Sunday, January 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናግለሰቦችን አሳልፎ መስጠትን በተመለከተ ከሱዳን ጋር የተደረገውን ስምምነት ምክር ቤቱ አፀቀደው

ግለሰቦችን አሳልፎ መስጠትን በተመለከተ ከሱዳን ጋር የተደረገውን ስምምነት ምክር ቤቱ አፀቀደው

ቀን:

  • ከቱርክ ጋር የተደረገው ወታደራዊ ስምምነትም ፀደቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያና በሱዳን መንግሥታት መካከል በወንጀል የሚፈለጉ ግለሰቦችን አሳልፎ ለመስጠት የተፈረመውን ስምምነት ሰኔ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በዋለው መደበኛ ጉባዔ አፀደቀው፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት ለምክር ቤቱ ቀርቦ ወደ ውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተመራው የማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅ በሁለቱ አገሮች በኩል ሰላምና መረጋጋት ለማስፈንና በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሊቃጣ የሚችልን ወንጀል ለመከላከል ይረዳል ተብሏል፡፡ ለዝርዝር ዕይታ የተመራለት የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ዳባ፣ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲዋ ትኩረት ከሰጠችባቸው ጉዳዮች መካከል ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ተባብሮ ለመሥራትም ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ምክር ቤቱ ስምምነቱ እንዲያፀድቀው የኮሚቴው አባላት በሙሉ ድምፅ መስማማታቸውን ጨምረው አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአገሮችና ለሕዝቦች ደኅንነት ሥጋት እየሆኑ ከመጡ ጉዳዮች ውስጥ የተደራጀ ወንጀል ድርጊቶች፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሕገወጥ ንግድ፣ ሽብርተኝነት የመሳሰሉት ተጠቃሽ መሆናቸውን  በመጥቀስ የእነዚህን ወንጀሎች ፈጻሚዎች ከተጠያቂነት እንዳያመልጡ ያደርጋል ሲሉም አብራርተዋል፡፡

በስምምነቱ መሠረት ሁለቱ አገሮች በብሔራዊ ሕጎቻቸው ከአንድ ዓመት ጀምሮ ሊያስቀጣ በሚችል ወንጀል ክስ የቀረበበት ወይም የተቀጣ ግለሰብን ለጠያቂው አገር አሳልፎ ለመስጠት ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ ከላይ የተገለጸው እንዳለ ሆኖ የታክስ፣ የጉምሩክና የውጭ ምንዛሪን በተመለከቱ የወንጀል ድርጊቶች የተጠረጠረ ግለሰብ ተላልፎ እንዲሰጥ በሚጠየቅበት ጊዜ ጥያቄው በቀረበበት ወገን ሕግ መሠረት መሰል የግብር ወይም የቀረጥ ግዴታ አለመኖሩ የቀረበውን አሳልፎ የመሰጠት ጥያቄ ውድቅ ለማድረግ እንደማይቻል በስምምነቱ ተገልጿል፡፡

የኮሚቴውን የውሳኔ ሐሳብ ያደመጠው ምክር ቤትም ያለ ተጨማሪ ጥያቄና ማብራሪያ በቀጥታ በሙሉ ድምፅ ተቀብሎ አፅድቆታል፡፡

በተያያዘ ዜናም ቋሚ ኮሚቴው እንዲሁ ተመርቶለት የነበረውን በኢትዮጵያና በቱርክ በወታደራዊ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተፈረመውን ስምምነት አቅርቦ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሊቀመንበር በቀረቡት የውሳኔ ሐሳብ በሁለቱ አገሮች የመከላከያ ሚኒስትሮች በ1998 ዓ.ም. የተፈረመው ስምምነት አገሮቹ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓላማዎችና መርሆዎች ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን ዓለም አቀፍ ግዴታቸውን ለመወጣት እንደሚያስችላቸው አቶ ተስፋዬ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም አገሮቹ በወታደራዊ ሥልጠናና ትምህርት፣ በመከላከያ ኢንዱስትሪ፣ ለአየር ኃይል፣ በምድር ጦርና በሎጂስቲክ ዙሪያ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ካስረዱ በኋላ ‹‹ቱርክ በምድር፣ በአየርና በባህር የተደራጀ ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል ካላቸው አገሮች ውስጥ የምትመደብ በመሆኗ፣ የትብብር ስምምነቱ ለአገራችን የመከላከያ ሠራዊት ግንባታ ጠቀሜታው የጎላ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ምክር ቤቱም የውሳኔ ሐሳቡን ካደመጠ በኋላ ስምምነቱን በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...