የአገራችን ልጆች በነፍስ ወከፍ 200 ሺሕ ዶላር ነው ያገኙት (ጥሩ ሰዓት ካስመዘረቡ ከትጥቅ አምራች ኩባንያ ካገኙት ሽልማት በዓመት ቢያንስ ሁለት ዕጥፍ ያገኛሉ)፡፡ ባለፈው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ካሜሩን የአፍሪካን እግር ኳስ በበላይነት በመራችበት ወቅት በዓመት በእግር ኳስ ተጫዋቾቿ አማካኝነት 270 ሚሊዮን ዩሮ (6.5 ቢሊዮን ብር) ወደ አገሯ ታስገባ ነበር፡፡ ኃይሌ፣ ቀነኒሳ፣ ገብረ እግዚአብሔር፣ ወርቅነሽ፣ ስለሺ፣ ደራርቱ፣ ጌጤ፣ መሠረት፣ ብርሃኔ፣ ጥሩነሽ፣ ዘነበች ወዘተ. ለአገር ያስገቡትን ገንዘብ እንዲሁም ምን ሥራ ላይ እንደሚያውሉት ስናይ በአቅማቸው ለአገር ዕድገት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ የሚደነቅ ነው፡፡ ስለሆነም አንድ የአገራችን ተጫዋች ዲሲፕሊን ተላብሶ በትኩረት ቢለማመድ፣ ክለቡ ቢከፍልለትም ባይከፍልለትም በራሱ ወጪ ጂም ሄዶ ጡንቻዎቹ እስኪቆስሉ ድረስ ብረት ቢገፋ፣ ቤቱ ባገኘው አጋጣሚ ፑሻፕ፣ ሲታፕ ቢሠራ፣ ገመድ ቢዘል፣ ዙረት ቢያቆም፣ ከሌሊት ወፍ ኑሮ ቢርቅ፣ ምግቡን ቢቆጣጠር በትንሽ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ እንደሚደርስ አያጠራጥርም፡፡ የመጨረሻውን የአሜሪካን ስፖርት ሙያተኞች የሚናገሩትን ልጥቀስ ‹‹ልምምድ ሥራ ነው፣ ውድድር ጨዋታ ነው›› የስፖርት ሥነ ልቦና ሙያተኞች ለልምምድ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ልምምድ ከውድድር መክበድ እንዳለበት አሠልጣኞችን አሳምነዋል፣ አስተሳሰባቸውንም ቀይረው በሥራ ላይ እንዲያውሉት አድርገዋል፡፡ ታዲያ መሃል በገባ እንደ ትልቅ የልምምድ ስልት እየተጠቀሙ፣ እየተለማመዱበት ከፍተኛ ውጤት መጠበቅ ከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ሆኖ እየታየ ነው፡፡ በልምምድ ጊዜ የሳቀ በውድድር ጊዜ ያለቅሳል፣ በተቃራኒ መንገድ ደግሞ በልምምድ ወቅት ያለቀሰ በውድድር ጊዜ ይስቃል፡፡ ልምምድ ከበድ ካለ ተጫዋቾች አድማ መትተው አሠልጣኙን እንዲባረር ያደርጋሉ እየተባለ በየቦታው ይወራል፡፡ ሆኖም ከባድ ልምምድና ጨፍጫፊ ልምምድ ፈጽሞ የተለዩ ናቸው፡፡ ከባድ ልምምድ ተጫዋቹን ማድከም አለበት እንጂ መጉዳት የለበትም፡፡ በሳምንት ከአንድ ጊዜ በላይ ከባድ ልምምድ መመደብ የለበትም፡፡ ከሳምንቱ ግጥሚያ ቀን ራቅ ማለት አለበት፡፡ ሰውነት ለማገገም የራሱ የሆነ የጊዜ ገደብ አለው፣ ስለሆነም ይህን መርህ ሳይረሳ አሠልጣኙ የሳምንቱን መርሐ ግብር በደምብ ማዘጋጀት አለበት፡፡ ከባድ ልምምድ በተጨማሪ የሠልጣኙን ሥነ ልቦና ስለሚፈትነው ጠንካራ መንፈስ እንዲላበስ ይረዳዋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

 

 

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...