Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየጁሊ ምሕረቱ ‹‹አዲስ ባዲሳባ››

የጁሊ ምሕረቱ ‹‹አዲስ ባዲሳባ››

ቀን:

የካይሮን ጥንታዊ ሥነ ሕንፃ፣ የከተማዋ ተቃርኖ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሕይወት የሚያሳየው ‹‹ካይሮ›› የተሰኘው የሥነ ጥበብ ሥራ ከዓለም የጥበብ ማኅበረሰብ ዘንድ ሂሳዊ አድናቆት እንዲሁም አክብሮት ተችሮታል፡፡ ይህ ሥራ ግብፅ ላይ አብዮት ማምጣት የቻለውን የጥምረት ኃይልና መንፈስን ጥንታዊ ሥልጣኔ፣ የእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ በሥነ ሕንፃ ላይ ያሳረፈውን አሻራ እንዲሁም አሁን ያለውን የግብፅ ገጽታ የሚያሳዩ የሥነ ሕንፃ ጥበቦች የተካተቱበት ነው፡፡

የሥነ ጥበብ ሥራው በዓለም አቀፍ የሥነ ጥበብ ሥፍራ ትልቅ ቦታ የተቸራት ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊት አርቲስት ጁሊ ምህረቱ ሲሆን፣ ሥራዎቿ ለመጀመሪያ ጊዜ በትውልድ አገሯ ኢትዮጵያ፣ በአዲስ አበባ ከሐምሌ 1 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በሞደርን ዓርት ሙዚየም በገብረ ክርስቶስ ደስታ ማዕከል ይቀርባሉ፡፡

ባለፈው ሳምንት ስለ ዐውደ ርእዩ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ‹‹ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዐውደ ርእይ ነው፡፡ ምክንያቱም ሊገለጽ የማይችል ታላቅ ችሎታና ፀጋ ያላትን በክፍለ ዘመናችን የትውልዱ ታላቅ ሠዓሊያን አንዷ የሆነችው ጁሊ ሥራዎች ይቀርቡበታል፤›› በማለት የገለጸው የዐውደ ርእዩ ኪውሬተር ዶ/ር ዳግማዊ ውብሸት ነው፡፡ የጁሊ ሥራዎች በሥነ ሕንፃ ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ፣ የቦታዎችን ታሪካዊ አሻራ፣ የከተሞችን የሥነ ሕንፃ ታሪክ፣ ከመኖር ጋር የሚደረግ ትግልን፣ በካፒታሊዝም ርዕዮተዓለም የተዋጀ ሕልምንና ጦርነትን ማሳየት የሚችሉ ናቸው፡፡

- Advertisement -

በትልልቅ ሥራዎቿ የምታተወቀው ጁሊ ዐውደ ርእይ፣ የተለያዩ የሥነ ጥበብ ጽንሰ ሐሳቦችን እንደ የጣሊያን ፊውቸሪዝም (በመጀመሪያዎቹ 20ኛው የክፍለ ዘመን ዓመታት የነበረ የሥነ ጥበብ እንዲሁም የማኅበራዊ እንቅስቃሴ ጽንሰ ሐሳብ ሲሆን ፍጥነትን፣ ቴክኖሎጂን፣ አመፀኝነትን እንዲሁም መኪናን፣ አውሮፕላንና የኢንዱስትሪ ከተሞችን የያዘ ነው፡፡) የሩሲያ ኮንስትራክቲቪዝም (ይህ የሥነ ጥበብና ሕንፃ ጽንሰ ሐሳብ ሲሆን፣ ሥነ ጥበብንና ሥነ ሕንፃን ለማኅበራዊ አገልግሎት ከማዋል ጋር የተያየዘ እንቅስቃሴ ነው፡፡)  አብስትራክት ኤስፕረሺንዝምንና (ይህ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ የመጣ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ ሥዕልን ረቂቃዊ በሆነ መንገድ ከመግለጽ በላይ የሠዓሊዎቹን አሻራ የሚያሳይ ነው፡፡) የምሥራቅ ካሊግ ራፊን (በምሥራቅ ኤዥያ አካባቢ ቻይና፣ ጃፓንና ኮሪያ ውስጥ የቻይና ፊደላትን ጥበባዊ በሆነ መንገድ ተቀምሮ የሚሠራ ሥራ ነው፡፡) ሥራዎች ይዟል፡፡

ጁሊ የተወለደችው እ.ኤ.አ. በ1970 ኢትዮጵያዊ ከሆነው የኮሌጅ ፕሮፌሰር አባቷና ከአሜሪካዊ እናቷ አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ የመዋዕለ ሕፃናት ትምህርቷን እስከ ሰባት ዓመቷ ድረስ ኦሎምፒያ አካባቢ በነበረው ፒተር ፓን መዋዕለ ሕፃናት የተከታተለች ሲሆን፣ በሰባት ዓመቷም ከቤተሰቦቿ ጋር በስደት ወደ አሜሪካ ሄዱ፡፡

በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር በሚገኘውና ‹‹የግብፅ ጥንታዊ ሥልጣኔ የጥቁር ሥልጣኔ ነው›› በሚል ፈንጣቂ ሐሳቡ አንቱታ የተቸረው አፍሪካዊ ምሁር ሼክ አንታ ዲዩፕ በተሰየመው ሼክ አንታ ዲዩፕ ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ዓመት ያጠናች ሲሆን፣ የሴኔጋል ዋነኛ ቋንቋ የሆነውን ወሎፍ ቋንቋን እንዲሁም በተለያዩ ቀለማት የሚሠሩ ልብሶችን የማቅለም ሥራም ከአካባቢው ከአዋቂዎች ጋር በመሆን አጥንታለች፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ሚቺጋን ከሚገኘው ካልማዙ ኮሌጅ ያገኘች ሲሆን፣ ከሮዴ አይላንድ ስኩል ኦፍ ዲዛይን ሁለተኛ ዲግሪዋን በሥነ ጥበብ ትምህርት አግኝታለች፡፡

ዐውደ ርእዩ ‹‹አዲስ ባዲሳባ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ የዚህ ዐውደ ርእይ ሐሳብ ከተጠነሰሰበት ጊዜ ጀምሮ፣ ዐውደ ርእዩን ከመደገፍ በተጨማሪ በደስታ እንደተቀበለችውም ዳግማዊ ይናገራል፡፡ ለጁሊ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ዐውደ ርእይ በመሆኑም፣ ዳግማዊ ‹‹ቤት የምትመጣበት›› ዝግጀት ነው ይላል፡፡

‹‹ይህን ዐውደ ርእይ ‹‹አዲስ ባዲሳባ›› ያልነው የተለያዩ ጉዳዮችን እንዲያካትት ነው፡፡ በአንድ በኩል ሥራዎቿን በትውልድ አገሯ የምታሳይበት ነው፡፡ ችሎታዋና ጥረቷን ከአገሯ ሰዎች ጋር የምትጋራበትም ነው፤ አዲስነትንም ታላቅነትንም የሚያሳይ ዐውደ ርእይ ነው፤›› የሚለው ዳግማዊ ጁሊ በዐውደ ርእዩዋ ቀጣይነት ያለው ጥምረት የምትፈጥርበት እንደሚሆንም ያምናል፡፡ ‹‹እንደ ጁሊ ያለች እውቅ አርቲስት ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ዐውደ ርእይ ስታሳይ፣ የኢትዮጵያን የሥነ ጥበብ ማኅበረሰብና መገናኛ ብዙኃን ብቻ ሳይሆን የዓለምንም የሥነ ጥበብ ትዕይንት የሚስብ ነው›› ሲል ይገልጻል፡፡

ዐውደ ርእዩ ከተማዋ ላይ ያለውን ድንቅ የጥበብ እንቅስቃሴ እንደሚያደምቅ፣ የከተማውን ገጽታ እንዲሁም የአገሪቱን የኪነ ጥበብ ድባብ በማጉላት ረገድ ዐውደ ርዕይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ይናገራል፡፡ ዐውደ ርእዩን ለማዘጋጀት የነበረውን ሒደት ዳግማዊ ሲገልጽ፣ ሥዕሎቹ የሚታዩበትን ቦታ ከመምረጥም ይጀምራል፡፡ አብዛኞቹ የጁሊ ሥራዎች ግዙፍ በመሆናቸው የትኛው ቦታ ሥራዎቿን ሊይዙ እንደሚችሉ ማሰብ ዋናውና ትልቁ ሥራ ነበር፡፡ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ሴንተርን ከመረጡ በኋላ፣ ለትልልቆቹ እንዲሁም ለአነስተኛ ሥዕሎቿ ማሳያ ቦታ እንድትመርጥ የጋለሪውን ይዘት የሚያሳይ ሳምፕል ልከውላታል፡፡ ከ15 እስከ 19 ለሚደርሱ ሥራዎቿ ጋለሪው እንደሚበቃቸው ሲገነዘቡም 17 ሥራዎች መርጠዋል፡፡ ምንም እንኳን ቦታው ለሥራዎቿ የሚበቃ ቢሆንም አንደኛው ትልቅ ሥራ በር ስለማያስገባው አማራጭ በር እንደሚጠቀሙ ዳግማዊ ይናገራል፡፡

በዐውደ ርእዩ ጁሊ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ካገኘች በኋላ የሠራቻቸውና የግል ስብስቧ የሆኑ ሥራዎች ይካተታሉ፡፡ ከ17ቱ ሦስቱ ሥራዎች ቀድሞ የሠራቻቸው ሲሆኑ፣ በሌላ ዐውደ ርዕይ ያልቀረቡ አዳዲስ ሥራዎችም ይገኙበታል፡፡

ዳግማዊና የሞደርን አርት ሙዚየም ገብረ ክርስቶስ ደስታ ሴንተር ዳይሬክተር ዶ/ር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ እንደሚናገሩት፣ ጁሊ በርካታ ዐውደ ርዕዮችን በታላላቅ ዓለም አቀፍ ሙዚየሞችና ጋለሪዎች ከማሳየቷ አንፃር፣ የአዲስ አበባውን ዐውደ ርዕይ ዕውን ማድረግ ቀላል አልነበረም፡፡ ትልቁ ፈተና የበጀት እጥረት ነበር፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ የሷን ሥራዎች ለማጓጓዝ አቅሙ ያለው ጋለሪ የለም፡፡ እንደ ዳግማዊ ገለጻ፣ 17 ሥራዎቿን ለማጓጓዝ፣ 58,000 ዶላር ወጥቶ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ በገንዘብ ረገድ ከአሜሪካ ኤምባሲና ማሪያን ጉድማን ጋለሪ በተጨማሪ ጁሊም ድጋፍ አድርጋለች፡፡

ዶ/ር ኤልሳቤጥ እንደሚሉት፣ ከማጓጓዣ ወጪ በተጨማሪ ለሥራዎቿ ኢንሹራንስ ለማግኘትም ከባድ ነበር፡፡ የሠዓሊቷ ኢንሹራንስ ድርጅት ለጋለሪው በ28 ገጽ ቅድመ ሁኔታ የላከ ሲሆን፣ ለሥራዎቿ የስድስት ሚሊዮን ዶላር ኢንሹራንስ ተገብቶላቸዋል፡፡ ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከል ጋለሪው ውስጥ ያለው የእሳት ማጥፊያ ቦታ ቅርበት፣ ሒውሚዲፋየር (ቅዝቃዜ ወይም ርጥበትን የሚጨምር መሣሪያ) ሥፕሪንክለር (እሳትን በፍጥነት ሊያጠፋ የሚችል ውኃ የሚተፋ መሣሪያ) መኖር ይገኙበታል፡፡ ‹‹ቅድመ ሁኔታዎቹ ከውጭ ሙዚየሞች አሠራር ጋር ተያይዘው የሚመጡ ናቸው፡፡ እኛ ከምንሠራበት አነስተኛ ሁኔታ አንፃር እዚህ ሥራዎቿን ለማሳየት ፍቃደኛ መሆኗ ቀናነቷን ያሳያል፤›› ትላለች፡፡

አምና በጋለሪው ውስጥ የዕውቁ አርቲስት ኦላፉር ኤሊያሰን ሥራዎች ታይተው ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ ሥራዎቹ በቦታው ላይ የሚተከሉ ስለሆኑ፣ በአገር ውስጥ የጋለሪው ባለሙያዎች ሥራው ተጠናቋል፡፡ የጁሊን ሥራዎች ለማሳየት ግን የኢንሹራንስ ድርጅቱን ቅድመ ሁኔታዎች ጋለሪው ማሟላት አልቻለም ነበር፡፡ እሷ ግን ሥራዎቿ በአገሯ እንዲታዩ ግፊት በማድረጓ ከስኬት ደርሷል፡፡ ኢንሹራንስ ድርጀቱም ኢንሹራንሱን ለመሸፈን ተስማምቷል፡፡

ከዐውደ ርእዩ በተጨማሪ ከአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ከተመረጡ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ጋር የሚደረግ ወርክሾፕ፣ ከአርክቴክቶች፣ ኪውሬተሮችና አርቲስቶች ጋር የሚካሄድ ውይይትም ይኖራል፡፡ መርሐ ግብሩ ላይ ኬንያዊቷ አርቲስት ዋንጌቺ ሙቱ እና ናይጄሪያዊ አሜሪካዊው ጸሐፊና ፎቶግራፈር ተጁ ኮሌም ይገኛሉ፡፡

በሥነ ጥበብ ሥራዎቿና በምታነሳቸው ጥልቅ ሐሳቦቿ እንዲሁም፣ የካፒታሊዝም ርዕዮተ ዓለምን በመተቸትም ጁሊ ትታወቃለች፡፡ አሜሪካ የምታደርጋቸውን አንዳንድ እንቅስቃሴዎች በቸልታ የማታልፈው ጁሊ፣ አሜሪካ በኢራቅ ውስጥ ትልቅ ኤምባሲ ስትገነባም በትችት አይታዋለች፡፡ ይኼንንም ዕቅድ ‹‹በጭፍን ካፒታሊስት ርዕዮተ ዓለም የተቃኘና የቅኝ ግዛትን ሐሳብ ያቀፈ ነው፡፡ ዕቅዱ የሚተገበረው አስከፊና የፈራረሰ ሁኔታ ባለበት ቦታ ነው፤›› በማለት ለቦምብ መጽሔት ቃለ መጠይቅ ባደረገችበት ወቅት ተናግራለች፡፡

ሌላኛው ሥራዋ በዓለም ላይ ያሉ የስታዲየሞችን ፕላን አወቃቀር ያጠናችበት ሥራ ሲሆን፣ በዚሁ መጽሔት ላይ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ ‹‹በስታዲየሞች አሠራር እገረማለሁ፣ ስታዲየሞች የሁሉም ነገር ማከናወኛ ቦታ እየሆኑ ነው፡፡ ኢስታንቡል፣ ጀርመንና አውስትራሊያ ቆይቼ ወደ አሜሪካ ስመለስ ዓለምን በምናይበት መንገድ ተገርሜያለሁ፤›› ብላ ገልጻለች፡፡

ከጥልቅ የሥነ ሕንፃ እውቀቷ ከመነጩ ሥራዎቿ በተጨማሪ፣ የአውሮፖውያን አብስትራክሽን (የረቂቅ የሥዕል ሥራ)፣ የቻይና ካሊግራፊና (በቻይና ፊደሎች የተመሠረተ የጥበብ ሥራ) የኢትዮጵያ ማኒስክሪፕቶችም (የኢትዮጵያ ጽሑፎችም) የሥራዎቿ መነሻ ናቸው፡፡ ጁሊ በሥራዎቿ ላይ ባላት ጥልቅ ዕይታ የከተማን ሕይወት በተለየ መንገድ የምታሳይ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ ከተሞች የመጡበትን ሥልጣኔ፣ የተለያዩ ባህሎች ተፅዕኖ ለበላይነት የሚዳርግ እሽቅድምድም፣ የመኖርን ትርጉም በተለያዩ ሥራዎቿ ላይ አሳይታለች፡፡

በሥነ ጥበቡ ባደረገችው አስተዋፅኦ የተለያዩ ሽልማት ያገኘችው ጁሊ፣ እ.ኤ.አ. በ2000 ከፋውንዴሽን ፎር ኮንቴምፕረሪ አርትስ፣ ግራንትስ ቱ አርቲስትስ ሽልማት አግኝታለች፡፡ የ2001 ፔኒ ማዕከል ተሸላሚ ስትሆን፣ በ2005 የማክ አርተር ፊሎሺፕን ‹‹ጂኒየስ ግራንት›› በመባል የሚታወቀውን ካገኙ አርቲስቶች አንዷ ናት፡፡

በ2007 በርሊን ውስጥ የአሜሪካን አካዳሚ ሬዚደንሲዋን ካጠናቀቀች በኋላ፣ የ15ኛ ኮሚሽን ኦፍ ዘ ደች ባንክና ሰለሞን አር ጋንሔን ፋውንዴሽን አግኝታለች፡፡ ‹‹ግሬይ ኤር›› የተሰኘው ሥራዋ፣ ከ2007 እስከ 2009 በርሊን ስቱዲዮ የተሠሩ ስድስት ትልልቅ ሥዕሎች ይይዛል፡፡

ኒዮርክ ከተማ ማንሀተን ሞደርን ዓርት ሙዚየም ውስጥ ሥራዎቿ ይገኛሉ፡፡ በ2010 የተሠራውና 7.1 በ24.3 ሜትር የሆነው በኒዮርክ ጎልድማን ሳችስ ባንክ ሕንፃ ውስጥ የተሰቀለ ሲሆን፣ በአካባቢው ለሚተላለፉ ሰዎች በመስኮት በኩል ይታያል፡፡  

በ2015 የአሜሪካ ዲፓርትመንት ኦፍ ስቴት ሜዳል ኦፍ አርትስ ሰጥቷታል፡፡ ይኼ እውቅና ከተሰጣቸው ሰባት አርቲስቶች  ጁሊ አንዷ ስትሆን፣ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ላገኙ ሥራዎቿና ባህልን በማስተዋወቅ ለምታደርገው እንቅስቃሴ የተበረከተላት ነው፡፡ በአርትኔት ቶፕ ቴን ሞስት ኤክስፔንሲቭ ውሜን አርቲስት (ሥራዎቸው እጅግ በጣም ውድ ከሆኑ አሥር ሴት አርቲስቶች) መካከል ሰባተኛውን ቦታ ይዛለች፡፡ በ2001 የሠራችው ‹‹ሬቶፒስቲክስ ኤሬኔጌድ፤ ኤ ሬንጌጅ ኤክስካቬሽን›› ከሦስት ዓመት በፊት 4.6 ሚሊዮን ዶላር በክሪስትስ ሙዚየም ተሸጧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...