Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የፍትሕ ሥርዓቱ አመኔታ ያተረፈ ሕዝብ የሚቀበለውና በሕግ ብቻ የሚመራ መሆን አለበት››

አቶ ጌታሁን ካሳ፣በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብት ማዕከል የሰብዓዊ መብት መምህርና ተመራማሪ

አቶ ጌታሁን ካሳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብት ማዕከል የሰብዓዊ መብት መምህርና ተመራማሪ ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሕግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሰብዓዊ መብትና በግጭት ማስወገድ ከእንግሊዝ አገር አግኝተዋል፡፡ አሁን በሰብዓዊ መብት  የፒኤችዲ ትምህርት በመከታታል ላይ ይገኛሉ፡፡ በሥራው ዓለም  የትግራይ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ፣ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ዲን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኤግዚኪዩቲቭ ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ከአመሀ መኮንን እና ተባባሪዎቹ የሕግ ቢሮ ጋር በመተባበር ሚያዝያ 29 ቀን ባዘነጀው ዓውደ ጥናት ላይ ‹‹በወንጀል ጉዳዮች የፍትኃዊ ዳኝነት መመዘኛዎች /Fair Trial Standards/ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ተግባራዊ ዕይታ›› በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበው ነበር፡፡ ሰለሞን ጐሹ በጥናታዊ ጽሑፋቸውና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አቶ ጌታሁንን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አጠቃላይ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ይዞታን ለማሻሻል የሕግ ማዕቀፍ ከመዘርጋት፣ ተቋማትን ከመገንባትና አፈጻጸሙን ከማረጋገጥ አኳያ እየሄደችበት ያለው አቅጣጫ ምን ይመስላል?

አቶ ጌታሁን፡- በዚህ በኩል ባለፉት 25 ዓመታት አገሪቱ የሕግ ማዕቀፉን በመዘርጋት፣ ሕጎቹን የሚያስፈጽሙና ዳኝነት የሚሰጡ ተቋማትን በመገንባትና እነዚህ ተቋማት ምን እንዳከናወኑ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት አንድ መለያው ተደርጎ የሚወስደው ሰብዓዊ መብትን በስፋት ዕውቅና መስጠቱ ነው፡፡ ሰብዓዊ መብትን ማክበርና ማስከበር የመንግሥት ግዴታዎች አድርጎ አስቀምጧል፡፡ መብት የመንግሥት ስጦታ አይደለም፡፡ ስለዚህም የመንግሥት ግዴታ መብቶችን ማክበርና ማስከበር ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታት ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ በርካታ የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተዋል፡፡ ዝርዝር ሕጎችና ማሻሻያዎችን ስንመለከት በብዙዎቹ  ሰብዓዊ መብት ዋና ጉዳይ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ሰብዓዊ መብቶች ተግባራዊ ለማድረግ ይኼ ኃላፊነት ያላቸው የመንግሥት ተቋማት ተፈጥረዋል፡፡ እርግጥ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ሰብዓዊ መብትን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡ ስለዚህ መንግሥት መብትን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት፣ መብት ሲጣስ ደግሞ ውጤታማ የሆነ የመፍትሔ ሥርዓት የመዘርጋት ግዴታውን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር የመንግሥት  ተቋማት ይህን ማረጋገጥ ችለዋል ወይ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ መብት አስከባሪ ተቋማት ሥራቸውን የሚያከናውኑበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ወይ ብለንም ልንጠይቅ ይገባል፡፡ የዚህ ምቹ ሁኔታ መገለጫዎችስ ምንድን ናቸው? እዚህ ላይ በአገራችን የሚያሳስቡ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በወንጀል ጉዳዮች ፍትሐዊ ዳኝነት ማግኘት ከእነዚህ አሳሳቢ ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ የገለጹት በምን ምክንያት ነው?

አቶ ጌታሁን፡- የዳኝነት መዋቅር ዋነኛ  መብት ማስከበሪያ ተቋም  ነው፡፡ በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ሕግንና ማስረጃን መሠረት አድርጎ ውሳኔ በመስጠት የሰዎችን የሕይወት፣ የንብረት፣ የነፃነት፣ የእኩልነት  መብቶች ማስከበር አለበት፡፡ አስፈጻሚው አካል ደግሞ ይህንን ማክበርና የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ማስፈጸም አለበት፡፡ የመብት ጥሰት ሲኖርም የሚታረምበት ተቋማዊ አሠራርና ባህል እንዲዳብር የሚያስችሉ ሥራዎችን ማከናወን አለበት፡፡ በሕግ መሠረት ብቻ መሥራት፣ ከሕግ ውጭ ወይም ደግሞ ለሕግ ተፃራሪ የሆኑ ተግባራት ሲፈጸሙ ተጠያቂ እንዲሆን ይጠበቅበታል፡፡ ነገር ግን በአገራችን  ከዚህ አንፃር የሚታዩ ክፍተቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ በሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ስምምነት ላይ ከተደነገጉት አንዱ ማንኛውም ሰው ነፃ በሆነ የዳኝነት ሥርዓት መብቱን የሚወስንበት ሁኔታ መኖር አለበት ይላል፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ነፃነቱን፣ ሀብቱንና ሕይወቱን በሚመለከት የሚሰጡ ውሳኔዎች ከአድልዎ በፀዳ መልኩ ሊሰጡ ይገባል፡፡ ከግለሰብም ጋር ሆነ ከመንግሥት ጋር የሚያገናኝ ጉዳይ በሚፈጠርበት ጊዜ በእኩልነት ማስተናገድ የሚችል የፍትሕ ሥርዓት ሊፈጠር ይገባል፡፡ በእነዚህ መብቶች አፈጻጸም በተለይ ከወንጀል ጉዳዮች አንፃር የሚስተዋሉ ችግሮች መኖራቸው የሚያስማማ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ከአገራችን ሕጎች በተጨማሪ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንም ፈርመናል፡፡ ምን ያህሉ ተግባራዊ እየሆኑን ነው ብልን ብንጠይቅ ግን መልሱ ብዙም አስደሳች የሚሆን አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ሰው ሚዛናዊ የሆነ ፍትሕ (Fair trial) አገኘ የምንለው ምን ሲሟላ ነው? የሚታዩ ችግሮችስ ምንድን ናቸው?

አቶ ጌታሁን፡- በዋነኛነት ማንኛውም ሰው በሕገወጥና በዘፈቀዳዊ አሠራር መብቱን እንዳያጣ ጥበቃ የሚያገኝበት ዋስትና ሲረጋገጥ ነው፡፡ ይኼ የአንድ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊነትም መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ተጠያቂነት ያለበት፣ በሕግ የሚመራ ሥርዓት ስለመኖሩ ለማሳየት የሚያገለግል ነው፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በኢትዮጵያ በርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ ችግሮቹ እንዳሉ ማመን የመፍትሔው መጀመሪያ ነው፡፡ የአፍሪካ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በተደጋጋሚ ባወጣቸው ሪፖርቶችና የውሳኔ ሐሳቦች በአፍሪካ ውስጥ ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ እንደ አንድ ጉልህ ችግር የለየው የፍትሕ ሥርዓት ሚዛናዊነት ማጣትን ነው፡፡ በሕግ ያልተመሠረተ እስር፣ የተራዘመ እስር፣ ምክንያታዊ ያልሆነ የፍትሕ መዘግየት፣ እንደ ንፁህ የመቆጠር መብት መጣስ፣ ኢ ሰብዓዊ የሆነ አያያዝ  ለአብነት ተጠቃሽ የችግሩ መገለጫዎች ናቸው፡፡ የእኛም የፍትሕ ሥርዓት እነዚህ አካባቢዎች ላይ ችግሮች አሉበት፡፡ የመንግሥት ጥናት ሰነዶችም ጭምር ይህንኑ ያሳያሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የችግሩ ዋነኛ ምንጭ ምንድን ነው?

አቶ ጌታሁን፡- የችግሩ ምንጭ በርካታ መልክ ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድ የተለመደ  የአፈጻጸም ችግር ነው የሚል መልስ አለ፡፡ ፖሊሲ ወይም ሕግ  የማይፈጸም ከሆነ ካለመኖር ምንም አይለይም፡፡ የአፈጻጸም የአቅም ክፍተት የሚለው ምላሽ አሁን መልስ ለመሆን አቅም የለውም፡፡ ፖሊሲና ሕግ የሚወጣው ሊፈጸም ነው፡፡ ምናልባት በጣም ውስብስብና የተራቀቁ በሆኑ አንዳንድ ጉዳዮች የአቅም ውስንነት እንደ ምክንያት ሊነሳ ይችል ይሆናል፡፡ ፍትሐዊ ዳኝነትን በተመለከተ ግን ሁሉም የሚታዩት ችግሮች  መፈታት የሚችሉ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ የተራቀቀ አቅም የሚጠይቁ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ አንዱ እንደ ንፁህ የመቆጠር ወይም አስቀድሞ አለመፈረጅ መርህ ነው፡፡ ሁለተኛ ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መርህ ነው፡፡ ሦስተኛ በሕግ አማካሪ የመታገዝ መብት ነው፡፡ አራተኛ በእኩል የመዳኘት መብት ነው፡፡ አምስተኛ በነፃ የዳኝነት አካል የመዳኘት መብት ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የሚታየው ችግር በአቅም ማነስ የመጣ ነው ብሎ ማስቀመጥ ችግሩን መሸሽ ነው፡፡ ጥፋት ተፈጽሟል የሚለው ወገን ጥፋት መፈጸሙን ማስረዳት አለበት፡፡ ተጠርጣሪው ግን ንፁህ ሆኖ ስለሚገመት የማስረዳት ኃላፊነት የለበትም፡፡ ተጣርቶ ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ ቅጣቱን ይቀበላል እንጅ የማስረዳት ሸክም በመሠረቱ የከሳሽ ነው፡፡ እንደ ንፁህ የሚቆጠር ተጠርጣሪ ከፍርድ በፊት የተጋነነና የተራዘመ ቀጠሮና እስር እንዳይጉላላ ተገቢ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ የዋስትና መብቱም ሊጠበቅ ይገባል፡፡ ሁለቱም ወገኖች በፍትሕ ሒደት ውስጥ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በእኩል ጉዳያቸውን እንዲያስረዱ ማስቻል ይገባል፡፡ እነዚህን ለማድረግ ብዙ ጊዜ የሚሰጠው የአፈጻጸም ችግር የሚለው መልስ በእኔ እምነት መልስ ሊሆን የማይገባው ነው፡፡ በአንድ ወቅት ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል እጥረት በነበረበት፣ ከፍተኛ የሆነ ተቋማዊ የአቅም ውስንነት በነበረበት ጊዜ የነበሩ መልሶች ናቸው፡፡ የተቋማት የአቅም ውስንነት አሁንም ያለ ቢሆንም ከሞላ ጎደል እነዚህን ነገሮች ማከናወን የሚችሉ ተቋማት አሉ፡፡ ይልቁንም ችግሩ የተጠያቂነት ሥርዓትን በሚገባ ያለመገንባታችን ውጤት ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- ዋነኛ ችግሩ ከአፈጻጸም ክፍተት ጋር ቢያያዝም የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ዘርፉ ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎች በርካታና ቶሎ ቶሎ መደረጋቸው ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ አድርጓል የሚሉ አሉ፡፡ በዚህ ግምገማ ይስማማሉ?

አቶ ጌታሁን፡- የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓቱ በየጊዜው የማሻሻያ  ፕሮግራሞችን ማከናወኑ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ማሻሻያና ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ ማኅበረሰባዊ ግንኙነት የራሱ የሆነ ውስጣዊ መለዋወጥ (internal dynamics) አለው፡፡ አዳጊና ተለዋዋጭ ግንኙነት ነው፡፡ ስለዚህ የፍትሕ ማሻሻያ ፕሮግራሞች መደረጋቸው ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ፕሮግራሞች ላይ የሚታየኝ ችግር አንዳንዶቹ ሐሳቦችና ማሻሻያዎች ተጀምረው ከመታወቃቸው በፊት ሌላ ማሻሻያ የሚከተልበትን አሠራር ነው፡፡ ይኼ ተቋሞቹ እርጋታ ኖሯቸው እንዳይሠሩ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ አንድ ወቅት ላይ የፍትሕ ቢሮው ሥር ፖሊስና ማረሚያ ቤት ነበሩ፡፡ ሌላ ወቅት ላይ ፖሊስ የሥራ ነፃነት ያስፈልገዋል፣ ስለዚህ ሁለቱ መቀላቀል አይችሉም ተባለ፡፡ በአንድ ወቅት የዓቃቤ ሕግ ሥራ ለብዙ ተቋማት ተከፋፍሎ ነበር፡፡ አሁን ተመልሶ ወደ አንድ ተቋም መጥቷል፡፡ እንደዚህ ዓይነት በበቂ ያልተጠኑ የሚመስሉ መለዋወጦች የተለመዱ ናቸው፡፡  ይኼ ተቋሞቹ ቀጣይነት ያለው ሥራ እንዳይሠሩ እዚህ መሐል የሚፈጠረው የመደራጀትና መልሶ መደራጀት ሥራዎች ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ስለዚህ የተሰጠው አስተያየት የተወሰነ እውነት አለው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2005 ትልቅ የፍትሕ ማሻሻያ ፕሮግራም ጥናት በአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ተደርጎ ነበር፡፡ ጥናቱ መሠረታዊ የሆኑትን ነገሮች ወደ ውይይትና ዕይታ ያመጣ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በተደጋጋሚ ሌሎች የፍትሕ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ጥናቶች ተካሂደዋል፡፡ ለምሳሌ በ2003 ዓ.ም. የፌዴራል ፍትሕ ተቋማት አንድ ላይ ያወጧቸው የፍትሕ ማሻሻያ ፕሮግራም ሰነድ አለ፡፡ ሰነዱ በርካታ ችግሮችን ይዘረዝራል፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት ምን መደረግ አለበት የሚለውን ያስቀምጣል፡፡ ተቋማቱ ይህንን ምን ያህል ይተገብሩታል ብለን ጥያቄ ብናነሳ ግን፣ አጥጋቢ መልስ የምናገኝ አይመስለኝም፡፡   

ሪፖርተር፡- በፖሊሲዎች፣ ሕጎችና የተቋማት አፈጻጸም መካከል በመናበብ ያለመሥራት ችግር በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ በቅርቡ የተቋቋመው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ይህን ለማስተካከል ትልቅ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ ባሻገር ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት?

አቶ ጌታሁን፡- በበቂ ደረጃ የአሠራር ግልጽነት ያለው ሲያጎድል የሚጠየቅ ተቋም መገንባት  ቁልፉ ጉዳይ ነው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አሁን ትልቅ ተቋም ሆኗል፡፡ ያንን ኃላፊነት መወጣት የሚያስችል ተቋማዊ አቅም አለው ወይ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ እሱን ለመመለስ ቆይተን ልናይ ይገባል፡፡ አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ የፍትሕ ሥርዓቱ አንዱ ችግር የአስፈጻሚው ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ የተጠያቂነት ባህላችንና የአስፈጻሚው ተቋም ሥልጣንን የመገደብ ልምዳችን ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ በቅርቡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሬዲዮ ፋና ጋር በመተባበር በተዘጋጀው ውይይት፣ በመንግሥት ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በተዘጋጀ ጥናትና ከተለያዩ ሚዲያዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ከዛሬ 15 ዓመት በፊት እንነጋገርባቸው የነበሩ የፍትሕ ተቋሞቻችን ችግሮች አሁንም እንዳሉ ናቸው፡፡ በሚገባ የሚጠየቅ መንግሥታዊ መዋቅር ገንብተናል ብዬ አላምንም፡፡ ተቋሞቻችን የማይጠይቁና የሚጠየቁ ማድረግ አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ የአስፈጻሚው ተቋም ሥልጣን በሕግ ብቻ ሳይሆን በተግባር የተገደበ ማድረግ ይጠይቃል፡፡ በ2006 ዓ.ም. በመንግሥት የተሠራው የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ጥናት አንኳር ችግሮች በማለት ከለያቸው ሦስት ጉዳዮች አንዱ የአስፈጻሚው ጣልቃ ገብነት በፍትሕ አስተዳደር ሥርዓቱ ጉልህ መሆኑን ያሳያል፡፡ ይኼ አሁንም የተለወጠ የማይመስል መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ቢፒአር ሰነድ በዋነኛነት ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ እንዴት ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው የተስማሙበት ሰነድ ቢሆንም፣ በተወሰነ መልኩ ፍርድ ቤትን ጨምሮ ሌሎች የፍትሕ አካላት ጋር ስላላቸውም ግንኙነት ያስቀምጣል፡፡ አንዳንድ ሕጎች ተረቀው እስኪጠናቀቁ ለጊዜው ክፍተት ለመሙላት እንዲያገለግል የተዘጋጀ መመርያ ነው የሚሉ ያሉትን ያህል እንደ ሕግ ሰነድ የሚጠቅሱትም አሉ፡፡ ለእርሶ የዚህ ሰነድ ደረጃ ምንድን ነው? ተፅዕኖውንስ እንዴት ያዩታል?

አቶ ጌታሁን፡- የቢፒአር ሰነድ እኔ እንደሚገባኝ ሕግ አይደለም፡፡ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱም፣ በአጠቃላይ ባለን የሕግ አወጣጥ ሥርዓትና ልምድ ሕግ አውጭው አካል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ በፓርላማው ፀድቆ በነጋሪት ጋዜጣ ያልታተመ ሰነድ ሕግ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚያ በመለስ ሕግ አውጭው በዋናው ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ተቋማት ዝርዝር ሕጎችን እንዲያወጡ ውክልና ሊሰጥ ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር ቢፒአር ሰነድ ሕግ አይደለም፡፡ በሰነዱ አገልግሎትን ለማቀናጀት የተደረገው መልካም ተነሳሽነት መነቀፍ የለበትም፡፡ ነገር ግን መስመሩ የት ጋር እንደሚቆም በግልጽ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ለምሳሌ የፍትሕ ማሻሻያ የጋራ ኮሚቴ ተብሎ ሰዎች ተሰብስበው የፍርድ ቤትን ውሳኔ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ  ከሆነ ይሄ አደገኛ ነው፡፡ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ እኔ ድንበሩ ላይ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ የዳኝነት ሥርዓታችን የአስፈጻሚው ተፅዕኖ አሁንም ጎበጥ ያደርገዋል፡፡ ይኼ ከሆነ ደግሞ ሁለቱንም ወገን እኩል ለማዳመጥ ሊቸግረው ይችላል፡፡ ለምሳሌ  በፍርድ ሒደት ውስጥ አንዳንድ ጊዜ የሚነሳው የፍትሐዊ ዳኝነት ጥያቄ ዓቃቤ ሕግና ተከሳሽ ወይም መንግሥት ተከራካሪ በሚሆንባቸው ጉዳዮች ተከራራካሪ ወገኖች እኩል አይታዩም የሚል ነው፡፡ ይኼ አንዳንዴ ግምታዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን በግል በሥራ ላይ ካሉ ጠበቆችና ዳኞች ጋር በምትወያይበት ጊዜ ነገሩ በተወሰነ ደረጃ እውነትነት እንዳለው ትረዳለህ፡፡ ግልጽ ባልሆኑና የዳኛው የውሳኔ ነፃነት ሰፊ በሆነባቸው ቦታዎች ዳኞች ዓቃቤ ሕግንና ፖሊስን ከተከሳሽ ይበልጥ ያዳምጣሉ፡፡ ዋስትና መፈቀድ ሲገባው ይከለክላሉ፣ ምርመራው ባለቀ ምንም ተጨማሪ ጊዜ በማያስፈልገው ጉዳይ ላይ ጊዜ ቀጠሮ ይፈቅዳሉ፣ ለዓቃቤ ሕግ ምቾት ቀጠሮ ይቀይራሉ፣ በሚል ጥያቄ ይነሳባቸዋል፡፡ የተከሳሽን ወገን እኩል የመዳኘት መብት ሳያዩ የመንግሥት ወገንን ጡንቻ ይጋራሉ በሚል ይተቻሉ፡፡ እነዚህ አስተያየቶች በጥቅል መሠረት የለሽና ስም ማጥፋት አይመስሉኝም፡፡ ለፍትሕ ሥርዓቱ ጥንካሬ የሚሻለው እነዚህን እውነታዎች ደፍሮ መቀበል ነው፡፡ ‘አልፎ አልፎ የሚታዩ’፣ ‘አንዳንድ የሚያጋጥሙ’ በሚል ለረጅም ጊዜ የለመድነው ቋንቋ መቅረት አለበት፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ አመኔታ ያተረፈ፣ ሕዝብ የሚቀበለውና በሕግ ብቻ የሚመራ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ የደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቱን የመጥራት አቅም አለው፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮችም በሕገ መንግሥታቸው ለተቀመጡት መብቶች ዋስትና የሚሆን የዳኝነት ተቋም በመፍጠር ሒደት ላይ ናቸው፡፡ እኛ ይህን ማድረግ ችለናል ወይ ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን፡፡    

ሪፖርተር፡- ከፍትሐዊ ዳኝነት መለኪያዎች አንዱ የሆነው እንደ ንፁህ የመቆጠር መርህ በኢትዮጵያ በአፈጻጸም ብቻ ሳይሆን በሕግ ማዕቀፉም ክፍተት አለው ብለው የሚተቹ አካላት አሉ፡፡ በተግባር ላለው ችግር የሕግ ማዕቀፉ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለው ያምናሉ?

አቶ ጌታሁን፡- የሕግ አተረጓጎም ጥያቄ የሚነሳው ሕግ ግልጽ ባልሆነበት ጊዜ ነው፡፡ አሁን ሕገ መንግሥቱ በዚህ ጉዳይ ግልጽ ነው፡፡ አስቀድሞ እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር መብትን በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ ትርጉም አይጠይቅም፡፡ ተግባራዊ ማድረግ ብቻ ነው የሚጠይቀው፡፡ ከዚያ ባለፈ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ስምምነት አንቀጽ 14 ላይ በጣም ዝርዝር የሆኑ ድንጋጌዎችን ያስቀምጣል፡፡ ሕገ መንግሥታችን ይህን ስምምነት የአገሪቱ የሕግ አካል ነው ይላል፡፡ ስለዚህ በዚህ ጉዳይ የሕግ ድንጋጌን ምክንያት ማድረግ አሳማኝ አይሆንም፡፡  

ሪፖርተር፡- እንደተባለው የበላይ ሕጎች ግልጽ ናቸው፡፡ ነገር ግን እንደ ፀረ ሽብርተኝነት፣ ፀረ ሙስናና በቅርብ የወጣው የኮምፒውተር አዋጅ የማስረዳት ሸክምን ወደ ተጠርጣሪው በማዞር ይህን መርህ ይጣረሳሉ በሚል የሚከራከሩ ምሁራን አሉ፡፡ ይኼ እንደ ሕግ ክፍተት አይታይም?

አቶ ጌታሁን፡- ሕጎቹ መታየት ያለባቸው ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ጋር ነው፡፡ አስፈላጊ ከሆነ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡ እንደተባለው የማስረዳት ሸክምን ለማሸጋገር የተቀመጡ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ ድንጋጌዎቹ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መንፈስ አንፃር  መተርጎም ይገባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ፍትሐዊ ዳኝነት እንዲሰፍን ለማድረግ ድርሻ ያላቸው ነፃና ገለልተኛ ተቋማትን አስተዋጽኦ  እንዴት ያዩታል?

አቶ ጌታሁን፡- በሕገ መንግሥቱ ሥልጣን የተገደበ ነው፡፡ ሥልጣን የሚመነጨው ከሕዝብ ፈቃድ ነው፡፡ ስለዚህ የሕዝብ ፈቃድ በተገለጸበት መጠን ነው መንግሥት ሥልጣኑን ተግባራዊ ማድረግ ያለበት፡፡ አንዱ የሕዝብ ፈቃድ መገለጫ የተወካዮቻቸው ድምፅ ነው፡፡ በተወካዮቻቸው አማካይነት ፖሊሲዎችና ሕጎች ያወጣሉ፡፡ መንግሥት ከተቀመጠለት ክበብ ሳይወጣ እየሠራ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጥያቄ የሚያረጋግጡ የተለያዩ ተቋማት አሉ፡፡ በመጀመሪያ ሕግ አውጭው አካል ሁለት ዋና ሥራዎች አሉት፡፡ አንደኛው ሕግ ማውጣት ነው፡፡ እሱም የሥልጣን ገደብ ማሳወቂያ መንገድ ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ በሕጉ መሠረት ሠርታችኋል፣ አልሠራችሁም ብሎ የሚጠይቅ ተቋም አለው፡፡ ፓርላማው እነኝህን ሥራዎች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ እስከ ምን ድረስ ሄዷል ብለን ስናስብ ሕግ አውጭው አካል የሕግ አስፈጻሚውን ክፍል በሚገባ ቁጥጥር ያደርግበታል፣ ተገቢ ዕርምጃዎችን እየወሰደ እያስተካከለ ሄዷል ብዬ አላምንም፡፡ ያለ ተጠያቂነት የሚያልፉ በርካታ ነገሮችን እናያለን፡፡ ለምሳሌ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ጥናት ችግሮች ብሎ ከሚጠቅሳቸው መካከል የፍትሕ አካላት ነፃ ያለመሆን፣ የአስፈጻሚው አካል በፍትሕ ሥራው ውስጥ ጣልቃ መግባቱ፣ የውሳኔዎች መዘግየት፣ ብቃት የሌላቸው ኃላፊዎች መሾም፣ የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ሲከሰቱ የፓርላማው ግብዓትና ሚና ምንድን ነው? የቁጥጥር ሥራውን በሚገባ ተግባር ላይ ማዋሉ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የሕግ አውጭው በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ካለው በእጅጉ የተሻለ እንዲሠራ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህም ባለፈ  ለዚህ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ሌሎች  ተቋማትም አሉ፡፡ በዚህ በኩል ሙከራ እያደረጉ ያሉት ተቋሞች የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ናቸው፡፡ የእነዚህን ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ በአንድ ወቅት አነስተኛ ጥናት ሠርቼ ነበር፡፡ ከቆዩበት ጊዜና ከሚጠበቅባቸው አንፃር ያከናወኑት ሥራ በጣም ትንሽ  ነው፡፡ በርካታ ሰዎች ነፃነታቸውና ገለልተኝነታቸው ላይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ተቋሞቹ ዋናውን ተግባራቸውን ትተው ጥቃቅኑን ነገር ነው የሚሠሩት በሚል ይተቻሉ፡፡ ከዚያም አልፎ አስፈላጊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ሳያነሱ ዝም ብለው ያልፋሉ፣ አንዳንዴም እውነትን አዛብተው ያቀርባሉ በሚል  ይወቀሳሉ፡፡ ፍትሐዊ የሆነ የዳኝነት ሥርዓት እንዲኖር የሰጡት አገልግሎት የለም፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም የራሳቸው ሚና ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ ሦስት ዘርፎች ስንመለከት የፍትሕ ሥርዓቱ ከእነርሱ ዕይታ ሊያገኝ ይችል የነበረው ድጋፍ አላገኘም ማለት እንችላላን፡፡ ያ አለመኖሩ ደግሞ የተጠያቂነት ሚዛንን የማስጠበቅ ሁኔታ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ በበቂ ሁኔታ እንዳይኖር አድርጓል፡፡  

ሪፖርተር፡- የወንጀል ሕግ ከተሻሻለ ከበርካታ ዓመታት በኋላም የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ አሁንም በረቂቅ ደረጃ ነው ያለው፡፡ የተጠቃለለና አንድ ወጥ የማስረጃ ሕግ የማውጣት ጉዳይም አከራካሪነት እንደቀጠለ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት የሕግ ዘርፎች በፍትሐዊ ዳኝነት ላይ ተፅዕኖ የላቸውም?

አቶ ጌታሁን፡- በቂና ዝርዝር የሆኑ ሕጎች መኖር ሁልጊዜም ለሕግ የበላይነት አስፈላጊ ነው፡፡ በእነዚህ ሕጎች ላይ ለረጅም ዓመታት የቆየ ሥራ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ያ ሥራ ተጠናቆ ሥራ ላይ ቢውል ተጨማሪ አቅም ይሆናል፡፡ ነገር ግን የዳኝነት ሥርዓቱን ፍትሐዊ ለማድረግ አሁን ባሉት ሕጎች በሚገባ ከተሠራ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ስለዚህ የእነዚህ ሕጎች ጉዳይ ዋነኛ ችግር አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡- የፍትሕ ሥርዓቱ የፖለቲካ መሣሪያ የመሆን አዝማሚያው ተጠናክሯል የሚሉ አስተያየቶችን መስማት የተለመደ ነው፡፡ በዚህ ግምገማ ይስማማሉ?

አቶ ጌታሁን፡- ይኼ በጣም ሰፊ ጥያቄ በመሆኑ ቀጥተኛ መልስ አለኝ ብዬ አልገምትም፡፡ ነገር ግን የፍትሕ ሥርዓታችን የሁሉም ሕዝብ እኩል መገልገያ መሆኑን ደግመን መፈተሽና መልስ ማግኘት  አለብን፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ በአንዳንድ ወገኖች በኩል እየታየ ያለበት መንገድ ያሳስበኛል፡፡ ሥልጣንና ሀብት ካለ በፍትሕ ተቋማቱ አገልግሎት ማግኘት ይቻላል፣ ደሃ ከሆንክ ፍትሕ ታጣለህ የሚል አመለካከት እየዳበረ ያለ ይመስለኛል፡፡ ይኼ ዕይታ ነው፣ እውነት ሊሆንም  ላይሆንም ይችላል፡፡ በዕይታ ደረጃ ብቻ እንኳን ቢሆን መኖሩ በራሱ አሳሳቢ ነው፡፡ ፍትሕ የሚጓደለው በፍትሕ አስተዳደር ሥርዓቱ ብቻ አይደለም፡፡ በሌሎችም ዘርፎች ፍትሕ ይጓደላል፡፡ በአጠቃላይ የፖለቲካ መሣሪያ ሆኗል ብሎ ለመናገር ለሕግ የቆሙና የአቅማቸውን ያህል የሚፍጨረጨሩ ሰዎች ሥራ ውጤትንም መዘንጋት ስለሚሆን፣ ይህንን ጥቅል ድምዳሜ እንዳለ ለመውሰድ አልደፍርም፡፡ ያም ሆኖ ደግሞ ይህ አስተያየት መነሻ የሌለው እንዳልሆነና መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ መሆኑን አምናለሁ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...