Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሲከር ይበጠሳል!!

እነሆ መንገድ። ከቦሌ ድልድይ ወደ ፒያሳ ልንጓዝ ነው። ወስዶ ወስዶ ያሳረፈን ጎዳና ደግሞ ለሌላ ሽኝት ያሰናዳል። ጊዜና መንገዱ በሹክሹክታ ያጓኑትን ሚስጥር ላንደርስበት ስንዛክር ዘላለማውያን እንመስላለን። ሠልፍ እንደ ጉትቻ ግፊያ እንደ ድሪ፣ ጠብ እንደ አልቦ በጠለቁበት የሕይወት መንገድ ውበትና ፀያፍ ስፍራ ተመዳድበው እኩል ያገጣሉ። ይህ የትላንቱና የዛሬውም የነገውም ጎዳና ገጽ ነው። በስሎ በማረር የኑሮ ምጣድ ላይ ለአመል መገላበጥ ብቻ የፍጥረት ዕጣ ፈንታ ይመስላል። ‹‹ማነህ ጫማዬን ወለቀ እስኪ ወዲህ በለው?›› ይላሉ አንድ አዛውንት ወያላው የሚመረኮዛት መቀመጫ ላይ እየተደላደሉ። ‹‹እያዩ አይረግጡም እንዴት ነው ነገሩ?›› ይላል ጠና ያለው ወያላ እየተፍለቀለቀ። ‹‹ምን ላርግ ዕድሜ ደግሞ ብሎ ብሎ በየሄድኩበት እግሬን የጎተተው ሳያንስ ሌጣህን ተጓዝ ይለኛል፤›› ብለውት ለአፍታ ዝም አሉና ‹‹መስሎን ነው እንጂ ለነገሩ ሁላችንም ባዶ እግር ነን፤›› አሉ። ‹‹ኧረ ወጣቶቹ እንዳይሰማዎት። ሌላው ቢቀር እነሱ ዝም ቢሉ ይኼ ሁሉ ብራንድ ጫማ አፍ አውጥቶ ይጮሃል፤›› እያለ ወያላው ጎርፍ የገባ ጫማቸውን አራግፎ ሲያቀብላቸው ቀበል አርገው፣ ‹‹አይምሰልህ ልጄ። የጊዜ እንጂ የጫማና ልብስ ብራንድ የለውም፤›› አሉት። ይኼኔ ካጠገባቸው የተሰየመች ቀዘባ ‹‹ታዲያ ምንድነው የዘመኑ ሰው ትርፍ? ጫማና ልብሱ ካላጽናናው መንገዱንማ ይኼው እንደሚያዩት ሁሉ እየረገጠው የሚቀናው ለጥቂቶች ብቻ ሆኗል፤›› ብላ ዓይን ዓይናቸውን ስታይ ‹‹አንቺ ሴት ከእኔና ከመንገዱ ምን አለሽ? ዝም ብለሽ ሰማዩን አታይም፤›› ብለው ፈገግ አሰኙን። ደግሞ ይኼኔ መሀል መቀመጫ አጠገቤ የተሰየመ ባለመነፀር ጎልማሳ ‹‹ሰማዩንማ ዓይተነው ዓይተው ይኼው ዓይናችን ታወረ። ወዶ መሰልዎ፣ ፀሐይ በሰወረ ክቡድ ደመና ጭምር ሰው ሁሉ መነፀር መነፀር ያለው፤›› ብሎ ዞር ዞር እያለ የድጋፍ ድምፅ ፈለገ። ሲጨልምብንም ያለድጋፍ ሲበራልንም ያለአጀብ አይሆንልንማ!

ታክሲያችን መንቀሳቀስ ጀምራለች። መጨረሻ ወንበር የተየሰሙ ሦስት ወጣቶች በአንደኛው ስልክ ባህር ማዶ የሚኖር ወዳጃቸውን ያናግራሉ። ‹‹ኮንግራ ኮንግራ! ሴት ወለድክ ወንድ?›› ይጠይቃል አንደኛው። ‹‹ምን እዚህ አገር እኮ እንደዚያ ብሎ ነገር የለም። አድገው አሥራ ስምንት ዓመት ካልሞላቸው ወላጆች ፆታ መምረጥ አይችሉም ይሉሃል፤›› ብሎ ሲመልስ ታክሲያችን በድንጋጤ መብረቅ ተመታች። ጆሮ ሁሉ ወደ ስልክ ጭውውቱ ተወሰደ። ‹‹አንተ ቆይ ምን ሲያንቀዥቅዥህ ነው ከአገር የወጣኸው?›› ይላል ባለስልኩ ኤያላገጠ። ባህር ማዶ ያለው ‹‹እንዴ አንተ አልነበርክ እንዴ አንደኛው ከዚህ አገር ካልወጣህ ሰው አትሆንም እያልክ መቆሚያ መቀመጫ ታሳጣኝ የነበርከው?›› ይላል። ሳቅና ቀልድ መሃል መሃል ይቀጣጠላል። ‹‹ታዲያ ያኔ ነዋ። ያኔ መንገድ የለ መብራት የለ። ውኃ የለ። ሞባይል የለ፤›› ብሎ ተከሳሹ ወጣት ሲያስተባብል በጥግ በኩል ቆዝማ የተቀመጠች ወይዘሮ ‹‹እና ዛሬ እነዚህ ሁሉ የጠራሃቸው አሉ እያልክ ነው?›› አለችው። ወጣቶቹ ስልኩን ረስተው ‹‹ባይሆን ፅንሰ ሐሳቦቻቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ አሉ። ቀስ በቀስ ደግሞ ሁሉም ነገር ይሻሻላል፤›› አሉዋት እንደተመካከረ ሰው በትብብር። ይኼኔ ተሰዳጁ ሰምቶ ኖሮ ‹‹እናንተ ግምገማ ላይ ሆናችሁ ነው እንዴ ይምታናግሩኝ?›› ቢላቸው ታክሲ ውስጥ መሆናቸውን ይነግሩታል። ‹‹ታክሲ አይብስም ታዲያ?›› ሲል አሁንም ደግሞ የሩቅ አገሩ ሰው ሦስቱም እየተቀባበሉ ‹‹ያኔ ነዋ። ያኔ ቫይበር የለ፣ ፌስቡክ የለ፣ ቱዊተር የለ፣ ኢሜል የለ። ሰው የሚገናኘው ታክሲ ውስጥ ከዛ በዓመት አንዴ ለደመራ መስቀል አደባባይ ነበር። አሁን እኮ ዕድሜ ለኢኮኖሚና ለቴክኖሎጂ ዕድገቱ ታክሲ ውስጥ አይደለም ቤተሰብም ወሬ ጠፍቶበታል፤›› እያሉ ተቀባበሉብን። ‹‹ኧረ እንኳን ልሳን ተዘጋጋን፤ የሚያዘጋጋን ባይኖር እስካሁን ጉሮሮ አንዘጋጋም ነበር?›› አለ ጋቢና የተሰየመ ተሳፋሪ!

ጉዟችን ቀጥሏል። በአንዱ የኤፍኤም ጣቢያ ስለውስልትናና የኤችአይቪ ሥርጭት ከአድማጮች ጋር ውይይት ሲደረግ እናደምጣለን። አንዱ የራሱን የአባቱና የአያቶቹን አድራሻ ከተናገረ በኋላ ‹‹ውስልትና ያለ የነበረ ወደፊትም የሚኖር ነገር ነው፤ ዛሬ ምን ተገኘ? ነው ኮኔክሽን እንቢ ብሏችሁ ከኢንተርኔት ወሬ መለቃቀም አቃታችሁ?›› ብሎ ደነፋ። ይኼኔ ከአዛውንቱ አጠገብ የተሰየመችዋ ቀዘባ፣ ‹‹በለው ሰው ተናጋሪ ሆኖል አይገልጸውም?›› አለች። ጎልማሳው ቀበል አርጎ ‹‹እቴም ተናጋሪ እቴ። ተናጋሪ መች ጠፋ። ተናግሮ የሚያስደነግጥ እንጂ። አይደለም እንዴ? ተናጋሪ ቢኖር ዓይን በዓይን የሕዝብ ሀብት ሲመዘበር አይቶ ጉድ የሚያፈላ ይጠፋ ነበር?›› ብሎ እጆቹን በቁጭት አማታ። ቀጠለ ሌላ አድማጭ ‹‹ትውልዱንና ራዕይውን ለመጠበቅና እውን ለማድረግ ከተፈለገ ገላቸውን ሽጠው የሚያድሩ እህቶቻችንን መንግሥት መላ ፈልጎ ወደሌላ ዓይነት ሕይወት እንዲገቡ ማድረግ መቻል አለበት፤›› አለ። ይኼኔ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመች ቁንድፍት ቀበል አድርጋ ‹‹መንግሥት ያለ እኛ ድጋፍ ምን ማድረግ ይችላል?›› ከማለቷ ወይዘሮዋ ከአፏ ነጥቃ ‹‹እውነት ቢል ግፋ ተደራጁ ቢል ነው፤›› ብላ ቁጣ ቁጣ አላት። ጎልማሳው ሹክክ ብሎ ‹‹ምነው ግን ሰውን መደራጀት እንዲህ አስፈራው?›› ሲለኝ ከኋላዬ ምሁር መሳይ ወጣት ሰምቶት ኖሮ መቼ ከመደራጀቱ ሆነ ፀቡ። ‹‹አደረጃጀቱ አልገባ ብሎን ነዋ›› ብሎ አልተሰማሁም ያለውን ጎልማሳ ቀልቡን ገፈፈው። የአንዳንዱ ሰው ቀልብና ገበና ሲገፈፍ ደግሞ ቅፅበት አይፈጅም ጃል። ምነው ታዲያ ወስላታና መዝባሪውን የሚታገሰው በዛ?!

ወያላው መልሳችን ያከፋፍላል። ገሚሱ ስለታላቂቷ ብሪታኒያ ከአውሮፓ አባል አገርነት መውጣት በከፊል ዕውቀት ብዙ ግምት መፃኢ ዕድሏን ይፈተፍታል። አንዱ ለምሳሌ በቃ የእንግሊዝ ክለቦች በአውሮፓ ሻንፒዎስ ሊግ ላይሳተፉ ነው ማለት ነው ይላል። አንዱ ቀበል አርጎ የገዛ ሕይወቱን ሞራ ማንበብ ተስኖት ሲያበቃ ስለኳስ ድልድል ሲያወራ ግን አይቻልም ባካችሁ ይላል በስላቅ። ቀዘቢት ቀበል አርጋ እኮ በየት በኩል? አቅጣጫችን ቢጠፋብን እኮ ነው የሰው አገር ሰዎች አቅጣጫ ተንታኝ የሆነው ትላለለች። አቅጣጫችንም ተሰረቀ እንዴ? ይላል ጋቢና የተየሰየመው ምኑም ሳይገባው። የምን አቅጣጫ? ነበረን እንዴ ለመሆኑ? ትጠይቀዋለች ከጎኑ የተሰየመች። ኧረ ከአቅጣጫችን በፊት እኛስ ነበርን እንዴ? ይላል መጨረሻ ወንበር ከተሰየሙት አንዱ። በሉ በቃችሁ። ደግሞ ይህችን የመሰለች ታላቅ አገር ብላችሁ ብላችሁ ያለ አቅጣጫ ስታስቀሯት ትንሽ ቅምም አይላችሁ? ማትሪክ መሰላችሁ እንዴ የአገርን አቅጣጫና ራዕይ ማንም የሚሰርቀው? ብላ ወይዘሮዋ አምቶ አሳሚውን ሰቅዛ ያዘችው። ጉድ እኮ ነው፤ ማትሪክ ፈተናውን የሰረቀው ማንም እንደሆነ ታወቀ እንዴ? ሲላት አጠገቧ ጎልማሳው ጣልቃ ገብቶ ከእገሌ ከእገሌ ማንም ማለቱ ይሻላል በሚለው ያዘው ወንድሜ ብሎ ወጣቱን አረጋጋው። ግን ቆይ እስከመቼ ነው? አለች ሦስተኛው ረድፍ ጥጓን ይዛ የተሰየመችው ንቁ። ምኑ? ሲላት ተሳፋሪው እንዲሁ በአቦ ሰጡኝ የዘረፈንን፣ ያዋረደንን፣ የግሉ አጀንዳ አስፈጻሚ ያደረገንን ግለሰብም ሆነ አንጃ ስም ሳናውቅ በጥቅል ስም ስንጠዛጠዝ የምኖረው እስከመቼ ነው? ስትል አዛውንቱ ቀበል አድርገው፣ ምናልባት እኛም እንደታላቋ ብሪታኒያ ከህቡው ኅብረት አባል ራሳችንን አግልለን ነፃ እስክንሆን ድረስ ይሆናላ ብለው መለሱላት። ሰሞንኛ ነገር ተገኘ ተብሎ እስኪ አሁን በሰው ማሽን ፖለቲካ እንደ ወረደ ይጨመቃል? ጉድ እስከ ወዲያኛው አሉ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ታክሲያችን ልታወርደን ጥጓን እያየዘች ነው። ‹‹አውርደና›› ብሎ ጎልማሳው ወያላው ላይ ጮኸ። ‹‹ቆይ ቦታ ይያዝ። ደግሞ ምን ያስጮሃል?›› አለ ወያላው። ‹‹አሁን በአሁን ምን ተገኘ ሰላም አልነበር እንዴ አየሩ?›› ብላ ወይዘሮዋ በወያላውና ጎልማሳው መሃል ስትገባ አዛውንቱ ፈገግ ብለው ‹‹ጊዜው የቱግ ቱጎች ሆና ምን ይደረግ። ደርሶ እሳት መጫር፣ ደርሶ ነገር ማክረር፣ ደርሶ የመገንጠል የመለየት ሐሳብ ማሰብ፣ ደርሶ የብቸኝነት የግለኝት ስሜት መውረር አላስኖረን አላ። ሰው እኮ ሲበርደው ግድ የለም ከጎረቤት እሳት መጫር ያለ ነው። ግን እሳት ልጫር ብሎ የጎረቤቱን ቤት በእሳት ማያያዝ ምን ማለት ነው?›› እያሉ ብዙ አወሩ። ወይዘሮዋ በድንገት ‹‹ምን ይደረግ? በመሰለንም ባልመሰለንም ነገር ማክረር ሆነ ሥራችን›› ከማለቷ ተሳፋሪው በሙሉ በአንድ ድምፅ ‹‹ሲከር ይበጠሳል ነዋ ተረቱ›› እያላት ተራ በተራ ወርዶ ተበታተነ። መልካም ጉዞ!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት