Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የኢንተርኔት አገልግሎት ፈረቃ ከገባ ይነገረን?

የኢትዮ ቴሌኮም የአገልግሎት አሰጣጥ አንፃራዊ መሻሻል እየታየበት በመሆኑ ለውጡን ስናደንቅለት ቆይተን ነበር፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ያለው የሞባይል ኔትወርክና የኢንተርኔት አገልግሎት ቀድሞ ከነበረው የተሻለ ሆኖ ስንገለገልበት ነበር፡፡ በአንዳንድ የክልል ከተሞች ያለው የኔትወርክ መቆራረጥ ችግር ግን ለዓመታት የዘለቀና እስከ ዛሬ ድረስም መፍትሔ ያልተበጀለት መሆኑን በግልጽ መናገር ያሻል፡፡

በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ ይገጥመን የነበረው የኔትወርክ ችግር ተቀርፏል ማለት በጀመርንበት ወቅት ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ወደሚገኙ እንደ ዱከም፣ ሞጆና አዳማ ከተሞች ስንጓዝ ግን በሞባይሎቻችን ‹‹ሃሎ›› ለመባባል መከራችንን እናያለን፡፡ ወደ ሐዋሳና አሰላ ብንጓዝም ተመሳሳይ ችግር ይገጥመናል፡፡

በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተሞች ከቀድሞው የተሻለ አገልግሎት መስጠት ቢጀምርም ሰሞኑን ግን እክል ያጋጠመው ይመስላል፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች ያለው ኔትወርክ ‹‹ኖት ዎርክ›› ሆኖብናል በማለት ወቀሳ የሚሰነዝሩ ደንበኞች ተበራክተዋል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለነበረው አገልግሎት ቴሌን አመስግነን ሳንጨርስ ኔትወርኩ መልሶ ወጣ ገባ የማለቱ ነገር እንድናማርረው እያስገደደን ነው፡፡

ከሞባይል ኔትወርክ መቆራረጥ ባሻገር ሰሞኑን ኢንተርኔት ለመጠቀም ያለው ችግርም ቢሆን የኢትዮቴሌኮም የአገልግሎት አሰጣጥ እንደቀድሞው አበሳ ሊሆንብን ይሆን? ብለን እንድንሠጋ አድርጓል፡፡

‹‹የሞባይሎቻችንም ሆነ የኮምፒውተሮቻችን የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦብናል፣ ፍጥነቱ አዝጋሚ ሆኖብናል፤›› የሚሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው፡፡ ከቢሮ ውጭ በኢንተርኔት ካፌዎች የመጠቀም ልምድ ያላቸው ተገልጋዮች ደግሞ በአንደኛው መንደር የሚሠራ ኢንተርኔት ካፌ በሌላኛው መንደር ፀጥ ረጭ እያለባቸው ነው፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢዎች የኢንተርኔት አገልግሎት አሰጣጥ አንዱን ቀን የሚሠራ በሌላው ቀን የሚቋረጥ ሆኖባቸው የተቸገሩ ደንበኞች ‹‹ቴሌ አገልግሎቱን በፈረቃ መሰጠት ጀመረ እንዴ?›› ብለው እስከመተቸት እንደደረሱ ሰምቻለሁ፡፡

በምሥራበት መሥሪያ ቤት የኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ እንኳ ከሳምንት በላይ ሆኖታል፡፡ በሌሎች የከተማዋ ክፍሎችም ተመሳሳይ ችግር የገጠማቸው ተገልጋዮች አሉ፡፡ ችግሩን አይቶ መፍትሔ መስጠት ግን አልተቻለም፡፡ ይህ ችግር በብዙዎቹ የከተማዋ አካባቢዎች በግልጽ ታይቷል፡፡ የአገልግሎቱ መቆራረጥ ግን  የዕለት ሥራቸውን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከቴሌ የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎት ጋር ያቆራኙ ሁሉ ሰሞኑን ፈተና ውስጥ መግባታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

በባንኮች የሥራ ሒደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲፈጥር ታይቷል፡፡ የቀደመ ምሬታችንን የሚያስታውሰን የሰሞኑ የቴሌ አገልግሎት አሰጣጥ ወጣ ገባ እያለ ማስቸገሩ፣ ጭርሱኑ አገልግሎቱ የተቋረጠበትን ምክንያት ባናውቅም ጉዳዩን ቴሌ ጠንቀቆ እያወቀው ለደንበኞቹ መፍትሔ አለማበጀቱ ግን ጥያቄ መፍጠሩ አይቀርም፡፡

ምናለ ምክንያቱን ቢነግረን፡፡ ችግሩን አውቆ አገለግሎቱ የተቋረጠው ይኼ ችግር  ስለተፈጠረ ነው በማለት ደንበኞቹ እንዲታገሱ ማድረግም አንድ ነገር ነበር፡፡ ይሁንና ግን ያጓደለብንን አገልግሎት ይመልስልን፡፡

የኔትወርክ መቆራረጥ ችግር ከተነሳ አንድ ነገር ልጨምር፡፡ እንደ ቴሌ መረጃ ከሆነ በአሁኑ ወቅት ከአገሪቱ የቆዳ ስፋት ወደ 80 በመቶ የሚሆነው ተጠቃሚ ለሞባይልና ለተመሳሳይ አገልግሎት የኔትወርክ ሽፋን አለው፡፡

ይህ ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ ነገር ግን የኔትወርክ ሽፋን ካላቸውና በተባሉና ከመሃል አገር በርቀት ላይ ከሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ግን የተባለው የኔትወርክ ሽፋን የለም፡፡ ኔትወርክን ለሞባይል ስልኮቻችን ብቻ የምንጠቀምበት አይደለም፡፡ ዘመናዊ አገልግሎት ሲታሰብ የቴሌ ኔትወርክ ያስፈልጋል፡፡ ሌላ ሌላውን ትተን ሰሞኑን የኔትወርክ ችግር እክል የሆነበትን የትራንስፖርት ዘርፍን እንጥቀስ፡፡ የኔትወርክ መቆራረጥ በአንዳንድ አካባቢዎች ጭርሱኑ አለመኖር የትራንስፖርት አገልግሎታችንን ለማዘመን እያደረግን ያለነው እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡

አንዳንድ ኩባንያዎች ተሽከርካሪዎቻቸው ላይ በሳተላይት አቅጣጫ አመላካች ሥርዓት (ጂፒኤስ) በመግጠም የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን አገልግሎት ቢጀምሩም በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው ደካማ ኔትወርክ አገልግሎቱን ጐዶሎ እንዳደረገባቸው ሲገልጹ ሰምቻለሁ፡፡ በዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ራሳቸውን ለማዘመን እየሠሩ ካሉ ተዋናዮች እንደሚሰማው፣ ኔትወርክ በሌለበት ወቅት ተሽከርካሪዎቻቸው የት እንደደረሱ፣ ምን እያደረጉ እንደሆኑና ሌሎች መረጃዎችን ለማግኘት ያዳግታቸዋል፡፡ መቆራረጥ አንዳንዴም ጨርሶ የኔትወርክ መጥፋት ምኞታቸውን ለማሳካት እንዳላስቻለው ይናገራሉ፡፡

ስለዚህ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች በዚህ ወቅት የቴሌን አገልግሎት አሰጣጥ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ተፈላጊ ያደርጉታል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጡ ከተቋረጠ የሚፈጥረው ቀውስ ቀላል እንዳልሆነም መረዳት ያስችላል፡፡ ስለዚህ ቴሌ ክፍተቶቹን ለመድፈን አሁንም ብዙ የሚቀሩት ሥራዎች አሉ፡፡ ዘመናዊ አገልግሎት ሲታሰብ ቴሌን ይዞ መጓዝ ግድ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ኃላፊነት በመሆኑ የአልግሎቱን ጥራትና አሰጣጥ ታሳቢ በማድረግ ቴሌ ይትጋ፡፡ አገልግሎቱንም ያጥራ፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት