Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየቴምብር አገሯ ወዴት ነው?

የቴምብር አገሯ ወዴት ነው?

ቀን:

ቴምብር መለጠፍ ግብር መክፈል ነው፡፡ የሚፈጸምበት የራሱ ሕግና መመርያ አለው፡፡ የቴምብር ቀረጥ አዋጅ ቁጥር 110/90 በሕጉ በግልጽ የተዘረዘሩ ሰነዶች የቴምብር ቀረጥ እንዲከፈልባቸው ግዴታ የጣለ ሲሆን፣ ግብሩን አለመክፈልም ያስቀጣል፡፡ ፍትሐ ብሔራዊ ውጤቱም ሰነዱን በፍርድ ቤት መብት ለመጠየቅ እንደማስረጃነት መጠቀም አይቻልም፡፡ የቴምብር ቀረጥ በሁለት መልኩ ሊፈጸም ይችላል፡፡ እስከ 50 ብር ያሉትን ቴምብር ከግብር ሰብሳቢው አካል በመግዛት በመለጠፍ ሲሆን፣ ከዚያ በላይ የሆኑትን ደግሞ በሕጉ የተመለከተው መጠን ስለመከፈሉ በግብር ሰብሳቢው በሚመታ ማህተም ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ በዋናነት የምንዳስሰው ስለ ‹‹5 ብር ቴምብር›› ነው፡፡

የአምስት ብር ቴምብር ከሚለጥፍባቸው ሰነዶች መካከል በብዛት በፍርድ ቤት በየዕለቱ የሚቀርቡት የቃለ መሃላ አቤቱታ አንዱ ነው፡፡ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 205 መሠረት በቃለ መሃላ መረጋገጥ ያለባቸው ለፍርድ ቤት የሚቀርቡ አቤቱታዎች የቴምብር ቀረጥ ሊከፈልባቸው ይገባል፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የአምስት ብር ቴምብር ማግኘት ፈጽሞ የማይቻል ሆኗል፡፡ በዚህ ሰሞን ለፍርድ ቤት በቃለ መሃላ የተረጋገጠ አቤቱታ ለማቅረብ የለፋሁበት መንገድ ችግሩን በትንሹም ቢሆን ሳይገልጸው አይቀርም፡፡ ለወትሮው በፍርድ ቤት ዙሪያ በተኮለኮሉ ራፖር ጸሐፊዎች የማይጠፋው ቴምብር አሁን ራፖርተሮቹ ስሙንም ከሰሙት ዓመት አልፏቸዋል፡፡ ለፍርድ ቤቱ ቅርብ በሆነች ሱቅ ቴምብር እንደሚገኝ ተነግሮኝ ባለሱቁን ስጠይቀው ‹‹ባለ 5 ቴምብር የለኝም፣ ባለ 10 ነው ያለኝ፡፡ ዋጋውም 25 ብር ነው፤›› አለኝ፡፡ እንዴት በዚህ ዋጋ እገዛለሁ ብዬ በአካባቢው ሌላ ሱቅ ወይም ተቋም ብፈልግ አልተሳካልኝም፡፡ ለፍርድ ቤቱ ቅርብ በሆነ የወረዳ ግብር መሰብሰቢያ ቢሮም ብሄድ በክፍለ ከተማ ደረጃ እንጂ በወረዳው እንደማይገኝ ተረዳሁ፡፡ ጉዳዬ ለሚገኝበት ፍርድ ቤት በሚቀርበው የግብር ሰብሳቢው ዋና መሥሪያ ቤትም ብሄድ የለም፡፡ በመጨረሻ የተጠቆምኩት የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ግቢ ውስጥ ስሄድ ተሳካልኝ፡፡ ያገኘሁት ግን የ5 ብር ወይም የ10 ብር ቴምብር ሳይሆን የ20 ብር ቴምብር በብር 21 ብር ዋጋ ነው፡፡ ያንኑ ገዝቼ ቃለ መሃላዬን ለመፈጸም ወደ ፍርድ ቤት አቀናሁ፡፡ የአምስት ብር ቴምብር እንደ አልማዝ ተፈልጋ የማትገኝ መሆኗን የዚያን ዕለት ተረዳሁ፡፡

ቴምብር እንደ ግብር

የቴምብር ቀረጥ የግብር አንዱ ክፍል እንደመሆኑ መልካም የግብር አሰባሰብ ሥርዓት ሊያሟላው የሚገባውን ሥርዓት ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡ አንድ ግብር ፍትሐዊ፣ ተደራሽ፣ ተለጣጭ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ከእነዚህ ባህሪያት ውስጥ ተደራሽነት ለቴምብር ቀረጥ መፈጸም የሚገባው ግን በተግባር የሌላው ባህርይ ነው፡፡ ተደራሽ ሲባል ለግብር ከፋዩ በበቂ ብዛት የቀረበ፣ ለአገልግሎቱ የሚመች ሥርጭት ያለው፣ በትክክለኛ ዋጋው ለሕዝቡ የሚቀርብ ሊሆን ይገባል፡፡ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ የቴምብር ቀረጥ በተለይ ባለ አምስት ብር በገበያ ላይ የለም፡፡ ቢኖር እንኳ መኖሩን ተጠቃሚዎቹ ለመመስከር አይችሉም፡፡ እንዲያውም ግብር ሰብሳቢዎቹ ሳይቀሩ ቴምብር ስለሌላቸው በማህተም የአምስት ብር ግብር ሲሰበስቡ መዋል መደበኛ ሥራቸው ሆኗል፡፡ መንግሥት በአዋጅ እንደቀረ ያልገለጸውን የአምስት ብር ቴምብር ማተም፣ ማብዛት፣ እና ማሠራጨት ለምን እንደከበደ መገመት ያስቸግራል፡፡ በማህተም የቴምብር ቀረጥ ሲሰበሰብም ግብር ሰብሳቢው ተደራሽ ካልሆነ መከፈል ከባድ ነው፡፡ በወረዳ ደረጃ እንኳን አለመገኘቱ የሚገርም ነው፡፡ የቴምብር ቀረጥ ውስብስብ ስለሆነ ነው በክፍለ ከተማ ደረጃ እንዲሰበሰብ የተደረገው? ግብር የበጀቱ ብዙ ድርሻ ያለው አገር ተደራሽነትን የሚያረጋግጥ ሥርዓት ይከተላል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ማስረጃ በሚቀርብባቸው ፍርድ ቤቶች፣ ውል በማያዋውሉ ተቋማት የባለቤትነት መብት የሚተላለፍባቸው ሌሎች ተቋማት የባለቤትነት መብት የሚተላለፍባቸው ድርጅቶች፣ ቃለ መሃላ በሚፈጸምባቸው ሌሎች ተቋማት ቴምብሯ ተደራሽ ካላደረግን እንዴት የመንግሥትን ገቢ ማሳደግ እንችላለን፡፡ የአምስት ብሯ ቴምብር ተደምራ ነው የመንግሥትን ገቢ የምታሳድገው፡፡

የቴምብሯ መጥፋት ውጤት

የአምስት ብር ቴምብር በገበያው ላይ አለመኖሯ ሕዝቡ የሚፈጽመውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግብይት በአግባቡ እንዳይፈጽም ያደርገዋል፤ የግብር መክፈያ ጥቁር ገበያ እንዲስፋፋ ያደርገዋል፣ በተነሳንበት ጉዳይ ደግሞ የሕግ ባለሙያዎች ለፍርድ ቤት አቤቱታ እንኳን ለማቅረብ ይቸገራሉ፡፡

በአምስት ብር ቴምብር ማጣት ውል የማይዋዋሉ፣ ለፍርድ ቤት ቃለ መሃላ የሚያቀርቡ፣ ወዘተ. አካላት ብዙ ናቸው፡፡ ግብር ለሥራ መደናቀፍ መሆን አይገባውም፡፡ ግን ቴምብር ከሌለ ብዙ ነገር መፈጸም አይቻልም፡፡ ለአብነት መነሻ ያደረግነውን ጉዳይ ብንመለከት ጠበቃው ቴምብር ካለጠፈ በቃለ መሃላ የተደገፈ አቤቱታ ለፍርድ ቤት ማቅረብ አይቻልም፡፡ እግድ፣ መጥሪያ መመለስ፣ በሌለበት የተሰጠ ውሳኔ ማስነሳት ወዘተ. አይቻልም ማለት ነው፡፡ በተለይ በጊዜ የተገደበ አቤቱታ ካጋጠመውና ቴምብሯን በፈለጋት ጊዜ ካላገኛት መብቱን በይርጋ ማጣቱ የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡

ቴምብሯ በበቂ መጠን ከሌለች

ሌላው ግብር የሚሰበስብ አካል ባለበት አገር የግብር አሰባሰብ ጥቁር ገበያ ይፈጠራል፡፡ የአምስት ብር ቴምብር 25 ብር የሚሸጥ ከሆነ ከአንድ ሰነድ መንግሥት አንድ እጅ ነጋዴው አምስት እጅ ግብር ሰበሰበ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሕዝቡ በግብር አሰባሰቡ ሥርዓት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው፣ የመንግሥት ሠራተኞች በሥርዓቱ ክፍተት በብልሹ አሠራር እንዲዘፈቁ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የቴምብሯ መጥፋት ውጤቱ ሰፊ በመሆኑ ጆሮ ያለው ሊሰማው የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

ቴምብሯን ምን ይታደጋት?

ችግሩ በጣም የሰፋና የታወቀ ጉዳይ መፍትሔውን መጠቆም ቀላል ነው፡፡ መፍትሔውን መፈጸምም በቂ ዝግጅትና ቁርጠኝነት ከተሰጠው እንዲሁ ቀላል ነው፡፡ የአምስት ብር ቴምብር እንደ አንድ የግብር ዓይነት በአሁኑ ወቅት ያጋጠማት ፈተና የሕልውና ሳይሆን አይቀርም፡፡ በዚህች አጭር ዳሰሳ ለመገንዘብ እንደሚቻለው የቴምብር ቀረጥ አሰባሰብ ቢያንስ ሁለት መሠረታዊያን ችግሮች አሉበት፡፡ የመጀመሪያው የቴምብሯ በበቂ ብዛት ታትማ ለገበያ የመቅረቧ ነገር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የቴምብር ቀረጥ የመሰብሰቢያው የታክስ አስተዳደር ተደራሽነት የማጣት ጉዳይ ነው፡፡ ለችግሩ የሚሰጠው መፍትሔው በእነዚህ ሁለት ነጥቦች ላይ ያጠነጥናል፡፡

የመጀመሪያው መንግሥት ማለትም የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የቴምብር ቀረጥን በበቂ ብዛትና ስፋት እትም ማሠራጨት ይጠበቅበታል፡፡ ቴምብር ለማተም የተለየ ፖሊሲና ሰፊ ተቋማዊ ሥራ የማይፈልግ ሥራ ነው፡፡ ቴምብር በበቂ ሁኔታ አትሞ ሳያቀርብ የቴምብር ቀረጥ የመክፈል ግዴታን በዜጋ ላይ መጣል ፍትሐዊ አይሆንም፡፡

ሁለተኛው መፍትሔ የአምስት ብሯ ቴምብር በበቂ ብዛት ከታተመች በኋላም ለተፈለገው ዓላማ እንድትውል ተቋማዊ ተደራሽነቷን ማረጋገጥ ነው፡፡ ከአምስት ብር እስከ 50 ብር ዋጋ ያላቸው ቴምብሮች ለምን አገልግሎት እንደሚውሉ ይታወቃል፡፡ ቴምብሮቹ ከሚያስፈልጉበት ዐበይት ጉዳዮች አንፃር ባለድርሻ አካላትን በመለየት ግብር ሰብሳቢው አካል የመሰብሰቢያ ዘዴውን ማስፋት ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች፣ ሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ተቋማት፣ መንገድ ትራንስፖርት፣ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ተቋም ወዘተ. በውክልና ቴምብሮቹን ለሕዝቡ ተደራሽ የሚሆንበትን መንገድ ማመቻቸት ይገባል፡፡ በገቢዎች ቅርንጫፎችም ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክፍለ ከተማ ድረስ ቴምብር የሚገኝበትን ሁኔታ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ችግሩ የሚቀጥል ከሆነ ግን ግብር በጥቁር ገበያ እንዳይሰበስቡ ሥጋት አለ፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው ራሚስ ባንክ ዛሬ ሥራ ይጀምራል

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው...