Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹መንግሥት ሕግ ጥሶ ሲወስን ምክንያት ነበረው››

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቶ ዘሪሁን ቃሚሶን፤ የደቡብ ክልል ቡና አጣቢዎች፣ አበጣሪዎችና አቅራቢዎች የዘርፍ ማኅበር መሥራችና ፕሬዚዳንት 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በደቡብ ክልል የሚገኙ የቡና አቅራቢዎች ከተለያዩ ባንኮች የተበደሩትንና በተቀመጠላቸው ገደብ መሠረት መመለስ ያልቻሉትን ብድር በሒደት መመለስ ይችሉ ዘንድ መፍትሔ ይሆናል ያለውን ውሳኔ በቅርቡ ለባንኮች አስተላልፏል፡፡ ቡና አቅራቢዎቹ የተከማቸባቸውን ዕዳ መክፈል ባለመቻላቸው ከፍተኛ ችግር ውስጥ ስለመግባታቸውና ያጋጠማቸው ኪሳራም በቢሊዮን ብር የሚገመቱ ንብረቶቻቸው ሐራጅ ሊባሉ መሆኑን በመሥጋት ሲገልጹ ስለነበር በዚሁ መነሻነት ብሔራዊ ባንክ ያሳለፈው ውሳኔ ነው፡፡ ውሳኔው ተበዳሪ ከሦስት ጊዜ በላይ የብድሩ መክፈልያ ጊዜ ሊራዘምለት እንደማይችል ከተቀመጠው የገዥው ባንክ መመሪያ ውጭ ባንኮች የቡና አቅራቢዎቹን ጥያቄዎች እንዲያስተናግዱ ያስችላቸዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከተላለፈው ሰርኩላር ቀደም ብሎም የቡና አቅራቢዎቹ ለብድር ማስያዣነት ያቀረባቸው ንብረቶች በባንኰች እንዳይሸጥባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡ በዚሁ ማሳሰቢያ መሠረት ባንኮች የተበዳሪዎቹን ንብረቶች በጨረታ ለመሸጥ የጀመሩትን እንቅስቃሴ አቁመዋል፡፡ የብሔራዊ ባንኩ ባሰራጫቸው ሁለት ሰርኩላሮች ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶች መደመጥ ጀምረዋል፡፡ በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያልተለመደ የተባለው የመንግሥት ውሳኔ ግን ከብዙ ውጣውረዶች በኋላም ቢሆን የግድ መደረግ የነበረበት መሆኑን በመግለጽ የሚከራከሩም አሉ፡፡ ባንኮቹ ከተቀመጠላቸው መመሪያ ውጭ የቡና አቅራቢ ተበዳሪዎችን እንዲያስተናግዱ የተደረገበት ዋነኛ ምክንያትም ሊደርስ የሚችለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከፍተኛ መሆኑ ቀድሞ ስለታመነበት ነው፡፡ ከተለመደው ሕጋዊ አሠራር ውጭ የደቡብ ክልል ቡና አቅራቢዎች ለሁለት ዓመት የሚቆይ የብድር ማራዘሚያ እንዲሰጣቸው፤ ብድር ከፈለጉም ምንም ዓይነት እገዳ እንዳይኖርባቸው የተፈቀደው ችግሩ ምን ያህል ቢሆን ነው? የሚለውን ጥያቄ ያስከትላል፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች የመንግሥት ውሳኔ ትክክል ስለመሆኑ ያምናሉ፡፡ መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከቡና አቅራቢዎቹ በተደጋጋሚ የቀረቡ ጥያቄዎችና የመፍትሔ ሐሳቦችን የያዙ አማራጮች ቀርቦለት ሲመከርበት ቆይቶ የተወሰነ ስለመሆኑ ቡና አቅራቢዎቹን የሚወክለው የደቡብ ክልል የቡና አጣቢዎች፣ አበጣሪዎችና አቅራቢዎች ዘርፍ ማኅበር አመራሮች ይገልጻሉ፡፡ ይህ ባይሆን ኑሮ ግን ከፍተኛ ቀውስ ይከሰት ነበር ይላሉ፡፡ ቡና አቅራቢዎቹ ለገጠማቸው ችግር በደቡብ ክልል ብቻ ለብድር ማስያዣነት ያዋሏቸው ከ2,500 በላይ ሕንፃዎችና መኖሪያ ቤቶች ቤቶች በሃራጅ በጨረታ ሊሸጡ ተቃርበው እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ በአነጋጋሪው የመንግሥት ውሳኔ ላይ የፊት አውራሪነቱን ሚና ተጫውቷል የተባለውን ማኅበር መሥራችና ፕሬዚዳንት አቶ ዘሪሁን ቃሚሶን ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡ በደቡብ ክልል ተፈጠረ የተባለውን ችግርና አሁን የተደረሰበት ውጤት አጠቃላይ ይዘት ለማሳየትም ከኋላ ታሪኩ በመንደርደር የተደረገው ቃለ ምልልስ ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበሩ አፈጣጠር በክልሉ ከተከሰተው የቡና አቅራቢዎች ኪሣራ ጋር የተያያዘ ነው ይባላል፡፡ እርስዎም የማኅበሩ ምሥረታ ሐሳብ አፍላቂ ስለነበሩ የማኅበሩ አመሠራረትና የኋላ ታሪክ  ምን እንደሚመስል ቢነግሩን? አርሶ አደሮችስ እንዴት ነበር ወደ ቡና ማቅረብ ሥራ የገቡት?

አቶ ዘሪሁን፡- ማኅበሩ የተቋቋመው የመንግሥትን ፖሊሲ መሠረት በማድረግ ወደ ቡና ንግድ በገቡ የግል ቡና አቅራቢዎች ነው፡፡ በደርግ ጊዜ የታጠበ ቡና ሥራ በማኅበራት እጅ ይካሄድ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ፣ የእዝ ኢኮኖሚ ሥርዓት ፈርሶ ወደ ነፃ ገበያ በሚመጣበት ጊዜ በማኅበራት ብቻ ሲካሄድ የነበረው የታጠበ ቡና ንግድ ሥራ ግለሰቦችም እንዲገቡበት መመሪያ ወጥቷል፡፡ በመመሪያው መሠረት የታጠበ ቡና አቅራቢነትለ የግሉ ዘርፍንም አካተተ፡፡ ቡናው ያለው በአርሶ አደሩ ጓሮ ነው፡፡ የታጠበ ቡና የማቅረብ ሥራ ደግሞ ያለ ውኃ የማይካሄድ ስለሆነና ለአጠባ የሚፈለገውም ውኃ መገኛው ወንዝ በአርሶ አደሩ ደጃፍ የሚያልፍ በመሆኑ ይህንን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ያስቻለ ነው፡፡ ይህንን ሀብት አገሪቱ ተግባራዊ ባደረገችው የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንደተመለከተው የአካባቢው ሕዝብ ባለው ሀብት የመጠቀም መብትን ያጐናፀፈ ሆኗል፡፡ አርሶ አደሩ በቀዬው ያለውን ሀብት፣ በጓሮው ያለውን ወንዝ እንደ መዋጮ ይዞ ባህር ዛፍና አሸዋ ከአካባቢው ወስዶ፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የመፈልፈያ፣ የመገንቢያና የሥራ ማስኬጃ ብድር ሰጥቶት ሥራ ውስጥ እንዲገባ አስችሎታል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ የተደረገው መቼ ነበር? በአካባቢያችሁ ያሉ አርሶ አደሮች ወደ ቡና አቅራቢነት እንዴት እንደተሸጋገሩ ቢያስትውሱንና ከፍተኛ እንደሆነ በሚነገርለት ኪሳራ ውስጥ የተገባበት ምክንያትም ምንድን እንደነበር ቢገልጹልን?

አቶ ዘሪሁን፡- በ1986 ዓ.ም. ነው፡፡ በአዲሱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሠረት የመጀመሪያውን መፈልፈያ በማቋቋም ወደ ሥራ የገቡት አቶ ሲላዳ ኤ የሚባሉ የአካባቢው ተወላጅ ናቸው፡፡ እኚህ ሰው ቀድሞም በኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት መፈልፈያ የነበራቸው ቢሆንም፣ በደርግ ተወረሰባቸው፡፡ ደርግ ሲወድቅ ቀድሞ ይሠሩበት የነበረው ቦታ ተፈቅዶላቸው ተመልሰው ወደ ቡና መፈልፈል ሥራቸው ገቡ፡፡ የእርሳቸው ዳግመኛ ሥራ መጀመር ጥሩ ምሳሌ ሆኖ ሌሎችም በመፈልፈያ ሥራ ውስጥ መግባት እንደሚችሉ ማረጋገጫ ሆነ፡፡ ሁሉም አርሶ አደር ቡናውን፣ ወንዙን፣ መሬቱንና በአካባቢው ያለውን የግንባታ ግብዓቶች በመዋጮነት በሚያስያዝ በርካታ አርሶ አደሮች ኃላፊነቱ በተወሰነ የግል ማኅበር በመደራጀት  በቡና ማቅረብ ንግድ ውስጥ ገቡ፡፡ ነገር ግን ወደዚህ ንግድ ሲገቡ በቂ የንግድ ክህሎት አልነበራቸውም፡፡ የኋላ ታሪካቸውንም ብታይ በንግድ ሥራው ዕውቀት የሌላቸው ስለመሆኑ ትገነዘባለህ፡፡ ሆኖም በተፈጠረላቸው አጋጣሚ ንግዱን የጀመሩት ቡና ሁልጊዜ አትራፊ ያደርጋል በሚል ስሜት ነው፡፡  የአጋጣሚ ሆኖ ደግሞ አርሶ አደሮቹ ወደ ቡና ማቅረብ ሥራ በገቡበት ወቅት አገሪቱ የምንዛሪ ለውጥ ያደረገችበት ጊዜ ስለነበር በርካታ አርሶ አደሮች በእጃቸው ያለውን ቡና ሲሸጡ ከፍተኛ ገንዘብ አገኙ፡፡ ይህ ክስተት ቡና ሁልጊዜ አትራፊ እንደሚያደርግ በማመን ዋጋ እየጨመሩ ሥራውን መሥራት ቀጠሉ፡፡ በመሆኑም ከ1989 እስከ 1990 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ በጥሩ ሁኔታ ተሠራ፡፡ ከ1990 እስከ 1991 ዓ.ም. ግን የቡና አቅራቢዎች ከፍተኛ ኪሣራ ውስጥ ገቡ፡፡  

ሪፖርተር፡- የኪሣራው ምክንያት ምንድነው?

አቶ ዘሪሁን፡- በወቅቱ ለነበረው ከፍተኛ ኪሣራ ዋነኛ ምንጩ የዓለም የቡና ዋጋ መውደቅ ነው፡፡ የዓለም የቡና ዋጋ ከግምት ውስጥ ሳይገባ ይከናወን በነበረ የእሸት ቡና ግዥዎች ምክንያት የተፈጠረ ቀውስ ነው፡፡ ሌሎች ምክንያቶችም ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- ቡና አቅራቢዎች የዓለምን የቡና ዋጋ ሳይመዝኑ የተደረገ ግዥ የፈጠረው ችግር ነው ሲባል ምን ማለት ነው?

አቶ ዘሪሁን፡- ከመነሻው የነበው የእሸት ቡና ግዥ ነው፡፡ በውድ ዋጋ ገዝተው እዚህ አምጥተው የሚሸጡበት ዋጋ ዝቅተኛ ሲሆን ኪሣራው መጣ፡፡ በመግዛት እንጂ በመሸጥ አይደለም የምታተርፈው፡፡ ትርፍህ ስትገዛ ነው፡፡ ትርፍህ ስትገዛ ነው ማለት ለምሳሌ ከአምራቹ በአሥር ብር እንገዛለን እንበል፡፡ በአሥር ብር ስትገዛው ግን 15 ብር እንደምትሸጠው አውቀህ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ የትርፉ ግዥው ዋጋ ላይ መሠረት ያደረገ ነው ማለት ነው፡፡ በዚያን ወቅት ግን እንዲህ ያለውን መሠረታዊ ነገር ወይም የዓለም ቡና ዋጋን ግምት ውስጥ ሳያስገቡ በውድ ዋጋ ግዥውን ፈጸሙ፡፡ ይህንንም ያደረጉት በቀደመው ዓመት ትርፍ ስለተገኘ ዘንድሮም ትንሽ ጨምረን ብንገዛ ያተርፈናል ከሚል መነሻ በስሜት በመሠራቱ ነው፡፡ ቡና አያከስርም የሚለው ስሜት የፈጠረው ነው፡፡ ሆኖም ከፍተኛ ኪሣራ አመጣ፡፡ ያኔ ለሥራው ማስኬጃ ብድር የሰጠው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ስለነበር፣ በተፈጠረው ኪሣራ ምክንያት አቅራቢዎቹ ብድሩን መክፈል ባለመቻላቸው ባንኩ ተበዳሪዎች ያስያዙትን ንብረት ለመሸጥ ጨረታ ማውጣት ጀመረ፡፡ ይህንን መቋቋም አልተቻለም፡፡ ይህንን ከፍተኛ ኪሣራ ለመቋቋም በኅብረት መሥራትና ድምፅን ማሰማት ግድ ሲሆን፣ የምንቀራረብ ሰዎች በጋራ ሆነን ማኅበሩን ልንፈጥረው ቻልን፡፡ ነገር ግን የግል ዘርፍ ማኅበራትን ለማቋቋም መመሪያም ደንቦችም አልወጡም፡፡ ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ መደራጀት አይከለከልም ብለን በመነሳት የክልሉን መንግሥት ስንጠይቅ ተባበረን፡፡ ሒደቱ ተግዳሮት የበዛበት ቢሆንም ማኅበሩ ግን ተቋቁሟል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩን ለመመሥረት የእርስዎን ሐሳብ የተቀበሉና በመሥራች አባልነት የተመዘገቡ ቡና አቅራቢዎች ምን ያህል ነበሩ? በወቅቱ ለመክፈል ያልቻላችሁት ብድር መጠንስ ምን ያህል ነበር?  

አቶ ዘሪሁን፡- ሲጀመር የማኅበሩ አባላት 120 አካባቢ ነበርን፡፡ ያኔ የነበረብንም ዕዳ ከ300 ሚሊዮን ብር አይበልጥም ነበር፡፡ ምክንያቱም ያኔ የእሸት ቡና መግዣ ዋጋ አነስተኛ ስለነበር ነው፡፡ ቢበዛ አንድ ኪሎ እሸት ቡና ከሁለት እስከ አራት ብር ይገዛ ነበር፡፡ ስለዚህ የብድር መጠኑም በዚያው ልክ ነው፡፡ እንዲያውም በ1989 ዓ.ም. ገደማ አካባቢ የአንድ ኪሎ እሸት ቡና መግዣ ዋጋ ከ50 ሳንቲም እስከ አንድ ብር ነበር፡፡ ብዙ ገንዘብም አይጠይቅህም ነበር፡፡ ይህም ቢሆን ግን ብድሩን መመለስ አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ችግራችንን አስረድተን መንግሥት እገዛ እንዲያደርግልን ጠየቅን፡፡ ነገር ግን ለኪሳራችን የኋላ ታሪካችን ችግርም የራሱ ድርሻ ነበረው፡፡

ሪፖርተር፡- የኋላ ታሪካችን ችግር አለው ሲሉ ምን ማለትዎ እንደሆነ ቢያብራሩልን?

አቶ ዘሪሁን፡- የኋላ ታሪካችን ወይም ወደ ሥራ ስንገባ ችግር ነበር ያልኩበት ምክንያት ወደ ሥራው የገባው አርሶ አደር የነጋዴነት ባሕሪይ ያልነበረው በመሆኑ ነው፡፡ በቃ ቡና ውስጥ ግባ በመባሉና መንግሥትም ገንዘብ ሰጥቶት ሥራውን የጀመረ በመሆኑ ነው፡፡ ቡና አቅራቢ እንዲሆን፣ የመፈልፈያ ባለቤት እንዲሆን ሲደረግ አርሶ አደሩ በጥሬ ገንዘብ አስተዋጽኦ አላደረገም፡፡ መዋጮው በዓይነት ነበር፡፡ ገንዘብ ወደ ማፍራቱ ገባ፡፡ ገንዘብ እያፈራ ሲሄድም ንግዱ እየገባው ነበር፡፡ ነገር ግን ንግዱን እንዴት ማስተዳደር እንዳለበት፤ በተለይ የዓለም ገበያን የመከታተል፤ የቡና ንግድን የዓለም ገበያ ችግሮች ለይቶ አለማወቅና፣ ቡና የዓለም ገበያ ተፅዕኖ እንዳለበት እንዲሁም የሚወሰነውም በዓለም ገበያ ስለመሆኑ ብዙም ግንዛቤ ባለመኖሩ ችግሩ የመጣው፡፡ ይህንን ለማስጨበጥ ቢሞከርም ለመመለስ አልተቻለም፡፡ ቡና ያተርፋል የሚል እምነት ብቻ ይዞ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ በንግድ ዙሪያ ያለው የግንዛቤ ችግር ነበረበት ያልኩት፡፡ በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቡና ማቅረብ ሥራ ላይ ዕንግዳ ነበርን ብለዋል፡፡ በወቅቱ ብድሩን የሚሰጧችሁ ባንኮች አያማክራችሁም ነበር ማለት ነው? ባለሙያዎችስ አያግዛችሁም ነበር?

አቶ ዘሪሁን፡- ከአበዳሪ ባንኮች ዋናው ልማት ባንክ ነበር፡፡ መጀመሪያው ላይ ባንኩ ይህንን ይሠራ ነበር፡፡ ያማክር ነበር፡፡ ከ100 እስከ 200 የሚሆኑ መፈልፈያዎች በሉበት  ሁሉንም ተበዳሪ ለማማከር ግን አቅም ይጠይቃል፡፡ በየቅርንጫፉ የሚመድበው ሁለትና ሦስት ሰዎችን ስለነበር ሁሉንም መከታተል አይችልም፡፡ የገቢና ወጪ ሥርዓቱን ከመመልከት የዘለለ አልነበረም፡፡ በኋላ ላይ የብድሩ መክፈያ ጊዜ ደርሷል ከማለት ያለፈ የባንኮች እገዛ አልነበረም ሊባል የሚችልበት ደረጃ ላይ ተደረሰ፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ ጭምር ነው ወደ ኪሳራ የተገባው፡፡ መንግሥትን እነዚህ ችግሮች አሉብን፣ አንዴ ስንመታ መነሳት አልቻልንምና ደግፉን ወደ ማለት የገባነው፡፡ ቡና ሲሰጥህ ዳጐስ ያለ ነገር ያመጣል፡፡ ሲያከስርህም የዚያን ያህል ይወስድብሃል፡፡ ስለዚህ ከተመታህ በኋላ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለመመለስም እንደገና ቡና መሥራት አለብህ፡፡

ስለዚህ ቀደም ብሎ በነበረው አሠራር ስንከስር መፈልፈያዎቹን ልማት ባንክ ይረከባቸውና በሃራጅ ይሸጣቸዋል፡፡ በሃራጅ ሲሸጥ ደግሞ ቡና አቅራቢው ገንዘብ በእጁ ስላልነበረው ንብረቱን ማስጣል አይችልም፡፡ ባልተጠበቀ መንገድ በሚፈጠር ኪሳራ ለባንክ ብድሩን መክፈል ባለመቻሉ ለማስያዣ የተጠቀመበት ንብረት ከእጁ እየወጣ ሄደ፡፡ ሀብቱም በዚሁ ሥርዓት የመጣ ነውና አሁንም ቡና አቅራቢው ተደግፎ መንግሥት የሆነ ነገር አድርጐለት የክህሎትም የፋይናንስም ድጋፍ ተደርጐለት ከችግሩ መውጣት አለበት ብለን ሐሳብ አቀረብን፡፡ ይህንን ሐሳብ ስናቀርብ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ መመሪያ ተሰጠን፡፡  

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት መመሪያ ነበር የተሰጠላችሁ?

አቶ ዘሪሁን፡- ባንኮች ብድሮቹን አስታመው ተበዳሪዎቹን ደግፈው ከገቡበት ችግር እንዲያወጡ ማለት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሰጡት መመሪያ መሠረት በዚያን ወቅት የተፈጠረብንን ችግር አለፍነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ መመሪያ በወቅቱ ያለባችሁን ብድር መክፈል አስቻላችሁ? መፍትሔስ ተገኘ?

አቶ ዘሪሁን፡- የነበረብንን ብድር አስታመሙ፡፡ ተጨማሪ ዋስትና አቅርቡ እየተባለም የሥራ ማስኬጃ ተሰጠ፡፡ ማኅበሩም ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመሆን መቆጣጠርና የግዥ ሥርዓቱን መከታተል ጀመረ፡፡ ነፃ ገበያ ነው ቢባልም ግብይቱ የዓለም ገበያን መሠረት ያደረገ ስለሆነና ዋጋውም ሊዋዥቅ ስለሚችል መረጃዎችን እየተከታተልን በዚያ መሠረት መሄድ አለብን ብለን እየሠራን ነበር፡፡ በዚህም ማንሰራራት ተቻለ፡፡ ነገር ግን ልማት ባንክ ቀስ በቀስ እየወጣ መጣ፡፡

ሪፖርተር፡- ልማት ባንክ የወጣው ለቡና ሥራ ከሚሰጠው ብድር ነው?

አቶ ዘሪሁን፡- አዎ፡፡ ልማት ባንክ ለትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ብድር ወደ መስጠቱ ይሂድ ተባለ፡፡ የቡና አቅራቢዎች ተበዳሪዎችን የግል ባንኮች ይረከቡ ተባለ፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ የግል ባንኮች ብድር ለመስጠት ማስያዣ ይፈልጋሉ፡፡ ከልማት ባንክ ስንበደር መፈልፈያውን ብቻ በማስያዝ 400 ሺሕ ብር ይሰጡን ነበር፡፡ ተጨማሪ ማስያዣ ካለህ ደግሞ የተወሰነ ገንዘብ ይጨምርልሃል፡፡ ሥራው የሚፈልገውን ያህል ገንዘብ ነው የሚሰጥህ፡፡ ስለዚህ የእኛ ብድሮች ወደ ግል ባንኮች ሲዛወሩ ማስያዣና ሥራውን የሚገልጽ ፈቃድ ያቀረበ በሙሉ ተበዳሪው ያቀረበው ዝርዝር ለቡናው ምን ያህል ገንዘብ ያስፈልገዋል? ሳይባል ከቡናም ውጭ ላለው ሥራውም ገንዘብ በብዛት መስጠት ተጀመረ፡፡

ሪፖርተር፡- ለቡና ተብሎ የተሰጠ ብድር ለሌላ ሥራ እየዋለ ነበር ማለት ነው?

አቶ ዘሪሁን፡- ለቡና ተብሎ የተሰጠ ለሌላ የዋለም አለ፡፡ እዚህ ላይ አላግባብ የተደረገ ነገር አለ፡፡ የግል ባንኮች ዋና ዓላማቸው ትርፍ ነው፡፡ በሕዝብ ገንዘብ የተቋቋሙ ናቸው፡፡ ባለ አክሲዮኖች አሏቸው በየዓመቱ ትርፍ ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን ሌሎች ነገሮችን ከግምት ውስጥ አላስገቡም፡፡ በማበደር ብዙ ትርፍ ታገኛለህ፡፡ በዚህ አመለካከት ነው ሲሄዱ የነበሩት፡፡ ብዙ ዋስትና ያቀረበ ብዙ ገንዘብ ይበደራል፡፡ የእሸት ቡና ግዥ ዋጋ እየጨመረ ሲሄድ ብዙ ቡና ለመሰብሰብ ብዙ ገንዘብ ያስፈልግሃል፡፡ የአንድ ኪሎ እሸት ቡና ዋጋ ከ50 ሣንቲም ተነስቶ ሰባትና ስምንት ብር ገባ፡፡ ብዙ ገንዘብ ለማግኘት ደግሞ ብዙ ማስያዣ ያስፈልገሃል፡፡ ይህ አካሄድ ግን አንድ ነገር አመጣ፡፡ አቅራቢው ብዙ ገንዘብ ለመበደር የግድ ለብድሩ ማስያዣ የሚሆን ንብረት እንደሚያስፈልገው በመረዳት በእጁ ያለውን ገንዘብ ለባንክ ማስያዣ ይሆነኛል በማለት ቤት ወደ መገንባት ገባ፡፡ ቡና አቅራቢዎቹ በየዓመቱ ከሚያገኙት ገንዘብ ወደ ከተማ መጥተው ቤት መገንባት ጀመሩ፡፡ ግንባታውን የሚያከናውኑት  በዋስትና ለማስያዝ ነው፡፡ ነገር ግን በእጃቸው ያለውም ንብረት ለዋስትና አልበቃ ሲላቸው የቤተሰቦቻቸውን፣ የጓደኞቻቸውን ቤቶች እያስያዙ ለሥራ ማስኬጃ ዕጥረት ማቃለያነት አዋሏቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በአካባቢያችሁ ያሉ አቅራቢዎች የሌሎች ሰዎችን ንብረት ለብድር  ማስያዣነት ሲያቀርቡ ለባለንብረቱ ኮሚሽን እንደሚከፍሉም ይነገራል፡፡

አቶ ዘሪሁን፡- አዎ፡፡ ቤት ላስያዘለት ሰው ከሚበደረው ገንዘብ ላይ በማስላት ኮሚሽን ይከፍላል፡፡ በቀረው ደግሞ ይሠራል፡፡ ይህ አካሄድ መጠላለፍ ፈጥሯል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት ቡናው ተሰብስቦ ለማዕከላዊ ገበያ ይቀርብለታል፤ ይሸጣል፡፡ ዶላር ይመጣል፡፡ ባንክ በምንም ዓይነት መንገድ ይሁን ወለዱን ያገኛል፡፡ መሃል ላይ ግን ቡና አቅራቢው በየጊዜው በሚመጣበት ኪሣራ እየተመታ ሄደ፡፡ ከዚያም ከማይወጣበት ችግር ውስጥ ገባ፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሩ እየተባባሰ የመጣው ከመቼ ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ዘሪሁን፡- ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ በመሃልም የመንገዳገድ ነገር ነበር፡፡ በእኛ ጥናት ወደዚህ ችግር የከተቱን የተለያዩ ምክንያቶች ሊሆኑ አንዱ ለቡና ትኩረት አለመሰጠቱ ነው፡፡ ቡና ከታች ሲሰበሰብ ለግዥው የሚሆን የሥራ ማስኬጃ ካፒታል እጥረት እንዴት ይቀረፋል ተብሎ አለመሠራቱ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ መንግሥት በሚፈልገው መጠን ቡና እየቀረበለት ቢሆንም ታች ያለው ችግር አልታየም ነበር፡፡ እኛም ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሥራ ማስኬጃ እጥረት ስለመኖሩ በተደጋጋሚ ስንገልጽ ነበር፡፡ የአንድ ኪሎ እሸት ቡና መግዣ 10 ብር በሚደርስበት ጊዜ ግዥ ፈጽሞ ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ወደማይችልበት ደረጃ ይደርሳል ብለን ስንገልጽ ቆይተናል፡፡ ለላኪዎች እንደሚደረገው በአነስተኛ ወለድ ለእሸት ቡና መግዣ ይሆን ዘንድ የመፈልፈያዎቹ ግምት በትልቅ ዋጋ ተሰልቶ ብድር ይፈቀድ ብለናል፡፡ መንግሥት ቁጥጥር እያደረገ ይሠራ ብለናል፤ ትኩረት ግን አላገኘም፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ስናሳስብ ቆየን፡፡ ሌላው የምርታማነት ችግር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የምርታማነት ችግር ሲሉ?

አቶ ዘሪሁን፡- ምርታማ አለመሆን ነው፡፡ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ቡና አራት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ነው ያለው፡፡ በፊት ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ነበር፡፡ ደርግ ቡናና ሻይ ሚኒስቴር አቋቁሞ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ከገባ በኋላም ለተወሰነ ጊዜ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ተብሎ ሲሠራ ነበር፡፡ በኋላ ቡና ግብርና ሚኒስቴር ውስጥ ገባ፡፡ እንደ ማንኛውም ሰብል መታየት አለበት ተብሎ የተደረገ ነው፡፡ በእኛ እምነት ግን ቡና እንደ ማንኛውም ሰብል መታየት የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- ቡና እንዲህ በተለየ መታየት አለበት ስትሉ ምን ምክንያት ኖሯችሁ ነው?

አቶ ዘሪሁን፡- ምክንያቱም ቡና ዶላር የማምጣት አቅሙ በየጊዜው እየጨመረ ነው፡፡ በምርቱም ሆነ በገበያ ባህሪው ልዩ እንክብካቤ ያስፈልገዋል፤ ባለቤት ይፈልጋል፡፡ ጥያቄያችንም ይሄ ነው፡፡ ጥያቄያችን ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ በዚህ መካከል የጠቀስኩልህ ቀውስ ተፈጠረ፡፡ የቀውሱ መፈጠር ደግሞ የሥራ ማስኬጃ ካፒታል እጥረት በማስከተሉ ቡና አቅራቢው የአማቹን፣ የጓደኞቹን፣ የዘመዶቹን በአጠቃላይ የሦስተኛ ወገን ንብረትን ሆነው በዋስትና የተያዙ ቤቶች በሙሉ ብድሩ መክፈል ሳይችል ሲቀር ወደ ሃራጅ ሽያጭ ተገባ፡፡ ታውቃለህ በዚህ ችግር በሐዋሳ ከተማ ብቻ ወደ 2,400 ቤቶች በብድር ዋስትና ምክንያት ተይዘዋል፡፡ እነዚህ ቤቶች በሙሉ ግን የቡና ነጋዴው አይደሉም፡፡ የሦስተኛ ወገን ብረቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ከ2,400 በላይ ቤቶች ከተሸጡ ከ10 ሺሕ በላይ ሰዎች ይፈናቀላሉ ማለት ነው፡፡ መፈናቀሉም ተጀምሮ ነበር፡፡ ምክንያቱም ባንኮች ያበደሩትን ገንዘብ ለማስመለስ ቤቶቹን ወደመሸጡ ገብተው ነበር፡፡ የብሔራዊ ባንክ መመሪያ ደግሞ ባንኮች አንድን ብድር ከሦስት ጊዜ በላይ ማራዘም አልችሉም ይላል፡፡ ስለዚህ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ባንኮች ብድሩን ሦስት ጊዜ ቢያራዝሙ 2006 ላይ የተራዘው ጊዜ አለቀ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ንብረቶቹን ለማትረፍ የሚያስችል አቅም ሊፈጠር አልተቻለም፡፡

ከ2005 እስከ 2006 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ችግሩ ከባድ በመሆኑ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመነጋገር ብሔራዊ ባንክን በማስፈቀድ ተጨማሪ ማራዘሚያ ጊዜ ተጠየቀ፡፡ ተፈቀደ፡፡ አሁንም ግን ከቀውሱ መውጣት አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ቀውሱ ካልተስተካከለ የብድር መክፈያውን ጊዜ ማራዘም መፍትሔ አይሆንም ማለት ነው፡፡

ሌላ ሰው ንብረቱን ሊያሲዝልህ አለመፈለግም መጣ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ልትነግድ የማትችልበት ደረጃ ላይ ተደረሰ፡፡ ባንክም ያንተን ብድር ከሦስት ጊዜ በላይ ካራዘመ በኋላ ብድር አይሰጥም፡፡ ስለዚህ ንብረቶቹ ሊሸጡ ሆነ፡፡ ይህ ክስተት ሐዋሳን የባንክ ከተማ አድርጓታል፡፡ አሁን እየተፈናቀለ ያለው ነጋዴው ብቻ አይደለም፡፡ ኅብረተሰቡ ነው፡፡ ለክልላችን ፖለቲካዊና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ነው፡፡ የተፈጠረውን ቀውስ ከመንግሥት ጋር በመነጋገር ለመቅረፍ ኃላፊነት አለብን፡፡ መፍትሔ ይሆናል የተባለ ሐሳብም ተፈጠረ፡፡ ማራዘም መፍትሔ አይሆንም፡፡ ከ2004 እስከ 2006 ብድሩ እየተራዘመ መጣ፡፡ ነገር ግን ብድርን ከሦስት ጊዜ በላይ ማራዘም ስለማይቻል የክልሉ መንግሥትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባደረጉልን ድጋፍ እንደገና ባንኮች የተበዳሪዎችን ብድር መክፈያ ጊዜ እንዲያራዝሙ ፈቀዱ፡፡

ሪፖርተር፡- ከባንኰቹ የተበደራችሁት ምን ያህል ይሆናል?

አቶ ዘሪሁን፡- የብድሩ መጠን ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአጠቃላይ የቡና አቅራቢዎች ለወሰዱት ብድር ያስያዟቸው ንብረቶች መጠንስ ምን ያህል ይሆናል?

አቶ ዘሪሁን፡- ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ይደርሳል፡፡

ሪፖርተር፡- የተያዙት ቤቶች በሐዋሳ ብቻ ነው ወይስ ከሐዋሳ ውጭም አሉ?

አቶ ዘሪሁን፡- ከሐዋሳ ውጭ ያሉም አሉ፡፡ ዲላ ላይ አሉ፡፡ አለታ ወንዶና ሌሎች ቦታዎችም አሉ፡፡ ትልቁን ቁጥር የያዘው ግን የሐዋሳ ከተማ ነው፡፡ አሁን ቀውሱን እጅግ አሳሳቢና አስፈሪ አድርጐት የነበረው በሐዋሳ ከተማ በባንክ ዕዳ የተያዙት ከ2,400 በላይ ቤቶች ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ ወቅቶች የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘም ተደርጐ ብድሩ ባለመክፈሉ የተሸጡ ቤቶችና ንብረቶች አሉ?

አቶ ዘሪሁን፡- የተሸጡ ንብረቶች አሉ፡፡ እስካሁን እንኳ 18 የቡና መፈልፈያዎችና 78 ቤቶች ተሸጠዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበራችሁ ጉዳዩን አጠንክሮ በመያዝ በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያልታሰበ ውሳኔ እንደወሰን አድርጓል እየተባለ ነው፡፡ ብድር እንዲራዘምላችሁ የሚያስችል የተለየ ዕድል እንዲሰጣችሁ ተደርጓል፡፡ ብሔራዊ ባንክ እናንተን ለማገዝ ብሎ ከመመሪያ ውጭ ውሳኔ እስከማስተላለፍ የደረሰው ከችግር ትወጣላችሁ ብሎ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህንን ያህል መስዋዕትነት ከተከፈለላችሁ በኋላስ ብድሩን ከፍላችሁ ከገባችሁበት ቀውስ ወጥታችሁ ውጤታማ የምትሆኑት እንዴት ነው?

አቶ ዘሪሁን፡- ተመሳሳይ ችግር ከዚህ ቀደም በማኅበራት ላይ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ብድር ዋስትና አይጠይቃቸውም፡፡ መንግሥት ዋስትና ይወስዳል፡፡ ምክንያቱም በኅብረት የተደራጁ አርሶ አደሮች ናቸው ተብሎ ስለሚታሰብ መፈልፈያው ብቻ ይያዝና ቀሪው ገንዘብ የመግዛት አቅማቸው በፈቀደው መሠረት በመንግሥት ዋስትና አማካይነት ገንዘብ ይበደራሉ፡፡ እንደዚህም ተደርጐላቸው ችግር ውስጥ ገቡ ለምን ሲባል በቂ የመንግሥት ክትትልና ድጋፍ ስላልነበር፡፡ እንዲሁም ሥራውን የሚመሩ ሰዎች ብቃትና ሥራውን በአግባቡ ባለመያዛቸው ነው፡፡ ይህ እንደታወቀ ማኅበራቱ ብድሩን እንዲያገኙ መንግሥት ዋስትና ገብቷልና መንግሥት ገንዘቡን ክፈል ሲባል የክልሉ መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ ገባ፡፡ ምክንያቱም የተበደሩት የአገር ገንዘብ ነው፡፡ ልማት ባንክም ቢያበድር ገንዘቡ የሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ምን እናድርግ ለሚለው መንግሥት ሌላ ዋስትና ገብቶ አብሮና ተከታትሎ እንዲሠራ፤ ሌላው ቀርቶ ከባንክ የሚያወጡት ገንዘብ በትክክል ቡና ላይ ስለመዋሉ እያረጋገጡ ደግፈው በመሄዳቸው ዛሬ የይርጋ ጨፌና የሲዳማ ዩኒየኖች ከፍተኛ ገንዘብ ያላቸው በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት እንዲያፈሩ ያደረጋቸው መንግሥት ነው፡፡

አሁንም ለእኛ ተብሎ የተወሰነው ውሳኔ ዝም ብሎ አይደለም፡፡ ብድር ይራዘም፣ ንብረታችን አይሸጥ ሲባል ለሁለት ዓመት ይህንን ጉዳይ የሚከታተል ኮሚቴ እንዲሰየም ተደርጐ ነው፡፡ ከአበዳሪ የፋይናንስ ተቋማት፣ ከመንግሥት፣ ከቡና አቅራቢው መንግሥት የሚመርጠው አምስት አባላት ያለበት ኮሚቴ አለ፡፡ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ የገንዘብ ፍሰቱ ቁጥጥር ይደረግበታል፡፡ እስከዛሬ የነበው አንዱ ክፍት ክትትልና ድጋፍ አለማድረግ ነበር፡፡ ምክንያቱም ገንዘብ ይሰጡና የብድር መክፈያ ጊዜ ሲደርስ ብቻ ነው ባንኰቹ የሚደውሉት፡፡ ቢሯቸው ሆነው ገበያው እንዴት ነው የሚቆጣጠሩት፡፡ በዚያ ገንዘብ ተበዳሪው መኪና ይግዛበት፣ ቤት ይሥራበት ወይም ሌላ ነገር ያድርግበት የመከታተልና የመደገፍ ሥራ አልነበረም፡፡ አሁን ግን እንዲህ ዓይነቱ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ መሠረታዊ የሆነ ሌላም ጉዳይ አለ፡፡ ችግሩ ባንኮች ላይ ብቻ እንዲነጣጠር ማድረጉ ተገቢ የማይሆንበት ምክንያት አለ፡፡ በእናንተ ዘርፍ ብቻም ሳይሆን በሌሎችም በኩል ተበዳሪዎች የወሰዱትን ገንዘብ ከተበደሩበት ዓላማ ውጪ ለሌላ ነገር ሲያውሉ ይታያሉ፡፡ በቡና አቅራቢዎች ውስጥም  ብድርን ለሌላ ዓላማ እያዋሉ ተቸግሬያለሁ የሚሉ ባንኰችም አሉ፡፡ እንዲያውም አንዱ ችግር ይህ ስለመሆኑ ይታመናል፡፡

አቶ ዘሪሁን፡- አዎን አሉ፡፡ ቡና ያመጣው ኪሣራ ብቻ አይደለም፡፡ አስተዳደራዊ ጉድለትም አለ፡፡ ይኼ ደግሞ የኋላ ቀርነት ውጤት ነው ብዬሃለሁ፡፡ ችግር በራሱ እንድትገዛ ያደርጋል፡፡ አሁን እንዲህ ዓይነት ክፍተቶች ይደፈናሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ስንት ዓመት ነው ኋላቀር በሆነ የንግድ አሠራር የተፈጠረ ችግር ነው እየተባለ ምክንያት የሚቀርበው? ቡና አንድ ዓመት ከሰጠ በቀጣዩ ላይሰጥ ይችላል፡፡ ከዚህ ቀውስ ለመውጣት ምን ትጠብቃላችሁ?

አቶ ዘሪሁን፡- እንዲህ የሚባለው እስከዚህች ምዕራፍ ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ የመጨረሻችን ነው ትላላችሁ?

አቶ ዘሪሁን፡- አዎ፡፡ ይህንን የምንለው እኛ ይህንን ችግር ለክልል መንግሥት አሳውቀን፣ በማውገዝ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት ጠይቀናል፡፡ ውሳኔውን ሰጥቶናል፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው የእኛ ኃላፊነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ታደርጋላችሁ?

አቶ ዘሪሁን፡- መንግሥት ይህንን ውሳኔ የወሰነልን ከሕጉ በጣም ርቆ በመምጣት ነው፡፡ ሕገ ጥሶ ሲወስን ግን ምክንያት ነበረው፡፡ ይህም ሕዝባዊ መንግሥት ስለሆነ ነው፡፡ አስረግጬ ልነግርህ የምፈልገው የሚያዳምጥ መንግሥት ያለን በመሆኑ የተወሰነ ውሳኔ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን ዕድል መስጠቱ ራሱ ሕዝባዊነት ነው፡፡ ይሄ ውሳኔ ሲወሰን የብሔራዊ ባንክ ኃላፊ እስከመቼ ነው እንዲህ የምንደግፋችሁ ብለውናል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ወደዚህ ውሳኔ ለመግባት መንግሥት ምን ያህል እንደተጨነቀ ነው፡፡ ወደዚህ ውሳኔ ባይገባ ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጐች እንደሚፈናቀሉ በመረዳት ነው፡፡ ለነጋዴው ብቻ ተብሎ አይደለም፡፡ በዚህ ችግር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ስለተፈጠረና ከዚህም በላይ እንዳይሄድ ስለታሰበ ነው፡፡ ይህንን ዕድል በአግባቡ ሠርተንበት ውጤት እንዲመጣ የተወሰነ ነው፡፡ ይህንን ተአምራዊ ውሳኔና ባገኘነው ዕድል በመጠቀም የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ እናደርጋለን፡፡ ሠርተን መለወጥ ነው፡፡ አጥፊዎችንም እንቆጣጠራለን፡፡ አላስፈላጊ ውድድሮችንም እየተዋጋን እንሠራለን፡፡ በተሰጠን ዕድል ለመጠቀም ለአባሎቻችን ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- ይህ ውሳኔ ግን ብደር መክፈል የሚችለውንም የማይችለውንም ያጠቃልላል፡፡ ይህ እንዴት ይለያል?

አቶ ዘሪሁን፡- አሁን የምናስተምረው ብድር የመክፈል አቅም ያለው ብድሩን ቢከፍል ዕዳውን ነው የሚቀንሰው ብለን ነው፡፡ ችግር ያለባቸውና የሌለባቸውን ለይተን እናውቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- በማኅራችሁ የዚህ ዕድል ተጠቃሚዎች ምን ያህል ትሆናላችሁ?

አቶ ዘሪሁን፡- 250 አካባቢ እንሆናለን፡፡ አባሎቻችን 400 አካባቢ ናቸው፡፡ ዕድሉ እነሱንም ይመለከታል፡፡

ሪፖርተር፡- በሐዋሳ ከተማ ውስጥ ከ2,400 በላይ ቤቶችና ሕንፃዎች በባንክ ዕዳ ከተያዙ የእናንተ ቁጥርና የተያዘው ንብረት መጠን ግን አይመጣጠንም?

አቶ ዘሪሁን፡- ምን መሰለህ፡፡ አንዱ ተበዳሪ ሰው እኮ የ30 ሰው ቤት ነው የሚያስይዘው፡፡ ለምሳሌ 10 ሚሊዮን ብር ለመበደር ከፈለግህ ሁለት ቤቶች ለባንክ ማስያዣነት ብታቀርብ አይበቃም፡፡ ስለዚህ ባንኩ አንዱን ቤት ለማስያዣነት ለመጠቀም የሚያወጣው ግምት አንድ ሚሊዮን ብር ከሆነ አሥር ሚሊዮን ብር ለመበደር አሥር ቤቶች ያስፈልጉሃል ማለት ነው፡፡ 38 ቤት ያስያዘ ሰው አለ፡፡ የ38 ሰዎችን ቤት አስይዞ የተበደረው ብድሩን ባለመክፈሉ ከስሯል፡፡ ቤቶቹም ለጨረታ ቀርበው ነበር፡፡ ለዚህ ነው መንግሥት የወሰነው ውሳኔ ትክክለኛ የሆነው፡፡ ሕዝባዊ መንግሥት ነው የምልህም ለዚህ ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኑሮ ዛሬ የለንም ነበር፡፡ ከከፋ ነገር ወጥተናል፡፡ በምድር ላይ ሊሰጠን የሚችለው በላይ ዕድል ስለተሰጠን አሟጠን እንጠቀምበታለን፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች