- ጤፍ ከባዕድ ቁሶች የቀላቀሉ 15 ነጋዴዎች ተያዙ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአትክልት ተራ የተንሰራፋውን ሕገወጥ ንግድ ለማስቆም ያቋቋመው ግብረ ኃይል በዘጠኝ ከባድ ተሽከርካሪዎች ከነተሳቢያቸው የተጫነ አትክልትና ፍራፍሬ ወረሰ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በስድስት መለስተኛ የጭነት ተሽከርካሪዎች የተጫነ አትክልትና ፍራፍሬም ወርሷል፡፡
ሰኔ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደው ድንገተኛ ዘመቻ በሕገወጥ መንገድ ለተጠቃሚው በሽያጭ ሊቀርቡ የነበሩት ምርቶች ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቀይ ስርና አናናስ ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ እነዚህን ምርቶች በመውረስ ለተጠቃሚው በሽያጭ ያስተላለፈ ቢሆንም የተገኘው ሒሳብ አልተገለጸም፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ከበደ የሚመራው ግብረ ኃይል፣ የተወሳሰበውን የአትክልት ተራ የንግድ ሥርዓት ለማስያዝ ባለፉት ሦስት ወራት ሲመረምርና ራሱን ሲያዘጋጅ መቆየቱ ታውቋል፡፡
ግብረ ኃይሉ ሰኔ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በወሰደው ዕርምጃ፣ በሕገወጥ መንገድ ለግብይት የቀረቡ ምርቶች ከመውረሱ በተጨማሪ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ነጋዴዎች መኖራቸውም ተገልጿል፡፡
ሕገወጥ የተባሉት ነጋዴዎች ከሱዳንና ከተለያዩ የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች አካባቢዎች የሚያመጧቸውን ምርቶች፣ ከሌሊቱ 10፡00 እስከ 12፡00 ድረስ ግብይት ይፈጽማሉ፡፡
በዚህ የንግድ ሰንሰለት ውስጥ ሕገወጥ ደላሎችና ተቀባይ ነጋዴዎች በሰፊው በመኖራቸው ከባድ ተሽከርካሪዎቹ ሽያጫቸውን ጨርሰው ከለቀቁ በኋላ ንግዱ ወደ መካከለኛ የጭነት ተሽከርካሪዎች ተዛውሮ ያለ ደረሰኝ ግብይቱ ይካሄዳል፡፡
በሕገወጥ መንገድ ሲነግዱ የቆዩ ነጋዴዎች በሁለት ተከፍለው የተመደቡ ሲሆን፣ 180 ነጋዴዎች ያለፈቃድ፣ 2000 የሚሆኑ ደግሞ በጎዳና ንግድ የተሰማሩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በዚህ ሒደት በተለይ ከከሊፋ ሕንፃ እስከ አፍሪካ አንድነት ትምህርት ቤት ድረስ ያለው መንገድ ጭራሹኑ የሚዘጋ ሲሆን፣ መንገዱ የተዘጋበትን ምክንያት ለሚጠይቅ አካል፣ ለትራፊክ እንቅስቃሴ የሚያስተጓጉል የቆሻሻ ክምር በምክንያትነት ይቀርባል፡፡
ከንቲባ ድሪባ ኩማ ያቋቋሙትን ግብረ ኃይል የሚመሩት የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ከበደ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ምክንያቱም የንግድ ሰንሰለቱ ግብይቱን የሚፈጽመው ያለደረሰኝ በመሆኑ መንግሥት በዚህ ሕገወጥ ተግባር በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ ያጣል፡፡
አቶ ተስፋዬ ጨምረው እንደገለጹት፣ በአካባቢው የጽዳት ጉድለት በመኖሩና የሚከማቸውን ቆሻሻ ለሕገወጥ ተግባር ማስፈጸሚያ እየዋለ በመሆኑ፣ ለተለያዩ በሽታ ሊያጋጥል ስለሚችል ዕርምጃው ሊወሰድ ችሏል፡፡ የአዲስ አበባ አትክልትና ፍራፍሬ ዋነኛ ማከፋፈያ በሆነው አትትክልት ተራ ግብይት የሚካሄደው በማለዳ ነው፡፡
የአትክልትና ፍራፍሬ የንግድ ሰንሰለት ሕገወጥነት የሚታይበት መሆኑ ይነገራል፡፡ አቶ ተስፋዬ እንደሚሉት፣ በቅድሚያ በሕጋዊ መንገድ የንግድ ሥራ ከሚያካሂዱ ነጋዴዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕገወጥነትን መከላከል ባለመቻሉ፣ ከንግድ ሥራ ውጪ እየሆኑ መሆኑንና እንዲያውም ሕገወጥ ሥራ ለመሥራት እያቅማሙ መሆናቸውን ነጋዴዎቹ መናገራቸውን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ እንዳሉት፣ በሕገወጥ መንገድ ከሚነግዱ ነጋዴዎች ጋርም ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ወቅት በሕግ መሥራት እንደሚችሉ፣ ይህ ካልሆነ ግን ዕርምጃ እንደሚወስድባቸው እንደተገለጸላቸው አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን በአካባቢው የተሻሻለ ነገር ባለመኖሩ መንግሥት ወደ ዕርምጃ የገባ ሲሆን፣ የንግድ አሰፈሩን ወጥ በሆነ መንገድ ለማስተካከል እየተሠራ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የጤፍ ዱቄት ከሠጋቱራና ከኖራ ጋር በመቀላቀል ለተጠቃሚው እንጀራ ሲያቀርቡ የተገኙ ነጋዴዎች አሉ፡፡
አቶ ርስቱ ይርዳው ሰኔ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በቦሌ፣ ኮልፌ ቀራኒዮና አቃቂ ክፍላተ ከተሞች 15 ነጋዴዎች ይህንን ሕገወጥ ተግባር ሲፈጽሙ እንደተገኙና እንደተያዙ ገልጸዋል፡፡
ይህ ድርጊት ተጠቃሚውን ካንሰርን ለመሳሰሉ በሽታዎች የሚዳርግ በመሆኑ፣ ኅብረተሰቡ የተለየ ነገር ሲያጋጥመው ጥቆማ እንዲያደርግ አቶ ርስቱ አሳስበዋል፡፡