Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የታቀደው ማስፋፊያ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተለያዩ ዘርፎች የንግድ ትርዒቶች ሲዘጋጁና ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ በዚህ መስክ የንግድ ምክር ቤቶች ድርሻ ጐልቶ ይታያል፡፡ በንግድ ትርዒት ዝግጅት ሥራ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በንግድ ትርዒቶች ላይ የሚሳተፉ የውጭ ኩባንያዎች ቁጥርም ዕድገት እየታየበት ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ኤግዘቢሽን ማዕከል ብቻ ከ44 በላይ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች በያመቱ ይካሄዳሉ፡፡ የንግድ ትርዒቶች ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ቢታመንም ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ማሳያነት የሚሆን ደረጃውን የጠበቀ ምቹ ሥፍራ የላትም፡፡ ይህ ደግሞ የንግድ ትርዒቶችን ዝግጅት ጐዶሎ አድርጐታል፡፡ ከቢዝነሱ አሁን ከሚገኘው የበለጠ ተጠቃሚ እንዳይኮንም እንቅፋት መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡ እርጅና የተጫጫነው ብቸኛው የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልም ቢሆን ለዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ብቻ ሳይሆን ለተራ ዝግጅትም አልመጥን እያለ መምጣቱን በርካቶች  ሲተቹበት ቆይተዋል፡፡ አማራጭ ባለመኖሩ ግን ዓለም አቀፍ ስያሜ ያላቸው የንግድ ትርዒቶች በኤግዚቢሽን ማዕከሉ ታጭቀው እንዲካሄዱ አስገድዷል፡፡ አዲስ አበባ ስሟን የሚመጥን የንግድ ትርዒት ማዕከል እንዲኖራት ለማስቻል የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የጀመረው እንቅስቃሴም ቢሆን ሲጓተት ቆይቷል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ዘመናዊ የንግድ ትርዒት ማሳያና የኮንቬንሽን ማዕከል ለመገንባት ቦታ የተረከበው ከ12 ዓመታት በፊት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዕቅዱ 12 ዓመታት ዘግይቶም ቢሆን ይህ ፕሮጀክት በቅርቡ ወደ ግንባታ ይገባል ተብሎ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን አንድ ለእናቱ የሆነውን የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እንደ አዲስ ለማስገንባት ወደሚያስችል አዲስ እንቅስቃሴ ተገብቷል፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያካበተውን ማዕከል እንደ አዲስ ለመገንባትና ለዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች ምቹ ለማድረግ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት፤ በንግድ ትርዒት ዝግጅትና ማስተዳደር ሥራ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ አስቆጥሯል ከተባለው ፌራ ሚላኖ ከተባለ የስፔን ኩባንያ ጋር በአጋርነት ለመሥራት ያደረገው ስምምነት ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልን መልሶ ለመገንባት ስለተደረገው ስምምነትና በኢንዱስትሪው ዙሪያ ስለሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳን ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡

 

ሪፖርተር፡- ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመዋዋል የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልን እያስተዳደራችሁ ነው፡፡ ነገር ግን ማዕከሉ አንድ የንግድ ትርዒት ማሳያ ሊኖረው የሚገባውን ይዘት ያላሟላ፣ አገልግሎቱም ያልተመቸ ነው፡፡ ይህንን ማዕከል ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲኖረው መልሶ ለመገንባት ጥረት ስለመጀመሩ ተነግሯል፡፡ ስለ ኤግዚቢሽን ማዕከሉና ወደፊት ስለተያዘው ዕቅድ ቢነግሩኝ?

 

አቶ ጌታቸው፡- ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ንግድ ምክር ቤታችን የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልን የማስተዳደር ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር የነበረን ውል እንደገና ታድሶ የማስተዳደሩን ሥራ አሁንም እየሠራን ነው፡፡ እንዳልከውና እንደሚታየውም ማዕከሉ ያረጀና አገልግሎት መስጫዎቹም በሙሉ የደከሙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በንግድ ምክር ቤታችን በኩል በያመቱ በምናካሂደው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ላይ ከ300 በላይ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ፡፡ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ አይተው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራትና ቢዝነሶቻቸውን ለማስተዋወቅ የሚመጡ ኩባንያዎች፣ የንግድ ትርዒት ማሳያውን ሥፍራ ሲመለከቱ ግር ይላቸዋል፡፡ ምክንያቱም ስለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሰምተው የመጡት ኩባንያዎች የንግድ ትርዒት ማሳያው ሥፍራ የሰሙትን ያህል ወይም የአገሪቱን የዕድገት ደረጃ የሚገልጽላቸው ባለመሆኑ ነው፡፡   

በአጠቃላይ ሲታይ ማዕከሉ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም፡፡ ኋላቀር ነው፡፡ ሕንፃዎቹ፣ ማሳያዎቹ፣ ሽንሽኖቹ ሳይቀር ኋላቀር ናቸው፡፡ የማዕከሉ ይዘት ሲያስጨንቀን ቆይቷል፡፡ ይህ ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ ያሳስበን የነበረው ከሚመጡት ተሳታፊዎች መካከል በርካቶቹ ዳግመኛ አለመምጣታቸው ነው፡፡ በእርግጥ አገሪቱ ውስጥ ባለው መልካም ዕድል እየተሳቡ የሚመጡ አሉ፡፡ የንግድ ትርዒት ማሳያው ሥፍራ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ያለመዋቀሩ ግን ሁልጊዜ አስቸጋሪ ነው፡፡ ማዕከሉን ለማሻሻል ስንመክርበት ቆይተናል፡፡ ባለበት ሁኔታ ብናሻሽለው ምን ያህል ወጪ ይጠይቀናል? ብለን ነገሩን ስንፈትሽ ቆይተናል፡፡ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ አማራጮችን ተመልክተናል፡፡ ልምድ ለማግኘት ይረዳናል በማለት የተለያዩ አገሮች የንግድ ትርዒት ማሳያዎችን ጎብኝተናል፡፡ የዱባይና የኢስታምቡል ኤግዚቢሽን ማዕከሎችን አይተናል፡፡ የሚላንን ኤግዚቢሽን አይተናል፡፡ ወደ ባርሴሎና በመሄድ ፌራ ሚላኖ የሚባለውን ኤግዚቢሽን ጎብኝተናል፡፡ ፌራ ሚላኖ በዓለም ትልልቅ ከሚባሉት የኤግዚቢሽን ማዕከሎች አንደኛ ወይም ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነው፡፡ በተለይ ትርዒት በማዘጋጀትና በማደራጀት የታወቁ ናቸው፡፡ ወደዚህ ሥራ የገቡት እ.ኤ.አ. በ1842 ነው፡፡ የካበተ ልምድ አላቸው፡፡ ስለዚህ የእነሱን ማዕከልና አጠቃላይ አሠራራቸውን በማየት ጥሩ ተሞክሮ አግኝተናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከእነርሱ ጋር በመነጋገር በእኛ አገርም እንድንገነባው ጥያቄ አቅርበንላቸዋል፡፡ እነሱ ጥናቱን ለማጥናት ፈቃደኛ ሆነዋል፡፡ በባርሴሎና ከንቲባ ጋባዥነትም በክቡር ከንቲባ ድሪባ ኩማ የተመራ የልዑካን ቡድን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ባርሴሎና በመጓዝ ኤግዚቢሽን ማዕከሉን በመጐብኘትና አዲስ አበባ ላይ ደረጃውን የጠበቀ ማዕከል ለመገንባት እንደሚቻል በመነጋገር ከተስማማን በኋላ የመጀመሪያው የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል፡፡

ሪፖርተር፡- በእናንተና በስፔኑ ኤግዚቢሽን ማዕከል መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ይዘቱ ምን ነበር?

አቶ ጌታቸው፡- የተፈረመው መግባቢያ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልን በተሻለ ደረጃ ለመገንባት የሚያስችል ጥናት እንዲያካሂዱልን ነው፡፡ ለምናስገነባው ማዕከል የዲዛይን ሥራ መሥራት የስምምነቱ አንድ አካል ነው፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት አዲስ አበባ ላይ የተፈረመው ስምምነት በአጠቃላይ ሥራውን የማስጀመርና የተሟላ ጥናት ለማጥናት እንዲቻል ነው፡፡ ጥናቱና የዲዛይን ሥራው እስከ ጥቅምት 2009 ዓ.ም. ተጠናቅቆ እንዲቀርብ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት ፌራ ሚላኖ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል ጥናትና የፕሮጀክቱን ዲዛይን በጥቅምት 2009 ዓ.ም. አጠናቀው ያስረክቡናል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ የምታስተዳድሩት ተቋም ነው፡፡ እናንተ እያስተዳደራችሁ፤ ገቢውን በመካፈል የምትሠሩበት ነው፡፡ ከአዲሱ ኩባንያ ጋር በአጋርነት እንሠራለን ካላችሁ አብሮ መሥራቱ በምን መልኩ የሚሆን ነው?

አቶ ጌታቸው፡- የፌራ ሚላኖን ተሞክሮ ስናይ፣ የኤግዚቢሽን ማዕከሉ ባለቤቶች የባርሴሎና ከተማ አስተዳደርና የባርሴሎና ንግድ ምክር ቤት ናቸው፡፡ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ የአሠራር ሒደት አለው፡፡ ማዕከሉን የገነቡትም በጋራ ከባንክ ተበድረው ነው፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ የባንክ ዋስትና ከመንግሥት ተፈቅዶለት የተወሰነ ገንዘብ ተበድሯል፡፡ የባርሴሎና ከተማ አስተዳደርም ከባንክ ብድር ከተፈቀደለት በኋላ ሁለቱም ያገኙትን ገንዘብ አጋጭተው ማዕከሉን በጋራ በመገንባት ማስተዳደር ጀመሩ፡፡ የንግድ ትርዒት ማሳያ ቦታዎቹ በባህሪያቸው ያለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ መንግሥት ለብቻው የሚሠራቸው አይደሉም፡፡ ይህ ተሞክሯቸው ትኩረት የሰጠንበት ነው፡፡ አካሄዱ እንግዲህ ወደፊት ከግንባታው በኋላ የሚታይ ይሆናል፡፡ ከእኛ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ምክር ቤታችን ከአስተዳደሩ ጋር በአጋርነት መሥራቱን ይቀጥልበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ጥያቄዬ ግን ከአጥኚው ኩባንያ ጋር የሚኖራችሁ አጋርነት  እንዴት ይገለጻል የሚል ነው፡፡

አቶ ጌታቸው፡- እሱንም ከጥናታቸው ጋር አያይዘው የሚያመጡት ነው፡፡ ጥናቱን ጨርሰው ካቀረቡልን በኋላ ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናል፡፡ የከተማው አስተዳደርና የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በጋራ የማልማትና በጋራ የመሥራት አጋርነት መኖር እንዳለበት ከወዲሁ ታስቧል፡፡ ነገር ግን ከጥናቱ በኋላ የሚመጣ ነው፡፡ ለምን ታሳቢ ይሆናል ከተባለም የንግድ ትርዒት ሥራዎች በባህሪያቸው ያለ ግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በመንግሥት ብቻ የሚሠሩ ባለመሆናቸው ነው፡፡ በዱባይም ሆነ በሚላን እንዲሁም በሌሎች ከተሞች ያለውን ልምድ ስናይ፣ መንግሥት በዚህ ሥራ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን የግሉ ዘርፍ የሚሳተፍባቸው ናቸው፡፡ የዓለም ተሞክሮ ይኼው ነው፡፡ አጋርነቱም ይቀጥላል፡፡ በተለይ የአዲስ አፍሪካ ኤግዚቢሽንና ኮንሽንሽን ማዕከልን ለማስገንባት የተጀመረው አጋርነትና በጋራ የመሥራቱ ሒደት እያደገ እንደሚሄድ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከስፔኑ ኩባንያ ጋር ስምምነት ስታድጉ ጉዳዩን ለአዲስ አበባ አስተዳደር አቅርባችሁ ነበር? ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላስ የሚኖራችሁ ሚና ምንድን ነው?

አቶ ጌታቸው፡- ሁኔታውን አጥንተን ሐሳቡን አቀረብን፡፡ የማዕከሉ ባለቤት የከተማ አስተዳደሩ ስለሆነ እኛ በተናጠል ሄደን ልንፈራረም አንችልም፡፡ የባለቤትነት ጥያቄ አለበት፡፡ ስለዚህ ሐሳቡን አቀረብን፡፡ ሐሳባችንን በደስታ ነበር የተቀበሉት፡፡ የእኛ ድርሻ ሊሆን የሚችለው ከጥናቱ ውጤት የሚመጣ ነው፡፡ ባለቤቱ የከተማው አስተዳደር ነው፡፡ እኛ ማኔጅመንቱን ነው የወሰድነው፡፡ በዚሁ መሠረት ጥናቱ ተጠንቶ ይመጣል፡፡ ጥናቱ የሚለውና ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ተወስዶ በጋራ የምንሠራበት ሞዴል ይዘረጋል፡፡ በእርግጠኝነት ግን ይሄ ነው ለማለት አሁን ጊዜው አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ያረፈበት ቦታ ትልቅ ኤግዚቢሽን ማዕከል ሊያስገነባ እንደማይችል ይነገራል፡፡ አሁን ባለው ቦታ ብቻ እየታሰበ ያለውን ዓይነት ማዕከል መገንባት ይቻላል?

አቶ ጌታቸው፡- ቢሆንም ሊሰፋ የሚችልበትን ዕድል፣ የማዕሉን ይዘት ጥናቱ ያሳየናል፡፡ በጥናቱ መሠረት እንዲሁም ከሚያቀርቡት የግንባታ ዲዛይን ይህንን ያህል ቦታ ያስፈልጋል ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ በዚህ መሠረት ይሠራል፡፡ ማስፋቱ ግን ግዴታ ነው፡፡ አሁን ባለው ቦታ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ኤግዚቢሽን ማዕከል መገንባት አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- በኤግዚቢሽን ማዕከሉ ዙሪያ ያለው ቦታ ወደፊት ለሚገነባው ማዕከል ሊውል እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡ ቦታው ተፈቅዶላችኋል?

አቶ ጌታቸው፡- ይኼ የአስተዳደሩ ሥራ ነው፡፡ እንደ ሐሳብ ጥናቱ ሲመጣ የሚካተት ይመስለኛል፡፡ በዚህ መልኩ ነው የምናየው፡፡ የጥናቱ ውጤትም ወደፊት የሚሆነውን ያሳየናል፡፡ አሁን ያለው ቦታ ግን ለሚባለው ዓላማ በቂ እንዳልሆነ የጋራ መግባባት አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ተጨማሪ ቦታ ያስፈልጋል? ዲዛይኑም ይህንን አገናዝቦ የሚሠራ ነው ማለት ነው?

አቶ ጌታቸው፡- ብለን እንገምታለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከኤግዚቢሽን ማዕከል ግንባታ ጋር በተያያዘ ከዓመታት በፊት የተጀመረውና እስካሁን ተግባራዊ ያልሆነው የአዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማዕከል አለ፡፡ የዚህ ማዕከል ግንባታ ይጀመራል ከተባለ ቆይቷል፡፡ የዚህ ግንባታ ሳይጀመር ግን የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልን መልሶ ለመገንባት እየተንቀሳቀሳችሁ ነው፡፡ አንዱን ሳትጨርሱ ወደሌላው መሄድ አይሆንባችሁም?

አቶ ጌታቸው፡- ለዚህች ከተማ በአጠቃላይ የሚያስፈልጋት የኤግዚቢሽን ማዕከል ስንት ነው? እንደ ኢኮኖሚው እንቅስቃሴና እንደ አስፈላጊነቱ የሚታይ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ኮንቬንሽን ማዕከሎች የሉም፡፡ የአገሪቱ ተነጻጸሪ ተጠቃሚነት የሚታየውም የአፍሪካ ማዕከል ከመሆኗ ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ የአዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ፕሮጀክት ትልቅ በመሆኑ ግንባታው ተጠናቅቆ ሥራ እስኪጀምር በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል እየሠራን እንቆያለን፡፡ ዞሮ ዞሮ ሁለቱም የተለያየ ተግባር ይኖራቸዋል፡፡ አዲስ አፍሪካ ትልልቅ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች የሚዘጋጁበት ይሆናል፡፡ ይኼኛው በመለስተኛ ደረጃ ይሠራል፡፡ ተመጋጋቢ ሥራ እንዲሠሩ ታሳቢ ተደርጐ የሚሠራ ነው እንጂ ተወዳዳሪ አያደርጋቸውም፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ ያሉትን የኤግዚቢሽን ማዕከሎች ኡጋንዳ፣ ኬንያና ሩዋንዳ ለመሥራት ሐሳብ አላቸው፡፡ እኛ ቶሎ ወደ ሥራ መግባታችን በምሥራቅ አፍሪካ ተነፃፃሪ ተጠቃሚ የመሆን ዕድሉን ለመውሰድ ያስችለናል፡፡    

ሪፖርተር፡- ከስፔኑ ፌራ ሚላኖ ጋር ባደረጋችሁት ውል ለጥናቱና ለዲዛይን ሥራው ምን ያህል ትከፍላላችሁ?

አቶ ጌታቸው፡- እስከ ስድስት ሚሊዮን ብር ይደርሳል፡፡

ሪፖርተር፡- ሲኤምሲ አካባቢ ይገነባል የተባለው አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽንና የንግድ ትርዒት ማዕከል የግንባታ ፕሮጀክት አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ ጌታቸው፡- የመጀመሪያውን የግንባታ ምዕራፍ ለመጀመር ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቷል፡፡ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የጨረታ ሰነዱን ገዝተው በማስገባት ላይ ናቸው፡፡ ስለዚህ በቅርቡ የመጀመሪያው ክፍያ ተከፍሎ ሥራ እንጀምራለን ብለን እንጠብቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አፍሪካ ኮንፌንሽንና የንግድ ትርዒት ማዕከል እስካሁን ምን ያህል አክሲዮን ሸጧል፡፡ ምን ያህል ባለአክሲዮኖችስ አሉት?

አቶ ጌታቸው፡- ባለአክሲዮኖቹ ብዙ ናቸው፡፡ ትልቁን ድርሻ ከያዙት ውስጥ የከተማው አስተዳደር አንዱ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ150 ሚሊዮን ብር አክሲዮን ገዝቷል፡፡ ሁለተኛው በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ዲያስፖራዎች ናቸው፡፡ እነሱ ወደ 115 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ አክሲዮን ገዝተዋል፡፡ ከፊሉን የአክሲዮን ዋጋ አስገብተዋል፡፡ ቀሪውን ያስገባሉ ብለን እየጠበቅን ነው፡፡ ንግድ ምክር ቤታችን ለጊዜው የ10 ሚሊዮን ብር አክሲዮን ገዝቷል፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን ምን ያህል አክሲዮን ሸጣችኋል?

አቶ ጌታቸው፡- የ300 ሚሊዮን ብር አክሲዮን ሸጠናል፡፡ የአንድ ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው አክሲዮን ለመሸጥ እየተዘጋጀን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የንግድ ትርዒቶች ደረጃ እንዴት ይመዘናል? በአጠቃላይ ኢንዱስትሪውስ ምን ይመስላል?

አቶ ጌታቸው፡- የንግድ ትርዒት ማዘጋጀት በንጉሡ ጊዜ የተጀመረ ነው፡፡ ኤክስፖ ይባል ነበር፡፡ በደርግ ጊዜ የግል ዘርፉ ብዙም ስላልነበር ተቀዛቀዘ፡፡ በአጠቃላይ ግን ከ20 ዓመት ወዲህ፣ በተለይ ንግድ ምክር ቤቱ በንግድ ትርዒት ሥራ ዘርፍ ውስጥ ከገባበት ጊዜ ወዲህ በርካታ ለውጦች ታይተዋል፡፡ ወደዚህ ሥራ ስንገባ ንግድ ትርዒት ብዙም የሚታወቅ አልነበረም፡፡ በመንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ እንኳ ግንዛቤው አልነበረም፡፡ ሥራው ከኢኮኖሚና ከንግድ ዕድገት ጋር የሚመጣ ነው፡፡ ላለፉት 20 ተከታታይ ዓመታት ኤግዚቢሽን አካሂደናል፡፡ በዚህ መነሻነት የተሠራው ሥራ ብዙ ለውጥ ታይቶበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንኳ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ብቻ በዓመት ከ44 በላይ የንግድ ትርዒቶች ይካሄዳሉ፡፡ የውጭ ተሳታፊዎችም ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ ስለዚህ  የቦታው ጥበት ካልሆነ በቀር ቢዝነሱ አዋጭ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በያመቱ የሚካሄዱና በዓላትን ታከው የሚሰናዱ ዝግጅቶችን ለማካሄድ ከፍተኛ ዋጋ እየቀረበ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ እንዴት ይታያል?

አቶ ጌታቸው፡- እንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት ባዛር ነው የሚባለው፡፡ ዕቃ የሚሸጥበት ነው፡፡ ንግድ ትርዒት ስንል ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት ብቻ ነው፡፡ ሽያጭ ማካሄድ አይመከርም፡፡ ስለዚህ ባዛር በዓላትን አስታከው ሰዎች በርካሽ ዋጋ እንዲገበያዩ ዕድል ከመፍጠር አኳያ የመጣ፣ እንዲያውም ከሶሻሊስት ሥርዓቱ ጋር የተጀመረ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ሰዎች በበዓል ወቅት በርካሽ ዋጋ ዕቃ እናገኛለን ብለው የሚጠቀሙበት የተለመደ አካሄድ ነው፡፡ ይህ ከእኛ አካሄድ ጋር ብዙ የሚገናኝ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ ናችሁና ማዕከሉን የምታስተዳድሩት፣ ጨረታውንም የምታወጡት ይህ አካሄድ እንዴት ይታያል?

አቶ ጌታቸው፡- ከማስተዳደር ጋር ሲተያይ ነፃ ጨረታ ነው የምናካሂደው፡፡ ስለዚህ በቢዝነሱ ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች እርስ በርሳቸው በሚያደርጉት ውድድር ነው ዋጋው ወደላይ የወጣው፡፡ እኛ ዋጋ አንወስንም፡፡ ሌላው ቀርቶ መነሻ ዋጋ አናወጣም፡፡ ገበያው በሚሰጠው ውድድር ነው ዋጋው እዚህ ደረጃ የደረሰው፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የንግድ ምክር ቤቱ ነበር፡፡ ይመለስ ተብሎ ሙግት ተጀምሮም ነበር፡፡

አቶ ጌታቸው፡- ዱሮ ማዕከሉ የንግድ ምክር ቤቱ ነበር፡፡ እንዲያውም ለማዕከሉ አንዳንድ የውኃና የመብራት የተከፈለባቸው ደረሰኞችም የእሱ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው የሚባል ነገር አለ፡፡ ነገር ግን በፍርድ ቤት አዋጅ ተወርሷል፡፡ ማዕከሉ ብቻ ሳይሆን ሕንፃውም ተወርሷል፡፡ የሚወረስ ንብረት ሁሉ የፌዴራል መንግሥት ንብረት ነው፡፡ ስለዚህ አስተዳደሩ ይህንን ማዕከል እንዲያስተዳድር የፌዴራል መንግሥት እንደሰጠው ነው ታሳቢ የሚደረገው፡፡ ይህ ሥራ የግሉን ዘርፍ ያማከለ ስለሆነ፣ ንግድ ምክር ቤቱ ቢያስተዳድረው የበለጠ ውጤታማ ይሆናል ተባለ፡፡ እንደተባለውም በገቢም ሆነ ዘርፉን በማሳደግ ረገድ ውጤታማ ሆነናል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች