- ለካፒታል ፕሮጀክቶች ከተመደበው በጀት የአንበሳውን ድርሻ ለነባር ፕሮጀክቶች ይውላል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ለቀጣዩ 2009 በጀት ዓመት ካፀደቀው 35.4 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ 58 በመቶ የሚሆነውን ለነባር ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ መደበ፡፡ ካቢኔው በአጠቃላይ ከያዘው በጀት ውስጥ 64 በመቶ ለካፒታል ፕሮጀክቶች የያዘ ሲሆን፣ ቀሪውን ለመደበኛ በጀት መድቧል፡፡
ለካፒታል ፕሮጀክት ከተመደበው 58 በመቶ ለነባር ፕሮጀክቶች ሲመድብ፣ ቀሪው ስድስት በመቶ ትኩረት ለሚሰጣቸው ፕሮጀክቶችና ነባሮቹ ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ጉድለት ካጋጠማቸው ተብሎ በመጠባበቂያ የተያዘ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ርስቱ ይርዳው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ ለካፒታል ፕሮጀክቶች የመደበው በጀት ድህነትን ለመቅረፍ ለተዘረጉ ፕሮጀክቶች የሚውል ነው፡፡
በተለይም ለመንገድ ግንባታዎች፣ ለንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ ለቤቶች ልማት መሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ ለአዳዲስ ሆስፒታሎችና ለአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እንዲሁም ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የማምረቻ ቦታ ግንባታ በቅደም ተከተል ከፍተኛ በጀት እንደተመደበና እነዚህ ፕሮጀክቶችም ከተመደበው በጀት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዙ አቶ ርስቱ ገልጸዋል፡፡
አቶ ርስቱ እንደገለጹት፣ የተያዘው በጀት በአብዛኛው በአስተዳደሩ የሚሸፈን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ገቢ የመሰብሰብ አቅም እያደገ ነው፡፡ የከተማው አስተዳደር ቀደም ባሉት ዓመታት በዓመት የመሰብሰብ አቅሙ ሁለት ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡
‹‹ነገር ግን ይህም ቢሆን ካለው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አንፃር በቂ ነው ተብሎ አይታሰብም፡፡ በከተማው ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እየተካሄደ ነው፡፡ የታክስ ሪፎርም ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ የኅብረተሰብ ግንዛቤ እያደገ ነው፡፡ የንግድ ሥርዓቱም መሻሻል አሳይቷል፡፡ በዚህ መሠረት ወደ ታክስ መረብ ያልገቡትን በማስገባት በቀጣዩ ዓመት በከተማው ታሪክ ትልቁን (34.5 ቢሊዮን ብር) ለመሰብሰብ ታቅዷል፤›› በማለት አቶ ርስቱ ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባ ከፌዴራል መንግሥት የድጎማ በጀት ተጠቃሚ አለመሆኗ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን አቶ ርስቱ እንደገለጹት፣ የፌዴራል መንግሥት በአዲስ አበባ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
ለአብነት የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት፣ የቴሌኮም ማሻሻያ ፕሮግራም፣ ግዙፍ መንገዶች (አዲስ አዳማ ፍጥነት መንገድ) የጤና ተቋማት በተዘዋዋሪ ከተማውን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል፡፡
‹‹የፌዴራል መንግሥት በቀጥታ በጀት ባይመድብም በራሱ መንገድ የሚገነባቸው ፕሮጀክቶች ከተማውን ቀጥተኛ ተጠቃሚ እያደረጉ ነው፤›› በማለት አቶ ርስቱ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለ2007 ዓ.ም. በ31.8 ቢሊዮን ብር በጀት ማፅደቁ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ውስጥ ለካፒታል ፕሮጀክቱ 19 ቢሊዮን ብር፣ ለመደበኛ ወጪዎች 12.7 ቢሊዮን ብር በጀት ይዟል፡፡
ለቀጣዩ 2009 በጀት ዓመት የተያዘው ከ2008 በጀት ጋር ሲነጻጸር የ3.7 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው፡፡