Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤትና ከፍተኛው ፍርድ ቤት በክራውን ሆቴል ላይ የሰጡት ውሳኔ በሰበር ተሻረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ክራውን ሆቴል (CROWN HOTEL) እና ክራውን ፕላዛ (CROWNE PLAZA) በንግድ ስያሜና በንግድ ምልክት ምዝገባ ላይ ባደረጉት ክርክር፣ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤትና የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ሁለቱም ስያሜውን መጠቀም እንደሚችሉት አስተላልፈውት የነበረውን ውሳኔ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት፣ ውሳኔውን በመሻር፣ የንግድ ምልክቱንም ሆነ ስያሜውን የመጠቀም ሕጋዊ መብት ያለው ክራውን ሆቴል ነው፤›› ሲል ሰኔ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ሰጠ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የሆቴል ሥራ ለመሥራት ከንግድ ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው ሌሎች ተቋማት ፈቃድ ሳይኖረው ‹‹CROWNE PLAZA›› የሚለውን የንግድ ምልክት ለማስመዝገብ፣ ሲክስ ኮንትኔትንስ ሆቴልስ ኢንክ (Six Continents Hotels Inc) ለአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ማመልከቻ ማቅረቡን ተከትሎ፣ የንግድ ምልክቱንም ሆነ ስያሜውን ከ20 ዓመታት በላይ የተቀመጠበትና እየተጠቀመበት መሆኑን በመግለጽ፣ ለጽሕፈት በቱ ተቃውሞ ባቀረቡት ክራውን ሆቴል ባለቤት ወ/ሮ ዘውዲቱ መስፍን ምክንያት ጽሕፈት ቤቱ የምዝገባ ማመልከቻውን ውድቅ ማድረጉን ሰበር ሰሚ  ችሎት በዋነኛነት መመርመሩን ፍርዱ ያብራራል፡፡

የክራውን ሆቴል ባለቤት ወ/ሮ ዘውዲቱ በጠበቆቻቸው አቶ ወንድአወክ አየለና አቶ ተሻገር ደሳለኝ አማካይነት በጽሕፈት ቤቱና በፍርድ ቤቱ መሠረታዊ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን ገልጸው ሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ያቀረቡት አቤቱታ መመርመሩን የገለጸው ችሎቱ፣ ክራውን ሆቴል የምስልና የቃል (CROWN HOTEL/Design /Logo) በንግድ ሚኒስቴርና በአዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት አስመዝግበው፣ በየጊዜው እያሳደሱ የሚጠቀሙበት መሆኑን እንዳስረዱና፤ መረጃም እንዳቀረቡ አብራርቷል፡፡ ሲክስ ኮንትኔንትስ ሆቴል ኢንክ ግን በሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ካለመመዝገቡም በተጨማሪ፣ ጽሕፈት ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ እንዳደረገበት አስታውሷል፡፡ ነገር ግን ሕጋዊ ውክልና በሌለው ፀሜክስ ግሎባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አማካይነት በድጋሚ ባቀረበው የመመዝገብ ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ መሠረታዊ የሕግ ጥሰት መሆኑን ያስረዱበትን አቤቱታ ሰበር ችሎቱ በጥልቀት መመርመሩን በፍርዱ አብራርቷል፡፡ ሲክስ ኮንትኔንትስ ሆቴል ኢንክ በበኩሉ፣ ክራውን ሆቴል በአዋጅ ቁጥር 501/1998 አንቀጽ 46(1) መሠረት በ18 ወራት ውስጥ ባለማስመዝገቡ አዕምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ለክራውን ሆቴል የሰጠው የንግድ ምልክት፣ ውድቅ መደረግ እንዳለበት ያቀረበውን መቃወሚያ መልሶም መመርመሩን ችሎቱ ገልጿል፡፡ ሲክስ ኮንትኔንትስ ሆቴልስ ኢንክ ‹‹ክራውን ፕላዛ›› የሚለውን የንግድ ምልክት በመጠቀም ኢትዮጵያ ውስጥ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል ለመክፈት፣ ከፀሜክስ ግሎባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር የፍራንቻይዝ ሆቴል ማኔጅመንት ስምምነት መፈራረሙንና በጉዳዩ ላይ እንደሚያገባው በመጥቀስ በመቃወሚያ መልኩ ያቀረበውን ሀተታም መመርመሩን ችሎቱ በፍርዱ ገልጿል፡፡ ሲክስ ኮንትኔንትስ ሆቴልስ ኢንክ በትክክለኛ ወኪሎች የተወከለና ጽሕፈት ቤቱም ሆነ ከፍተኛው ፍርድ ቤት CROWNE PLAZA የንግድ ምልክትን በኢትዮጵያ መመዝገብ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው ታዋቂነትና ዝና አንፃር፣ ለአገሪቱ ኢንቨስትመንት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን መግለጹንም ችሎቱ መመርሩን አስታውቋል፡፡ የሕግ ድጋፍ ያለው መሆኑን፣ ሁለቱ የንግድ ምልክቶች (ክራውን ሆቴልና ክራውን ፕላዛ) በዕይታ፣ በንባብና በድምጸት እንደሚያለያዩ የተሰጠው ውሳኔ ትክክለኛ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ ሕግ የንግድ ምልክት ምዝገባ፣ የንግድ ስምን አስቀድሞ ማስመዝገብ እንደ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ አለመሆኑን ጠቅሶ መስከረም 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲክስ ኮንትኔንትስ ሆቴልስ ኢንክ ያቀረበውን ተቃውሞም መመርመሩን ችሎቱ በፍርዱ አስፍሯል፡፡

ሰበር ሰሚው ችሎት ትኩረት ሰጥቶ የሰበር አቤቱታውንና በአቤቱታው ላይ የቀረበውን መቃወሚያ መመርመሩን ገልጿል፡፡ አዕምሯዊ ጽሕፈት ቤት መጀመሪያ ውድቅ ያደረገውን የመመዝገብ ጥያቄ፣ በራሱ ለመሻር ምክንያት ያደረገው፣ ሲክስ ኮንትኔንትስ ሆቴልስ ኢንክ እንዲመዘገብለት ያቀረበው የንግድ ምልክት የሚኖረው የኢንቨስትመንት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መሆኑን እንደጠቆመ ችሎቱ ገልጿል፡፡ ጉዳዩን በይግባኝ የተመለከተው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ደግሞ፣ የንግድ ምልክቶቹ ተመሳሳይ አለመሆናቸውን ጠቅሶ፣ ክራውን ፕላዛ ቢመዘገብ ከኢንቨስትመንት አንፃር ሊያበረክተው የሚችለው ከፍተኛ አስተዋፅኦን፣ የሆቴሎቹ ተጠቃሚዎች የማገናዘብ አቅም፣ የኢኮኖሚና የትምህርት ደረጃቸው ሲታይ ተጠቃሚዎችን ያሳስታሉ (ያሳክራሉ) ተብሎ ስለማይታመን፣ ሁሉቱም ሆቴሎች የያዙትን የንግድ ምልክት መጠቀም እንደሚችሉ በመግለጽ፣ የጽሕፈት ቤቱን ውሳኔ ያፀናበትን ምክንያት ሰበር ችሎቱ በጥልቀት መመርመሩን በፍርዱ ተንትኗል፡፡

በጽሕፈት ቤቱ የንግድ ምልክትና ኢንዱስትሪያዊ ንድፍ ጥበቃና ልማት ዋና የሥራ ሒደት፣ ለፀሜክስ ግሎባል ኢንተርፕራይዝ በጻፈው ደብዳቤ፣ ድርጅቱ ከሚሠራው ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ኢንቨስትመንት አንፃር፣ የንግድ ምልክቱ ቢመዘገብ ሊያበረክት ከሚችለው አስተዋፅኦ መነሻነት መሆኑን ችሎቱ መረዳቱን ጠቁሟል፡፡

የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤትም ሆነ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጡት ውሳኔ፣ አዋጅ ቁጥር 501/98ን በማክበር መሆኑን ወይ ከአዋጁ አንፃር ውሳኔ ስለ መስጠታቸው ለማወቅ የአዋጁን መግቢያ ችሎቱ ማየቱንም ገልጿል፡፡ የአዋጁ መግቢያ  ለንግድ ምልክቶች ጥበቃ ማድረግ፣ ለብሔራዊ ኢኮኖሚ መዳበር፣ ለንግድና ኢንዱስትሪ ልማት አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዳለው፣ ኢንቨስትመንቶችን የሚያበረታታውም የንግድ ምልክት ጥበቃ ሲደረግ መሆኑን መደንገኑን ችሎቱ ጠቅሷል፡፡ አዋጅ ቁጥር 501/98 ከወጣበት ምክንያት መካከል ዕቃ በማምረትና በማከፋፈል ወይም አገልግሎት መስጠት የንግድ ሥራ ላይ የሰዎችን መልካም ስምና ዝና ለመጠበቅ፣ በተመሳሳይ ዕቃዎች ወይም አገልግሎቶች መካከል መሳከርን ለማስወገድ፣ የንግድ ምልክት ጥበቃ ማድረግ ማስፈለጉ የንግድ ምልክቶች በነፃ ገበያ ሥርዓት ውስጥ የሸማቾችን ምርጫ በመምራትና ጥቅማቸውን በማስጠበቅ አዋጁ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ሰበር ችሎቱ አስገንዝቧል፡፡

የአዋጁ ዓላማ ክርክር የተነሳበት የክራውን ሆቴል የንግድ ምልክት ለኢንቨስትመንት ተግባር እስከሆነ ድረስ አስቀድሞ የሕግ ጥበቃ የተደረገለት ቢሆን፣፣ ተመሳሳይ የንግድ ምልክትና አገልግሎት ደርቦ ለመስጠት ማስቻል አለመሆኑን ሰበር ችሎቱ በፍርዱ ገልጿል፡፡ በአዋጁ መግቢያ ላይ በግልጽ እንደተደነገገው፣ ለንግድ ምልክት የሕግ ጥበቃ እንዲያገኝ ማድረጉ፣ ኢንቨስትመንትን የማበረታት ፋይዳ አለው በሚል፣ የንግድ ጥበቃን የሚገዛው ሕግ ከኢንቨስትመንት ጋር እንዴት ቁርኝት እንዳለው ከመግለጽ በቀር ለኢንቨስትመንት ከታሰበ አገልግሎት ዘርፍ እስከሆነ ድረስ፣ በአዋጁ ስለ ንግድ ምልክትና ጥበቃ ጉዳይ የሚመለከቱትን ድንጋጌዎች አፈጻጸም ወደ ጎን ሊያስቀር የሚችል አለመሆኑን ሰበር ችሎቱ በፍርዱ አትቷል፡፡

ኢንቨስትመንትን አስመልክቶ የወጡ ሕጎችም አዋጅ ቁጥር 501/98ን ድንጋጌ ተፈጻሚነት የሚያስቀሩ አለመሆናቸውንም ችሎቱ አክሏል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ ስድስት ሥር በዝርዝር መገለጹን የጠቆመው ችሎቱ፣ ኢንቨስትመንት በራሱ የአዋጁን ዓላማ ዝርዝር ድንጋጌና ለተቋሙ በሕግ የተጠሰውን ተግባርና ኃላፊነት ለማስመለስ የሚያስችል አለመሆኑንም ችሎቱ ገልጿል፡፡

የንግድ ምልክቱ ኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት ላይ ከዋለ የንግድ ምልክት ጋር አንድ ዓይነት ወይም ሊያሳስት በሚችል ደረጃ ተመሳሳይ ከሆነ፣ ሊመዘገብ እንደማይችል አዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ ሰባት ላይ መደንገኑን ችሎቱ ጠቁሟል፡፡ ጽሕፈት ቤቱም በአዋጁ መሠረት ሲክስ ኮንትኔንትንስ ሆቴልስ ኢንክ ያቀረበው CROWNE PLAZA ከCROWN HOTEL ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ገልጾ ግንቦት 9 ቀን 2005 ዓ.ም. የምዝገባውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ ተገቢ እንደነበር አክሏል፡፡    

ፀሜክስ ግሎባል ኢንተርፕራይዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በድጋሚ ክራውን ፕላዛ እንዲመዘገብ ለጽሕፈት ቤቱ  ሲያመለክት፣ ከኢንቨስትመንት አንፃር የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጾ ሲመዘግበውና ጎን ለጎን ቢሠሩ እንደማያሳክሩ ሲተነትን ከአዋጅ  ቁጥር 501/98 ጋር ተገናዝበው መተርጎም ያለባቸውን የሕግ ሁኔታ አለማስፈራቸውን ሰበር ችሎቱ ገልጿል፡፡ ሥልጣን ሰጪ ድንጋጌዎች በሌሉበት በደፈናው ‹‹ኢንቨስትመንትን ከማበረታታት አንፃር››  በሚል ብቻ ውሳኔ መስጠት፣ አግባብ ካለመሆኑ በተጨማሪ የሕግ መሠረት እንደሌለው ሰበር ሰሚ ችሎቱ በፍርዱ ገልጿል፡፡ አስቀድሞ የሕግ ጥበቃ እንዲያገኝ ከተደረገው፣ የንግድ ምልክትና አገልግሎት ዘርፍ ጋር ተመሳሳይ የንግድ ምልክትና አገልግሎት ዘርፍ እንዲመዘገብለት ጥያቄ ያቀረበን አካል፣ ‹‹ኢንቨስትመንት እስከሆነ ድረስ ተመሳሳይነቱን ብቻ በማየት ሊከለከል አይገባም›› የሚለው ድምዳሜ የሕግ መሠረት እንደሌለው ሰበር ችሎቱ አስታውቋል፡፡

በንግድ ሥራ የተሰማራ ሰው ቀድሞ ያስመዘገበውን የንግድ ምልክት በሌላ ሰው እንዲወሰድበት ማድረግ፣ የመልካም ስሙንና ዝናውን የማያስጠብቅ፣ በንግድ ምልክቶቹ ላይ ጥበቃ የማያደረግ፣ ነፃ የንግድ ውድድር እንዳይኖርና ተጠቃሚዎች በሚጠቀሙት ምርት ወይም አገልግሎት ላይ ተገቢው ምርጫ እንዳይኖራቸውና ኢንቨስትመንትን የሚያቀጭጭ መሆኑን ሰበር ችሎቱ አስረድቷል፡፡

የንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ አምስት፣ ስድስትና ሰባት ሥር የተደነገጉት ድንጋጌዎች ተፈጻሚነት የሚያስቀር፣ ሌላ የሕግ ድንጋጌ አለመኖሩን ሰበር ሰሚ ችሎቱ ገልጾ፣ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጽሕፈት ቤትና ከፍተኛው ፍርድ ቤት አዋጁን መነሻ በማድረግ ‹‹ለአገር የሚሰጠውን አስተዋፅኦ›› በማለት በአዋጁ መግቢያ ስለ አዋጁ ዓላማ የተገለጹትን በማለፍ፣ የሰጡት ውሳኔ መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ ማግኘቱን፣ ሰበር ሰሚው ችሎት ገልጾ፣ ውሳኔዎቹ መሻራቸውን በማሳወቅ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች