ድመትን የቤት አውሬ፣ ለማዳ የሚሏት አሉ፡፡ ዓይኗ ልዩ በመሆኑም ድብርቅ ዓይን፣ ያይጥ ጠላት የሚላት መዝገበ ቃላቱ፣ ዐይጥን የሚያስደምም፣ የሚያስፈራ፣ የሚያፈዝ፣ ዐይጥ ለመያዝ፣ ዝም፣ ጸጥ የሚል ሲልም ያክልበታል፡፡ ዐይነ ምድሩን መሬት ቆፍሮ የሚቀብር፣ ነገዱ ያንበሳ የነብር ነው፡፡ ከቤት የማይለይ፣ ከሰው ዘንድ ከሚኖረው ለማዳ ድመት ሌላ በበረሃ የሚኖር ፍጹም አውሬ የሆነ የዱር ድመት አለ፡፡
መጠኗ አነስተኛ የሆነ የዱር ድመት በሰሜን አፍሪካ፣ በደቡብ ምዕራብና መካከለኛ እስያ ውስጥ እንደምትኖር ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡
‹‹ሳንድ ካት›› የምትባለው የዱር ድመት፣ በአገርኛ ብሂል ‹‹ቀን ቀን ለሠራዊት ማታ ማታ ለአራዊት›› እንደሚባለው፣ የዱር ድመቷ ግዛቷ ሌሊት ነው፡፡
በጄ ደብሊው ዶት ኦርግ ድረ ገጽ እንደተጻፈው፣ ቀለቧን የምትሠፍረው ሌሊቱን ሙሉ በማደን ነው፡፡ በአሸዋማ መሬት ላይ እየተመላለሰች የዐይጥ ዝርያዎችን ታንቃቸዋለች፡፡ የምትበላውን በልታ ስትጠግብ የተራረፉትን አሸዋ ውስጥ ትቀብራለች፡፡