Wednesday, February 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ3.4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባው የሰበታ ጂቡቲ የባቡር መስመር የኃይል አቅርቦት እስከ ነሐሴ ወር ይፈታል ተባለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በ3.4 ቢሊዮን ዶላር የተገነባውና በአሁኑ ወቅት ከሞላ ጎደል ተጠናቆ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ወደ ሙከራ መግባት ያልቻለውን የሰበታ ጂቡቲ ወደብ የባቡር መስመር በቀጣዩ ዓመት መጀመርያ ላይ ወደ አገልግሎት ለማስገባት ማነቆ የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል እስከ ነሐሴ ወር ለመፍታት የሚመለከታቸው ሦስት ተቋማት በጋራ ጥረት ላይ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

ግንባታው በሁለት የቻይና ኮንትራክተሮች በመከናወን ላይ የሚገኘው ከሰበታ በመኤሶ ጂቡቲ ወሰን ደወሌ የሚደርሰው 656 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ሦስተኛ ዓመቱን ለመያዝ እየተቃረበ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም የፕሮጀክቱ 98 በመቶ መጠናቀቁን የሰበታ መኤሶ ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጂነር ሚካኤል ተፈራ ገልጸዋል፡፡

ይህ የግንባታ አፈጻጸም የትራንስፖርት አገልግሎት ሙከራ መካሄድ የነበረበት ቢሆንም፣ አስፈላጊው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ከብሔራዊ ቋት እንዲሁም ወደ ባቡር መስመሩ ተዘርግቶ አለመጠናቀቁን ይገልጻሉ፡፡

የባቡር መስመሩ ከሰበታ እስከ ጂቡቲ ደወሌ ድረስ 16 ጣቢያዎች ያሉት ሲሆን፣ ከመኤሶ ሰበታ ለቡ ፉሪ ጣቢያ ድረስ ስድስት የመንገደኞችና አራት የጭነት ጣቢያዎች ሲኖሩ፣ ከመኤሶ ጂቡቲ ድረስ ደግሞ ስድስት ጣቢያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

የሁሉም ጣቢያዎች ግንባታ 99 በመቶ የተገባደደ መሆኑን፣ የሐዲድ ዝርጋታ፣ የኤሌክትሪክ መስመር እንዲሁም ድልድልዮች ግንባታ መቶ በመቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

የፉሪ ለቡ ጣቢያ ትልቁ የባቡር መስመሩ የመንገደኞች ጣቢያ ሲሆን፣ 2,000 መንገደኞችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ ይቻላል፡፡ የክብር እንግዶችን ማስተናገጃ ላውንጅም አለው፡፡

ይህ ጣቢያ በአስፋልት መንገድ ከአዲስ አበባ የሚገናኝ መሆኑንና ይህ ግንባታም በመከናወን ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ኢንጂነር ሚካኤል ‹‹በእኛ በኩል ሥራውን ጨርሰናል፡፡ በሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ለመስመሩ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በዋናነትም ኤሌክትሪክ ከቀረበ የሙከራ ሥራ ውስጥ መግባት እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡

ይህንን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሸን ከኃይል አቅራቢው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የኃይል አቅርቦትና ማስተላለፍ ከሚሠራው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር እንደተነጋገረና እስከ መጪው ነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም. ለማቅረብ ቃል መግባታቸውን ኢንጂነር ሚካኤል ይገልጻሉ፡፡

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጎሳዬ አሰፋ፣ የኃይል አቅርቦቱን በተገለጸው ወቅት ለማቅረብ በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የእሳቸው መሥሪያ ቤት ድርሻ የኃይል ማሰራጨት መሆኑንና በ16 ጣቢያዎች ላይ ሰብስቴሽን መገንባት መሆኑን ጠቅሰው፣ በተባለው ጊዜ መድረስ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን ዋናው የኃይል አቅርቦት ማለትም ከብሔራዊ የኃይል ቋት ወደ አካባቢው በጊዜው መቅረብ ይኖርበታል፡፡ ይህ ሥራም ዋናው ጉዳይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ይህንንም ዕውን ለማድረግ ሦስቱም ተቋማት በጋራ እየተነጋገሩና እየጣሩ እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡

የባቡር ትራንስፖርቱን ለመጀመር የሚያስፈልጉ 1,171 የጭነት፣ የፈሳሽ ጭነትና የመንገደኞች ባቡሮች ጂቡቲና ድሬዳዋ ደርሰዋል፡፡ እስካሁን ድረስ 826 የጭነትና የመንገደኞች ባቡሮች የገቡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ በቻይናና በጉዞ ላይ እንደሚገኙ የኮርፖሬሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተፈራ ተናግረዋል፡፡

ከለቡ ፉሪ የመንገደኞች ጣቢያ ቀጥሎ በሚገኘው ኢንዶዴ የጭነት ጣቢያ 30 የመንገደኛ ባቡሮች መቆማቸውን ሪፖርተር የተመለከተ ሲሆን፣ ተቀጣጥለው 800 ሜትር መርዘም ይችላሉ፡፡ ባቡሮቹ በተለያዩ ማዕረጎች የተዘጋጁ ሲሆኑ መኝታ ያላቸው በተለይም የቤተሰብ ክፍል ያላቸው ለማንኛውም ደረጃ የሚሆኑትም ምቾትን የሚሰጡና ያልተጨናነቁ መሆናቸውን ለመታዘብ ተችሏል፡፡

በውስጣቸው ዘመናዊ መፀዳጃ፣ ምግብ ማብሰያና ካፍቴሪያዎች፣ ሲጃራ ማጨሻ አካባቢዎችንም ይዘዋል፡፡

የመንገደኞችና መሳፈሪያ ጣቢያዎች በዲዛይን ላይ እንደሆኑም ተነግሯል፡፡   የአካባቢውን ማኅበረሰብ ባህል እንዲያንፀባርቁ ተደርገው የተሠሩ መሆኑን በዚህም የኦሮሚያ፣ የአፋርና የሶማሌ ብሔረሰብ እሴቶችን እንደሚያንፀባርቁም ተገልጿል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች